የኢትዮጵያ ዋንጫ ከረጅም ዓመታት መቋረጥ በኋላ በአዲስ የውድድር ሥርዓት ወደ ፉክክር ተመልሶ፣ ሊጠናቀቅ የፍጻሜ ፍልሚያ ብቻ ይቀረዋል፡፡ ውድድሩ ከመጀመሪያ ዙር አንስቶ በክለቦች መካከል አስደናቂ ፉክክር እያስተናገደ የፍጻሜ ተፋላሚ ክለቦችን የለየ ሲሆን፤ በመጪው የሰኔ ወርም አሸናፊው ክለብ የሚለይ ይሆናል፡፡ ታሪካዊውን ዋንጫ ለማንሳት የፍጻሜ ተፎካካሪ መሆናቸውን ያረጋገጡት ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻም ኢትዮጵያን ወክለው በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመሳተፍ ይፋለማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም የተካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ለፍጻሜው ማለፍ ችለዋል፡፡ ወላይታ ድቻ የፕሪምየር ሊጉን ጠንካራ ክለብ ኢትዮጵያ መድንን አንድ ለምንም እንዲሁም ቡናማዎቹ ሀዋሳ ከተማ(ሀይቆቹን) 2 ለ 0 በመርታትም ነው ለዋንጫው ፍልሚያ የደረሱት፡፡ በአራቱም ዙሮች ጠንካራ የፕሪምየር ሊግና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ጋር ተፋልመዋል፡፡
ቡናማዎቹ ለፍጻሜ ለማለፍ ያደረጉትን ጨዋታዎች ጨምሮ 12 ጎሎችን በተቃራኒ ማረብ አስቆጥረው የተቆጠረባቸው አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው 10 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ አስቆጥረው 5 ጎሎችን አስተናግደዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በ2ኛ ዙር ወልዲያ ከተማን 4 ለ 0 ፣ በ3ኛ ዙር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን 2 ለ 0 እና በ4ኛ ዙር የመድረኩ አንድ ጊዜ ቻምፒዮኑን ፋሲል ከነማን 4 ለ 1 በማሸነፍም ለግማሽ ፍጻሜው በቅቷል፡፡ ወላይታ ድቻ በ2ኛ ዙር ደሴ ከተማን 3 ለ 1፣ በ3ኛው ዙር ሀዲያ ሆሳዕናን 5 ለ 2 እና በ4ኛ ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 1 መርታቱ ለግማሽ ፍጻሜው አብቅቶታል፡፡
በግማሽ ፍጻሜው ፍልሚያ ቡናማዎቹ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ እና ማራኪ እግር ኳስን ከሚጫወቱት ክለቦች አንዱ የሆነውን ሀዋሳ ከተማን ገጥመው ብልጫ በመውሰድ ነበር ያሸነፉት፡፡ ይህም ደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁት እንደመሆኑ ዋንጫውን በማንሳት ዓመቱን በድል የሚያጠናቅቁበትን መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ የጦና ንቦችም ቢሆኑ፣ ዋንጫ ድል በማድረግ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እኩል የሆነ እድልን ይዘው ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት፡፡
በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ከሰርቢያዊው አስልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች ጋር የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከቀድሞ የክለቡ ተጫዋችና የአሁኑ የቡድኑ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ስር የተዘበራረቀ የውድድር ዘመንን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡ ሊጉ አዳማ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የውጤት መሻሻልና የቡድን መነቃቃት ላይ የነበሩት ቡናዎቹ በድሬዳዋ የሊጉ ቆይታ ቢቀዛቀዙም በኢትዮጵያ ዋንጫው ለፍጻሜ የሚያበቃ ጠንካራና ወጥ ጉዞ ማድረግ ችለዋል፡፡ ለፍጻሜ እንዲበቁ ያስቻላቸውን ሁለት ግቦች በባከነ ሰዓት ዋሳዋ ጆፍሪ እንዲሁም በክለቡ አስደናቂ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው አንተነህ ተፈራ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ዋንጫውን ለማንሳት በሚደረገው ጨዋታም ከጦና ንቦቹ ከባድ የሆነ ትንቅንቅ ይጠብቃቸዋል፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ጠንካራ ጨዋታ ማድረጋቸውንና የእነሱን ፈጣን የማጥቀት እንቅስቃሴ በመቋቋም ማሸነፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ለፍጻሜ መድረሱ ጥሩ እድል እና ኢትዮጵያን በትልቁ የአፍሪካ ክለቦች መድረክ ወክሎ ለመወዳደር መልካም አጋጣሚ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለፍጻሜ መድረሳቸው ክብር በመሆኑ ዋንጫውን በማንሳት ለደጋፊ ለማበርከት ይጫወታሉ፡፡
ወላይታ ድቻ በግማሽ ፍጻሜው ኢትዮጵያ መድንን ገጥሞ በጠባብ ውጤት ወደ ፍጻሜው ጨዋታ ማለፍ ችሏል። ኢትዮጵያ መድን በጉዞው አዳማ ከተማን እና ድሬዳዋ ከተማን የመሰሉ የሊጉ ጠንካራ ክለቦችን በመጣል በግማሽ ፍጻሜ በሌላኛ ጠንካራ ክለብ ተረቶ ከመድረኩ ለመሰናበት ተገዷል፡፡ የጦና ንቦቹ እሰከ አሁን ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ በመቻላቸው በፍጻሜው ዋንጫውን ለማንሳት ከቡናማዎቹ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡ ከመድን ጋር ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴን በማድረግ የዋንጫ ተፋለሚነታቸውን ያረጋገጡበትን ብቸኛ ግብም ብስራት በቀለ በማጠናቀቂያው ሰዓት ላይ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዋንጫ እአአ በ1940 መካሄድ የጀመረ ሲሆን ዋንጫውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለበርካታ ጊዜ በማንሳት ቀዳሚው ክለብ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ 11 ጊዜ ዋንጫውን ሲወስዱ መቻል በትንሽ ዝቅ ብሎ ይከተላል፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከጊዮርጊስ በግማሽ አንሶ ዋንጫውን ለብዙ ጊዜ ያነሳ ክለብ በመሆን ተቀምጦ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ውድድር 7 ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ በአምስቱ ድል ማድረግ ችሏል፡፡ ወላይታ ድቻ ደግሞ አንድ ጊዜ ለፍጻሜ በመድረስ ዋንጫውን ካነሱት ክለቦች መካከል አንዱ መሆን የቻለበትን ታሪክን ጽፎ ይገኛል። ቡናማዎቹ ዋንጫውን ካነሱ 16 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የጦና ንቦች በበኩላቸው የመጀመሪያውን ዋንጫ ካነሱ ሰባት ዓመት ሲሆናቸው የዘንድሮውን ዋንጫ የግላቸው በማድረግ ታሪካቸውን ለመጻፍ ተዘጋጅተዋል፡፡ ክለቦቹ ዋንጫውን ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ እጅጉን ሲጠበቅ የውድድር ዓመታቸውን በድል ለማጠናቀቅና በአፍሪካ ክለቦች መድረክ ተሳትፎን ለማረጋገጥም ትልቅ እድልን ይፈጥርላቸዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም