
ሰላም ዋጋ አይወጣለትም። ተመንም የለውም። ፍጥረት ሁሉ ሰላም ያስፈልገዋል፤ ሁሉም ሰላምን ይሻሉ። ከየትኛውም ፍጥረት በላይ ለሰው ልጅ ደግሞ ሰላም ከምንም በላይ ዋጋ አለው። የሰው ልጅ የሕልውና መሠረት በመሆኑ ዓለም ሁሉ ስለ ሰላም ይዘምራል። የሰላም መደፍረስ ሁሉንም የሚያስጨንቀውና የሚያሳስበው ለዚህ ነው። ጉዳቱ ከባድ ነው፤ ከጦርነት ወጥቶ ለማገገም ደግሞ እልህ አስጨራሽና አድካሚ ነው። ጠባሳው በሰው ልጅ አእምሮ ታትሞ የሚኖር መጥፎ ስዕል ነው። ለዚህ ነው ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው የሚባለው።
የሰላም መደፍረስ የማያስጨንቀው ሰው ቢኖር እራሱ አደፍራሹ ነው ለዛም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እሱንም ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። የሰላም መደፍረስ በተለይ የሚጎዳው ሴቶችን፣ ሕጻናት እና አረጋውያንን መሆኑን ለሚያስብ ደግሞ ስጋቱም ጉዳቱም እጥፍ ድርብ ይሆንበታል።
የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልገው ዋናው መሰረታዊ ፍላጎቱ እንዲሟላለት ነው። መጠለያ፣ ምግብና አልባሳት መሰረታዊ እየተባሉ ከልጅነታችን ጀምሮ ስንማረው፣ ስንናገረው ኖረናል። አሁንም መሰረታዊ እየተባሉ ከሚገለጹት ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ይሁን እንጂ ማንኛውንም መሰረታዊ ጉዳይ ለማሟላት ቀዳሚ ሆኖ መምጣት ያለበት ሰላም ነው፥።
ሰላም ከሌለ የተሟሉ የሚባሉትን መሰረታዊ ፍላጎቶች ስለመሟላታቸውም ሆነ ስለመጠቀም ማንሳት አይቻልም። የሰው ልጅ ሰርቶ ለመለወጥ በቅድሚያ መማር፣ መስራት የመሳሰሉትን ማስቀደም መቻል አለበት። ምንም ነገር ለመስራት ብቻ ሳይሆን ለማሰብ መጀመሪያ መቅደም ያለበት ሰላም መሆኑ አያጠያይቅም።
ሌላው ቀርቶ ሰው የሚያመልከወን አምላኩን ለማምለክ ሰላም ያስፈልገዋል። የጸሎትም ሆነ የሶላት ሰዓት ደረሰ ብሎ ምስጋና ለማቅረብ፣ ስለ ሀገር ሰላም ለመጸለይ፣ የምንሻው እንዲሞላለን ለመማጸን በምንቆምበት በምንሄድበት ቦታ ሁሉ ሰላም መኖር አለበት። ለዚህ ነው ከምንም በላይ ለሰው ልጅ ሰላም ያስፈልጋል የሚባለው።
ሌላው ቀርቶ እንሰሳት ሰላም ከሌለ ደመነፍሳቸው ይጨነቃል። ከበረት የሚያወጣቸው፣ መኖ የሚያቀርበላቸው አያገኙም። ከበረትና ከጋጣቸው ቢወጡም የጥይት ሲሳይ እስከመሆን ይደርሳሉ። ይሄ ለቤት እንስሳት ብቻም ሳይሆን የዱር እንሰሳትም በጦርነት ምክንያት ተጎጂዎች ናቸው።
ሕይወታቸውን ከማጣት እስከ መሰደድ የሚደርስ አደጋ ይገጥማቸዋል፤ በሚፈጠር የእሳት አደጋ አስከፊ ጉዳትን ይደርስባቸዋል። እናም የሰላም ጉዳይ የማይመለከተው፣ የማይነካውና የማይጎዳው የምድር ፍጥረት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ለዚህም ነው ሁሉም ስለሰላም የሚሰበከው። ለሰላም ዘብ እንቁም የሚባለው። ሁሌም ሊዘመርለት የሚገባው የሰላም ጉዳይ ነው የሚባለው።« ሰላም… ሰላም… ሰላም ለሀገራችን ፤ሰላም ለምድራችን። ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ» ተብሎ የተዜመውም ያለ ምክንያት አይደለም።
የሰላም አለመኖር፤ የሰላም መደፍረስ በሀገራችን በተለያየ ጊዜ ምን እንዳደረሰ ሁላችንም አይተናል። ላለፉት 50 ዓመታት በተለያየ ወቅት የታየው የሰላም እጦት ሀገራችንን ከየት ተነስታ ወደየት እንዳወረዳትም ለመገመት አይከብድም። የስንት ዘመን ቀደምት የስልጣኔ ታሪክ ያላት ሀገር አሁን የት እንዳለች የሚታወቅ ነው። ባለፈው ዘመናትም ሆነ አሁን ድረስ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ በእያንዳንዳችን የእለት ተእለት ሕወት ላይ ምን ያህል ጥፋት፤ የስነልቡና ጫና እያስከተለ እንደሆነ እዚህ ላይ መንገድ አያስፈልግም።
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል በሌሎችም አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩና የሚሰሙ የሰላም መደፍረሶች ዜጎች እንደ ልባቸው ወጥተው ለመግባት፤ ተንቀሳቅሰው ለመስራት፤ ሰርተው ለመለወጥ፤ ተምረው ለማደግ እና ሀብት ንብረት ለማፍራት እንዲሁም ራስን ለማሻሻል ጭምር ስጋት ሆነዋል።
ችግሩ በአካባቢያዊው በሚኖሩ ሕዝቦች እና በአጠቃላይ በሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛ ጫናዎችን ሲያሳድር ቆይቷል። ይሄ በሀገር ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸም የሰላም መደፍረስ ታዲያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ ሰላም በመላው ሀገራችን ሰፍኗል ለማለት ግን አይቻልም። አሁን በተለያየ አካባቢዎች የሰዎች ሞት ይደመጣል፤ መፈናቀል ይታያል። የንብረት ውድመት ይከሰታል፤ ስደትን ይስተዋላል።
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በነበረው አለመግባባት በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች አሁንም ድረስ እድላቸውን እያማረሩ በአካል ጉዳታቸው እያዘኑ ይገኛሉ። ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው፣ ሴቶች የመደፈር ችግር ገጥሟቸው ምን ያህል መጯጯህ እንደነበር ይታወቃል።
ይሄ ችግር በወቅቱ የአንድ ክልል ችግር ብቻም አልነበረም፤ እንደ ሀገር ሁሉም ዜጋ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው የተጨነቀበት፤ ሀገራችንም ወደ አስጊ ሁኔታ ገብታ የነበረችበት እንደነበር ማስታወስ ይገባል። በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶች የክልል ወይም የክልሉ ነዋሪዎች ሀብትና ንብረት ብቻ አይደለም።
የተቸገሩት የተሰደዱት እና ጉዳቱን ያስተናገዱት የክልሉ ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም። በአካል ባንሰደድም በመንፈስ አብረን ተሰደናል። በቀጥታ የገፈቱ ቀማሽ ባንሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ የችግሩ ተካፋይ ሆነናል። ችግሩ የሀገር ችግር፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ያንዣበበ የሀገርን ኢኮኖሚ የጎዳና አሁንም እየጎዳ ያለ ነው።
ጦርነቱ እንደ ሀገር ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለን ነው ። የትግራይ ክልል ሕዝብ አሁን ላይ ስለጦርነት በብዙ የታከተው እንደሆነ ደፍሮ ለመናገር መሽኮርመም አያስፈልግም። ጦርነት ጎዳው እንጂ አልጠቀመውም፤ አቆረቆዘው እንጂ አላሳደገውም፤ አሁን ለትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም ልማት ነው።
ሁሉም ዜጋ እንደ ዜጋ፤ እንደ ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ታማለች፤ ተጎድታለች። ልማትና እድገቷን በሚሹ ሳይሆን በተቃራኒው በቆሙ ኃይሎች አሁንም ድረስ ሰላሟን ማረጋገጥ አልቻለችም። በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ የነበረው የስነልቡና ጉዳትም አሁንም ድረስ የጠገገ አይደለም። ቁስሉ አልሻረም። አገግሞ ሙሉ ለሙሉ ለቀጣይ እድገትና ብልጽግና ሰላማዊ የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ አይደለም።
አሁንም ከወደ ትግራይ ክልል የሚሰሙና የሚታዩ ጦርነት ጠሪ ችግሮች ለሕዝቡ ተጨማሪ የጦርነት ስጋት ምንጭ ሆነውበታል። ዛሬ ወይ ነገ ጦርነት ተቀሰቀሰ ብሎ በመጨነቅ ስጋት ላይ ነው። መድረሻውን እያማተረ ያለም አለ። ይሄ ለምን ይሆናል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል።
ያውቃሉ፣ ይመራሉ፣ ሀገር ያስተዳድራሉ፣ ፍትህን ያሰፍናሉ፤ ሌላም… ሌላም ተብለው የሚጠበቁት ፖለቲከኞች ግን የተራው ዜጋ ያህል ስለ ክልላቸውም ሆነ ስለ ነዋሪው ለአንድ ሰከንድ እንኳን እያሰቡ አይመስልም። ምስኪኑን ነዋሪ ምንም የማያውቀውን ወጣት የጥይት ሲሳይ ሊያደርጉት ዳር ዳር እያሉ መሆናቸውን በሚያወጡት መግለጫ በሚወራወሩት የቃላት ጦርነት መገንዘብ ይቻላል።
የትግራይ ሕዝብ ባለፉት 50 ዓመታት በጦርነት ውስጥ በስቃይና ሰቆቃ ሕይወቱን አሳልፏል። የከባድ መሳሪያ ድምጽ መስማት ሰልችቶታል። ቤቱን ትቶ በየምሽጉ ማሳለፍ መሮታል። አሁን ደግሞ አንጻራዊ ሰላም አገኘሁ ብሎ ለመረጋጋት ሲያስብ ከግራም ከቀኝም የሚመላለሱ የቃላት ጦርነቶች እረፍት ነስተውታል።
ቀደም ሲልም በጦርነት ሲማገድ የነበረው የደሀው ልጅ ነው፤ አሁንም ችግር ቢፈጠር የሚያልቀው ለፍታና ጥራ ግራ፤ መከራዋን አይታ፤ ሁለት ቀለም አውጥታ ያሳደገች የደሀዋ እናት ልጅ ነው። ስታሳድግ መከራዋን ጠብሳ በጦርነት ልጇን ስታጣ አንጀቷ በሀዘን አሮና ደብኖ ነው። እባካችሁ ስለ ሕዝቡ ስትሉ ለሕዝቡ ሰላም ስጡት። ስለ ሕጻናቱ ስትሉ የግል ጥቅማችሁን፤ የስልጣን ሽኩቻችሁን አቁሙና ሰላምን አስፍኑ።
በየትኛውም ዓለም ጦርነት የሚቋጨው በድርድር፣ በንግግር ነው። የእኛም የሰሜኑ ጦርነት የተቋጨው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲተገበር በመስማማት ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም መተባበርና ለተግባራዊነቱ ቀናኢ ሆኖ መቆም ያስፈልጋል።
ፖለቲከኞች ዛሬም ሰላም ሳይሆን ጦርነት ቀስቃሽ የሆኑ ንትርኮችን እያሰሙ ናቸው። ይሄ ለማንም ለምንም የሚጠቅም አይደለም። ይሄ ለትግራይ ሕዝብ፤ ለሀገር ጭምር የሚበጀው አይደለም። የትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም ነው። ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል ለተደረሰበት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገዥ መሆን ያስፈልጋል።
የትግራይ ሕዝብ መሻትም በሰላም ስምምነቱ መሰረት ችግሮች ተፈትተው በሰላም መኖርን ነው። የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ በመጠገን ኢኮኖሚውን ማሳደግ ነው። ሰላም በሁሉም መልኩ ሰፍኖ ማህበራዊ እንቅስቃሴውን በተሟላ መልኩ ማሳለጥ ነው።
ተማሪው ደብተር ይዞ ተምሮና ተፈትኖ በጥሩ ውጤት ማለፍን፤ ዩኒቨርሲቲን በጥሩ ውጤት መቀላቀል ነው የሚፈልገው። ለዚህ ደግሞ በቁጭት መስራትና መበልጸግን ይፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ለዚህ እንደፍላጎቱ በሰላም እንዲኖር የተፈቀደለት አይመስልም። አሁንም የጦርነት ቋስቋሽ ንግግሮች ደመቅ ብለው እየተሰሙ ነው። አሁንም የሕግን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ነው።
የሀገሪቱን ሕግና ሕገመንግሥት ማክበርና ለሕጉ መገዛት ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። የሕግ ጥሰት ጎልቶ ይታያል። ሕግ ባልተከበረበት ሁኔታ ደግሞ ሰላም ይሰፍናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ሕግ ሊከበር ይገባል፤ መደማመጥ ሊሰፍን ይገባል። ከምንም በላይ የሕዝቡ ሰላም ሊጠበቅለት ያስፈልጋል።
ቀደም ሲል ባየነው ጦርነት በጦርነት የትም መድረስ እንደማይቻል ነው። ጦርነት ጎጂ እንጂ ጠቃሚ አለመሆኑን አይተናል። ለሰላም ሲባል ቀደም ብሎ ማሰላሰል፤ ደጋግሞ ማሰብ ይገባል። የጦርነት አስከፊነት በቀላሉ ከቀደሙ የጦርነት ታሪካችን ማስተዋል ይቻላል። ከትናንቶቻችን ልንማር ይገባል።
”ብልጥ ከሌላው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱ ይማራል” የሚል አንድ አባባል አለ። እኛ ግን የጦርነት አስከፊነት በራሳችን በደንብ አድርገን አይተናል። በተለይ በሰሜኑ ክልል የጦርነት አስከፊነትን ኖረነው አይተነዋል፤ ግን ደግሞ አልተማርንበትም። ወደ አእምሯችን መንፈሳችን ልንመለስ ይገባል።
አሁን ለትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገው ጦርነት ቀስቃሽ ምልልሶች አይደለም። ልቡን ዝቅ የሚያደርግ ንግግሮች አይደለም። በየስብሰባዎች የይዋጣልን ፉከራ አይደለም። ትከሻ እንለካካ አይነት ልበ ደንዳናነት አይደለም ። ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም ነው። ትናንትም ሰላም ሰላም ሲል ያደመጠው አልነበረም። ዛሬ ግን ድምጡ ሊሰማ ይገባል።
አሁንም በጦርነት ልጆቹን ፣ ሀብት ንብረቱን ማጣት አይፈልግም። ተጨማሪ ስቃይና እንግልትን ማስተናገድ አይፈልግም። አሁን የሚፈልገው ሰላም ነው። የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ ኃይሎች በሕግ አምላክ ሊባሉ ይገባል። ሁሉም ነገር ሕግና የሕግ ስርዓት አለው። የፕቶሪያው የሰላም ስምምነት ሕግና ሕግን የተከተለ ነው፤ ስምምነቱን በሚፈለገው ልክ ወደ ትግበራ ማስገባት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በኃላፊነት ልንቀሳቀስ ይገባል።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም