
በምሥራቅ እና ምዕራባዊ የአሜሪካ ክፍል በተከሰተ ከፍተኛ አውሎ ንፋስ የ42 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በንብረት ላይም ከባድ ውድመትንም አስከትሏል። አቧራ የቀላቀለው እና ሰደድ እሳትን ያስከተለው አውሎ ንፋስ በ8 ግዛቶች ላይ ውድመትን አድርሷል።
ሚዙሪ፣ ካንሳስ እና አላባማ ከፍተኛ የሟች እና የውድመት መጠንን በቅደም ተከተል ያስተናገዱ ግዛቶች ናቸው። አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው አደጋው ለመብራት እና የትራንስፖርት መቋረጥ፣ ለትምህርት ቤቶች እና አውራ ጎዳናዎች መዘጋት እንዲሁም ለበርካታ አገልግሎቶች መስተጓጎል ምክንያት ሆኗል። ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአደጋው ተጋላጭ መሆናቸው በአየር ትንበያ መረጃ ተመላክቷል።
ይህንንም ለመቋቋም የግዛቱ አመራሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን ከፌዴራል መንግሥት እገዛን እየጠየቁም ይገኛሉ። በአደጋው ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊ ሁኔታዎችን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ዜጎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ሲኤንኤን በዘገባው ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም