
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን የሰላም ስምምነት ዙሪያ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሊያደርጉት ካሰቡት የስልክ ውይይት በፊት በበርካታ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ቢደርሱም በቀጣይ የሚሠራባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ገለጹ። ትራምፕ ማክሰኞ ጠዋት ከፑቲን ጋር እንደሚወያዩ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ አጋርተዋል።
ምንም እንኳን በበርካታ ነጥቦች ላይ መግባባት ላይ ቢደርሱም ትራምፕ በጽሑፋቸው ብዙ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሚቀሩ ተናግረዋል። አክለውም ‹‹በእያንዳንዱ ሳምንት በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በኩል ሁለት ሺህ አምስት መቶ ወታደሮች ይቀጠፋሉ። ስለሆነም አሁኑኑ ጦርነቱ ማብቃት አለበት። ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሚደረገውን የስልክ ውይይት በጉጉት እጠብቀዋለሁ›› ሲሉ አጋርተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ለጋዜጠኞች ‹‹የሰላም ስምምነት ላይ የተኩስ አቁም ላይ በመድረስ ሰላምን ማምጣት እንችል እንደሆነ እናያለን እናም ይሄንን ማድረግ የምንችል ይመስለኛል›› ሲሉ ተደምጠዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ሰኞ ምሽት ባደረጉት ንግግር ፑቲን ጦርነቱን አራዝሞታል ሲሉ መክሰሳቸው ይታወቃል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጅዳ ከዩክሬን ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ እንደተናገሩት ‹‹ውይይቱ ጠቅለል ባለ መልኩ የድርድር ሂደቱ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የተደረገ እንጂ ነጥብ በነጥብ የተደረገ አልነበረም›› ያሉ ሲሆን አያይዘውም ‹‹ይህ ምክረ ሀሳብ ከረጅም ጊዜ በፊት ተግባራዊ ሊሆን ይችል ነበር። በጦርነት ውስጥ እያንዳንዱ ቀን የሰው ሕይወት ማለት ነው›› እንዳሉ ተሰምቷል።
ሞስኮ ውስጥ ሐሙስ እለት ከፑቲን ጋር የተገናኙት የዩናይትድ ስቴትስ ተወካይ ስቲቭ ዊትኮፍ በጉዳዩ ላይ ቁጥብ መረጃ ሰጥተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ፑቲን ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጉ ከሆነ እንዲያረጋግጡ በማለት ጠይቀዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዘለንስኪ የተኩስ አቁም ሃሳብ ላይ በመስማማት ያሳዩትን ዝግጁነት አድንቀው ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ መጠየቃቸው ታውቋል። እንደዚሁም በኤክስ ገጻቸው ላይ ‹‹ሞት በቃ፣ በቂ ሕይወት ጠፍቷል፣ በቂ ውድመት ደርሷል፣ አፈሙዞች ዝም ማለት አለባቸው›› ሲሉ ጽፈዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ‹‹ፑቲን ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው›› ማለታቸው ተሰምቷል። በተጨማሪም ‹‹ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ ሩሲያ ያለማወላወል እንድትደራደር ለማስገደድ የሚሆኑ ካርዶች አሉን›› በማለት ማስጠንቀቂያቸውን አሰምተዋል። ኋይት ሓውስ በበኩሉ ትራምፕ እና ፑቲን ከሚያደርጉት የስልክ ውይይት አስቀድሞ ‹‹የዩክሬን ሰላም እንደአሁኑ ቀርቦ አያውቅም›› ሲል መናገሩ ተሰምቷል።
በትናንትናው እለት ለጋዜጠኞች መልዕክት ያስተላለፉት የኋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ‹‹ትራምፕ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ ናቸው›› ማለታቸው ታውቋል። በመቀጠልም ‹‹በሩሲያ እና በዩክሬን ድንበር ላይ የሚገኝ የኃይል ማመንጫ አለ። ከጉዳዩ ጋር ከዩክሬናውያን ጋር መወያየት አለብን። ነገ በሚደረገው የስልክ ውይይትም ትራምፕ ከፑቲን ጋር ይወያዩበታል›› ሲሉ ገልጸዋል።
እሁድ ዕለት የተኩስ አቁም ድርድሩ ምን አይነት ነጥቦችን ታሳቢ እንደሚያደርግ የተጠየቁት ትራምፕ ‹‹ስለመሬት እንነጋገራለን፣ ስለኃይል ማመንጫ እንወያያለን፣ አንዳንድ ሀብቶችን በመከፋፈል ላይ እንደዚሁ ንግግር ጀምረናል›› ብለዋል። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሁለቱ መሪዎች ስለሚወያዩበት ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹ይህን በጭራሽ አናደርግም›› በማለት ዝርዝር ጉዳይ ከመስጠት ተቆጥበዋል። መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም