የዱር እንስሳት መመናመን የደቀነውን ስጋት ለመከላከል

በዓለማችን ላይ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ እፅዋትና እንስሳት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ዓለም አቀፍ ጥናቶችን ጠቅሶ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። የብዝኃ ሕይወት መመናመን የሰው ልጆች ሕልውናን አደጋ ላይ ለሚጥል ስጋት እንደሚዳርግም የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ምን ያህል ያሰጋታል? እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የዱር እንስሳት ሀብት ለሰው ልጅ ብሎም ለምድር ሕልውናም በጣም ወሳኝ እንደሆነ ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ የሰው ልጆች ለሚያገኙት ንፁሕ አየር፣ ንፁሕ ውሃ እና ለም አፈር፣ የዱር እንስሳት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ የላቀ ነው። ለፓርኮችና ለብዝኃ ሕይወት በሚፈለገው ልክ ጥበቃ ባለመደረጉ ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ውስጥ ትገኛለች።

ፓርኮች፣ እንስሳትና እፅዋት የማይጠበቁ ከሆነ ምድር አደጋ ውስጥ ትወድቃለች የሚሉት አቶ ኩመራ፤ እንደሀገር ይህንን የሕልውና ስጋት ለመቀነስ ፓርኮችንና የተለያዩ የጥበቃ ቦታዎችን በማቋቋምና በመከለል እንስሳትና እፅዋት እንዲጠበቁ ላለፉት 60 ዓመታት ጥረቶች ሲደረጉ መቆየቱን ይናገራሉ።

ብዝኃ ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ቢሆንም የሰው ልጅ ግን አነስተኛ የጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት እንደሚሰጡት የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ለግብርና፣ ለአፈር ለምነትና ለሰው ልጆች የመኖር ሕልውና ትርጉም ያላቸው የብዝኃ ሕይወት አካላትን የሚይዙ ፓርኮችንና ጥብቅ ቦታዎችን መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ጥብቅ ቦታዎቹ የመኖር ሕልውናን ከማረጋገጥ ባሻገር በቱሪዝም የኢኮኖሚ አቅምን የማጠናከር ፋይዳቸው ጉልህ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት መኖሪያ ደኖችን፣ ወንዞችን፣ ሐይቆችን፣ እርጥበታማ ቦታዎችን በጥበቃ ስልት ውስጥ በማካተት ብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ እየሠራች መሆኑን የሚገልፁት አቶ ኩመራ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥበቃ ቦታ ሽፋንን ለማሳደግ እና የብዝኃ ሕይወት መመናመንን ለመከላከል እየተሠራ እንደሆነ ይገልፃሉ። አሁን ያለው የኢትዮጵያ የጥበቃ ቦታ ሽፋን 14 በመቶ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥበቃ ሽፋንን በ2030   ወደ 30 በመቶ የማሳደግ ግብ ተቀምጧል።

‹‹የምድራችን የጥበቃ ሽፋን 30 በመቶ ካልደረሰ በሰው ልጆች ላይ ብዙ ቀውስ ይመጣል። የአየር ንብረት ለውጥ፣ እንደኮቪድ አይነት የማይገመቱ ተላላፊ በሽታዎችና አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ›› የሚሉት አቶ ኩመራ፣ ኢትዮጵያም የዚሁ ስጋት ሰለባ እንደሆነች ይናገራሉ። ይህንን ለመቋቋም ኢትዮጵያ የጥበቃ ሽፋኗን ማሳደግ እንዳለባትም ይናገራሉ። በመጠነኛ ሁኔታ የኢትዮጵያን የብዝኃ ሕይወትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎችን ለመንከባከብ እስከ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ይህን የፋይናንስ ክፍተት መሙላት እንደሚገባም ያስረዳሉ።

አቶ ኩመራ እንደሚሉት እ.አ.አ በ1973 ሀገራት ቁጥራቸው እየተመናመኑ የሚገኙ እንስሳት እና ዕፅዋትን ከጥፋት ለመታደግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ‹‹ሳይተስ›› የሚባል ስምምነት አድርገዋል፤ ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ንግድን የሚቆጣጠር አሠራር ነው። ኢትዮጵያም ከ1989 ጀምሮ የስምምነቱ አካል ሆናለች።

‹‹ከስምምነቱ አስቀድሞ በርካታ የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች ለዓለም አቀፍ ንግድ ይውሉ ነበር። አብዛኞቹም ከምድረ ገጽ ለመጥፋት የተቃረቡበት ወቅት ነበር›› የሚሉት አቶ ኩመራ፤ አሁን ላይ 38 ሺህ የሚደርሱ ዕፅዋትና የዱር እንስሳት ዓለም አቀፍ የንግድ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ያስረዳሉ።

ይህም ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ብርቅዬ የዱር እንሰሳት ቁጥር የሚቀንስባቸው ሁኔታ እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ። ለአብነትም አንድ ሺህ መድረስ ችሎ የነበረው የሰሜን ተራሮች የዋልያዎች ቁጥር ወደ 300 መውረዱን ገልጸዋል።

የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩማራ ዋቅጅራ፤ በሰሜን ተራሮች የብርቅዬ ዋልያዎች ቁጥር ከዚህ በፊት አደጋ ላይ መውደቁን ተከትሎ የተለያዩ እንክብካቤዎች ሲደረጉ ነበር። የተሠራው የእንክብካቤ ሥራም የብርቅዬ ዋልያዎቹ ቁጥር አንድ ሺህ መድረስ ችሎ ነበር ብለዋል።

ሆኖም በሰሜኑ ክፍል ካለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ የቁጥጥር መላላት መፈጠሩ፣ የእሳት አደጋ እና የሕገወጥ አደኖች መበራከት ብርቅዬዎቹ ተመልሰው እንዲመናመኑ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜም የዋልያዎቹ ቁጥር ተመናምኖ ወደ 300 ዝቅ ማለቱን ነው የተናገሩት።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) የብዝኃ ሕይወት መመናመንን እና የዱር እንስሳት የጥበቃ ስጋትን መቀነስ እንደሚገባ ይገልፃሉ። ጥበቃውን ማጠናከር የሰው ልጆችን ሕልውና ከማረጋገጥ ባሻገር የቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይ የዱር እንስሳት ጥበቃ ለኢኮኖሚ እና ለቱሪዝም ሥነ ምሕዳር እድገት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሮን የማስቀጠል ሥራ በእቅድ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑንም ይገልፃሉ።

‹‹ኢትዮጵያ ለዱር እንስሳት ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጡ አዳዲስ መፍትሔዎች ላይ የማተኮር ሥራ እየሠራች ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ ደግሞ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። በኢኮቱሪዝም፣ በዘላቂ ግብርናና በደን አያያዝ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሕይወት ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመው፣ የዱር እንስሳትን ጥበቃ ማጠናከር ከሀገር እድገት ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ይረዳል ይላሉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፓርኮችን መሠረት ያደረገ የቱሪዝም ልማት እንዲኖርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጥበቃ ሥራው መጠናከር አለበት። ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዱር እንስሳት ሀብትንና የብዝኃ ሕይወት ጥበቃን በተለያዩ ፕሮጀክቶች ትግበራ አማካኝነት እያጠናከረች ትገኛለች። ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የምድራችንን የብዝኃ ሕይወትና የዱር እንስሳት ጥበቃ በበቂ ሁኔታ ለማካሄድ እስከ 800 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ መጠነኛ የጥበቃ ተግባር ለማከናወን ሦስት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት በየዓመቱ ልትመድብ ይገባል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You