የባዮ ቴክኖሎጂ ልማት በኢትዮጵያ

ይህ ጸሐፊ ከባዮ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ሃሳቦችን ሲያነሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በተለይም ከርእሰ-ጉዳዩ “እንግዳነት” የተነሳ ምንነቱ፣ አስፈላጊነቱና ዳራውን አስመልክቶ የተለያዩና ተገቢ ምንጮችን በመጠቀም የተወሰኑ ሃሳቦችን ለማስተጋባት ሙከራ አድርጓል። “የባዮ ቴክኖሎጂ ልማት በአፍሪካ” በሚል ርእስም ጉዳዩን አህጉር አቀፍ ገጽታ በመስጠትና የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመፈተሽ ሰፋ ያለና ጥናት አከል (“ሚኒ ሪሰርች” ይባል ዘንድ አቅም ያለው) ሥራን ለንባብ አብቅቷል።

በእነዚህ ሥራዎች ውስጥም ባዮ ቴክኖሎጂንና ልማቱን አስመልክቶ የተሰነዘሩ የተለያዩ ተቃራኒ አስተያየቶችን (“Pros and Cons” እንዲሉ) ለማከራከር ተሞክሯል፤ በተለይ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ፣ በሀገራችንም ሆነ በአጠቃላይ አህጉራችን ባዮ ቴክኖሎጂ ያለበትን የአሁን ዘመን ሁኔታና አጠቃላይ ይዞታ ለማሳየት ጥረት ተደርጓል። ዋቢዎችን በመጠቀም የተሠሩና የሚቀሩ ተግባራትን ለመጠቆም የተሞከረ ነው።

በዘርፉ ያሉ ምሁራንን ሚና ከነ ሰፊና አበረታች ጥረትና ሥራዎቻቸው ጋር በማንሳት አርአያ ይሆኑ ዘንድ የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል። (ምሳሌ ፦ አዲስ ዘመን፣ ኀዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ ዘመን፣ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም እና ሌሎችንም መመልከት ይቻላል።)

በስሩ ከ17 የማያንሱ ብሔራዊ የምርምር ማእከላት ያሉትን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥራ ኃላፊዎችንና ፕሮጀክት አስተባባሪዎችን በማነጋገር የሰጡትን አስተያየት ለሕዝብ ለማስተላለፍ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ ዶ/ር ታደሰ፣ ዶ/ር ድሪባ፣ ፕ/ር ፍሬው፣ ዶ/ር ካሳሁን እና ሌሎችንም (በአፍሪካ ደረጃ Biotech­nology Hero የተባሉትን “የባዮቴክኖሎጂ ጀግኖች” ጭምር) በመጠቃቀስ ሀገርና አህጉር አቀፍ ሥራዎቻቸውን ለማስታወስ ጥረት ተደርጓል። ጉዳዩ ግብርና፣ ባለድርሻ አካላቱም እህል የሚበላ ሁሉ (ፕ/ር ፍሬው እንዳሉት) ነውና ይህ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

በተለይ “የባዮ ቴክኖሎጂ ልማት በአፍሪካ” ልክ እንደ ርእሱ ሁሉ በይዘቱም ጉዳዩን አፍሪካዊ በማድረግ፣ ከአፍሪካ ግብርና ኋላ ቀርነት ጋር በማያያዝ ሳይንሱንና ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም እንደ ሀገር ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ምሁራን በዘርፉ እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ ፊት መሪነታቸውን ጭምር ሰፋ አድርጎ በማየት ለማሳየት ሞክሯል።

“በሀገር ደረጃ የምርምር ሥርዓቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሙሉ የተመራማሪነት ማዕረግ የተሰጣቸው፣ የመሪ ተመራማሪነት ደረጃን የጨበጡ፣ ለሀገራችን ግብርና ሳይንስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሀገሪቷን የግብርና ዘርፍ በተለያዩ ችግር ፈቺ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎችና እውቀትን በማመንጨትና በማቅረብ ለሀገራዊ ግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፣ ብዕር ያልዳሰሳቸው፣ ሚዲያው ያልደረሰባቸው (ባጭሩ ምንም ያልተዘመረላቸው) ተመራማሪዎች” መኖራቸውን በመግለፅም አድናቆታችንን በተለያዩ አውትሌቶች ገልጸናል።

ዛሬ ዓለም እየተጠቀመበትና ወደ ፊት እየተራመደበት፣ አንዳንዱም እያጣጣለው (አውቆም ቢሆን) ያለው ባዮ ቴክኖሎጂ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ጀምሮ በርካቶች የደከሙለት ሲሆን፤ በተለይም ካሮሊ (Károly Ereky, 1878–1952)፣ ኤቫ (Eva Ekeblad, 1724–1786)፣ ዊልሄልም (Wilhelm Roux, 1850–1924)፣ ሉድዊግ (Ludwig Haberlandt, 1885–1932)፣ (ሞሪስ Maurice Lemoigne, 1883–1967)፣ ጄን (Jean Purdy, 1945– 1985)፣ ብሪጌት (Brigitte Askonas, 1923–2013)፣ ዴይሲ (Daisy Roulland-Dussoix, 1936–2014) እና የመሳሰሉ ሳይንቲስቶች ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን ሰውተውለት ያለፉ ስለ መሆናቸውና መጪው የባዮ ቴክኖሎጂ ታሪክ ሳይቀር የሚያስታውሳቸው እንደሚሆን ሁሉ፤ ዛሬ እዚህ የምናነሳቸውና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ያሰባሰባቸው ምሁራንም የወደፊቱ የባዮ ቴክኖሎጂ ባለታሪኮች ናቸውና ወደ ሥራዎቻቸው እንዝለቅ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

በኢትዮጵያ የዘመናዊ መንግሥት ታሪክ፣ በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው፣ ከአዲስ አበባ ከንቲባነት (ከ1910 እስከ 1914 ዓ.ም) እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ በዘመን ተሻጋሪ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ከሃያ በላይ ድርሰቶችና የታሪክ መጻሕፍቶቻቸው፣ የባህር ማዶ የጉዞ ማስታወሻዎችን በማፍራታቸው እና ሌሎች በርካታ ሥራዎቻቸው “አንቱ!!!” የተሰኙት፤ ታላቅ ዲፕሎማትና ደራሲ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ (1870 -1931) በሕይወት እያሉ ይኖሩበት የነበረው (ከ13ሺህ 490 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ መሬት ላይ ያረፈው) ዘመናዊ ቤታቸው “የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከል” ሲሆን፤ ማዕከሉንም “የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ” እያስተዳደረው ይገኛል።

ይህ (በ2005 ዓ.ም. በዓዋጅ ቁጥር 783/2013 የተቋቋመ) አካዳሚም የተለያዩ ሀገራዊ ጥናቶችን እያስጠና ለፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎችም ግብአት እያደረገ ያለ ሲሆን፤ አንዱም ዛሬ እዚህ የምንመለከተው፤ በአካዳሚው ፕሬስ ክፍል አማካኝነት ለህትመት የበቃውና የስድስት ምሁራንን ስብስብ ሥራዎች በአንድ ያካተተው መጽሐፍ ነው።

ይህ መጽሐፍ “ባዮ ቴክኖሎጂ፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተከታታይ ከተካሄደ የሳይንስ ገለፃዎችና ውይይቶች መድረክ የተወሰደ” (ዲሴምበር 2013) በሚል መለያ የቀረበ መሆኑንም መግለፅ ያስፈልጋል።

የስድስቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ዳሰሳ

ወደ ዳሰሳው ከመሄዳችን በፊት ለጠቅላላ እውቀትና አጠቃላይ ግንዛቤ ይሆን ዘንድ ከ“የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ፍኖተ ካርታ” ሰነድ ላይ መገኘቱን ተጠቅሶ ለንባብ በቅቶ ያገኘነውን እና “ባዮ ቴክኖሎጂ ማለት ሥነ ሕይወታዊ መዋቅሮችንና የተለያዩ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ትስስራቸውን፣ አንድነትና ልዩነታቸውን በመመርመር፣ ለቴክኖሎጂው የሚያስፈልገውን የዘረመል መዋቅር በመተንተን የብዝሃ ሕይወትን ተለያይነትና ልዩ ተፈጥሮ፣ ምርታማነትና ጥራትን በመፈተሽ ውጤቶቻቸውን ለሚፈለገው ተግባር ወይም ጠቀሜታ ለማዋል የሚያስችል የዘመኑ ፊት ቀደም (frontier) ሳይንስ ነው።” የሚለውን በመግቢያ መልክ አስፍረን ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ።

በዳሰሳችን ከላይ በጠቀስነውና ከዓላማዎቹ አንዱና ቀዳሚው “የኅብረተሰቡ የሳይንስ ግንዛቤ እንዲጎለብት ማገዝ” በሆነው፤ “በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተከታታይ ከተካሄዱ የሳይንስ ገለጻዎችና ውይይቶች መድረክ” የተወሰዱ መሆናቸውን በገለጸው ተቋም አማካኝነት ለአደባባይ የበቁትን የምሁራኖቻችንን የዘርፉ አስተዋፅኦ (እንደ ሀገር በሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ተግባራት ይከናወኑ ዘንድ ለማሳሰብ ጭምር) የምንመለከት ይሆናል።

እነዚህ (“ሙዳየ ቃላት”ን ሳይጨምር) ሥራዎች  የቴክኖሎጂ አብዮቶች እና አፍሪካ” (ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ)፤ ባዮ ቴክኖሎጂ ታሪካዊ አመጣጥ፣ መሠረታዊ ምንነት፣ “ከቴክኖሎጂዎች ጋር ያለው ትስስር፣ ፍልስፍናና የወደፊት አቅጣጫ” (ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለ)፤ “ግብርና እና ባዮ ቴክኖሎጂ” (ዶ/ር በላይነህ አድማሱ)፤ “ባዮ ቴክኖሎጂ እና ጤና” (ዶ/ር አብርሃም አሰፋ)፤ “በባዮ ቴክኖሎጂ አካባቢ የደህንነት-ሕይወት የሕግ ማሕቀፎች” (ዶ/ር አዳነ አብርሃም)፤ እና “የባዮ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ አስፈላጊነት” (ዶ/ር እሌኒ ሽፈራው) ሲሆኑ፤ ሁሉም “ባዮ ቴክኖሎጂ”ን የጥናቶቻቸው ማእከላዊ ጭብጥ በማድረጋቸው አንድ ሲሆን፤ ባዮ ቴክኖሎጂን በተለያዩ ዘርፎች፣ ሰብአዊ ፋይዳዎች፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ወዘተ አኳያ መፈተሻቸው ደግሞ ልዩና የተለያዩ ያደርጋቸዋል።

በዚህ፣ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡት በባዮ ቴክኖሎጂ ላይ ያጠነጠኑ የሳይንስ ገለጻዎች “የቀረቡት በስድስት የሳይንስ ምሁራን ሲሆን፤ ሁሉም በሥነ-ሕይወት ሂደቶችና መሠረታዊ መዋቅር ላይ የተመሠረቱ ለውጦችን በሚያከናውነው ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ” መሆናቸውን ከስብስቡ መገንዘብ ተችሏል።

በ2007 “በኢትዮጵያ የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ” በሚል ርዕስ ብሔራዊ ዓውደ-ጥናት አካሂዶ በነበረው በዚሁ ተቋም ጥራዝ “መግቢያ” ላይ እንደ ሰፈረው የሰው ዘር በባዮ ቴክኖሎጂ መጠቀም ከጀመረ ምዕተ ዓመታት አልፈውታል:: በመሆኑም ሰው እንደማንኛውም እንስሳ ወፍ ዘራሽ እና ዙሪያ በቀል ዕፅዋት ላይ የምግብ ግብዓቱን መሠረት አድርጎ ከመኖር ተላቆ፣ የተመረጡ ዕፅዋትን ለይቶና አራብቶ ለምግብነት ተገልግሎባቸዋል::

በዚህ አድራጎቱ፣ በግብርና መሠማራት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የባዮ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ነው ማለት ይቻላል:: በተጨማሪም እንስሳትን አላምዶ ለሥራ አጋዥነት፣ ለምግብ አገልግሎት ማዋሉም የባዮ ቴክኖሎጂ አካል ነው:: የሰው ልጅ ዘር እየመረጠ፣ ብዙ ምርት የሚሰጡ ሰብሎችን ማምረት፤ እንዲሁም እንስሳትን በማዳቀል የተለያዩ ጠንካራ ዝርያዎች ማግኘት ተችሏል:: ይህም የግብርና የመጀመሪያው የባዮ ቴክኖሎጂ ውጤት እንደሆነ ያሳያል::

መጽሐፉ በዚሁ (ገጽ [i] ላይ) “ በአሁኑ ዘመን፣ በሕይወት ሂደት ላይ ጥቃቅን ለውጦችን በማከናወን ሰፊ ምርት ማምረት፣ የበሽታ መከላከያቸው የጠነከረ፣ ተባይና ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በማምረት መጠቀም ተችሏል:: ባለፉት 50 ዓመታት የተትረፈረፈ ምርታማነት ሩቅ ምሥራቅን ከቸነፈር ማላቀቁ በምሣሌነት ይጠቀሳል::

ዘመኑም የአረንጓዴ ለውጥ ዘመን (የቅጠልያው ለውጥ ዘመን) ይባል ነበር:: ሆኖም ለውጡ አፍሪካን ሳይዳስስ አልፏል:: አሁን የሚታየው የባዮ ቴክኖሎጂ ለውጥም እንዲሁ እንደዋዛ አፍሪካን ተራምዷት እንዳይሄድ ያሰጋል::” በማለት አስፍሯል። እኛም “አሁን የሚታየው የባዮ ቴክኖሎጂ ለውጥም እንዲሁ እንደዋዛ አፍሪካን ተራምዷት እንዳይሄድ ያሰጋል::” የሚለውን ከስሩ በደማቁ አስምረንበት ወደሚቀጥለው እንለፍ።

ቀጥሎ ላለው፣ አንባቢያንን በተለይ ከመጽሐፉ ገጽ iii እስከ vi ላይ ያለውን እንዲመለከቱ በመጋበዝ ወደ ሥራዎቹ አጠቃላይ ይዘት እንሸጋገራለን።

ተናጠላዊ ምልከታ

በመጀመሪያ የቀረበው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ማስረሻ በቀለ “የቴክኖሎጂ አብዮቶችና አፍሪካ” በሚል ርእስ የቀረበ ጥናት ሲሆን፤ ጥናቱ እንስሳትንና ዕፅዋትን ለማልመድ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የግብርና አብዮት በማብራራት ለከፍተኛ የምርት ዕድገት አስተዋፅኦ ያደረገውንና አፍሪካ ተጠቃሚ ያልሆነችበት ሁኔታ ላይ በማተኮር ሁለተኛውን የግብርና አብዮት ይዳስሳል::

በቴክኖሎጂ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ውስጥ የሚጠቃለሉ ለውጦችን ስለሚያስገኘው የኢንዱስትሪ አብዮትና ከሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንጻር ሲገመገም አፍሪካ ተጠቃሚ የሆነችበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት ያብራራል:: ረሃብን ከዓለም ገጽ ማጥፋት ዓላማው ካደረገው አረንጓዴው የግብርና አብዮትም አፍሪካ ተጠቃሚ እንዳልነበረችና ለምን ተጠቃሚ እንዳልሆነችም ይሄው ጥናት ያትታል::

ቀጣይ የአፍሪካ አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበት ሲጠቁም፤ እንደ ባዮ ቴክኖሎጂ ያሉ አዳዲስ የሳይንስ ውጤቶችን በሰፊው መጠቀም እንደሚገባ ያስገነዝባል:: በተጨማሪም፣ ባዮ ቴክኖሎጂን ከቀደምት ቴክኖሎጂዎች የሚለየው ዘርፈ-ብዙ ለሆነው የሰው ልጅ ችግር (በጤና፣ ግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ መስክ) የመፍትሄ ምንጭ መሆኑን ካስተነተነ በኋላ አፍሪካም ዘርፈ-ብዙ ችግሮቿን ለመፍታት ከተገቢው ጥንቃቄ ጋር ቴክኖሎጂውን መተግበር መጀመር እንዳለባት ያሳስባል::

ሁለተኛው ጥናት “የባዮ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥና ሂደቱ” በሚል ርእስ በፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የቀረበ ሲሆን፤ የባዮ ቴክኖሎጂን ታሪካዊ አመጣጥና መሠረታዊ ምንነት፣ ከቴክኖሎጂዎች ጋር ያለው ትስስር፣ ፍልስፍናና የወደፊት አቅጣጫ ላይ በማተኮር የተዘጋጀ ነው:: ጽሑፉ በመግቢያው ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገነባው ቴክኖሎጂ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚጠቃለል ጠቅሶ፤ ከእነዚህም ውስጥ ባዮ ቴክኖሎጂን የሚያካትተው፤ ሕይወትንና የሕይወት ምህንድስናን ያቀፈው ትኩረትን የሳበ የዘመኑ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ መሆኑን ይገልጻል::

ይህ ፕሮፌሰር እንደሻው ጥናት የባዮ ቴክኖሎጂን ትርጉምና ጠቀሜታውን፤ እንዲሁም የህዋና የሕይወት መከሰትን በአጭሩ ያብራራል:: የባዮ ቴክኖሎጂ ታሪክና አመጣጡን ለመረዳት፣ መሠረታዊ የዘመናዊ ባዮ ቴክኖሎጂ ይዘትና አሠራርንም ለመግለፅ የሚያስችለንን፣ የሥነ-ባህሪይ ሳይንስ የሚባለውን የጥናት ዘርፍ ይተነትናል:: ሥነ-ሕይወታዊ አብዮት በተለይም በዘረ-መል አካሎችና ተግባራቸው ላይ ጥልቅ የምርምር ግኝት ያበረከተውን የሞለኪላዊ ሥነ-ሕይወት ሳይንስን ዕድገት ያብራራል::

ለባዮ ቴክኖሎጂ ዕድገት ወሳኝ ቢሆኑም በደንብ ያልተጠኑትን ጉዳዮች በመዘርዘር ስለሰው ሠራሽ ሕይወትና የሰው ሠራሽ ሥነ-ሕይወት ሳይንስን አስፈላጊነት ያሰርፃል:: “በባዮ ቴክኖሎጂ አካባቢ መደረግ ያለበት ጥናትና አቅም ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ከመሆን ባሻገርም የሕይወት ጉዳይ ስለሆነ በጥንካሬ ልንሄድበት” የሚገባ መሆኑን በመግለፅም ርእሰ ጉዳዩን ያጠቃልላል።

ሦስተኛው “ባዮ ቴክኖሎጂ እና ግብርና” በሚል ርእስ የቀረበው የዶ/ር በላይነህ አድማሱ (የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) ጥናታዊ ጽሑፍ በመግቢያው የሰው ልጅ በአንድ ቦታ ረግቶ መኖር ከግብርና ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን በመግለፅ ግብርና በየትኛው የዓለማችን ክፍል እንደተጀመረና መጀመሩ ምክንያት የሆኑትን መላምቶች ይጠቅሳል::

ዕፅዋትንና እንስሳትን ማላመድ፤ በሂደትም ዝርያዎችን ወደ መምረጥ ተሸጋግሮ አሁን ወዳለንበት ዘመናዊ የባዮ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሊደርስ መቻሉን እየገለጸ፤ ባህላዊና ዘመናዊ የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርዘር ጠቀሜታቸውን ያብራራል:: ከዘመናዊ ባዮ ቴክኖሎጂ ውስጥ የዘረ-መል ምህንድስናን በተመለከተ ለሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ይሰጣል:: “የቴክኖሎጂን ጥቅምና ጉዳት በማወዳደር ጠቀሜታው ከጉዳቱ አመዝኖ ከተገኘ ዕውቀት ላይ በተመሠረተ መልኩ ጉዳትን በመቀነስ የጥቅሙ ተጋሪ መሆን የተሻለ” መሆኑን በማሳሰብ ይደመድማል።

አራተኛው ጥናታዊ ጽሑፍ “ባዮ ቴክኖሎጂና እና ጤና” በሚል ርዕስ ዶ/ር አብርሃም አሰፋ (አርመር ሃንሰን የምርምር ተቋም) የተዘጋጀ ሲሆን፤ ጽሑፉ የውርስና የሕይወት መሠረት የሆነው ዘረ-መል የባዮ ቴክኖሎጂ ዕምብርት መሆኑን በማብራራት ይጀምርና ዘረ-መልን የማንበብ ቴክኖሎጂ (ስኩዌንሲንግ) ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎች የተሻለ ሕክምና ለመሥጠት የሚረዳ መሆኑን ይዘረዝራል:: በተጨማሪም በዘረ-መል ምህንድስና (ዘረ-መልን በመቁረጥና በመቀጠል) ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎች የሚሆኑ መድኃኒቶችን ማምረት የሚቻልበት ላቅ ያለ የዘመናዊ ባዮ ቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ መድረሱን ይገልጻል::

በመቀጠልም፣ ከጥንት ጀምሮ ሰውና በሽታ ያደርጉት በነበረው ትግል ውስጥ በየደረጃው ባዮ ቴክኖሎጂ ለጤና ያበረከተውን አስተዋፅኦ ይዘረዝርና አሁንም ገና ብዙ ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያመለክታል፤ በአሁኑ ጊዜ ግንባር ቀደም የሆኑትን የጤና ባዮ ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ያብራራል:: በተለይም የስተም ህዋስ ቴክኖሎጂ ተዋናይ ሀገራትን ልምድ በመጥቀስ የጤና ባዮ ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ዕድሜ መራዘም ያደረገውን አስተዋፅኦ ያስረዳል::

የጤና ባዮ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አስፈላጊነት በመዘርዘር ለሀገራችን በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለውን የኩባ ባዮ ቴክኖሎጂ ልማትን ልምድ ያስተዋውቃል:: በመጨረሻም፣ ሀገራችን ለቴክኖሎጂው ግብዓት ሊሆን በሚችል ደረጃ የብዝሃ ህይወት ማዕከል ብትሆንም በአሁኑ ጊዜ የባዮ ቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዘመናዊው የጤና ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ ያላት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን በቁጭት ያነሳል:: ስለሆነም፣ አቅማችንን ገንብተን እያለፈ ያለውን የባዮ ቴክኖሎጂ አብዮት ልንሳተፍበት የሚገባ መሆኑን በጥብቅ ያሳስባል::

በአምስተኛነት የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፉ “በባዮቴክኖሎጂ አካባቢ የደህንነት-ሕይወት የሕግ ማሕቀፎች” በሚል ርዕስ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አዳነ አብርሃም (ዶ/ር) የተዘጋጀው ነው:: ጥናቱ የደህንነት-ሕይወት ምንነትና ሁለት ዋና ዋና ዘርፎቹን በመጥቀስ በዘረ-መል ምህንድስና ዘዴ ልውጠ-ህያዋንን የመፍጠር ሂደትን በአጭሩ ይዳስሳል::

በመቀጠልም በዘረ-መል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ጥቅምና ጉዳት ላይ ያለውን ሰፊ ክርክር በዝርዝር በማብራራት፤ የቴክኖሎጂው ውጤት ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አጠቃቀሙ በቁጥጥር ሥርዓት ስር መሆን እንዳለበት ያሳስባል:: ሆኖም ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ የቁጥጥር ሥርዓት ወይም አካሄድ አለመኖሩን በማስረዳት የባዮ ቴክኖሎጂ ደህንነት-ሕይወትን በተመለከተ የተመረጡ ዓለም አቀፍ ማሕቀፎችንና አግባብነት ያላቸው ስምምነቶችን በመዘርዘር አሠራርን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታስቧል::

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ደህንነት-ሕይወት ነክ ፖሊሲዎችና የሕግ ማሕቀፎችን ሲቃኝ አዋጅና ማስፈፀሚያ መመሪያዎቹ ልውጠ-ህያዋንን በጥቅል እንደ ጎጂ ነገሮች በሚፈርጅ፣ በጣም ጥብቅ በሆነ የቅድመ ጥንቃቄ መርህ ላይ በመመስረታቸው ከምርምር እስከ ምርትና ገበያ ላይ እስከ ማዋል ባሉ ሂደቶች ሊሟሉ የሚያዳግቱ ቅድመ- ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውን ያስረዳል::

በዚህም ምክንያት ሀገራችን ለበርካታ ዓመታት በጣም አስፈላጊ የሆኑ የባዮ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስገብታ መጠቀም አልቻለችም:: ስለሆነም ኢትዮጵያ ወደፊት ዘመናዊ ባዮ ቴክኖሎጂን ከተገቢው ጥንቃቄ ጋር ለመጠቀም አመቺ የደህንነት-ሕይወት ሥርዓት መዘርጋት ያለባት ሲሆን፤ ይህም የማያሠሩ የአዋጁንም ሆነ የመመሪያዎቹን አንቀጾች ማሻሻል ካስፈለገ ማሻሻል የሚገባ መሆኑን በማሳሰብ አጠቃላይ ይዘቱን በዚሁ ያሳርፃል።

በስድስተኛነት የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ “የባዮ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ አስፈላጊነት” በሚል ርዕስ፣ በዶ/ር እሌኒ ሽፈራው (ብዝሀ ሕይወት ምርምር ኢንስቲትዩት) የተዘጋጀ ነው::

ጥናታዊ ጽሑፉ ሀገራችን በቅርብ ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራት እንድትቀላቀል በመታቀዱ፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ለዕድገት መሠረት የሆነው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ በኢኮኖሚው ዘርፎች መተግበር እንዳለበት በመግቢያው ጠቅሶ፤ ከእነዚህም መካከል ባዮ ቴክኖሎጂ አንደኛው ቢሆንም ይህንን ቴክኖሎጂ በቀጥታ ከዘረ-መል ምህንድስና ጋር ብቻ እንደሚገናኝ አድርጎ በማሰብ የባዮ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ እንዳይቀረፅ መንስዔ መሆኑን ያመለክታል::

በመቀጠልም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ባዮ ቴክኖሎጂ ያለውን ሚና ሲያብራራ፤ ከግብርናውና ኢንዱስትሪው ዕድገት መሻሻል ጋር ያለውን ቀጥተኛ ተዛምዶ በመዘርዘር ይገልፃል:: ባዮ ቴክኖሎጂና ጤናን በተመለከተም አቅም መፍጠር ላይ ያተኮረ ዘርፍ እንደሆነና በቴክኖሎጂው በመታገዝ የሚደረጉ ለውጦች የአካባቢ ጥበቃ አስተዋፅዖ ያላቸው መሆኑን ያስረዳል:: በባዮ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ የሌሎች ሀገራት (የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት፣ የህንድ፣ እና የታንዛኒያ)ን ልምድ በመጥቀስ በኢትዮጵያ ያለበትን አነስተኛ ደረጃ ይጠቁማል:: የቴክኖሎጂውን ልማትም እውን በማድረግ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የአሠሪ ፖሊሲና መመሪያዎች ድርሻ ቀላል አለመሆኑን ያስገነዝባል።

ማጠቃለያ

ስድስቱ ባዮ ቴክኖሎጂ ተኮር የምሁራኑ ጥናቶች (ባጭሩ) ከላይ ያለውን ይመስላሉ። የየጥናቶቹን ዝርዝር ይዘቶችን፣ የተደረጉ ጥልቅ ውይይቶችን፣ የተሰጡ አስተያየቶችንና ሌሎች በምርምር ሥራዎቹ ውስጥ የተካተቱን ጉዳዮችን በሚገባ ለማስገንዘብ ሥራዎቹን ከላይ ከጠቀስነው መጽሐፍ ውስጥ ማንበቡ ተገቢ ይሆናል። የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያካፈሉትን ልምድ፣ የሰነዘሯቸውን ወርቃማ ምክሮችና ምክረ ሃሳቦች፣ ያቀበሏቸውን መረጃዎችና የመሳሰሉትንም በቅጡ ለመገንዘብ ስብስቦቹን መፈተሽ ተገቢ ነው።

እዚህ ላይ፣ ከማጠቃለላችን በፊት አንድ ነገር ማስታወስ ተገቢ ሲሆን፤ እሱም ምናልባት ከጥናትና ምርምር ሥራዎቹ ወዲህ ባዮ ቴክኖሎጂ ተኮር የሕግ ማሕቀፎች የወጡ ሲሆን፤ አንዱም በ”የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን” አማካኝነት የተዘጋጀውና የደህንነት ሕግ ማሕቀፎችን በአንድ አሰባስቦ የያዘው “BIOSAFETY REGULATORY LAGAL FRAME­WORKS OF ETHIOPIA” (Addis Ababa, 2022) ነው። ይህ ጸሐፊ ሊያገኘው አልቻለም እንጂ “የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ፍኖተ ካርታ” ሰነድ እንደተዘጋጀም ይነገራል።

ይህ ብቻም አይደለም፣ በሚመለከታቸው አካላት ሲነገር እንደሚሰማው፣ ዛሬ ላይ ከቀድሞው በተሻለ ከባዮ ቴክኖሎጂ ልማት አኳያ ኢትዮጵያ ሊያሠሩ የሚችሉ የሕግ ማሕቀፎች እንዳሏት (የሚቀሯት እንዳሉም ጭምር) ይነገራል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው፤ ከላይ የዳሰስናቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ለባዮ ቴክኖሎጂ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ግንዛቤን ከመፍጠርና ለሌሎች መሰል የወደፊት ጥናትና ምርምር ሥራዎች ጉዝጓዝ መሆን የሚችሉ ናቸውና አጥኚ ምሁራኑና አስተባባሪ ተቋሙ ሊመሰገኑ፤ ሌሎችም በየዘርፉ ያሉ አርአያነታቸውን ሊከተሉ ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You