የሸማቾች ጥበቃ ፅንሰ ሃሳብ

በዓለማችን ለ42ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ“ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለሸማቾች፤” በሚል ርዕስ የፊታችን መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። እኔም ይሄን ምክንያት በማድረግ ስለ ሸማች ማስነበቤን እቀጥላለሁ። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለዚህ ግብዓት የሚሆኑ ሰነዶችን ስላጋራኝ እያመሰገንሁ ወደ ዛሬው መጣጥፌ ላ ምራ።

የሸማቾች ጥበቃ ለሸማቾች አጠቃላይ ወይም ሙሉ ጥበቃን ለመስጠት ያለመ ተግባር ሲሆን፤ ጥበቃውም ማንኛውም ሸማች ላይ ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጊቶችን የሚከለክልና ስለ መብቶቻቸው እንዲናገሩ እና እንዲታገሉ የሚያስችላቸውን ኃይል ይሰጣል፡፡ የሸማቾች መብት ጥበቃ በውስጡ ሦስት ፅንሰ ሃሳቦችን የያዘ ሲሆን፤ አንድ ጉዳይ በሸማቾች ጥበቃ ስር የሚመጣው እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ከተጣመሩና በሕጉ ክፍሎች ውስጥ የተሰጡትን ትርጉሞች ካሟሉ ነው። እነዚህም “ሸማች”፣ “የሸማች መብት” እና “የሸማቾች ጥበቃ” ናቸው፡፡

ሸማች በማንኛውም ግላዊም ሆነ ሕዝባዊ የኢኮኖሚ ውሣኔዎች ተፅዕኖ የሚደርስበትና በውሳኔዎቹም ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ ትልቁ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመሆኑ፤ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥም ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ የሸማቾች ጥበቃ የምርቶችና አገልግሎቶች ገዥዎችን በገበያ ላይ ከሚፈጸሙ ኢ ፍትሐዊ ድርጊቶች መጠበቅ ነው። ሸማቾች በአምራቾች ፣ በሻጭና በአገልግሎት ሰጪዎች ከሚፈፀሙ ብልሹ የንግድ አሠራሮች ለመጠበቅ እና እንደ ሸማች መብታቸው ከተጣሰ የሕግ ተጠያቂነትን፣ ኃላፊነትን ባለመወጣት በደረሰው ጉዳት ልክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ዋነኛ አላማ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ሂደት ውስጥ ነጋዴዎች እና አቅራቢዎች ሊያደርሱት የሚችሉትን ተፅዕኖ ለመከላከልና በሸማቾ እና በነጋዴው መሀከል ያለውን የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግና ሸማቾች በግብይት ወቅት በሚገበዩት ምርትና አገልግሎቶች ላይ በነጋዴው የመጭበርበር ለደህንነታቸው አስጊ ግብይት ከማድረግና ከተለያዩ አሳሳችና ሀሰተኛ የግብይት ሁኔታዎች የሚጠበቁበት መንገድ ነው፡፡

በንግድ ሥራ ውስጥ የአምራች፣ የአከፋፋይ እና የቸርቻሪ መኖር የግድ እንደሆነ ሁሉ ሸማቾችም በሌላ ወገን የሚገኙ የንግድ ገፅታ በመሆናቸው አንድ ንግድ አቋሙን ይዞ በንግድ ሥራ ውስጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመሥራቱ ዋነኛ ምክንያት የሸማቾች መኖር ወይም ነጋዴው የሚያቀርበውን እቃ ወይም አገልግሎት የሚጠቀም አካል መኖሩ ነው፡፡ አንድ ነጋዴ በመረጠው የንግድ ሥራ ለመሠማራት ሲወስን የሚያቀርባቸውን ዕቃዎችና አገልግሎቶች ይዞ ወደ ገበያው የሚገባው ምርቶችን በሚያቀርበው ዋጋ ሸጦ ወይም ለሸማቾች አቅርቦ ትርፋማ መሆን ነው። አምራቾች አከፋፋዮችም ሆኑ ቸርቻሪዎች ምርቶችን የሚያመርቱት ፣ የሚያከፋፍሉት እና የሚቸረችሩት ለሸማቹ ማህበረሰብ ፍጆታ በመሆኑ ያለሸማች አንድ ንግድ ትርፍ ሊያገኝ ፣ ሊያድግና ሊኖር አይችልም፡፡

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ የሕግ ማሕቀፎች፣ የንግድ ውድድር ሕጎች በዋናነት የሚያተኩሩት በገበያ ሥርዓት ውስጥ ውድድርን ሊያዛቡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማስወገድ እንደየሀገሩ ሁኔታ ጤናማ ውድድር የሰፈነበት የኢኮኖሚ ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የሸማቾች መብቶችና ጥቅምን ለማስከበርና በገበያ ላይ ጤናማ ውድድር መኖሩን ለማረጋገጥ የውድድር ሕጎች እጅግ የላቀ ሚና እንዳላቸው ይታመናል።

በእዚህም ነው የንግድ ውድድር ሕጎችና የሸማቾች ጥበቃ ሕጎች ተነጣጥለው የማይታዩት፤ ለተመሳሳይ ዓላማ የቆሙ ተመጋጋቢ የሕግ ሥርዓቶች ናቸው ተብሎ የሚታመንባቸው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕጎች ዓላማቸው የሸማቹን ጥቅም ማስከበር ሲሆን፤ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚጠቀሙበት ዘዴም ሆነ መሳሪያ ሊለያይ ይችላል። የንግድ ውድድር ሕጎች ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ በነጋዴዎች መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሕግ እንዲገዛ ማድረግ ሲሆን፤ የሸማቾች ጥበቃ ሕግም በሸማቹ ማህበረሰብና በነጋዴው መካከል ያለውን ግንኙነት በሕግ እንዲገዛ በማድረግ ነው፡፡

የንግድ ውድድር በአንድ የገበያ ምህዳር ውስጥ የተለያዩ ድርጅቶች ወይም ሻጮች በየግላቸው ደንበኛ ለማፍራትና የተሻለ ትርፍ ለማግኘት እርስ በእርስ የሚፎካከሩበት ሂደት ሲሆን፤ በገበያ ውስጥ የሚደረጉ ማንኛውም አይነት የፀረ ውድድር ተግባራት የሸማቾችን ፍላጎት የሚጎዳ ሲሆን፤ የግብይት ሂደቱ በሕገወጥ ነጋዴዎች እጅ ይወድቃል። በእዚህም ምክንያት ገበያው ደረጃቸውን ባልጠበቁ እና ለደህንነት አስጊ በሆኑ ምርቶች ይሞላል። ይህም በውድድር በማይመራ ገበያ ውስጥ የአምራችና የአቅራቢ ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን ያደርጋል። በእዚህም የተነሳ ሸማቾችና ነጋዴዎች ከውሱን አምራችና አቅራቢዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርትና አገልግሎቶችን ለመግዛት እና ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ ለማውጣት ይገደዳሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ሸማቾች ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ጥራት ያለው ተመሳሳይ ምርት ማግኘት አይችሉም፡፡

የንግድ ውድድር ሕግ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የሚመራበት መሠረታዊ ሕግ ሲሆን፤ በተለይ በግሉ ባለሀብት መካከል የሚኖረው ግንኙነት በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ባለው አሠራር የሚፈቀዱ እና የሚከለከሉ የንግድ አሠራሮች ምንነት የሚገለጽበት፣የአንድ ሀገር የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከኢኮኖሚ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ፖሊሲዎች የሚደነገጉበት ሕግ ነው። የንግድ ውድድር ፖሊሲ እና ሕጎች በዋናነት የሚያተኩሩት በገበያ ሥርዓት ውስጥ ውድድርን ሊያዛቡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማስወገድ እንደየሀገሩ ሁኔታ ጤናማ ውድድር የሰፈነበት የኢኮኖሚ ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡

የሸማቾች ጥበቃ ሕጎች በአጠቃላይ ሸማቹ ማህበረሰብ ከነጋዴው ጋር የሚኖረው ግንኙነትን የሚመለከቱ ሲሆን፤ የሸማችን ጥቅም ማስጠበቅ ዋንኛው ዓላማቸው ሆኖ እነዚህ ሕጎች በገበያ ላይ ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች መከላከልን ጨምሮ የሸማቾችን ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን መስፋፋት መግታት የሚያስችል የሕግ ሥርዓት በመዘርጋት የሸማቹ ጥቅም እንዲረጋገጥ ያደርጋሉ። ሕጉ በዋነኛነት የሚሸፍናቸው ነጥቦች የሸማቾችን መብቶች እና የሸማቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነጋዴዎች ያሉባቸው ግዴታዎችና ክልከላዎች ናቸው።

የሸማቾች ጥበቃ ሕግ በአምራቾች ፣ ሻጮች እና በሸማቾች መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ፍትሐዊነትን እና ርትዕን የማረጋገጥ ዓላማ ያለው ሕግ ሲሆን፤ ሕጉ ሸማቾች በየቀኑ በአምራቾች ነጋዴዎች ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመታደግ እና የሸማቾችን ለችግር ተጋላጭነት ለማስቆም ይረዳል ።

የሸማቾች ጥበቃ ሕግ በዋነኛነት ሸማቾች የንግድ ዕቃና አገልግሎት ባህሪ እና ዋጋን አስመልክቶ በቂ እውቀትና መረጃ እንዲኖራቸው የማድረግ ዓላማ ያለው ሕግ ከመሆኑ በተጨማሪ ሕጉ የአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ግዥ ከመፈፀሙ በፊት ያለን የመረጃ እጥረትና ግዥ በሚፈፀምበት ጊዜ ለሸማቾች የሚፈጠርባቸውን አግባብ ያልሆነ ጫና ለመቀነስ እንዲሁም ሸማቹን የሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎችን የመገደብና የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች አቅርቦት ለሰው ጤናና ደህንነት ተስማሚ እንዲሆኑ በማድረግ የሸማቾችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ገበያ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡

የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ዋነኛ ዓላማ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ሂደት ውስጥ ነጋዴዎች እና አቅራቢዎች ሊያደርሱት የሚችሉትን ተፅዕኖ ለመከላከልና በሸማቾች እና በነጋዴው መሀከል ያለውን የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግና ሸማቾች በግብይት ወቅት በሚገበዩት ምርትና አገልግሎቶች ላይ በነጋዴው ከመጭበርበር ለጤናቸው አስጊ የሆነ ግብይት ከመፈጸምና ከተለያዩ አሳሳችና ሀሰተኛ የግብይት ሁኔታዎች የሚጠበቁበት ነው፡፡

ሌላው የሸማች መብት የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ ነው፡፡ ይህ የሸማች መብት በዋናነት ሸማቹ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን አጥንቶ፣ ዋጋውን አወዳድሮ እንዲገዛና በነፃነት እንዲሸምት የሚያስችል ነው፡፡ ከእዚህኛው መብት ጋር የሚያያዘው አራተኛው በአዋጁ ላይ የተቀመጠው የሸማች መብት ደግሞ፤ የሸማቹ በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ እንዲሁም በነጋዴው ከሚደርስበት ስድብ፣ ዛቻ፣ ማስፈራራትና ስም ማጥፋት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ የሸማች መብት የሸማቹን ሰብዓዊ ክብርና የመዋዋል ነፃነት ለመጠበቅ ያለመ ነው፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1679 ላይ ውል በተዋዋዮች ፈቃደኝነት ላይ መመሥረት አለበት የሚለውን ድንጋጌ ለማስፈጸም የሚረዳ ነው፡፡

የመጨረሻው የሸማች መብት ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን ያቀረቡ ሰዎችን (አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ ጅምላ ሻጮች፣ ቸርቻሪዎች ወይም ሌሎች በአቅርቦቱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች) በተናጠል ወይም በአንድነት ካሳ እንዲከፍሉት ወይም ሌሎች ተያያዥ መብቶች እንዲያሟሉለት መጠየቅ ነው። ይህ መብት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 ላይ የተደነገገውን ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማስፈጸም የሚረዳ ነው፡፡ አዲስ አበባ ወይም ድሬዳዋ ያለ ሸማች በነጋዴ ላይ የሚያቀርበው ክስ በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዳኝነት ችሎት መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ይገባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ቀጥሎም ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ በክልሎች ያሉ ሸማቾች የሚያቀርቧቸው ተመሳሳይ ክሶች ደግሞ በክልል ፍርድ ቤቶች ይስተናገዳሉ፡፡ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ጥራት ያለው፣ ጤንነቱ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ሸቀጥ አገልግሎት አማርጦ፣ አወዳድሮ የመሸመት መብት ቢኖረውም እውን ማድረግ ባለመቻሉ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዳርጎ ይገኛል። ለኑሮ ውድነት፣ ለጤና ጠንቅ ለሆኑ ሸቀጦች እና ጥራት በጎደላቸው ሸቀጦች ጤናው እየታወከ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ በሸማቹ፣ በሻጩና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ፣ ኢ ፍትሐዊና ኢ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ በተለይ ሸማቹን ሁልጊዜ ተበዳይ፣ ተገፊና ተጠቂ አድርጎታል። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ሸማች ባለበት ሀገር የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን ታጥፎ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር እንዲዳበል መደረጉ የሸማቾችን ጉዳይ አኮሳምኖታል። ስለሆነም የጥቅም ግጭት ስላለው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጥቶ ራሱን ችሎ ጎጆ ሊወጣ ይገባል።

ለመብቶቹ መተግበር የሚረዱ ሃሳቦችን ደግሞ እንመልከት፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ውስጥ የሸማቾችን መብቶች የሚጥሱ የተለያዩ ድርጊቶች በአንዳንድ ነጋዴዎች እየተፈጸሙ እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጤፍን ከተለያዩ ጎጂ ነገሮች በመቀላቀል እንጀራ መጋገርና መሸጥ፣ የጥራት ደረጃ ያላሟሉ የታሸጉ ውሃዎችን መሸጥና በሕገወጥ መንገድ የሚመረት የምግብ ዘይት ለገበያ ማቅረብ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት በጥቂቱ የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በጸሐፊው አመለካከት የሸማች መብቶችን በኢትዮጵያ ለማክበርና ለማስከበር በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ስለሸማቾችና መብቶቻቸው ሸማቾችን፣ ነጋዴዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ማስተማር ያስፈልጋል። ይህም ሸማቾች ያሏቸውን መብቶችና እንዴት መብቶቻቸውን ማስከበር እንደሚችሉ እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ መብቱን በጥቂቱ እንኳን የማያውቅ ሰው በራሱ ወይም በሌላ ሰው አጋዥነት (ለምሳሌ በጠበቃ) መብቱን ለማስከበር አይችልምና፡፡ የማስተማር ሥራው ከሸማቾች በተጨማሪ ሌሎችን አካላት ማካተት ይኖርበታል፡፡

ነጋዴዎች የሸማቾችን መብቶች ካወቁ እንዳይ ጥሷቸው እንዲጠነቀቁ ወይም የድርጊቶቻቸውን ውጤቶች አውቀው እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። በተለምዶ በሚደረጉ የንግድ ሥራዎች ላይ ያሉትን ለሸማች መብት ጥበቃ መሰናክል የሆኑትን አሠራሮችንም ለማስቀረት ይረዳል፡፡ ለምሳሌ በርካታ ነጋዴዎች ሰዎች ዕቃዎቻቸውን ወይም አገልግሎቶቻቸውን ዓይተውና ዋጋ ጠይቀው ሳይገዙ ሲሄዱ ደስተኞች ስለማይሆኑ ሸማቾችን ያመናጭቃሉ፤ በአግባቡም ሸማቾችን አያስተናግዱም፡፡ በተጨማሪም የሸማች መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ በሕግ ትምህርት ቤቶች የሸማች ጥበቃ ሕግ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ወይም በሌላ የትምህርት ዓይነት ውስጥ ተካቶ ቢሰጥ በሸማች ጥበቃ ሕግ የሠለጠኑ የሕግ ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል፡፡

ሌላው ለሸማች መብቶች መተግበር መወሰድ ያለበት እርምጃ ሕገወጥ ንግድን መከላከል ነው።ይህም ማለት ያለ ንግድ ፈቃድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለገበያ አለማቅረብ ነው፡፡ ምንም እንኳን በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውም ሰው የንግድ ሥራ እንዳይሠራ የተከለከለ ቢሆንም፤ ያለ ንግድ ፈቃድ የንግድ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ነጋዴዎች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡

ለእዚህ ችግር ቀላል ማሳያ ሊሆን የሚችለው በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የታወቀ አድራሻ የሌላቸው ነጋዴዎች ላይ የሸማች ጥበቃ ሕግን ተፈጻሚ ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የታወቀ አድራሻ ስለሌላቸው ጉዳት የደረሰበት ሸማች መብቱን ለማስከበር (ለምሳሌ ካሳ ለመጠየቅ) ቢፈልግ መክሰስ የሚፈልገውን ነጋዴ ድጋሚ ሊያገኘው ስለማይችል ነው፡፡ ስለዚህ ያለንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚደረግ ንግድን በተጠናከረ ሁኔታ መከላከል ይገባል፡፡

በገበያ ላይ ያለው የንግድ ውድድር ሕግን የተከተለ እንዲሆን ቢሠራ የሸማች መብቶችን ለማስከበር ትልቅ ሚና አለው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ (United Nations Con­ference on Trade and Development)በ2017 ‹‹Manual on Consumer Protection›› በሚል ርዕስ ባሳተመው ጥናት ላይ እንደተመለከተው፤ ጤናማ የንግድ ውድድር በዝቅተኛ ዋጋ፣ ጥራት ያላቸውና ብዙ ምርጫ ያላቸውን ዕቃዎችና አገልግሎቶች በገበያ ላይ እንዲያገኙ በማስቻል ሸማቾችን ይጠቅማል፡፡ በዚህም መሠረት በተግባር ላይ ያሉ ጤናማ የንግድ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርጉ አሠራሮችን በመቆጣጠር የኢትዮጵያ ሸማቾች በሕግ የተሰጧቸውን መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የሸማች ጥበቃ ሕግጋትን የሚያስፈጽሙ የመንግሥት አካላት (ባለሥልጣኑ፣ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት) ሠራተኞችም ሕግጋቱን ለማስፈጸም የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ተከታታይ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች ቢሰጧቸው ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም ለሚመለከታቸው አካላት የሚቀርቡ የሸማች መብት ጉዳዮች በፍጥነት የሚታዩበትና ውሳኔ የሚሰጥበት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ቢዘረጋ ይበጃል፡፡

ወደ ሀገራችን ስንመጣ በሸማቹ፣ በሸቀጥና አገልግሎት ሻጭ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ፣ ኢፍትሐዊ፣ መርህ አልባ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው። መንግሥትም ሆነ ሻጭ የየራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ይተጋሉ እንጂ ለሸማቹ ያን ያህል ደንታ የላቸውም ማለት ይቻላል። በተለይ መንግሥት በ“የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” አባዜ ነጋዴው ላይ የሚፈጥራቸው ማናቸውም ጫናዎች መዳረሻቸው ሸማቹ እንደሆነ እያወቀ እንኳ ጫናውን ቀለል ለማድረግ አጥጋቢ ጥረት ሲያደርግ አይስተዋልም።

ነጋዴው በግብይት ሰንሰለቱ ለተሰገሰጉ ደላላዎች ለሚከፍለው ኮሚሽን አያሳስበውም፤ አስልቶ ሸማቹ ላይ ይጥለዋል። ወደ ውጭ ልኮ ስለሚሸጠው ቡና፣ የቅባት እህል፣ የፋብሪካ ውጤት፣ ወዘተ… ዋጋ መውረድ አይጨነቅም። ከስሮ ሸጦ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ በአስመጪ ስም በሚያስገባው ሸቀጥ ለእዚያውም ጥራቱ እዚህ ግባ በማይባል በሳምፕል በተመረተ መናኛ ሸቀጥ ከ100 እስከ 1000 በመቶና ከእዚያ በላይ በማትረፍ ወደ ውጭ ሲልክ የከሰረውን በእጅ አዙር በብዙ እጥፍ የሸማቹን ጉሮሮ አንቆ ይቀበላል። በሀገሪቱ የትርፍ ሕዳግ የሚባል ነገር አይታወቅማ። ለነገሩ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ሲወሰን የወጪ ንግዱ አትራፊ እየሆነ ነው።

በዓለማችን የትርፍ ሕዳግ የሌላትም ሆነ በነፃ ገበያ ስም ስግብግብ ነጋዴ እንደ ፈለገ የሚፈንጭባት፣ የሚፋንንባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ትቀራለች? የነፃ ገበያ አባት በሚባሉት ምዕራባውያን እንኳ በማንኛውም ሸቀጥና አገልግሎት ላይ የትርፍ ሕዳግና የዋጋ ጣራ ተጥሎበት እያለ እኛ በመንግሥት ቸልተኝነት ፍዳችንን እንከፍላለን። በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተከሰተው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ቀማኛ የንግድ ሥርዓት የሸማቹን ታጋሽነት፣ ቻይነት በእጅጉ እየተፈታተነው ይገኛል።

የህንድን የሽንኩርት፣ የሱዳንን የዳቦ እና የቱኒዚያን አጠቃላይ የኑሮ ውድነት አብዮት ከአብዮቶች ሁሉ እናት ከፈረንሳይ አብዮት ጋር ቀምሮ ነገ የሚያመጣውን መዘዝ መዘንጋት አያስፈልግም። ሰሞኑን እንደ አዲስ ሸማቹ በስግብግብ ነጋዴዎች እና ሕገ ወጦች በቁም ሲገፈፍ መንግሥት መከላከል ሲገባው ችላ ማለትን መምረጡ ወቅታዊው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። በግብር ከፋዩ ዜጋ ገንዘብ ድጎማ በሌለ የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ዘይት፣ ሳይቀር ለስግብግቦች በአንድ ጀምበር መክበሪያ ሲሆን፤ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ እግሩን የሚጎትትበት ምክንያት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኖ ቀጥሏል።

ዓለም አቀፉ የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ሸማቾች የሚገበዩትን ምርት ወይም ሸቀጥ የመምረጥ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደመጥ፣ የመካስ፣ የጤነኝነት፣ የተሟሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን፣ አማራጭ አገልግሎትና ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ ስለሸቀጦችና አገልግሎቶች አጠቃቀም መረጃ የማግኘት፣ ወዘተ… መብት እንዳላቸው ያትታል። የሸማቾች ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1985 ስለ ሸማቾች መብት ጥበቃ ባወጣው እና አባል ሀገራት እንዲተገብሩት ጭምር በሚያሳስበው ሕግ ሀገራት፣መንግሥታት የሸማቾችን መብት፣ ጥቅም የሚያስከብሩ አሠራሮችንና አደረጃጀቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባል።

የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች የዋጋ ንረት የመጨረሻው ጫና የሚያርፈው በሸማቹ ላይ ነው። በኢትዮጵያ እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር፣ የሸማቹ ማኅበረሰብ መብት እንዳልተከበረና በእዚህም ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረገ ይገኛል። በአንጻሩ፣ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ ያለሙ በርካታ አዋጆች እና ሕጎች እንደወጡ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት(የግብይት ሥራ አመራር) ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጌቴ አንዱዓለም ያወሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አዋጆቹ እና ሕጎቹ፣ በሥራ ላይ ውለው በተጨባጭ ችግር ሲፈቱ እንዳልታዩ ለቪኦኤ ይገልጻሉ፡፡

በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፀረ ንግድ ውድድር እና የሕግ ጥሰት መከላከል ዴስክ ኃላፊ አቶ ጌትነት አሸናፊ በበኩላቸው፤ መንግሥት፣ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል፣ በዓመቱ ውስጥ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ መድቦ፣ ምርት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ አድርጓል ይላሉ፡፡ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅም፣ ልዩ ልዩ ሕጋዊ ርምጃዎችን እንደወሰደ በማውሳት፣ በመንግሥት ላይ የሚቀርበውን ወቀሳ ተከላክለዋል፡፡

ሻሎም!

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You