የትግራይ ወጣት ባልተገባ እሳቤ ታሪኩን አያጠለሽም!

በፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከሁሉም በላይ ጦርነት የማስቆም ዓላማ የነበረው ነው። በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ ጦርነት በራሱ ይዞት ከሚመጣው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋት እና ውድመት አኳያ ጦርነቱን ለማስቆም የተደረሰበት ውሳኔ ለመላው ሕዝባችን በተለይ ደግሞ የችግሩ ዋንኛ ገፈት ቀማሽ ለነበሩት የአማራ፣ የአፋር እና የትግራይ ሕዝብ ትርጉሙ ብዙ ነው።

የሰላም ስምምነቱ ጦርነቱ በሰው እና በንብረት ላይ ተጨማሪ ጥፋት እንዳያስከትል ከመርዳት ባለፈ ሕዝብን ከጥይት ድምጽ መታደግ አስችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር እና በውይይት መፍታት የሚያስችል ትልቅ ሀገራዊ ተሞክሮ፤ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሄ መሆን እንደሚችሉም ማሳያ ተደርጎም ተወስዷል።

የፌደራል መንግሥት ገና ከጅምሩ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ሰላማዊ አማራጮችን ሲከተል ቢቆይም፤ ሁኔታው ወደ ግጭት አምርቶ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል። በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን ሞት፤ ለከፍተኛ የሀገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆኗል። ጦርነቱ የፈጠረው የሥነ-ልቦና ስብራትም እስካሁን በአግባቡ አላገገመም።

ጦርነቱ ከፈጠረው ውድመት አኳያም ብዙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፤ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ እና ፍጥነት ወደ ሥራ ሊመለሱ አልቻሉም። ከዚህ የተነሳም ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ሊገኙ አልቻሉም። በከፋ የጤና ችግር ውስጥ ያሉም ፈውስ አጥተው እስከዛሬዋ ቀን ድረስ እስከ ስቃያቸው ያሉበት እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ አለመግባታቸውም አገልግሎት ፈላጊዎችን ለእንግልት ዳርገዋል፤ ራሱ የመንግሥት ሠራተኛውም ተረጋግቶ ወደ ሥራ ገብቶ በሙሉ ልቡ ሥራውን እንዳያከናውን ተግዳሮት ሆኖበታል። ይህም አጠቃላይ በሆነው በክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የፕሪቶሪያ ስምምነት በሚጠበቀው ደረጃ ተግባራዊ እንዳይሆን፣ በሕወሓት እና በውስጡ የተፈጠረው መከፋፋል ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። በዚህም የስምምነቱ ዋነኛ አካል የሆኑት ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ ሆነ በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራ ተስተጓጉሏል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እነዳስታወቁት ከሕወሓት የወጣ አንድ አንጃ ተፈናቃዮች ወደቀዬያቸው ተመልሰው ታጣቂዎች ወደመደበኛ ሕይወት የመመለሱ ሥራ እዳይሳካ አድርጓል ብለዋል።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር በተያያዘ ብዙ፣ በሁሉም በኩል ርብርብ በሚጠይቅበት በዚህ ወቅት፤ በሕወሓት በኩል የተፈጠረው አለመግባባት ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” በመሆን የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሆነውን የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ውስጥ የሚከትት ተጨማሪ ክስተት ብሎም ለሰላም ስምምነቱ ትግበራም ጋሬጣ ሆኗል።

ችግሩ ከቡድን አለመግባባት አልፎ ለሀገር እና ለሕዝብ፤ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ሌላ አስቸጋሪ የፈተና ጊዜዎችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል። የሀገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ውስጥ ለመክተት የሚጥሩ የውጪ ኃይሎችም ክስተቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውን ላልተገባ ጣልቃገብነት እያዘጋጁ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ችግሩ ከሁሉም በላይ የትግራይን ሕዝብ ያልተገባ ተጨማሪ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ይታመናል። በተለይም የትግራይን ወጣት ለከፋ አደጋ ተጋላጭ እንደሚያደርጉት ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

የትግራይ ወጣት አሁን ላይ ስለጦርነት አስከፊነት እንዲነገረው የሚጠብቅ አይደለም፤ ከቀደሙ የታሪክ ትርክቶችም ሆነ በቅርብ በራሱ ጊዜ በተፈጠሩ ግጭቶች የጦርነትን አሰከፊነት ከሚገባው በላይ መረዳት የቻለ፤ ለጦርነት እና ለጦርነት ዜማ እና ፉከራ የሚሆን አዕምሮም ሆነ ልብ እንዲሁም በጦርነት የሚያስጠብቀው ፍላጎት / መሻት የለውም።

ከዚህ ይልቅ የሚፈልገው ጦርነት ከፈጠረው የልብ ስብራት፣ የሕይወት ቁዘማ እና ድባቴ የሚያስወጣውን የሰላም እና የልማት መንገድ ነው። የሚፈልገው መሳሪያ ተሸክሞ ለትግራይ ሕዝብ ሆነ ለራሱ ምንም ሊፈጥር በማይችል ትርጉም አልባ ግጭት ውስጥ ገብቶ ራሱን መስዋዕት ማድረግ አይደለም። የሆነ ቡድን መሳሪያ በመሆን አጠቃላይ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ዛሬ እና ነገዎችን ማበላሸት አይደለም።

የትግራይ ወጣት ዘመኑን እንደሚዋጅ ትውልድ ግለሰቦች እና ቡድኖች ለፍላጎታቸው ጠላት አድርገው የሳሉዋቸውን አካላት ለመግጠም ለሚያሰሙት ”የተነስ ታጠቅ ” ዜማ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የራሱን እና የትግራይን ሕዝብ ብሩህ ነገዎች የሚያጨለም አይደለም። በተነስ ታጠቅ ዜማም ክቡር ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት የራሱን ታሪክ ባልተገባ እሳቤ የሚያጠለሽም አይደለም!

አዲስ ዘመን  መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You