
በአንድ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ያየሁት አንድ የባህር ማዶ ገጠመኝ የቤት እንስሳትን ባየሁ ቁጥር ትዝ ይለኛል። ነገሩ እንዲህ ነው:- በአሜሪካ ኮሎራዶ ውስጥ በሚገኝ አንድ የስጦታ መሸጫ መደብር ውስጥ አንዲት ያልታሰበች እንግዳ ድንገት ትመጣለች። ይህች እንግዳ በአካባቢው ከሚገኘው ጫካ እግር ጥሏት የመጣች አጋዘን ናት። እናም ይህች አጋዘን ልክ እንደቤቷ ሰተት ብላ ወደ መደብሩ ስትገባ ያየቻት የመደብሩ ባለቤት አላባረረቻትም። ይልቁንም እንኳን ደህና መጣሽ በሚል ስሜት ተቀብላት ከወንበሯ ተነስታ ዳበሰቻት፣ ኩኪስ ትበላ እንደሁ ብላ አውጥታ ሰጠቻት፡፡ አጋዘኗ የተሰጣትን ኩኪስ በላች እና ከመደብሩ ወጥታ ሄደች።
ከግማሽ ሰዓት በኋላም ያቺው አጋዘን ተመልሳ ኩኪስ ወደተሰጣት መደብር መጣች። አሁን ግን ብቻዋን አልነበረችም። እኔ የቀመስኩትን ይቅመሱ ብላ ነው መሰል ልጆቿንም አስከትላ ነበር የመጣችው።
“አዳኝ ብሆን ትሸሸኝ ነበር፤ ባባርራት ተመልሳ አትመጣም ነበር… ነገር ግን ለአጋዘኗ ጣፋጭ ኩኪስ ሰጠኋት። ይህን እሷ የቀመሰችውን ነገር ለልጆቿም እንድሰጥላት ልጆቿን አስከትላ መጣች ። በየትኛውም አጋጣሚ ለማንኛውም ፍጡር ፍቅርን ከመስጠት ወደኋላ አንበል” ስትል የመሸጫ መደብሩ ባለቤት ምስሉን በድረ ገፅ አጋርታለች፡፡
የእዚህች ሴትዮ ተግባር አስደናቂ ነው፤ ብዙዎችም ወደ ራሳቸው እንዲመለከቱ ያደረገ ትልቅ ትምህርት ነው። እንኳን የሰው ልጅ ለማዳ ያልሆኑ የዱር እንስሳት ፍቅር እንደሚፈልጉ ትልቅ ማሳያ ሆኖም ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ተቀባብለውታል። የሰው ልጅ ለየትኛውም ፍጡር ቢሆን ሳይለይ ፍቅር መስጠት እንዳለበት ከዚህ የበለጠ ትልቅ ምሳሌ የለም።
የኮሎራዶዋ ሴትዮ ለአጋዘኗ የሰጠችውን ፍቅር በማሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ለዱር አራዊት ለቤት እንስሳም የምንሰጠውን ቦታ መለስ ብዬ ሳስበው ትንሽ የተለየ ነው። እኛ ውሻ ያውም የማናውቀውን ድንገት መንገድ ስናይ በድንጋይ ማባረር እንደሚቀናን አንካካድም። እንደዚህ የምናደርግ ሰዎች ውሻው ይነክሰናል ወይም ያጠቃናል በሚል ስጋት አይደለም። ብቻ ባለቤት የሌለው ቢኖረውም ድንገት መንገድ ላይ የገጠመን ውሻ አይመቸንም። ይህ ልምድ ከየት እንደመጣና እንደዳበረ ምክንያታዊ ሃሳብ ማቅረብ አይቻልም።
እርግጥ ነው በእኛም ሀገር በርካታ ሰዎች የዱር አራዊትን አላምደው ፍቅር ሰጥተው አብረው ሲኖሩ የተመለከትንበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። የሐረር ጅቦች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ጅብ ብዙ ሰው የሚፈራውና በሰብአዊ ፍጡራን የማይወደድ አራዊት ነው። በእርግጥ ጅብ የሚወደድ አይነት እንስሳ አይደለም። ግን ደግሞ ካቀረብንና ከተንከባከብነው የአውሬነት ባህሪውን መግራትና ከእዚያም አልፎ የቱሪስት መስህብ መሆን እንደቻለ የሐረር ጅቦች ማሳያ ናቸው።
ከፈረንጆች ልንኮርጃቸው ከሚገቡ ልምዶች መካከል ለእንስሳት ያለን አመለካከትና የምንሰጠው ቦታ አንዱ ነው። እነሱ ለእንስሳት ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ። በተለይም ለውሻና ድመት የሚሰጡት ቦታ አስገራሚም የሚያስቀናም ነው። በኢትዮጵያም በተለይም ለውሻ የሚሰጠው ቦታ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እየተሻሻለ መጥቷል። ለእዚህ በመዲናችን አዲስ አበባ በአንዳንድ ጎዳናዎች ትንንሽ ውሾች ሲሸጡ ማየት እየተለመደ መምጣቱን መጥቀስ ይቻላል። ከጎዳና አልፎም የተለያዩ አይነት ውሾች በውድ ዋጋ የሚሸጡበት ቦታ እዚሁ አዲስ አበባ መኖሩን በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ መመልከቴን አስታውሳለሁ።
ሰዎች ውሻና ድመትን በዋናነት የሚንከባከቡትና የሚያቀርቡት ከእንስሳቱ የሚያገኙት አገልግሎት ስላለ ብቻ አይደለም። ትልቁ ምክንያታቸው ከእንስሳቱ የሚያገኙት ፍቅር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በብዛት ውሻ የምናሳድገው በራችን ላይ ቆሞ እንደ ዘበኛ እንዲያገለግለን ነው። ድመትንም ቢሆን አይጥን የመሳሰሉ ትንንሽ አጥፊ እንስሳትን እንድታድንልን እንጂ ለምትሰጠን ፍቅር ነው ብለን ደፍረን መናገር አንችልም። ያሳደግነው ውሻ ለማዳ ሆኖ ግቢያችን የገባ የወጣው ሰው ላይ ካልጮኸ ፈሪ ነው ተበላሽቷል ብለን አውጥተን የምንጥል ብዙ ነን። ድመትንም ቢሆን አይጥ አድና ትብላ ምግብ አትስጧት የሚሉ ሰዎች ገጥመውኝ ያውቃሉ። ይህ ትክክለኛ አመለካከት አለመሆኑን ለማስረዳት መድከም አያስፈልግም። ውሻን ማሳደግ ያለብን የሚሰጠንን ፍቅርና ታማኝነት በማሰብ መሆን ይገባል። ፈሪ ነው ብለን አውጥተን የምንጥለው ውሻ ከእኛ አልፎ የማህበረሰብ ችግር ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ተገቢ ነው። ምናልባት ስለማናስተውል ይሆናል እንጂ ውሻን ፈሪ ነው ብለን አውጥተን ባንጥለውና ብንንከባከበው እንዲጠብቅልን የምንፈልገውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። ባእድ የሆነ ነገር ሲያይ ፈሪም ይሁን ደፋር ጮኾ ለባለቤቱ ማሳወቁ ተፈጥሮው ነውና። ድመትም ብትሆን ምንም ያህል ብንንከባከባትና ብትጠግብ እንድታድንልን የምንፈልገውን አይጥ እየተመለከተች ዝም ብላ አትቀመጥም፤ ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ባህሪዋ ያስገድዳታልና።
እንዲያው ውሻና ድመትን ለምሳሌ አነሳን እንጂ ትልቅ አገልግሎት ለሚሰጡን የቤት እንስሳትም ቢሆን ያለን አመለካከትና የምንሰጠው ቦታ አስተዛዛቢ ነው። ለእዚህ ከአህያ የበለጠ ማሳያ ሊኖር አይችልም። አህያ አመመኝ ደከመኝ ሳትል የሰዎችን ሸክም ያቀለለች እንስሳ ነች፣ ለአንዳንዶችም የእንጀራ ገመድ ነች፣ ግን በእዚያ ልክ እንክብካቤ ሲሰጣት አይታይም። እንዲያውም ከአቅሟ በላይ ተሸክማ ቁና ቁና እየተነፈሰች ስታገለግል የሚወርድባት የዱላ መአት ምንያህል እንደሚያሳዝን ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ሳንመለከት አንቀርም። ተግታ ባገለገለች ስሟ የመጥፎ ስድብ መገለጫ ተደርጎ የምናይበት አጋጣሚም ብዙ ነው። ከአዲስ አበባ ትንሽ ወጣ ካልን ደግሞ አገልግለው ያረጁና የቆሳሰሉ የጋሪ ፈረሰኞች መሀል አስፋልት ላይ ቆመው ማየት እንግዳ አይደለም። እንደውም አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አይነት ፈረሶችን መሀል አስፋልት ላይ የሚያቆሟቸው ሆን ብለው እንደሆነ ሳንሰማ አንቀርም። ውሻም በሀገራችን እንደ መጥፎ ስድብ ይቆጠራል። ግን ደግሞ አሁን አሁን እየቀረ የመጣ ይምሰል እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች እናቶች የሚወዱትን ልጅ “ውሻዬ” ብለው ሲያቆላምጡና ፍቅራቸውን ሲገልጡ እንሰማለን።
ከእዚህ የምንረዳው በእንስሳት ላይ ያለን አመለካከት የተዛባ የሆነው ከጥንትም ጀምሮ አለመሆኑን ነው። መቼም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ነገስታት ስማቸውን ሳይቀር በፈረሶቻቸው ሲሰይሙ እንደነበር አይጠፋንም። ዛሬም ቢሆን የገጠሩ ሕዝብ ከእንስሳቱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። ታዲያ እኛ በተለይም ከተሞች አካባቢ የምንኖር ከየት አመጣነው? ለማንኛውም ፍጡር ፍቅር ከሰጠን ፍቅር እንደምንቀበል ግን መነሻችን ላይ ካነሳነው ከአጋዘኗ ገጠመኝ መማር አለብን፣ ሰው የዘራውን ያጭዳል እንደሚባለው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም