የኤክስ ደንበኞች ገጹን መክፈት እንዳልቻሉ ተገለጸ

ኤክስ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ባሉ ግዛቶች ሥራ አቋርጦ እንደነበር ተገለጸ፡፡ ከትናንት በስቲያ እንደታወቀው ከሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ገጹ መሥራት አቁሞ እንደነበር ሲገለጽ ፤በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቹ ኤክስን መክፈት እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡

በኤለን መስክ ስር ያለው የቀድሞው ቲዊተር የአሁኑ ኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መቋረጡን በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ የአሜሪካ ተጠቃሚዎች ሪፖርት እንደተደረገ ዳውንዲቴክተር የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም እንደዚሁ ከስምንት ሺህ በላይ ሪፖርቶች መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በገጽ ላይ ባጋጠመ መቆራረጥ ማህበራዊ ሚዲያውን ለመጠቀም የሞከሩ ሰዎች ገጹ ላይ አዳዲስ መረጃዎችን ማግኘት እንዳልቻሉ እንዲሁም ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ገጹ ላይ መቆራረጥ እንደተስተዋለ ተናግረዋል፡፡ ኤለን መስክ በበኩሉ የአገልግሎት መቋረጡ የተከሰተው ከዩክሬን አካባቢ በተቃጣ ከፍተኛ የበይነ መረብ ጥቃት ምክንያት እንደሆነ መናገሩ ተሰምቷል፡፡

ዩክሬንን እና ፕሬዚዳንቷን ቮሎድሚር ዘለንስኪን በመተቸት የሚታወቀው ኤለን መስክ ላቀረበው ክስ ማስረጃ ያላቀረበ ሲሆን በኤክስ ገጹ ላይ ለተፈጠረው ወቅታዊ መቆራረጥ ግን ከዩክሬን የተቃጣን ጥቃት ምክንያት አድርጓል፡፡ ሌሎች የተሳተፉ የውጭ ሃይሎች ስለመኖራቸው ያለው ነገር ባይኖርም ‹ከዩክሬን አካባቢ የተቃጣ ኤክስ ማህበራዊ ገጽን ለማስቆም ያለመ ትልቅ የበይነ መረብ ጥቃት› መፈጠሩን የገለጸ ሲሆን በማከልም ‹የተደራጀ እና ትልቅ ቡድን ወይም ደግሞ ለዚህ ጥቃት ብቁ የሆነ ሀገር እጁ አለበት› በማለት በኤክስ ገጹ ላይ መልዕክት ማጋራቱ ታውቋል፡፡

የድረ-ገጾችን ትስስር የሚቆጣጠረው ኔት ብሎክስ ዳይሬክተር አልፕ ቶከር እንዳለው ከሆነ ‹ኤክስ የተቋረጠው በበይነ መረብ ጥቃት ሊሆን ይችላል› በማለት ሲናገር አያይዞም ‹ስድስት ሰዓት ገደማ የቆየው የኤክስ አገልግሎት መቋረጥ በመላው ዓለም ከፍተኛ የሚባል ተጽዕኖ አሳድሯል› ሲል ገልጿል፡፡

ማህበራዊ መገልገያ ድረ-ገጽ ካለው ተጠቃሚ እና ተደራሽነት አኳያ በሚገጥመው እክልም የሚያስተጓጉለው ብዙ ነገር እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን ኤክስ ገጽም በተቋረጠባቸው ስድስት ሰዓታት ውስጥ በአገልግሎቱ እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑ ደንበኞች ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖን ማስተናገዱ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለብዙዎች ለመረጃ ምንጭነት እያገለገሉ ያሉ እንደኤክስ ያሉ ገጾች በርካታ ፖለቲከኞች እና መሰል ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሃሳባቸውን በቀላሉ ለተከታዮቻቸው የሚያጋሩበት ተመራጭ የመገናኛ መንገድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የኤክስ ባለቤት ባለጸጋው ኤለን መስክ ከዚህ ቀደም ኤክስ አገልግሎት እንዲቋረጥ የሚያደርግ ዲዲኦኤስ ሙከራ እንደተደረገ ገልጾ፤ ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ እውነትነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳልተገኘ ሲታወስ ከትናንት በስቲያ የተከሰተውን የአገልግሎት መቆራረጥ ተከትሎ በሰጠው አስተያየት የአሪዞና የሕዝብ እንደራሴ የሆነው ማርክ ኬሊን ከሀዲ ነው ሲል እንደከሰሰ ተረጋግጧል፡፡

የሕዝብ እንደራሴው ማርክ ኬሊ በባለጸጋው ኤለን መስክ ለውረፋ የበቁትም ለጉብኝት ወደ ዩክሬን መሄዳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሕዝብ እንደራሴው በምላሹ ‹ነጻነትን መጠበቅ አሜሪካን ታላቅ እና ደህንነቷ የተጠበቀ እንደሚያደርጋት የማትረዳ ከሆነ ሥራውን ለእኛ ተውልን› በማለት ለመስክ የመልስ ምት በኤክስ ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው ታውቋል፡፡

ከዶናልድ ትራምፕ መመረጥ በኋላ ፖለቲካዊ ይዘቶች ላይ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው መስክ፤ አነጋጋሪ ድርጊቶችን በመፈጸም ስሙ እየተወሳ ይገኛል፡፡ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ባለፉት ሶስት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ዘለንስኪ ሰላም ወዳድ አይደለም የሚለውን የትራምፕን አቋም በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ነው፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You