የገበያው ድምቀት- የቤታቸው መሠረት የሆኑ እንስቶች

በሾላ ገበያ ግብይቱ ደርቷል። ሁሉም የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ለማሟላት ተፍ ተፍ ላይ ነው። ሸማቾች ጓዳቸውን ለመሙላት፤ ሻጮችም የገዢዎችን ይሁንታ አግኝተው ጎጇቸውን ለማቃናት ቦታው ላይ ተገናኝተዋል። የተለያዩ እጣዎችን እያወጡ ኑሯቸውን የሚደጉሙ ወጣቶችም አንድ የቀረች… እያሉ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ይጥራሉ። በለስ ቀንቷቸው ትኬታቸውን ሸጠው እስኪጨርሱ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉም።

ዘመናዊና ባህላዊ ልብስ ስፌት፣ የባልትና ውጤቶች፣ ዶሮና እንቁላል፣ ምንጣፍና መጋረጃ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ነገሮች በሾላ ገበያ ይገኛሉ። የሻጩም የገዢውም ቁጥር ብዙ ነው። ‹‹ሾላ ላይ የሌለው የለም ብቻ ነው›› ይላሉ ተገበያዮች የገበያውን ሁኔታ ሲገልጹ። ቦታው ላይ የተገኘነው በንግድ ሥራ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሰዎች ውጣ ወረዳቸውንና ስኬታቸውን ለመቃኘት ነው።

የባልትና ውጤቶች መሸጫ ሱቅ ውስጥ ጠጋ ብለን ሰላምታ ሰጠናቸውና የሕይወት ልምዳቸውን እንዲያጋሩን ጠየቅናቸው። እናትነትን፣ ሩህሩህነትና ደግነትን በሚያሳብቅ ፈገግታ ፈቃደኝነታቸውን ገለጹልን።

ወይዘሮ ትዕግስት በንቲ ይባላሉ። ለ30 ዓመታት በባልትና ውጤቶች ንግድ ላይ አሳልፈዋል። ሥራው ልፋትና ድካም ቢኖረውም ዝቅ ብዬ ሠርቼ ከፍ ብዬ እንድኖር አስችሎኛል። ሠርቼ መግባቴም ከባለቤቴ እኩል በቤቴ ጉዳይ እንድወስን፣ የኢኮኖሚ ነጻነቴንም እንዳረጋግጥ አግዞኛል ይላሉ።

ሞት አይቁጠራቸውና ከልጅነት ባሌ በርከት ያሉ ልጆችን አፍርቻለሁ የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ከባለቤታቸው ጋር ተባብረው መሥራታቸው ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። ልጆቻቸውም ይህን ባህል አድርገው መውሰዳቸውን ይጠቅሳሉ።

እንደ ታታሪዋ እናት ገለጻ፤ ሴትነት የጥንካሬ፣ ጥበብና ታታሪነት ምልክት ነው። በመሆኑም መውለድና የእድሜ መግፋት ከሥራቸው ሳያስተጓጉላቸው ዛሬም ድረስ ሕይወትን ለማሸነፍ ይታትራሉ።

በእሳቸው ወጣትነት ከነበረው ይልቅ ዛሬ ሴቶች ተምረው መመረቅ ፣ ሠርተው መለወጥ እና ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን የሚጠቅሱት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ይህን መልካም አጋጣሚ ሳያባክኑ በየተሠማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሸክላና የእጅ ሥራ ውጤቶችን ሲሸጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ዘመድ ቢሰጥ በበኩላቸው፤ ሥራውን ከልጅነታቸው ጀምሮ ከእናታቸው ጋር ሆነው ሲሠሩት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ላለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ ሱቁን ተረክበው እየሠሩ መሆኑን የሚጠቅሱት ወይዘሮ ዘመድ፤ ለባህላዊ እቃዎች ያለው ተቀባይነት እያደገ መምጣት ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።

በዚህ ሥራ አንድ ልጃቸውን በሚፈልጉት መንገድ እያሳደጉና እያስተማሩ መሆኑን የሚጠቁሙት ወይዘሮ ዘመድ፤ ሥራውን ከዚህም በላይ አስፍተው ለመሥራት የፋይናንስ አቅርቦት እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ሰበብ አድርገው ወደ ኋላ ማለት አልፈለጉም። በመሆኑም ከሚያገኙት ገቢ ላይ እቁብ በመጣል ሥራቸውን ለማሳደግ ትልም አስቀምጠው እየሠሩ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሥራ መሥራት ለአእምሮ እረፍት፣ ለኑሮም መሠረት ነው የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ሴት ልጅ ብዙ ነገር ያስፈልጋታል። ለዚህ ፍላጎቷ መሟላት ደግሞ ጠንክራ መሥራት ይኖርባታል ። ይህን ማድረግ ካልቻለች ግን ለሌሎች የኢኮኖሚ ጥገኛ ትሆንና ሕይወቷን በምትፈልገው መልኩ መምራት አትችልም ይላሉ።

ሴቶች ከፍ ያለ ትዕግስተኝነት፣ ፈተናዎችን የመሻገሪያ ጥበብና ጥንካሬ አላቸው የሚሉት ወይዘሮ ዘመድ፤ ይህን ተፈጥሯችንን ወደ ሥራ መለወጥና ነጋችንን የተሻለ ለማድረግ መትጋት ይገባናል ሲሉ ይናገራሉ።

ዘመኑ የፈጠራቸውን ቴክኖሎጂዎችም ጊዜያችንን የምናባክንባቸው ሳይሆን ሥራችንን ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You