የሴቶችን ቀን ከማክበር ባሻገር

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ ግድያና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች መጨመራቸውን በሠብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የተለያዩ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበራት መረጃዎች ያሳያሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በጾታዊ ጥቃት ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ አካላቸው የሚጎድል ሴቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን በየጊዜው በማህበራዊ ሚዲያዎች የምናየውና የምንሰማው ነገር አንዱ ማሳያ ነው። ይህ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሰለባ በሆኑት ሴቶች ላይ ከማስከተሉም ባሻገር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወት እስከማሳጣት የሚያደርስ ነው፡፡

መንግሥትና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ ለመሄዱ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የጥቃቶች መደጋገምና አሳሳቢነት (ለምሳሌ በአሲድ የሴቶችን ገጽታ ማበላሸትና የነበራቸውን ሙሉ ጤንነት ማሳጣት) እንዲሁም አዳዲስ የጥቃት ዓይነቶች መምጣትም ሁላችንም እየታዘብነው ያለ ዕውነታ ነው፡፡ በተለይም በሚያሳዝንና በሚያሰቅቅ ሁኔታ በአብዛኛው ግድያው የሚፈጸመው በቅርብ ወዳጅ፣ በትዳር አጋር መሆኑ ነው።

ይህ ለቀጣዩ ትውልድም ስለ ትዳር ሕይወት ያለውን አዎንታዊ አመለካከት የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ የማኅበረሰብ ዋና ምሰሶ የሆነውን ቤተሰብ የሚያናጋና ማኅበራዊ መስተጋብርን ገደል የሚከት መሆኑ ይበልጥ አሳሳቢ ነው።

በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቁጥሩ እንደጨመረ ለመረዳት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጋር የሕግ ድጋፍ ፈልገው የሚሄዱ ተጠቂዎችን ብዛት መመልከት በቂ ነው። ማኅበሩ በፈረንጆች 2022 ዓ.ም. ብቻ በቢሮዎቹ ከተደረጉለት የእርዱኝ ጥያቄዎች 47ቱ የግድያ እና ግድያ ሙከራዎች ሲሆኑ፣ 32 አስገድዶ መድፈሮች እንዲሁም 158 በሴቶች ላይ የደረሱ አሰቃቂ ድብደባዎች መሆናቸውን የገለፀበትን መረጃ መመልከት ይቻላል።

ማህበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያሉት በተወሰኑ ከተሞች ወይም አካባቢዎች እንጂ በሁሉም ቦታ አይደለም። ስለዚህ ሀገር አቀፍ የሆነ ጥናት ቢደረግ ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሚሆን ከዚህ መገመት አይከብድም። አሁን ልብ ማለት የሚኖርብን ወደ ማህበሩ የሚመጡት የድረሱልኝ ጥሪዎች በሀገር ደረጃ እዚህ ግባ የሚባሉ አለመሆናቸውን ነው። ይህ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የጥቃት መደጋገም ነገሩ ‘የተለመደ’ እንዲሆን እያደረገው ይመስላል።

ጾታዊ ጥቃት ‘ያው ያለ ነው’ እየተባለ መታለፍ ከተጀመረ የማኅበረሰብ ዝቅጠት መባቻ ነው የሚሆነው። ይህ ሁሉንም ሰው ካላስደነገጠና ካላስቆጣ እንዲሁም ለመፍትሄ እንድንረባረብ ካላደረገ የከፋ መዘዝ አለው።

ቀደም ሲል የምናያቸውና የምንሰማቸው ውግዘቶች፤ በሀገር ደረጃ የሚሰሙ ጩኸቶች፣ ጥቃቶች እንዳይደገሙ የሚያስብሉ ብሔራዊ ኀዘኖች፣ ይመለከተኛል የሚሉ መቆርቆሮች እየጠፉና እየከሰሙ ነው። ጥቂቶች ብቻ ያውም አንድ ጥቃት ሲፈፀም ጠብቀው ድምፅ ማሰማታቸው እየተለመደ መጥቷል።

ይባስ ብሎ በእህቶቻችን ሞት መቆጨቱ ቀርቶ አሁን አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ አጥቂውን፣ ‘ደግ አረገ’ የሚሉ ድምጾች መስተጋባት ጀምረዋል። ከአሰቃቂ የሴቶች ጥቃት ማግስት “እና ምን ይጠበስ?” ዓይነት ስሜቶች ከተስተጋቡ ለአንድ ማኅበረሰብ የሞራል ዝቅጠት ምልክቶች ናቸው። አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው። የቁልቁለት መንገዱን እንደጀመርን ማሳያዎች ናቸው።

በቅርብ ያየናቸውና የሰማናቸው ለምሳሌ፣ “የእሱን ማን አየለት”፣ “ይሄኔ አቃጥላው ነው የሚሆነው” የሚሉ አስተያየቶች ለተጠቂ ሁለት ጊዜ ሞት ነው። አዎ እንዲህ ዓይነት ከአጥቂ ጎን የሚቆሙ አስተያየቶች መበርከታቸውን ልንሸሽግ አንችልም። ልንረዳ የሚገባው ግን ሴቷ ምንም ዓይነት በሞራል ተቀባይነት የለውም የምንለውን ነገር ብትፈጽም እንኳ ወንዱ እሷን የመግደል ወይም የማጥቃት መብትን እንደማያጎናፅፈው ነው። የመግደል መብት የሚሰጥ ጥፋት የለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰማናቸው ጥቃቶች ምን ያመሳስላቸዋል ካልን የቅርብ በሚባል ሰው መፈጸማቸው ነው። ባል፣ የእንጀራ አባት፣ ፍቅረኛ፣ እጮኛ፣ ወዘተ። አንዱ ፈተናም ይኸው ነው። ጥቃቶቹ በብዛት ተጠቂዎቹ ‘የእኔ!’ በሚሉት ሰው ነው የሚፈጸሙት። ነገሩን አስቸጋሪ የሚያደርገውም ይኸው ነው። ሰው አደጋ ሲገጥመው ሮጦ ከለላ የሚፈልገው ከቤተሰቡ ነው።

ባሎች፣ የፍቅር አጋሮች፣ እጮኛ፣ አባት የቤተሰብ አካል ናቸው። አደጋ ጣይ እነሱው ሲሆኑ ወዴት ይኬዳል?ሴቶች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ጥቃትን ቀድሞ ለማነፍነፍም ፈታኝ የሆነውም ለዚሁ ነው። ከለላ ሰጪዎች ራሳቸው አጥቂዎቹ ስለሚሆኑ ነው። ባእድ ከሆነ ጠላት ይሸሻል፤ ቤት ውስጥ ካለ ወገኔ ከምንለው ሰው ግን ወዴት ይሸሻል?

በእርግጥ በራስ ሰው መጠቃት አጥቂውን ቶሎ ለፖሊስ አካል ሪፖርት ለማድረግ ማመንታት ውስጥ ሊከት ይችላል። ነገር ግን አንዳንዶቹ ጥቃቶች ለፖሊስ ሪፖርት ተደርገውም ነው ኋላ ላይ ትልቁን መዘዝ ይዘው የሚመጡት። ቶሎ ርምጃ ስለማይወሰድ። ከሕግ አስፈጻሚው በኩል ክፍተት የለም ለማለት አይቻልም። ፖሊስ መረጃ የሚሰበስብበት መንገድ፤ ለማኅበረሰብ ጠንቅ የሆነን ሰው የሚከታተልበት መልክ ይበልጥ መዘመን አለበት።

በዚህ ዙሪያ እጁን ያነሳባት ሴት ጋር እንዳይቀርብ የሚያደርጉ ሕጎችን አልተለማመድንም። ከዚህ አንጻር የሕግ አስፈጻሚ አካላት ቸልተኝነት፣ ንቃት፣ ግንዛቤ ማነስ ሊኖር ይችላል።

የችግሩ ስር መሠረት አንድ አስፈጻሚ አካል ላይ የሚደፈደፍ ግን አይደለም። የችግሩ ክፍተት ፖሊስ ብቻ ነው ካልን ስህተት ላይ እንወድቃለን። ችግሩ ውስብስብ ነው። አንዱ ላይ ብቻ አድብተን ከሠራንም ችግሩ አንቀርም።

ከሕጉ በኩል፣ ሕጉን ከማስፈጸም በኩል፣ አስተማሪ ቅጣት ካለመወሰን ወዘተ ጥቃቶች ተበራክተው ይሆናል። ስር መሠረቱ ግን በዋናነት ሴትን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ማኅበረሰብ ነው። ጥቃት አድራሹም ያደገበት ማኅበረሰብ ውጤት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የሴቶች ጥቃት መጨመር ዋናው መንስዔ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው አድሏዊ አመለካከት መሆኑን ማስተባበል አያስፈልግም። ይህም ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ አመለካከት፣ በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል፣ ሱስ፣ መጠጥና አደንዛዥ ዕፆች ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ለዚህም ከሕግ ክፍተቶች በተጨማሪ በእጅጉ የሚስተዋለው የአፈጻጸምና ያሉትን ሕጎች የመተግበር ችግር እንዲሁም በጥቃት አድራሾች ላይ አስተማሪ የሆኑ ቅጣቶች አለመወሰናቸው እንዲባባስ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው።

የሕግ ባለሙያ ለጥቃቱ መበራከት የሕጉ ክፍተት ብቻ መንስኤ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ሁሉም ላይ መሠራት አለበት። ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ፣ እንደ ማኅበረሰብ ራሳችንን ስንፈትሽ፣ ለሴቶች ያለን አመለካከት ሲቀየር፣ በባህላችን ውስጥ ልክ ነው ያልነው ልክ እንዳልሆነ ሲገባን ጥቃቶች ቀስ በቀስ ሊቀንሱ ይችሉ ይሆናል።

ችግሩ የሚያሳየው በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ እንዳልሆነ፣ ሌሎች ጥቃቱን ለመከላከልም ሆነ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀየስ እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው፡፡ ስለዚህም የሴቶችን ቀን ከማክበር ባሻገር እንደሕዝብ ፆታን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎችን ማስቀረትና የሚወጡ ሕጎች ላይም በአግባቡ ክትትል የማድረግ ሃላፊነት እንዳለብን አንዘንጋ።

ፋናዬ በጅቷል

አዲስ ዘመን  መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You