
የዘመናዊ ትምህርት አጀማመር በኢትዮጵያ አወዛጋቢ የሚመስል ታሪካዊ ዳራ ቢኖረውም አብዛኛው ሰነድ እና ጥናት እንደሚያሳየው ግን በ 19ኛው መቶ ዓመት መባቻ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መጀመሩን መረዳት ይቻላል፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚገልጹት፤ ከኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት በኋላ ሀገሪቱ ከአውሮፓውያን ጋር የነበራት ግንኙነት ከፍ ያለበት ወቅት ነበር፡፡
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከውጪ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በመጨመሩ ዘመናዊነትን ለመረዳት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ የዘመናዊ ትምህርትን አስፈላጊነት እና የስልጣኔ መሠረትነት በመረዳት የተለያዩ አዋጆችን በማውጣት በዘመናዊ መልክ ትምህርት እንዲጀመር አደረጉ፡፡ በዚህም በ1906 የወጣውን አዋጅ ተከትሎ በ1908 ዓ.ም የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተጀመረ፡፡ በ1913 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሐረር፣ ደሴ እና አንኮበር ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጀመሩ፡፡
ታሪካዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የተገነባው በንጉሱ የግል ገንዘብ ሲሆን፤ ይህም ለትምህርት የሰጡትን ትልቅ ትኩረት ያሳያል።
በዚህ ወቅት በመደበኛነት ሲሰጡ የነበሩ የትምህርት አይነቶች አማርኛ፣ አረብኛ፣ ግዕዝ፣ ጣሊያንኛ፣ ሒሳብ፣ ሳይንስ እና ስፖርት ነበሩ፡፡ ሌላኛው ንጉሱ የትምህርትን አስፈላጊነት ያሳዩበት ነጥብ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የሚያስገድድ አዋጅ በተከታታይ ያወጡ ነበር፡፡
ለማሳያነትም “ልጁን ትምህርት ቤት የማያስተምር ሀብቱ ይወረስበታል” የሚለውን አዋጅ ማውሳት ይቻላል። ከእሳቸው ተከትለው የመጡት አፄ ኃይለ ሥላሴም ትምህርትን አጠናክረው በመቀጠል በ1930 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን አቋቋሙ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የትምህርት ጉዳዮችን ሲያማክር የኖረው አሜሪካዊው ኤርነስት ወርክ የትምህርት ቆይታን በዓመታት አስልቶ አቅርቧል፡፡ ስድስት (6) ዓመት ለመጀመሪያ ትምህርት፣ ስድስት (6) ዓመት ለሁለተኛ ደረጃ እና አራት (4) ዓመት ለዩኒቨርሲቲ መማሪያ ብሎ አስተዋውቋል፡፡ የትምህርት ጉዳይ እየሰፋ እና አስፈላጊነቱም ግልፅ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ አፄ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት በሚኒስቴር ደረጃ እንዲመራ ትምህርት ሚኒስቴርን አቋቋሙ፡፡
ከላይ በተመለከተው አኳኋን የተጀመረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን እና ፖሊሲዎችን እየቀረፀ ትምህርትን የተሻለ፣ ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ የተለያዩ መንግሥታት እንደየ ፖሊሲዎቻቸው አግባብ ብዙ ለውጦችን እያደረጉበት የቆዬ ተቋም ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት መስራችነቷ እና አባልነቷ ብሎም በትምህርት ዘርፍም ያሳየችው ታሪካዊ ቁርጠኝነት ጉልህ በመሆኑ እንደ አባልነቷ በኅብረቱ የሚወሰኑ እና የሚታቀዱ እቅዶችን ወደራሷ በማምጣት ስትተገብር ቆይታለች፡፡ በ2063ቱ አህጉራዊ እቅድ መሰረትም የአፍሪካ ሀገራት ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተጠቀሰው ዓመት ጥራቱን የጠበቀ ችግር ፈቺ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት እና የሰው ሀብት ማፍራት መቻል የሚለውን ለማሳካት የድርሻዋን ለመወጣት የተለያዩ እቅዶችን በፖሊሲ እና በአዋጅ እያስቀመጠች ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡
የትምህርት ጥራት ሀገራዊ እና አህጉራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው በ2015 “Sustainable Development Goal” በሚል መሪ ቃል በጄኔቫ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከተቀመጡት 17 ጎሎች ውስጥ በአራተኛ ደረጃ ላይ የተጠቀሰው “ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” የሚል ነው፡፡ በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ 193 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ፈራሚ ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ይህን እስከ 2030 ለመፈፀም በሥራ ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ገምግማለች፡፡
ይሄን አላማ ባገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያ ችግር ፈቺ እና በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ ትውልድ ለመቅረፅ በሚያስችል አግባብ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ በሱ ልክ እየተመራች ትገኛለች፡፡ ከለውጡ በፊት የትምህርት ተደራሽነት መልካም ሊባል የሚችል ቢሆንም ተፈላጊው ጥራት ግን ዝቅተኛ ነበር ይላሉ ያናገርኳቸው በትምህርት ሚኒስቴር የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዳይሬክተር እዮብ አየነው (ፒ ኤች ዲ)፡፡ ለውጡ ከተደረገ በኋላ የጥራት ጉዳይ ትልቁ የትምህርት ስብራት መሆኑ ስለታመነበት ጉዳዩ በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ መፍትሔ ጠቋሚ በሆነ አግባብ እንዲቃኝ ሁለት ቡድኖች ተቋቁመዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያው ቡድን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ የተደረገ ጥናት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በአጠቃላይ ትምህርት ዙሪያ የተደረገ ጥናት ነበር፡፡ በተደረገው ጥናትም በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ የትምህርት ጥራት ችግር በሰፊው ታይቷል በማለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዋናነት የተለዩ ስብራቶች እና የተወሰዱ ሪፎርሞች ምንድን ናቸው? ውጤታማነታቸውስ እንዴት ይገለጻል? እነዚህን ጥያቄዎች በሁለት ከፍዬ አሳያለሁ፡፡ ትምህርት ስንል ጠቅለል ባለ መልኩ ከፍተኛ ትምህርትን እና አጠቃላይ ትምህርትን ይይዛል፡፡ በአጠቃላይ ትምህርት ላይ የተሰመረባቸው ስብራቶች እና የተወሰዱ ርምጃዎች ምን እንደሆኑ እንመልከት፡፡
በአጠቃላይ ትምህርት ላይ በተደረጉ ጥናቶች ላይ የትምህርት ጥራት ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ ይህን በመገንዘብ የታየውን ስብራት ለመጠገን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ማሻሻያዎች እና ፖሊሲዎች በየጊዜው እየተደረጉ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፣ በመሠራትም ላይ ናቸው፡፡
ወ/ሮ አየለች እሸቴ በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጋር በነበረኝ ቆይታ እንደገለጹት፤ የትምህርት ፍኖተ ካርታውን መሰረት በማድረግ በ2015 ዓ.ም የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ ፀድቋል፡፡ በመቀጠል ካሪኩለም የማሻሻል ሥራ እንደተሠራ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ለውጥ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል አዲሱን ካሪኩለም መቀየር ተችሏል፡፡
ይህ የካሪኩለም ለውጥ የተደረገው በነበረው ካሪኩለም ውስጥ የዜጎች ሥራ የመፍጠር ችሎታ፣ ሀገር ወዳድነት፣ ታማኝነት፣ በምክንያት ማመን፣ ለተሠማሩበት ሥራ እና ሥነምግባር ምስጉን መሆን፣ በዙሪያቸው ካለው ጋር የሚከባበሩ መሆን እና የመሳሰሉት የቀነሱበት የትምህርት ካሪኩለም እንደነበር ስለተለየ እና ይህን ስብራት ለመጠገን የተደረገ ማሻሻያ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡
በካሪኩለሙ እነዚህ የተለዩ ጉዳዮችን ለማስተካከል ከመሠራቱም ባሻገር ሀገር በቀል እውቀቶችንም በማካተት ሀገራዊ ቅኝትን የያዘ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደገለጹት፤ የተዘረዘሩትን ስብራቶች ለመጠገን አዲሱ ካሪኩለም ቅድመ 1ኛ ላይ የሥነ ምግባር ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለመፍጠር የሙያ ትምህርት 11ኛ ክፍል ላይ መሰጠት ተጀምሯል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት ሥራ እና ተግባርን እንደ አንድ የትምህርት አይነት 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ላይ እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተደረገው ጥናት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸው አንዱ ግኝት ነበር፡፡ ይሄ ሲባል በተለይም የተለዩት ስብራቶች ይዘት እና የማስተማር ሥነ ዘዴ ላይ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከ9-12 ክፍል አስተማሪዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተለይም ወደ 53 ሺ ለሚጠጉ ለተፈጥሮ ሳይንስ እና ቋንቋ መምህራን የማብቃት ሥራ ተሠርቷል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ ከ27 ቢሊዮን በላይ ሀብት በማሰባሰብ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን ከነ ግብአታቸው መገንባት ተችሏል፡፡ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበሩ ትምህርት ቤቶችም የደረጃ ማሻሻል እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ ኩረጃን የሚፀየፍ፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ችግር ፈቺ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ተሠቶ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ውጤታማነትን ለመጨመርም ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል፡፡ ለፖሊሲዎች ተፈፃሚነት ሁሉም አካላት በተለይም ወላጆች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የልጆቻቸው ዕጣ ፋንታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ ደግሞ በትምህርት ፍኖተ ካርታው ከተነሱ 7 መሠረታዊ ጭብጦች መካከል የትምህርት ጥራት አንደኛው ነው፡፡ በዚህም ጥናት መሠረት በመንግሥትም ሆነ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱ በጣም ዝቅተኛ እንደነበረ ተመላክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር አቶ ኮራ ጡሽኔ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር በነበረኝ ቆይታ ለመረዳት እንደቻልኩት ሲሠራበት የቆየው የትምህርት ሥርዓት በክህሎት ደካማ ስለነበር በኢኮኖሚው ላይ ሊጨበጥ የሚችል ለውጥ አላመጣም። የተደረገው ጥናትም ይህንኑ አሳይቷል፡፡
የትምህርት ፍኖተ ካርታው ከዚህ እውነታ ላይ በመነሳት የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ መሻሻል/መቀየር አለበት ወደሚል አቅጣጫ አመራ፡፡ በዚህም አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ተቀርፆ በ2015 ዓ.ም ፀደቀ፡፡ ከትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲው መቀየር ጋር ተያይዞ የተለያዩ አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን የመከለስ/ አዲስ የማዘጋጀት ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህም ባለፈ የተፈጠረውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን በመደበኛ ሥራ እና አካሄድ ለመተግበር ስለማይቻል የተለየ ትኩረትና አካሄድ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በመለየት የሪፎርም ሥራዎችን መሥራት አስፈላጊ ስለነበር የለውጥ ሥራዎችን በመለየት በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ከእዮብ አየነው (ዶ/ር) ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡ ከእነዚህ የለውጥ ሥራዎች መካከል፡-
የመጀመሪያው የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ (Autonomous) ማድረግ ሲሆን፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ ሆነው የተቋማቸውን ሥራዎች ማለትም መማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ጥራት ባለው መልኩ እንዲሰሩ የተሻለ ኃላፊነት በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተያዘውን ሥራ በአግባቡ እንዲያከናውኑ ማስቻል ነው፡፡ በዚህም የለውጥ ሥራ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ይህንን ለማስፈፀም የሚያስችል ደንብም በ2016 ዓ.ም ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በቀጣይ ጊዜም ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሂደት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሆኑ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ኃላፊዎቹ፡፡
ሁለተኛ የለውጥ ሥራ ተቋማትን በተልእኮ የመለየት ሥራ ነው፡፡ ሚኒስቴር ዴኤታው እንደገለጹት፤ አሁን ያሉት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሯቸው የትምህርት ፕሮግራሞች በጣም የበዙና ተቋም ከተቋም የተለያዩ ሳይሆኑ ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በአባዛኛው በሁለም ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ በየተቋሙ የትምህርት ፕሮግራሞች ስለሚበዙ እና ለትምህርት ጥራት መውረድ አስተዋፅኦ አድርገዋል ተብሎ ስለሚታመን ተቋማትን በተልዕኮ የመለየት ሥራ ተሠርቶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
በዚህም መሠረት ተቋማትን የምርምር ዩኒቨርሲቲ፣ የተግባር፣ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ (Applied University) እና አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ (Comprehensive University) ተብለው ተለይተው እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይህም አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በብቃት የሰለጠነ ባለሙያ ለማግኘት እንቅፋት መሆኑ ከተለየ በኋላ የተወሰደ ሪፎርም ነው። ስለዚህ ተቋማት ባላቸው ልምድ እና ተፈጥሮ ላይ በማተኮር መለየት የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ እንዱ የመፍትሔ አካል ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ሦስተኛው ተቋማት መረጃዎቻቸውን ዲጂታላይዝ ማድረግ አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ የተማሪ፣ የአስተማሪ እና የመማር ማስተማር ጉዳይ በዲጂታል መልክ ሆኖ ትምህርት ሚኒስቴርም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ሊዚህ ማስተግበሪያ HEIMS የተሰኘ ማስፈፀሚያ ተዘጋጅቶ ከ2013 ጀምሮ የመንግሥትም የግልም ተቋማት መረጃዎቻቸውን ወደ ሚኒስቴሩ እያስገቡ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ይህ ሪፎርም የተደረገው የመረጃ ፍሰት እና አያያዝ ላይ ስብራት መኖሩ በጥናቱ ስለተደረሰበት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አራተኛው ጉዳይ አሰስመንት ሜትዶችን መለስ ብሎ ስለመቃኘት ያወሳል፡፡ በጥናቱ መሠረት ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ይዘውት የሚወጡት ውጤት እና ብቃታቸው የተራራቀ ነው፡፡ በመሆኑም በካሪኩለሙ የተካተቱ አሰስመንት መንገዶችን መቃኘት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች በመቀበል አቅማቸው መሠረት ብቻ ሲቀበሉበት የነበረውን መንገድ ቀርቶ በውጤት ብቻ ማለትም ከ50% በታች ያመጣ ተማሪ እንዳይገባ ተደርጓል፡፡
ይህም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አንዱ መፍትሔ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱም እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና በሁሉም መስኮች እንዲሰጥ በማድረግ ለጥራት ቁርጠኝነትን አሳይተናል ይላሉ ኮራ ሲያስረዱ፡፡ ይህ ለመጀመሪያ ዲግሪ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆን፤ ለሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት እየተሠራ ነው ሲሉም እዮብ (ዶ/ር) ያክላሉ፡፡ እነዚህ ሪፎርሞች የመጀመሪያ ደረጃ የመፍትሔ ርምጃዎች በመሆን ሁሉንም ወደ ሥራ በማስገባት ስብራቱን ለመጠገን የተኬደባቸው ርምጃዎች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ኮራ ጡሽኔ በትምህርት ስብራት ላይ የተወሰዱ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነታቸውን በዝርዝር ለመግለፅ ገና ቢሆንም፤ ጅምሩ ግን ጥሩ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን ሚኒስቴሩ እያየ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ በዋናነት የተዘመተበት ኩረጃ እየቀነሰ ነው፡፡ ተቋማት ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቁ ዜጋ ማፍራት ትልቅ ጉዳያቸው አድርገው በመውሰድ የተሻለ ለመሥራት በውድድር መንፈስ እየሠሩ ነው፡፡ ለትምህርት ጥራት የአመራሩ ሚና ጉልህ ስለሆነ ተጠያቂ አመራር መፍጠር እየተቻለ ነው፡፡ በተጨማሪም ከቀድሞው ሲወዳደር በችሎታ እና በዲሲፕሊን የተሻሉ ተማሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን በጥናት ባይደገፍም ለማስተዋል ችለናል ይላሉ ሚኒስትር ዲኤታው፡፡
መቅደስ ታዬ (ፒ ኤች ዲ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም