ከስኬታማ ሴቶች አንደበት …

ሴቶች ኃላፊነት በተሰጣቸው ጊዜ ግዴታቸውን በብቃት ለመወጣት ተፈጥሯዊ ማንነታቸው ያግዛቸዋል።ሴት ልጅ ቤተሰብን ከመምራት ጀምሮ ሀገርን በወጉ እስከ ማስተዳደር የሚኖራት ሚና የጥንካሬዋ መገለጫ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ እውነታ ማሳያ በርካታ የሀገራችንን ጠንካራ ተምሳሌቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

በቅርቡ ይህን እውነታ በሚያጠናክር አንድ መድረክ የታደሙ የሀገራችን ዕንቁ ሴቶች የሕይወትና የሥራ ልምዳቸውን ‹‹እነሆ›› ሲሉ አካፍለዋል። ከእነዚህ ድንቅዬ ሴቶች የተዘገነው የሕይወት ጥንካሬና ብርታትም የበርካቶችን ማንነት ለመገንባት ጥብቅ መሠረት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

በዕለቱ እነዚህ ሴት ምሁራን ከሕይወት ተሞክሯቸው፣ከሥራ ልምድና አጋጣሚያቸው ያለፉበትን ማንነት ለሌሎች በማጋራት በጎነታቸውን ለበርካቶች አጋብተዋል፡፡ የእነሱ ልምድ ለበርካቶች መሠረት ነው። ለብዙኋኑም በቀላሉ የማይፋቅ ደማቅ አሻራ ሆኖ በአርአያነት የሚጠቀስ ይሆናል፡፡

ከሀገራችን ሴት ምሁራን መሀል አንዷ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክም የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል፡፡ ዛሬ ለደረሱበት የስኬት ጉዞ ተራምደው የመጡበት የጥንካሬ መንገድ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለዓመታት የትምህርት ሚኒስትር በመሆን መርተዋል። በሀገረ- ህንድም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ፡፡

የአምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ የሕይወት ትግልና ጥንካሬ የሚነሳው ገና በአፍላነት ዕድሜያቸው ተማሪ ሳሉ ነበር፡፡ የእዛኔ ሴትን ልጅ ለማጀት እንጂ ለአደባባይና ለቢሮ ሥራ የሚያስባት አልነበረም፡፡ እሳቸውና ጥቂት ሴት ባልንጀሮቻቸው ግን በትምህርት ዓለም ለመሳተፍ አጋጣሚውን አግኝተዋል፡፡

ሴቶቹ የመማር ዕድል ቢያገኙም የትምህርት ምርጫቸው የሚወሰነው በእነሱ ሳይሆን በሌሎች ይሁንታ ነበር፡፡ በጊዜው ሴቶች ከወንዶች ተማሪዎች ባላነሰ አቻ የሚሆኑበት ዕድል የላቸውም፡፡ በርካታ በሚባሉ መገለጫዎች አድልኦና መገለል ያገኛቸዋል።

ሴቶች ከቢሮ ጸሐፊነት ከሚያበቃቸው ሙያ በዘለለ ተፈላጊ የሚባሉ የትምህርት አይነቶችን እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም፡፡ እንደ አካውንቲንግና መሰል የትምህርት ዘርፎችን የመማር ዕድል የተሰጠው ለወንዶች ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሀቅ በየጊዜው ቢያጋጥምም፤ ለምንና እንዴት ብሎ የሚሞግት፣ስለመብትና ነጻነት ደፍሮ የሚጠይቅ አልነበረም፡፡

ጊዜው የንጉሱ ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ አብዝቶ ባህልና ወግ ይከበራል፡፡ ሁሉም ለተጣለበት ሕግና ደንብም በወጉ ይገዛል፡፡ በድንገት ግን እሳቸውን መሰል ጥቂቶች ስለሴቶች መብትና ነጻነት የሚቆረቆሩበት፣ስለጾታቸው እኩልነት የሚሞግቱበት አጋጣሚ ሊፈጠር ጊዜው ሆነ፡፡

ከቀናት በአንዱ አብረዋቸው ይማሩ ከነበሩ ሴት ጓደኞቻቸው ‹‹ፀሐይ ሚካኤል›› የተባለችው ተማሪ ስለሴቶች ትግል የሚያወሳ ድንቅ ጽሑፍ አዘጋጅታ ለክፍል ጓደኞቿ አነበበች፡፡ ጽሑፉ በጊዜው ድንቅ የሚባልና ውስጥን የሚገዛ ነበር፡፡ በወቅቱ ጽሑፉን ያደመጡት መምህራቸው አድናቆታቸው ተለየ። በጊዜው ይህን መሰል ጽሑፍ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ፍጹም ያልተለመደና ከዚህ ቀድሞ ያልተሞከረ ነው፡፡

የተማሪዋን አነቃቂ ጽሑፍ ተከትሎ ነገሮች መለዋወጥ ያዙ፡፡ ገነትና ሌሎች ተማሪዎች ስለሴቶች ጭቆና፣ መብትና ነጻነት የሚነጋገሩበት፣ ለምን ብለው የሚሞግቱበት ጊዜው ደረሰ፡፡ ይህን ስሜት ተከትሎም ሴት ተማሪዎች የማትሪክ ፈተናን መውሰድ አለብን ሲሉ ሞገቱ፤ በዚህ ብቻ አልቆሙም፡፡ ውሎ አድሮ ጉዳያቸውን አጠንክረው ክስ ጀመሩ፡፡

ይህ የንቅናቄ ጅማሮ ገነትን ወደ አይቀሬው ትግል አስገባቸው፡፡ የእዛኔ እሳቸውና ጓደኞቻቸው የራስ መኮንን ትምህርት ቤት ፍሬዎች ነበሩ። በዘመኑ በትምህርት ቤቱ ታላቅ ስያሜ ሲባል የማትሪክ ፈተናን መውደቅ ክብርን እንደማዋረድ ይቆጠር ነበር፡፡ እንዲህ መሆኑ የሴቶቹን ጥያቄ ፈጥኖ ለመመለስ ስጋት ሆኖ ቆየ፡፡

የማትሪክ ፈተና ጥያቄ ሌላ ፈተና ሊያስከትል ግድ ነበር፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ የተማሯቸውን አራት የትምህርት አይነቶች ጠንቅቀው ማወቅና የማጣሪያ ፈተናውን በብቃት ማለፍ ይኖርባቸዋል ተባለ፡፡ በተጨማሪ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚሰጠውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መፈተንም ግድ ሆኖ ታዘዘ። የወቅቱ ሴት ተማሪዎች ግን በቀላሉ እጅ አልሰጡም። ፈረንሳይኛ የሚያውቁትን ጨምሮ ሁሉም ፈተናውን በድል ለመወጣት ሌት ተቀን መጣር ጀመሩ ፡፡

አምባሳደር ገነት በጊዜው ፈረንሳይኛን ከሚማሩት ወገን አልነበሩም፡፡ ሌሎቹን አራት ትምህርቶች ግን በአስደናቂ ድል በማለፍ አስገራሚ ውጤት አስመዘገቡ። ይህን ተከትሎም ያለአንዳች ከልካይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በሩ ተከፈተላቸው። የእሳቸውና የጓደኞቻቸው የመብት ጥያቄ ከወቅቱ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሀል ቀዳሚዋ አደረጋቸው፡፡

የተማሪዋ ገነት ዘውዴ የጥንካሬ ጉዞ በዚህ ብቻ አልተገታም፡፡ በትምህርታቸው ጉብዝና ማሳየታቸው ለሌላ መልካም ዕድል አሳጫቸው፡፡ ወደ አሜሪካን ሀገር ተጉዘው በነጻ የትምህርት ዕድል እንዲካፈሉ ሆነ።

የትምህርት ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የማስተማር ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ በርከት ያሉ ስኬታማ ዓመታትን ዕውቀታቸውን በማሻገር የቆዩት ገነት በዩኒቨርሲቲው እስከ 1983 ዓ.ም ረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ይዘው በጥንካሬ ጉዞ መራመዳቸው ብርታታቸውን አድምቆታል፡፡

አምባሳደር ገነት በተለይ የትምህርት ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ስለ ቦታው አግባብነት ቀድመው ያደረጉትን ዝግጅት አይዘነጉም፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በታጩ ጊዜ ስለ ሀገሪቱ የትምህርት ዓላማ፣ ግብና ተልዕኮ በግላቸው ለማጥናት ሞክረዋል።

የሚመሩት ተቋም ሁሉንም አካቶ የያዘ የትምህርት ጉዳይ ነውና በድፍረት ዘው ብለው አልተቀላቀሉም። በጥንቃቄና በተለየ ትኩረት ለማጥናትና ጠልቀው ለማየት ጥረት አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ከንጉሱ የትምህርት ሥርዓት ጀምሮ እሳቸው እስከደረሱበት ዘመን ድረስ ያለውን የትምህርት ፖሊሲ ዘልቀው ለማየት ሞክረዋል። ድክመት ጥንካሬውን ፣ዕድገት ውድቀቱን ለይተዋል፡፡

በወቅቱም ትምህርት የልማትና ዴሞክራሲ መሳሪያ፣ የዕውቀት መሸጋገሪያ ስለመሆኑ አውቀዋል። አውቀውም በቻሉት ልክ ለሌሎች ለማስረጽ ጥረት አድርገዋል፡፡ ትምህርት ሁሌም ጠቀሜታው ላይ ሊያተኩር ይገባል የሚሉት አምባሳደሯ፤ የዕውቀት ስር ከመሆን የዘለለ የእኔነት ማንጸባረቂያ ሊሆን እንደማይገባው አድምቀው ያሰምሩበታል፡፡

አምባሳደር ዶክተር ገነት ለዓመታት በተጓዙበት የማስተማር ልምድ የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ ሳያውቁት እንደቆዩ ያስታውሳሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ ደግሞ የእሳቸውና የሌሎች ምሁራን የአስተውሎት ችግር ስለመሆኑ ተምረውበት አልፈዋል፡፡ በሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ቀረጻ ወቅት ገነት ስለሴቶች ትምህርት ትኩረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

እሳቸው በትምህርት ዓለም የተሻገሩበትን የውጣ ውረድ መንገድ አሳምረው ያውቁታል፡፡ ሴት ተማሪዎች እንዳይማሩ እንቅፋት የሚሆኑባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ነቅሶ ለማውጣትም በቂ ጥናት ያስፈልጋል፡፡

በወቅቱ የራሱ ችግሮች ቢኖርበትም በሀገሪቱ በሴቶች ትምህርት ላይ የሚያተኩር ዲፓርትመንት በመክፈት የፖሊሲ ኮሚቴን ለማቋቋም ዕድሉ ተመቻቸ፡፡ በተለይ ደግሞ ሴት የገጠር ተማሪዎች ትኩረት ተችሯቸው የእኩል መብትን እንዲያገኙ የሚያስችል ሃሳብ ተንጸባረቀ፡፡

በወቅቱ አምባሳደሯ በሴቶች ጉዳይ ብዙ የሚያስገርሟቸውና ተቃራኒ የሚባሉ ጉዳዮች ተነስተው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ገነት በታሪክ ተሞክሮ የአፍሪካውያንን ልማድ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ እነሱ በፖለቲካ ቁርሾ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም በሴቶች ጉዳይ አቋማቸው ተመሳሳይ ነው፡፡

ገነት ይህ አይነቱ መልካምነት በሀገራቸውም እንዲጋባ ፍላጎታቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡ በብዙ ትግልና ውጣ ውረዶች፣ በእሳቸውና በሌሎች ጥቂቶች ጥረት ፖሊሲው ተቀርፆ ተግባር ላይ መዋሉ ዛሬ ላይ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነውም አምባሳደር ገነት ዘውዴ የትምህርት ሚኒስትርነት ዘመን ነበር፡፡

ይህንንም ሀቅ አምባሳደሯ ዛሬ ላይ ሆነው ትናንትን በትውስታ ሲያወሱት የሚያስታውሱት ሀቅ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ታሪክ መሀል ደግሞ እሳቸው ሳይማሩ ልጃቸውን በማስተማር ለቁም ነገር ያበቁትን ወላጅ እናታቸውን ውለታ መቼም አይዘነጉም፡፡ እሳቸው ማለት የእናታቸው መልካም ውጤትና ፍሬ ናቸው፡፡ በንግግራቸው መሀል ውድ እናታቸውን ደግመው ፣ ደጋግመው ያመሰግናሉ፡፡

ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋካልቲ የተገኙ ጠንካራ ምሁር ናቸው። እኚህ ሴት በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ ሴት ፕሮፌሰር መሆናቸው ተመዝግቧል። ይህች ድንቅዬና ብርቱ ሴት እንዲህ መሰሉን ማንነት ለማግኘት በበርካታ የጥንካሬ መንገዶች ተመላልሰዋል።

ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ አባታቸው ስለሴት ልጅ ትምህርት በጎ አመለካከት እንደነበራቸው ያወጋሉ፡፡ ይህ እውነት ታዲያ እሳቸው ከአብዛኞቹ እኩዮቻቸው ቀድመው የቀለም ሀሁን እንዲቆጥሩ ዕድል ቸሯል። እሳቸው ትምህርት በጀመሩበት ዘመን የሕዝብ ቁጥር እንደ አሁኑ ብዙ የሚባል አልነበረም። በመሆኑም የልጅነት ዕድሜያቸውን በትምህርት ለማሳለፍ አጋጣሚው መልካም ሆነላቸው፡፡

በወቅቱ የዓለምፀሐይ በደሴ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ከወንዶች እኩል ተሰልፈው መማር ጀመሩ፡፡ በጊዜው በውጭ ሀገራት መምህራን በተለይም በህንድ ዜጎች የታገዘ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ የዓለምፀሐይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እንደየትምህርቱ አይነት ምርጫ ይሰጥ ነበርና የእሳቸው ፍላጎት ወደሳይንሱ አጋደለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው የተቋጨው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን አኩሪ ውጤት በማስደረብ ነበር፡፡

ከተማሪዎች ሁሉ በዕድሜ ትንሸ ነበሩና የውጤታቸው መላቅ አግራሞትን አስከተለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ነበረባቸው። የዓለምፀሐይ የልጅነት ዕድሜ ከውስጣቸው ዕውቀት ተዳምሮ ‹‹አያቅተኝም ›› ይሉትን ልምድ ይዘው አድገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ይህ ኩራት አብሯቸው ነበር፡፡ የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት ሲጠናቀቅ ግን ውጤታቸው እንደታሰበው አልሆነም። በመጀመሪያ ከባድ ማስጠንቀቂያ ታልፈው ጊዜውን ተሻገሩ፡፡

ይህ ማስጠንቀቂያ ለእሳቸው ፈጣን የማንቂያ ደወል ሆነ፡፡ ጊዜ ሳይፈጁ ማንነታቸውን ፈለጉ፡፡ ራሳቸውን አላጡትም፡፡ ከመጀመሪያው ሴሚስተር በኋላ ሕክምናን ለማጥናት አሰቡ፡፡ የነበራቸው ውጤት እንዳሰቡት አላራመዳቸውም፡፡ ጥቂት አሰብ አድርገው ሰዎችን አማከሩ፡፡

ሰዎቹ ባዮሎጂን እንዲመርጡ ጠቆሟቸው። በይሁንታ ተቀብለው መማር ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዘርፉ ተመርቀው እንደያዙ በሀገሪቱ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት እሳቸው አንደኛዋ ተመራጭ ሆኑ፡፡ይህ ምርጫ ትኩረቱ ብርቱ ተማሪዎች ላይ ነበርና የዓለምፀሐይ አንደኛዋ ለመሆን አልዘገዩም፡፡ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው በ1958 ዓ.ም ወደ ጀርመን ሀገር ተጓዙ፡፡

እንዲህ በሆነ ማግስት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መሰጠት ተጀመረ። ተሽሎ መገኘት ለምርጫ ያበቃልና የዓለምፀሐይ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ብርታትና ጥንካሬያቸው ተመራጭ አድርጎ ለያቸው፡፡ በወቅቱ ትዳር መያዛቸው ነበርና የልጅ እናት ለመሆን አልዘገዩም። እንዲያም ሆኖ ኃይላቸው አልደከመም፡፡ ሁሉንም ጎን ለጎን እያራመዱ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት እየተስፋፋ መሄድ የፕሮፌሰሯን ፍላጎት ጭምር ማሳካቱ አልቀረም። ከዓመታት በኋላ በሀገሪቱ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት እውን መሆን ጀመረ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለጠንካራዋ ሴት መልካም አጋጣሚ ፈጠረ፡፡ አሁንም በዕድሉ ተጠቅመው ዶክትሬታቸውን ያዙ፡፡

የእዚህን ጊዜ ፕሮፌሰር በተለየ ትውስታ ያወጉታል። በወቅቱ የቴክኖሎጂው ምጥቀት እምብዛም የሚባል ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን በመሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ፈተናው የከበደ ነው። እሳቸው ግን በቻሉት አቅም የትምህርት ዕድል ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት ደብዳቤዎችን መጻጻፍ ጀመሩ፡፡

ይህ ትግል ውሎ አድሮ ውጤት አስገኘላቸው። በራሳቸው ጥረት አድራሻ በማጠያየቅ የፈለጉትን ትምህርት ከእጃቸው አስገቡ፡፡ እኤአ በ1988 ወደ ምዕራብ ጀርመን ተጓዙ፡፡ ስፍራው እንደደረሱ የሀገሪቱን ቋንቋ ግድ መማር ነበረባቸው፡፡ የስድስት ወር ቆይታቸው ከቋንቋው አስተዋውቆ ወደሚፈልጉት ትምህርት አደረሳቸው፡፡ የእዛኔ የዓለምፀሐይ የሁለት ልጆች እናት ነበሩ፡፡

የፕሮፌሰር የሕይወት መርህ አንድን ጉዳይ ለመሥራት ከመጀመራቸው በፊት ‹‹እችላለሁ›› ብሎ ራስን ማሳመን ነው፡፡ በእሳቸው ሕይወት ውስጥ አባታቸውን ጨምሮ ብዙ በጎ ሰዎች ቢኖሩም፤ የራሳቸው ዝግጁነት ግን ወደ ላቀ የውጤት ማማ ከፍ ሲያደርጋቸው ቆይቷል፡፡

የዓለምፀሐይ ጽኑ ዕምነት የእሳቸው ጥንካሬ ከማንነታቸው የተሻሉትን ጭምር ለማፍራት አግዟል፡፡ይህ እውነታ ደግሞ ሁሌም የሚኮሩበትና የድካማቸውን ፍሬ የሚያዩበት ስኬት ሆኗል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You