
በዚህ ዘመን በዓለም በየዕለቱ አዳዲስ እና የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች እየታዩ፣ የሰው ልጅን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እያሳለጡ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል የበለጸጉት ሀገሮች ብዙ ርቀት የተጓዙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ወደ ተራቀቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ ለማሸጋገር በእሽቅድድም ላይ ይገኛሉ፡፡
ቴክኖሎጂው በግልም፣ በተቋምም እንደ ሀገርም ያለው ተፈላጊነት በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል። የሀገር የልማት መሳሪያ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂን አለመጠቀምም ሆነ ከቴክኖሎጂ ውጪ መሆን ከዓለም ወደኋላ መቅረት ነው፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ብዙ ነገርም ያሳጣል፤ ከቴክኖሎጂ ውጪ መሆን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራትም የቴክኖሎጂውን አስፈላጊት በጽኑ በማመን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ምህዳር ውጪ መሆን እንደማይቻል አልፎም ተርፎ የልማት አንዱ ዋና መሳሪያ መሆኑን በማመን ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት በመስጠት ቴክኖሎጂውን የምጣኔ ሀብቷ ምሰሶዎች ካለቻቸው አምስት ዘርፎች አንዱ አድርጋ በስፋት እየሠራችም ነው፡፡
ዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ቀርጻ ወደ ተግባር በመግባቷም ባለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ በርካታ ለውጦችም ተመዝግበዋል፡፡ የገንዘብ ዝውውርን ወይም ክፍያን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማካሄዱ ተግባር ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰበትን እንዲሁም አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመፈጸም እየተሠራ ያለበትን ሁኔታም ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ቴክኖሎጂን ለሥራ ማቀላጠፊያ ማዋልና በመሳሰሉት ላይ ብቻ አይደለም እየተሠራ ያለው፡፡ በመተግበሪያና የመሳሰሉት ልማት ላይም ብዙ እየተሠራ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በዘርፉ ብዙ ርቀት እንዲሄዱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህም ከሕዝቧ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ለሆነባት ኢትዮጵያ እድል ይዞ መጥቷል፡፡ ብዙዎችም በእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በስልጠናው እየተሳተፉ ናቸው፡፡
ኮዲንግ ሰዎች ከሚጠቀሙበት ስልክ ሆነ ኮምፒውተር ጋር ለመግባባት የሚያግዝ የኮምፒውተር ቋንቋ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይህንን የኮምፒውተር ቋንቋ ሁሉም ሰዎች እንዲያወቁት ብሎም እንዲጠቀሙበት እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡ ሰዎች ኮዲንግን ተምረውና የተሻለ መረዳት ኖራቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙና የገቢ ምንጭ የሚያገኙበትን ሥራ እንዲሠሩ እንደሚያግዝም ያመላክታሉ፡፡
በተለይ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተከናወኑ ያሉት እነዚህ ሥራዎች ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነው ወጣት ንቁ፣ሥራ ፈጣሪ እና ለሀገር እድገትና ግንባታ የሚሠራና የሚቆረቆር እንዲሆን ለማድረግ በእጅጉ ያግዛል፡፡ ለወጣቶች ኮዲንግን ማወቅም ሆነ መማር የዓለምን አካሄድ ለማወቅም ሀገራቸውንም ሆነ ራሳቸውን በእዚያ እይታ ውስጥ በመመልከት በፈጠራ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ይበልጥ እንዲስፋፋ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር ወጣቶች ቴክኖሎጂውን እንዲማሩ፣ እንዲያውቁ፣ እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ እድሎች እየሰፉ ይገኛሉ፡፡
በተለይ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የተቋቋሙ የስቴም ማዕከላት በእዚህ በኩል እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ ማእከላቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝንባሌ ያላቸው ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎችን በትምህርት ቤቶቹ በማስተማርና በማሰልጠን ተማሪዎችን የማብቃት ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎችን ከማስተማር ባሻገርም በየዘርፉ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሮቦቲክስ ውድድር ይጠቀሳል፡፡ በባለፈው ህዳር ወር ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው ዘጠነኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሳይንስና የምህንድስና ቀን ከተዘጋጁ ውድድሮች መካከል የሮቦቲክስ ውድድር ይጠቀሳል፡፡
በሮቦቲክ ዘርፍ ከተወዳደሩት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ጸጋ ግርማ አንዷ ናት፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዋ ተማሪ ጸጋ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል ሮቦቲክስ ዘርፍ በክረምት መርሃ ግብር የሚሰጠውን ስልጠና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡
ተማሪ ጸጋ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች የነበራት ከፍተኛ ፍላጎት የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እያለች ስቴም ማዕከል መግባቷን ትናገራለች። ‹‹ከድሮ ጀምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ፍላጎቱ በውስጤ አለ፤ ይህን ከፍተኛ ፍላጎቴን የማወጣበት ቦታ ሳፈላልግ ቆይቻለሁ›› ስትል ጠቅሳ፤ የስቴም ማዕከሉ ቆይታዋ የሚወደድ እንደነበርም ተናግራለች።
በስቴም ማዕከሉ ብዙ መገልገሏን ጠቅሳ፣ በማዕከሉ የሚሰጡት ሁሉም አገልግሎቶች በነጻ እንደሚሰጡ ተናግራለች፡፡ መምህሮቹ የሚያስተምሩት በተማሪዎቹ ፍላጎት ላይ ተመስርተው መሆኑን ገልጻ፤ ይህም ተማሪዎቹ በትምህርቱ እንዲመሰጡ እንዳደረጋቸው ትገልጻለች። ‹‹ቤተሙከራ ስንገባ ሁሉም እየረዱን እንድናውቅና በጥልቀት እንድንረዳ እያደረጉን ነው፤ በዚህም ብዙ እውቀት እንድናገኝ እና ያለንን ሰፊ እድል አሳይተናል›› ትላለች፡፡
ከስልጠና በኋላም ትንሽ /ሚኒ/ ፕሮጀክት በሚል የራሳችንን ፕሮጀክት በሠራንበት ወቅትም ሙሉ ቀን አብረውን በመዋል ረድተውናል ብላለች። ‹‹ከመጀመሪያ አንስቶ እንማር የነበረው በየዙሩ ለውድድር በሚያዘጋጅ መልኩ ነበር፤ ማዕከሉ ከትምህርቱም በተጨማሪ በጣም ብዙ እድሎችን ያገኘንበት ነው፤ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የሮቦቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ መሆን ችለናል›› በማለት አስታውቃለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ ማዕከሉ እነ ተማሪ ጸጋ ከትምህርቱ በተጨማሪ ብዙ ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን እንዲያውቁና ልምድ እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡ የተማሪዎችን ፍላጎት ለመመለስም ብዙ ትብብር አድርጎላቸዋል፡፡‹‹በተለይ ለእኔ የክረምት ትምህርት ሌላ ቦታ እንዳገኝ አግዞኛል›› ትላለች፡፡
በስቴም ማዕከሉ በክረምቱ መርሃ ግብር የሮቦቲክስ ዘርፍ ስልጠና መውሰዷን የምትናገረው ተማሪ ጸጋ፤ ስልጠናውን ተጠቅማ በሠራችው የሮቦቲክስ ሥራ ተወዳድራለች፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውድድሩ በሮቦቲክስ ዘርፍ ሮቦትና ኮዲንግ በመሥራት ሁለተኛ መውጣቷን ትናገራለች፡፡
ውድድሩ ሮቦት መሥራትን ብቻ ሳይሆን ለሮቦቱ ኮድ በመስጠት በተግባር ተፈትሾ ማለፍን ይጠይቅ እንደነበርም አስታውሳ፣ የሮቦቲክስ ውድድሩ የሮቦት መኪናዎችን በመሥራትና በመገጣጠም ላይ የተመሰረተ እንደነበርም ገልጻለች፡፡ ሮቦቱ የሚያልፍባቸው መሰናክሎች እንዲኖሩ ተደርጎ ያንን መሰናክል ማሻገር ላይ ትኩረት ተደርጎ መካሄዱንም ታስታውሳለች፡፡
ተማሪ ጸጋ የሠራችው የሮቦት መጠን 30 በ20 ሳንቲ ሜትር ይገመታል፤ መካከለኛ የሚባል ነው፡፡ ርዝመቱም ቢበዛ ከ17 ሳንቲ ሜትር በላይ ይሆናል፡፡ ለውድድሩ የተፈለገው አጠር ያለ መጠን ያለው ሆኖ እንደልቡ መተጣጠፍ የሚችል ነው፤ ይህንን አይነት ሮቦት በተሻለ መልኩ መሥራት የሚቻልና የተመለደ አይነት መሆኑንም ትገልጻለች፡፡
እሷ እንደምትለው፤ ሮቦቱ የመስናክል ሯጮች እንደሚሮጡበት አይነት ጠመዝማዛ መንገድ ተዘጋጅቶለት በዚያ እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ የሮቦቱ መኪና በምን ያህል ደቂቃዎች ምን ያህል መንገድ መጓዝ እንዳለበት በሰዓት ተሰልቶ ኮድ ይሰጠዋል። መኪናው የተሰጠውን ኮድ ተከትሎ ምንም ሳያይ በራሱ እንዲጓዝ ይደረጋል፤ አቅጣጫ ሊጠቁሙት የሚችሉ እንደ ካሜራና የመሳሰሉትን ነገሮችንም በፍጹም መጠቀም አይፈቀድለትም፡፡
ሮቦቱን የሚሠራው ተወዳዳሪው ስለሆነ ሮቦቱንም ኮዱንም የሚሰጠው ተወዳዳሪው ራሱ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ከኮዱ ይልቅ ሮቦቱን መሥራት ብዙ የሚፈትን የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ የምትለው ተማሪ ጸጋ፤ ኮዲንጉ ከተሠራ በኋላ ሮቦቱ ትዕዛዙን ተከትሎ እንዲሠራ ማድረግ በእጅጉ ከባድና ፈታኙ ሥራ መሆኑን ትገልጻለች፡፡
‹‹ሮቦት በራሱ ሕግ መሠረት ይሠራል፤ በጣም ማነሱ ለመተጣጠፍ ይጠቅመዋል፤ ነገር ግን ከሕጉ ውጪ ነው፤ በጣም ትልቅ መሆንም ሌላ ችግር ያመጣበታል፡፡ እንዳይጋጭ ለማድረግ የሚረዱት መልእክቶች ሊኖሩትም አይገባም፡፡ አንድና አንድ በሕጉ መሠረተ ነው መሠራት ያለበት›› ስትል ታብራራለች፡፡
በዩኒቨርሲቲው ስቴም ማዕከል ስለሮቦቲክስ መማሯና ብዙ እውቀት ማግኘቷ በጣም እንደጠቀማት የምትናገረው ተማሪዋ፤ ባገኘችው ትምህርት ሮቦቶቹን መሥራት መቻሏን ትገልጻለች፡፡ ሮቦት መሥራትና መገጣጠም ብዙ ጥንቃቄ የሚፈልግ ሥራ መሆኑን ጠቅሳ፤ ሁሉም ክፍሎች በሚገባና በጥንቃቄ መገጠም እንዳለባቸው አስገንዝባለች፡፡ ሮቦቱ በጥንቃቄ ከተገጠመ በኋላ ገመዶቹን የማገናኘቱ ሥራ ከሁሉም ቀለል ያለ የሚባለው መሆኑን ጠቅሳ፤ በትክክል ሳይገጠም ከቀረና ጎማው ከተንሳፈፈ በራሱ ሮቦቱን ለማዘዝና ለመቆጣጠር ሊያስቸግር የሚችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ታስገነዝባለች፡፡
ተማሪ ጸጋ እንዳብራራችው፤ ወደ ኮዲንግ ሲገባም የራሱ የሆነ መተግበሪያ አለው፤ ያንን ተጠቅሞ ኮዲንግ መሥራት ይጀመራል፡፡ ሮቦቱ ኮድ ሲደረግ ለአንድ ደቂቃ ወይም የተፈለገውን ያህል ስኮንድ እንዲሄድ ተብሎ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ስለሚሆን አንድ ኪሎ ሜትር ሄደ ብንለው ስለማያውቀው ሊሄድልን አይችልም፡፡ እዚህ ጋ ያለው ችግር ደግሞ የሚሄድበት ፍጥነት እንደባትሪው ሁኔታ የሚወሰን መሆኑ ላይ ነው፡፡
ባትሪው እያለቀ ባለበት ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የሚደረግ ከሆነ ፍጥነቱ ይቀንሳል፤ ስለዚህ የምንሞክርበትን ጊዜ በራሱ መገድብ አለብን፤ ብዙ በሞከርን ቁጥር ባትሪው ያልቃልና፡፡ ባትሪው ስለሚያልቅ ሮቦቱ ሊዘገይብን ይችላል፤ ባትሪ ስንቀይር ደግሞ ፍጥነቱ ሊጨምር፣ ከውድድር ውጪ ሊያደርገን ስለሚችል ደቂቃውን ከባትሪው ኃይል ጋር አመጣጥኖ ለመጠቀም በጥንቃቄ መሥራት ይፈልጋል፡፡
ሮቦቱ በአንድ ሕግ ቢሠራም የሚሠራው አካል በሚፈልገው መንገድ በመሥራት የራሱን መፍትሔ የሚያመጣበት አሠራርን ለመከተልም ያስችላል ትላለች፡፡ ተማሪ ጸጋ፤ ሁሉም ሰው ራሱ ለሠራው ሮቦት የሚሰጠው ኮድ ይለያያል፤ የሚያለያየውም በሚሰጠው ኮድ ነው፡፡ አንዳንዱ በፍጥነት ሄዶ እንዲያልፍለት፣ ሌላው ደግሞ ዘግየት ብሎ እንዲሄድለት ሊፈልግ ይችላል፤ ሁሉም በሚመቸው መልኩ ቢሠራም መጨረሻ በሚፈለገው ልክ የሠራ አሸናፊ የሚሆንበት አሠራር እንዳለ አመላክታለች፡፡
‹‹ሮቦቱን ሥንሠራ ትንሽ ከተሳሳተን ስህተቱ እየተደማመረ ይመጣና ሌላ ችግር ይወልዳል። ቀደም ብሎ የሠራልን ሮቦት በአቀማመጥ ስህተት ብቻ ይሠራ የነበረው ላይሠራ ይችላል፡፡ በመሆኑም ቦታውን ማወቅ፣ ኮዱን መጻፍ ሕጉን ተከትሎ ሮቦቱን መሥራት ያስፈልጋል››ብላለች፡፡
ተማሪ ጸጋ እንደተናገረችው፤ የሮቦቲክስ ዘርፉን ማወቅና ማጥናት ከውድድር ያለፈ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ ሮቦቱ ለውድድር የተሠራ ቢሆንም ይሄው ሃሳብ በተሻለ መልኩ ከፍ ቢደረግ በዓለም ላይ እንደሚታዩት አይነት ሮቦቶች ብዙ አይነት ዘርፎች ላይ መጠቀም ያስችላል፡፡
ሮቦቱ በተሰጠው ኮድ መሠረት ያለምንም ተቆጣጣሪ በተሰጠው ሕግ እየተመራ ሥራውን ይፈጽማል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት የሰው ንኪኪ አይኖርም፤ ሮቦቱ በራሱ ይመራል፡፡
ቀደም ሲል ተማሪ ጸጋና የቡድን አጋሮቿ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ውክለው ተሳትፈዋል፤ በውድድሩ የሠሩትን ሮቦት ይዘው ተሳትፈዋል፤ እንደዚህ አይነት ሮቦቶች መሥራት እንደሚቻል ተማሪ ፀጋ በተለያዩ አጋጣሚዎች አይተናል ትላለች።
ተማሪ ጸጋ ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውድድር ይዛ በቀረበችው ሮቦት ሁለተኛ በመውጣቷ ታብሌት ከነኪቦርዱ ለመሸለም በቅታለች፤ ‹‹ይህ ሽልማት ሞራል ሰጥቶኛል፡፡ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በደንብ ትኩረት አድርጌ እንድሠራ ያበረታታኛል፡፡ ሥራው በአንድ ጀምበር የተሰራ አይደለም፤ ብዙ ጥረትና ልፋት የጠየቀ ነበር፤ በዚህም አሸናፊ በመሆኔ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብላለች፡፡
የሮቦቲክስ ትምህርትና ስልጠና በመውሰዴ ሮቦቱን ለመሥራትና ለመገጣጠም ሁለትና ሦስት ቀናት ብቻ ነው የፈጀብኝ፡፡ የሮቦቱ ሥራ ብዙ የማይቸግር ቢሆንም ኮዱን ለመስጠትና ሥራውን ለማጠናቀቅ ግን አንድ ሳምንት ያህል ጊዜ እንደፈጀባት ጠቁማለች፡፡
‹‹ሮቦቲክስ የምወደው የሙያ ዘርፍ ስለሆነ በሮቦቲክሱ ዘርፍ በመቀጠል ለሀገሬም ሆነ ለራሴ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት እቅዱ አለኝ›› የምትለው ተማሪ ጸጋ፤ ‹‹ለከፍተኛ ትምህርት ስገባም ትምህርቴን መቀጠል የምፈልገው በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ወይም በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በመሆኑ ይህን አላማ አንግቤ እየሠራሁ ነው›› ብላለች፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም