“የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ” ኢንዱስትሪ – ዘመኑን የዋጀ ተጨማሪ የመከላከያ አቅም!

የአንድ ሀገር የሀገርነት ክብርም፣ ልዕልናም ከምትጎናጸፍባቸው ቀዳሚ አቅሞች መካከል አንዱና ዋነኛው የመከላከያ ኃይል ነው፡፡ ዛሬ ላይ ዓለማችን በመከላከያ ዘርፍ ከፍ ያለ ሀብትን እያፈሰሱ አቅማቸውን የሚያጎለብቱትም ለዚሁ ነው፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን ከሚጠይቀው የመከላከያ አቅምና ቁመና አኳያ ደግሞ፣ ሀገራት የመከላከያ ተቋሞቻቸውን

የሳይንስ፣ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ማበልጸጊያ እያደረጓቸው ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ጊዜው እንደ ቀድሞው ፊት ለፊት አጋጥሞ አሸናፊና ተሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ ባለመሆኑ ነው፡፡

ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሀገራት የመከላከያ ተቋሞቻቸውን የሀገር ሁለንተናዊ ደህንነት ማስጠበቂያ አቅም የሚሆኑ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ማዕከል አድርገው የሚጠቀሙባቸው፡፡ ከፍ ያለ በጀት የሚመድቡት፤ ከፍ ያለ የሠለጠነ የሰው ኃይል መፍለቂያም የሚያደርጉት፡፡

እነ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሌሎችም ኃያላን ሀገራት፤ የመከላከያ ተቋማቶቻቸው የመከላከያውን ዘርፍ ከፍ ከሚያደርጉና ዘመኑን ቀድመው እንዲራመዱ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም አፍልቀውና አልምተው እንዲታጠቁ

እያደረጉ ያሉት፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ እነዚህ ሀገራት የሚፈሩ፤ ወታደር ወደ አንድ ቦታ ሳይልኩ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ብቻ ባሉበት ሆነው የሀገራትን ወሰን ያለ ከልካይ ዘልቀው ገብተው የሚፈልጉትን ጥቃት ሲሰነዝሩ የሚስተዋለው፡፡ ምዕራባውያኑን ከምስራቁ፤ ሩቅ ምሥራቁን ከአረቡ ዓለም፣ ወዘተ፣ እያፋጣጠ፤ ከሳይበር እስከ ሚሳይል የሚያዋክበውም

የዚሁ የመከላከያው ዘርፍ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና የፈጠራ ማዕከል እየሆነ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም፣ የመከላከያ ተቋማቶቻቸው የሀገራቱ የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን፤ ለሀገራቱ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ አቅም እስከመሆንም ደርሰዋል፡፡

ቱርክን፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ አሜሪካና ሌሎችም በጦር መሣሪያና ሌሎችም የጦር አቅሞች ገበያ ላይ ተመሥርተው የሚያገኙት ገቢ ለዚህ አብነት ነው፡፡ በየተቋሞቻቸው ከፍ ያለ በጀትን በመመደብ፣ የሰው ኃይሉን አቅምና ክህሎት በማሳደግ የአዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት፣ ከተተኳሽ ጀምሮ በምድርም በአየርም የሚሠማራ የውጊያ አቅሞችን የሚቸበችቡት፡፡

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ከትናንት እስከ ዛሬ ሉዓላዊነቷን በማስከበር ሂደት የእነዚህን ሀገራት ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ ሉዓላዊነቷን አጽንታ ቆይታለች፡፡ በየዘመናቱ ቴክኖሎጂውን በአንድም በሌላ መልኩ በራስ ሀገር ብሎም አቅም ለማምረት ሙከራዎች ሲደረጉ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ መድፍ በኢትዮጵያ እንዲመረት ያደረጉበት አግባብ እና የሴባስቶፖልን ታሪክ ማስታወሱ

ከሩቁ የሚጠቀስ ሙከራ ነው፡፡ ከቅርቡ ደግሞ በደርግ ዘመን ከፍ ብሎ የታየው ጥይትና መሰል መሣሪያዎችን ማምረት የተጀመረበትን የጋፋትን ስምና ዝና ማሰብ የኢትዮጵያን የዘርፉን መንገድ ለመገንዘብ ያግዛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ከፍ ባለ አቅምና ቁመና የመከላከያውን አቅም በልኩ የመግለጥና ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ ከማድረግ

አኳያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተሠሩት ሥራዎች ኢትዮጵያን በስሟ ልክ እንዲትገለጥ እያደረጓት ያሉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማትን ሪፎርም ከማድረግ አንስቶ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና ሌሎችም አቅሞች በልኩ እንዲዋቀር የተደ ረገበት አግባብ ፍሬ ማፍራት ጀም ሯል፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር በብዙ ፈተና ውስጥ ብንሆንም፤ የመከላከያው ኃይል ከፍ ባለ አቅምና ሞራል ሀገሩን አጽንቶ

እንዲራመድ፤ ከራስ አልፎም ለሌሎች አለኝታነቱን በተግባር እንዲገልጥ አድርጎታል፡፡ የምድር ኃይሉን፣ ሜካናይዝድ ኃይሉን፣ የአየር ኃይሉን፣ የባሕር ኃይሉን፣ የሳይበር ኃይሉን፣ የሥልጠናና ምርምር ኃይሉን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራውንናሌላውንም ባቀናጀና ባናበበ መልኩ ወደ ከፍታ እንዲገሰግስ አድርጎታል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ የሚያስችሉትን ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ከመግዛት ተጀምሮ፤ በሀገር ውስጥ ገጣጥሞና ጠግኖ ወደመጠቀም ተሸጋግሮ፤ በራስ አቅም አምርቶና አባዝቶ ወደ መጠቀም ልቆ፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች ወደ መትረፍና መሸጥ ተመንድጎ ሊገለጥ በቅቷል፡፡

ይሄንኑ ጉዳይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የተተኳሽ ማምረቻ የሆነውን የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪን መርቀው በከፈቱበት ወቅት፣ “ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ጥይቶችን የማምረት ሙከራዎች ቢኖሩም እስከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ድረስ ከውጭ በማስገባት ላይ ተመሥርታ ቆይታለች። አሁን ኢትዮጵያ

በሀገር ውስጥ ተተኳሽ የማምረት አልፎም ወደውጭ የመላክ አቅም አሳድጋለች።” በማለት አረጋግጠዋል፡፡ ከሰሞኑም፣ የድሮን ቴክኖሎጂ ማዕከል እና ማምረቻ የሆነውን “የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪን” መርቀው ከፍተዋል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ ድሮንን ስለማምረት ቀርቶ

ስለመጠቀም እንኳ ማሰብ የማይታሰብ ነበር። ዛሬ ላይ ብዙ ዓይነት ችሎታ ያላቸው ድሮኖችን በራሳችን ባለሙያዎች ዲዛይን ተደርጎ የማምረት አቅም ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው። ይኽን እድገት ለማዝለቅ ቀጣይነት ባለው የምርምር ሥራ ላይ፣ ገበያ በማስፋት ተግባር ላይ እና በሀገር ውስጥ የስማርት ሴንሰር ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ላይ መሥራት ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳብራሩትም፣ እንደ ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ እና እንደ ሆሚቾ የተተኳሽ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ያሉትን አቅሞቻችን ማሳደግ የሚያስፈልገው፣ ግጭትን ለማቀጣጠል ሳይሆን ግጭትን ለማስቀረት ነው። ቴክኖሎጂን ማምረትና መታጠቅ ሲቻል፣ ግጭትን በሚፈልጉ ተዋንያን ፊት ከፍ ብሎ መታየት ይኖራል፡፡ የመከላከያው

አቅም ይገለጣል፡፡ ይሄ ደግሞ ጠላትም ደጋግሞ እንዲያስብ ያስገድደዋል፡፡ የአቅም መገለጥና የጠላት ደጋግሞ የማሰብ ሂደትም ግጭትን ለማስቀረት የሚችል ስለሚሆን፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለማጽናት ያግዛል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You