
ታሪካዊው እና ፖለቲከኛው የየካቲት ወር እነሆ ዛሬ ሊጠናቀቅ ነው። የካቲት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በርካታ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች የተከናወኑበት ነው። በዋናነት ግን በሁለቱ ታሪካዊ ድሎች የድል ወር ሆኖ ይታወሳል።
ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ የሆነውን የኢትዮጵያን የድል ቀን የሆነውን ዓድዋን በድምቀት አክብረናል። ዓድዋ ብዙ የተባለለትና ብዙ ሰው የሚያውቀው ቢሆንም ‹‹ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት›› ስለተባለለት፤ ከታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› መጽሐፍ፣ ከተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› መጽሐፍ፣ ከተለያዩ ድረ ገጾች እና የመገናኛ ብዙኃን ባገኘናቸው መረጃዎች ዓድዋን እናስታውሳለን።
ሴራው የሚጀምረው ከዓድዋ ጦርነት 12 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 1884 ነው። የአውሮፓ ሀገሮች በርሊን ላይ ባደረጉት ስብሰባ አፍሪካን ለመቀራመት ሲወስኑ የጣሊያን ድርሻ ኢትዮጵያ ሆነች። ዳሩ ግን ያሰቡት ሊሳካ አልቻለም።
ኢትዮጵያ በቅድመ ዓድዋ ከወራሪዎችና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ተዋግታም ድል አድርጋለች። ከእነዚህም አንዱ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ መንግሥት 1879 ዓ.ም ዶግዓሊ ላይ በራስ አሉላ አባነጋ አዝማችነት በጣሊያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳጀችው ድል ነበር። በዚህም የጣሊያን ወታደሮች ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፉ በአሉላ አባ ነጋ ዶግዓሊ ላይ ዶግ አመድ ሆነዋል።
በጦርነቱ እንደማይሳካላት የገመተችው ጣሊያን እንደገና ደግሞ ውል ማጭበርበር አሰበች። በመሆኑም ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌው ውል፤ በአንቀጽ 17 በጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥብቅ ግዛት ነች። የውጭ ግንኙነቷም በጣሊያን በኩል ይሆናል የሚለው ሐረግ መዘዝ አመጣ። በዚች አንቀጽ ምክንያት ጦርነቱ የማይቀር መሆኑ ተረጋገጠና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለጦርነቱ የሀገራቸውን ሕዝብ ‹‹ክተት›› ጠሩ።
‹‹አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል ። በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፣ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፤ …›› የሚለውን አዋጅ ተናገሩ።
ኢትዮጵያውያንም የእርስ በእርስ ግጭታቸውን፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውንና አለመግባባታቸውን ወደጎን ትተው፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተጠራርተው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው የመሪያቸውን ጥሪ ተከትለው ወደ ጦር አውድማው ተመሙ።
የዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲከበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታተመ የጥናት መድበል ላይ እንደተጻፈው፤ የጦርነቱ አዝማቾች፡- ዳግማዊ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ አባነጋ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ስብሐት፣ ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) እና ዋግ ሹም ጓንጉል ናቸው።
እውቁ የታሪክ ጸሐፊው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚነግሩን፤ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የጣሊያንን ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ ጦር አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ። ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት። የአንደኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ‹‹ራአዮ›› ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ።
ከዚህም በኋላ፤ በመጨረሻ ያለው የጣሊያን ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ። ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር ቀልጣፎች ነበሩ።
ይሁን እንጂ ጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ሞተ።
የጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› መጽሐፍ በወቅቱ የነበረውን ክስተት እንዲህ ይተርከዋል።
‹‹የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ አውሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል። የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ ጠመንጃና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የጣሊያንን ጦር አሸበሩት››
በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያስተዋሉትን ‹‹ኦውቶ ባዮግራፊ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ጽፈውታል።
‹‹የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ። እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን። ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ። ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን።
ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር። ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ አረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ። የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን። አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል። ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት። ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ። እኔ ዝም ብዬ ወደ ግምባር አለፍኩ። የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም። ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ። የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም።
ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው። ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ። ዝም ብዬው እንዳላየ ሰው ወደ ግምባር ሮጥኩ። ጦራችን ተደባልቋል። ሰውና ሰው አይተዋወቅም። ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎዎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ። ሲነጋገሩ ሰማኋቸው። «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ። እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ።
ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል። የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ። ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን ጣልያኖችን እየነዱ መጡ። በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዓይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ። ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ። እንደዚህ የዓድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ። ››በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ የዓድዋ ጦርነት የተጠናቀቀው፤ ክብር ለጀግኖቻችን እና ታሪክን ሰንደው ላቆዩልን ጸሐፊዎች!
የካራማራ ድል
ሌላኛው የዚሁ የየካቲት ወር ድል ደግሞ የካራማራው ድል ነው።
ይሄኛውም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከወራሪ ራሳቸውን የተከላከሉበትና ነፃነታቸውን ያስጠበቁበት የድል በዓል ነው። በወቅቱ በዚያድ ባሬ ይመራ የነበረው ተስፋፊው የሶማሊያ መንግሥት ‹‹ታላቋን ሶማሊያ እገነባለሁ›› በሚል ህልም የኢትዮጵያን መሬት ለመውረር አስቦ እሱም ልክ እንደ ጌቶቹ አውሮፓውያን ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰ ነው።
ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን ቅጽ ፩›› መጽሐፍ እና የካራማራ ድል በተከበረባቸው ዓመታት ከተሠሩ ዘገባዎችንና ከተለያዩ ድረ ገጾች መረጃዎችን አሰባስበን በየዓመቱ የካቲት 26 የሚከበረውን የካራማራ ድል እናስታውሳለን።
ለወረራ አሰፍስፎ በመጣው የዚያድ ባሬ ጦር ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ድረስ ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ጦርነት ተካሄደባት። ሶማሊያን ለ21 ዓመታት የመራት ጀነራል ዚያድ ባሬ ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት የቆየ ራዕይ ነበረው። ጊዜ አይቶ ወቅትን ገምቶ ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል የተዳከመች ሲመስለው እቅዱን ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው አለ።
ዚያድ ባሬ ያሰበውን ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተጠቀመ። ያዋጣኛል ያለውን የሴራ መንገድ ሁሉ ተከተለ። ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ በተደራጀ ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም የሴራው አካል ነበር። ጦርነቱ በግልፅ በታወጀበት በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ድረስ ዘልቆ ገባ።
በመጀመሪያ በሶብየት ህብረት እና በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ። የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት የመጣው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር።
ልክ ዓድዋው በዚህን ጊዜም የኢትዮጵያው መሪ ለጀግና ሕዝባቸው የክተት ጥሪ አቀረቡ። ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም በብሔራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚከተለውን የክተት ጥሪ አቀረቡ።
‹‹… ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች። ለብዙ ሺህ ዓመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት! የኢትዮጵያ ሕዝብ! ለክብርህንና ነፃነትህን ለመድፈር አገርህን ለመቁረስ የተጀመረው ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!››
በተደረገለት ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ ወጣ። የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍፁማዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ ርምጃዎች መታየት ጀመሩ። ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከሚባለው ተራራ ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የኢትዮጵያ ወታደር የጦር አረሮች ምድሪቱን ዘነቡባት።
ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ህልም አንግቦ የነበረው የዚያድ ባሬ ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ። ኢትዮጵያ በታሪክ እንደለመደችው ድል አሁንም አደረገች።
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ የፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮዋ ኩባ አጋር ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት ታወጀ።
በመጽሐፋቸው ላይ ባስቀመጡት በአንዲት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ገጠመኝ እንሰናበት። በኩባ እና በሌሎች ወዳጅ ሀገራት አማካኝነት ኮሎኔል መንግሥቱ እና ዚያድ ባሬ ለውይይት ተጠርተው በየመን ይገናኛሉ። ዚያድ ባሬ እብሪተኛ ስለሆነ ኮሎኔል መንግሥቱ የእብሪት መልስ እንዳይመልሱ በወዳጆቻቸው ተመክረዋል።
የተፈራው አልቀረም በውይይቱ ላይ ዚያድ ባሬ ኮሎኔል መንግሥቱን ‹‹ጦርነት የት ታውቃለህና ነው! ጦርነት እንዴት እንደሆነ አሳይሃለሁ›› ብሎ ፎከረ። ዳሩ ግን ኮሎኔል መንግሥቱም እብሪተኛ ነበሩና (መታገስ አልቻልኩም ነው የሚሉ እርሳቸው) ምክሩን ጥሰው ‹‹ማን ጦርነት እንደሚችል እንተያያለን! እዚያው እንገናኝ!›› ብለው ፎከሩ። ውይይቱም ያለ ስምምነት ተቋጨ።
እነሆ ጦርነት ማን እንደሚችል ታየ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም