ንብ አናቢዋ የጤና ባለሙያ

ጥንካሬዋ በሕይወት ውጣ ውረድ ተፈትኖ ያገኘችው ሽልማቷ ነው። በሁለት ወገን የተሳለች ሰይፍ፤ መልካም እና ብርቱ ሴትነቷን ከአንደበቷ በላይ ድርጊቷ ይገልጸዋል። ተግባቢና ተጫዋች ግን ደግሞ ያለሥራ የሚባክን ጊዜ የሌላት ታታሪ፤ የሥራ አማራጮችን በመፍጠር ሁሌም ኑሮዋን ለማሸነፍ የምትጥር ባተሌ፤ የጤና ባለሙያ ብቻ ሳትሆን በሌማት ትሩፋት ሥራ በመሠማራትም ፈር-ቀዳጅም ነች ሲስተር ዘውዴ አበራ ።

ሲስተር ዘውዴ አበራ በወሎና ጎንደር መሐል ባለች ዳውንት በተሰኘች ስፍራ ነው የተወለደችው። ለመማር ብሎም ሕይወትን ለማሻሻል በሚል ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በልጅነቷ ነው። የአዲስ አበባ ኑሮዋ እንዳሰበችው አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ገና በልጅነቷ በብዙ መከራና ችግር ተፈትናለች፤ ከምትኖርበት የዘመድ ቤት ተባራ ደጀ ሰላም እስከማደር ደርሳለች ፡፡

እነዚያ ማረፊያ አጥታ የተንገላታችባቸው፤ ርቧት መከራ ያየችባቸው መጥፎ ገጠመኞቿ በዛሬው ሕይወቷ ውስጥ የሚተረጎም የብርታትና የጥንካሬን ስንቅ ስላስ ቋጠሯት በመልካም እንጂ በመጥፎ ልትመነዝራቸው አትፈ ልግም።

የሰው ልጅ ‹‹አንድም ከፊደል ሀ ብሎ ሁለትም ከመከራ ዋ ብሎ›› እንደሚማር ሁሉ ሲስተር ዘውዴም ከሁለቱም ያገኘቻቸውን ልምዶች ወደ ጥሩ ዕድል እየቀየረቻቸው ኑሮዋን እየገፋች ነው። በትምህርት ያገኘቻቸውን እውቀቶች ብቻ ሳይሆን የመጥፎ አጋጣሚዎቿን ተሞክሮዎችም ጭምር የጥንካሬዎቿ ምክንያቶች አድርጋ ስለምትመለከታቸው አትከፋባቸውም ።

ሲስተር ዘውዴ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ እዚሁ አዲስ አበባ በቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተምራ በነርስነት እንደተመረቀች ወዲያውኑ ወደ ትዳር ዓለም ተቀላቀለች ። የሦስት ልጆች እናት ለመሆንም በቃች፤ በአሁኑ ጊዜ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ቃሊቲ ወረዳ ሰባት ጤና ጣቢያ በነርስነት ታገለግላለች። ለስምንት ዓመታትም በሙያው አገልግላለች።

የጤና ባለሙያነት ልቧ የሚያርፍበት ሥራ እንደሆነም ትናገራለች ። ‹‹ሴት እህቶቼን ከአካላዊ ብቻ ሳይሆን ከው ስጣዊ ሕመማቸው መፈወስ ያስደስተኛል›› ትላለች ።

ሲስተር ዘውዴ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ቤት ለቤት የጤና አገልግሎት እንደሚሰጡ ትናገራለች። አብዛኛውን ጊዜ ይህን አገልግሎት የምትሰጠው ኮየ ፈጬ አካባቢ በአስር ዘጠና የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ለሚኖሩ ሰዎች ነው ። እነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቹ የገቢ አቅማቸው አነስተኛ አቅመ ደካሞች ስለሆኑ ሁሌም ከጎናቸው መሆን ያስደስታታል።

አገልግሎት የምትሰጣቸው ሰዎች አቅመ ደካ ሞችና ሕመምተኞች ብቻ ሳይሆኑ አጠገባቸው ሆኖ የሚደግፋቸው ሰው የሌላቸውና አንዳንዶቹም ምግብና አልባሳት እየተረዱ የሚኖሩ ናቸው፡፡

ሲስተር ዘውዴ ለእነዚህ ሰዎች ከምትሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪም አቅሟ በፈቀደ ሁሉ ካላት ላይ ትረዳቸዋለች፤ የልጅነቷን የማጣት ዘመን በሰዎች ድጋፍ አልፋ እዚህ መድረሷን እያሰበች እርሷም ለተቸገሩ መድረስን ትወዳለች፡፡

አሁን የምትኖርበትን ኮዬ ፈጬ አካባቢ በደንብ ያወቀችው በሥራዋ አማካኝነት ነው።ለኑሮም የመረጠችው ያኔ ነው። በምትሠራቸው መልካም ሥራዎች በኮዬ ፈጬ አካባቢ ታዋቂ እስከመሆን ደርሳለች። ሰዎች ክብር ይሰጧታል፤ ይመርቋታል፤ ትራንስፖርት ውስጥ ስትገባ ሂሳብ ይከፍሉላታል።

በሥራ ምክንያት ባወቀችው ኮዬ ፈጨ መንደር ቤት ሠርታ መኖር ከጀመረች ወዲህ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስታስብ መጀመሪያ የመጣላት ንብ ማነብ ነው። አሁንም በቋሚነት የሕክምና ሥራዋን እየሠራች ጎን ለጎን ባላት ትርፍ ጊዜ ንብ ታናባለች፡፡

‹‹ንብ ማነብ የሙሉ ቀን ጊዜ እና ክትትል ስለማይፈልግ መደበኛ የሥራ ጊዜዬ ላይ ጫና ሳያሳድር ማከናወን እችላለሁ›› ትላለች። በንብ ማነብ ሥራዋ በትንሽ ወጪ ጥሩ ገቢ ታገኝበታለች ። 28 የንብ ቀፎዎች አሏት።በዓመት ሦስት ጊዜ ታመርትባቸዋለች፤ በዚህም በአንድ ጊዜ ከ150 እስከ 200 ኪሎ ማር ታገኛለች። ይህም የእርሷን እና የቤተሰቧን ሕይወት በአግባቡ ለመምራት እንደረዳቸው ትገልጻለች።

ከንቦች ጋር ያላት ትውውቅ የቅርብ ጊዜ አይደለም። በትውልድ ቀዬዋም ሳለች ቤተሰቦቿ ንብ ያናቡ እንደነበር ታስታውሳለች ። የንብ ማነብ ፍላጎቱ ያደረባት ምናልባትም የልጅነት ምልከታዋና ትውስታዋ ያሳደረባት ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችልም ትገምታለች።

ባለቤቷና ቤተሰቦቿም ሥራዋን ይደግፉላታል፤ የመኖሪያ ሥፍራዋ ለዚህ ሥራ ምቹ መሆኑም ሕልሟን እውን ለማድረግ ረድቷታል፡፡ የገበያ ዕድሎችም አያመልጧትም፤ ባገኘቻቸው አጋጣሚዎች የምታመርተውን ማር ታስተዋውቃለች። የተፈጥሮ ማር ስለሆነ ምርቷ ተፈላጊ ነው፤ ታዋቂና በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነም ትናገራለች።

ሲስተር ዘውዴ መደበኛ የሥራ ጊዜዋን በማይነካ መንገድ ሌላም ሥራ እየሞከረች ስለመሆኑ ነግራናለች፤ ወደፊት በደንብ አስፋፍታ ለመሥራት የገበያ ጥናት ላይ እንዳለችም ገልጻለች ።

‹‹ሕይወት ዳገትና ቁልቁለት አለው›› የምትለው ሲስተር ዘውዴ፤ ‹‹የተደላደለ መንገድ ላይ መድረስ የሚቻለው ሥራን ሳይንቁና ሳያማርጡ መሥራት ሲቻል›› ነው ትላለች። ሌሎች ሴቶችም የወንድና የሴት፤ ትንሽ እና ትልቅ ሥራ ሳይሉ አካባቢያቸው የሚፈቅድላቸውን ሁሉ ሠርተው እንዲለወጡ ትመክራለች፡፡

‹‹ሰው ጤነኛ ከሆነና ዓላማ ካለው ሠርቶ መለወጥ ይችላል›› የምትለው ሲስተር ዘውዴ፤ በተለይም እኛ ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ ለመውጣት ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You