ራስን ፈልጎ የማግኘት ጥረት

መምህርት ናት፤ ትውልድን በእውቀት የምታንፅ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ሥነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት የህትመት ጥበባት ትምህርት ክፍል ትሠራለች። ተክለ ሰውነቷ ለመምህርነት የተሠራች የምትመስል ፍልቅልቅ ነች፤ እይታዋና ነገሩን የምትገልጽበት መንገድ ለአድማጭ ተመልካቹ እጅን በአፍ አስጭኖ ትኩረትን የሚወስድ ነው። ቁም ነገሩን በቀልድ፣ በሳቅ እያዋዛች ለማስረዳት ብዙ ሃይል አትፈጅም፣ ባለ ራዕይ ፣ ለሙያ ራሷን የሰጠች ‹‹ምነው በእሷ የመምህርነት ዘመን ተማሪ በሆንኩ›› ታሰኛለች። በዚያ ላይ ወጣት ነች። ይህቺ ሴት የዛሬው የሴቶች ቀን እንግዳችን መምህርት ሜሮን ኃይሉ ነች።

ተወልዳ ያደገችው ጅማ ነው። እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቷን የተከታተለችውም በዛው በትውልድ ሀገሯ ጅማ ከተማ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመማር ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርሺቲ ጎራ ብላለች፤ በቆይታዋም በአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል በዲግሪ ተመርቃለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በህትመት ጥበባት ዲግሪ አግኝታለች፤ በዚህም ሳታበቃ ደቡብ ኮሪያ በማቅናት በቴክስታይል አርት ሁለተኛ ዲግሪዋን ሠርታለች።

የሕይወት ዳዋን ስንበረብር

ሕይወት የራሷ ጎዳና አላት፤ እኛ ስላሰብን፣ አጋጣሚ ስለገጠመን የሚሆን ነገር የለም። ሕይወት በስሌትም በስሜትም አትመራም በራሷ ቀመር እንጂ። አንድን ነገር ይዞ ብቻ ‹‹ተሳካ አልተሳካ›› ከማለት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ማየትና ውስጥን መፈለግ ውጤታማ እንደሚያደርግ የመምህርት ሜሮን የሕይወት ጉዞ ያሳየናል።

ትምህርቷን በአንትሮፖሎጂ ታጠናቅ እንጂ በዘርፉ ከፎቶ ያለፈ ትውስታን አላስቀመጠችም። በተመረቀችበት ሥራ ለማግኘት ግን ወጣ ገባ ብላለች። የሥራ ማስታወቂያ ባየችባቸው ተቋማት ሁሉ ጎራ ብላ አለሁ ብላለች። ፈተና ተፈትናም ተጠባባቂ እስከመሆን ደርሳለች። ሥራውና እሷ ባይገናኙም እድል ግን ሌላ አቅጣጫ መኖሩን አሳየቻት።

«ከልጅነቴ ጀምሮ አርትን የመውደድ ነገር አለኝ። ስዕል የመሳል ዝንባሌ ነበረኝ ። ይሄ ግን በወረቀት ላይ ከመሞነጫጨር ከደብተር ጀርባ ላይ ከመጫጫር ያለፈ አልነበረም። ስዕል (አርት) በትምህርት ቤት ደረጃ እንደሚሰጥ እውቀቱ አልነበረኝ። ልጅ ሆኜም አባባ ተስፋዬ ፕሮግራም ላይ የሚታዩ የዓለም አቀፍ የህጻናት የስዕል ውድድር ሲባል እሰማ ነበርና ይሄ ይሄ ነገር ይመስለኛል ወደ አርቱ ዘርፍ የሳበኝ ትላለች።

በተማረችበት አንትሮፖሎጂ የትምህርት ዘርፍ ሥራ መፈለጉን ተያያዘችው ሆኖም ዕድል ፋንታዋ አልነበረምና በተወዳደረችባቸው ተቋማት የተለያዩ ምክንያቶች ሲሰጧት ፤ አንድ ሶስቱ ደግሞ ተጠባባቂ ሲያደርጓት። እሷ ግን ቁጭ ብላ መች ይጠሩኝ ይሆን ? እያለች አልተጠባበቀችም። ጊዜዋን በመጠቀም ያዋጣኛል ባለችው መስክ ለመሰማራት በልቧ ማሰብ ጀመረች። ይህም ተሰጦዋን እንድትሻ ምክንያት ሆናት።

ወደ አርት ስኩል

በአርት ስኩል አምስት አይነት የትምህርት ክፍሎች አሉ። የቀለም ቅብ፣ የህትመት ጥበባት፣ ኢንተር ዲስፕነሪ፣ ዲዛይንና የቅርጽ ትምህርት ክፍል። ተማሪዎች እነዚህን ዘርፎች አውቀውና ተረድተው መምረጥ የሚችሉት የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን ከተማሩ በኋላ ወደ ሁለተኛ ዓመት ሲገቡ ነው። የስዕል ትምህርት ሲባል በሁሉም ሰው አእምሮ የብሩሽ ቅብ ብቻ ነው የሚመስላቸው ። ወደ ትምህርት ግቢው ከገቡ በኋላ ግን የተለያዩ ዘርፎች እንዳሉ ይረዳሉ። ከዛም የበለጠ ወደሚሳቡበት ዘርፍ ይሄዳል። መምህርት ሜሮንም የህትመት ጥበብ ዘርፍ ስለሳባት ነው ወደዚሁ ሙያ የመጣችው።

«ይሄ ዘርፍ ብዙ አይነት ህትመት የሚታተምበት ብዙ መንገዶች አሉት። በብሩሽ ቀለም መቀባት ብቻ ሳይሆን ህትመትም በብዙ ቴክኒኮች ከአንድ በላይ የሆነ ውጤት ታገኛለሽ። ይሄ ያስደስተኝ ስለነበር መረጥኩት።» የሙያ አቅጣጫዋን እንዴት እንደወሰነች እየገለጸች።

የማህበረሰብ ተጽዕኖ

አንድ ሰው ከተመረቀ በኋላ የቤተሰቡ ጥገኛ መሆን የለበትም የምትለው ሜሮን ፤ እሷም ይህን በማመን የቤተሰባ ጥገኛ ላለመሆን የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጋለች። «በተማርኩበት ሙያ መሥራት ባለመቻሌ ወደ አርቱ መጣሁ፤ በወቅቱ ግን መንገዶቹ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ‹አሁን ደግሞ ይህን ልትማሪ› የሚሉ አስተያየቶች ሜዳውን ተቆጣጠሩት። ሌላው ቀርቶ የተማረ ከሚባል ጎረቤት የተሰጠው አስተያየት ከሁሉም የሚገርም ነበር። ለእናቴ ‹የት ልትገባ ምን ልትማር ብሎ ከጠየቀ በኋላ ለምን የማስተርስ ፕሮግራም አታስተምሪያትም› አላት። ይህ ሰው የዶክትሬት ትምህርትን የሚማር ውጪ ሀገር የሚመላለስ ያውቃል የሚባል ነው ። ሌሎችም ለምን ሌላ ፊልድ አትመርጥም የሚሉ እንዲሁ ድምጾች በረከቱ ። በተማርሽበት አትሠሪም የሚሉኝም ነበሩ፤ ግዜሽን ልታጠፊ ነው የሚሉም አልጠፉም። ምክንያቱም ከአርት ጋር ተያይዞ በሁሉም ሰው አእምሮ የተሳሉ ነገሮች አሉ። እንደ ሙያ ያለመቁጠር ። በድራማ፣ በሚዲያ፣ በሙዚቃው…አርት ጥሩ ተደርጎ አልታየም። እናም ዱርዬ ልትሆን ነው እብድ እብድ ልትጫወቺ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው» ትላለች ስዕል በሰዎች አእምሮ ያለውን አስተሳሰብ የታዘበችበትን አጋጣሚ ስታስታውስ።

በሜሮን አእምሮ ውስጥም ስለ ስዕል ያለው ግንዛቤም ብዙም የተለየ አልነበረም። ግን ደግሞ ድብቅ የሙያው ፍቅር አለ ። እናም ሥራ ፈላጊ ሆና ባለችበት ወቅት በቴሌቪዥን አንድ ማስታወቂያ ተለቀቀ። ማስታወቂያው በአንድ የግል የሥነ- ጥበብ ትምህርት ቤት በክረምት አጫጭር ሥልጠና ለመስጠት ነው። ይሄን በልቧ ይዛ ሳለ ቤተሰቦቿ ደግሞ ትምህርት ጨርሳ መቀመጧ ስላሳሰባቸው «ሌሎች ነገሮች አካውንቲንግም ቢሆን ብትማሪ» ሲሉ ሃሳብ አቀረቡ ። ይሄ መልካም አጋጣሚ በልቧ ያለውን ትምህርት የመማር ፍላጎት ገልጻ አወጣች።

«እኔም የስዕል ትምህርት ብማር ብዬ አስቤ ነበርና ይሄንን የክረምት ሥልጠና መውሰድ እንደምፈልግ ገለጽኩላቸው ፤ እነሱም ፈቃደኛ ሆኑና ሥልጠናውን ጀመርኩ» ይሄ መልካም አጋጣሚ ደግሞ ሥልጠናው ላይ በሥራዋ የሚያደንቃትን ሰው አገናኛት። ከአለ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር የነበሩ ሰው ሥልጠናው ላይ ይሳተፉ ነበርና ሥራዋን አይተው አበረታቷት ። 12ኛ ክፍል ጨርሳ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካመጣች መማር የምትችልበት እድል እንዳላትም ነገሯት፤ ይሄንንም አረጋጥኩላቸው። ከዛም የምዝገባውንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስፈላጊ የሆኑ መረጃ ሰጡኝ። በዚሁ መሠረት ተመዝግቤና የመግቢያ ፈተና ተፈትኜ የአለ ሥነጥበብ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆንኩ። አንዳንዴ የእግዜር መንገድ ይባል የለ ባላሰብኩትና ግን ደግሞ ወደምፈልገው ሙያ ተቀላቀልኩ» ትላለች።

ዛሬ ባለ ሁለት ዲግሪ ናት፤ ከደቡብ ኮሪያ ደግሞ በጨርቃጨርቅ ዲዛይን ሁለተኛ ዲግሪዋን ሠርታለች። መምህርነቷ ከልቧ እንደሚያስደስታት ትናገራለች። ምክንያቷ ደግሞ ሁልጊዜ የምታገኘው አዳዲስ ተማሪዎችን በመሆኑ ነው። ከአዳዲስ ተማሪዎች አዳዲስ ሃሳቦች ይፈልቃሉ። ሁልጊዜ ታነባለች ። «ተማሪዎች እያንዳንዱን ነገር የሚያዩበት መንገድ ለእኔ አስተማሪ ነው። ይሄ በጣም ያስደስተኛል፤ በቴክኒክ ደረጃ አንድ አይነት ቴክኒክ ብታስተምሪም በየሰው ጭንቅላት ያለው አተያይ ይለያያል። ግልጽ እና ነጻ መሆንን ሙያው ይጠይቃል። ስለዚህ በተቻለ መጠን ሙያው የሚፈልገውን ለመሆን ነው የምፈልገው»

የማይደፈሩ መስኮች

ወደ አርቱ አካባቢ ብዙውን ጊዜ የሚመጡት ወንዶች ናቸው። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ደግሞ ሴቶች ብቻም ሳይሆኑ ብዙ ሰዎችም አይመጡም። የመረጃ እጥረት እና አለማወቅ አንዱ ምክንያት ነው። ቢመጡም የትምህርት ቤቱ የመቀበል አቅም ውስን መሆን ደግሞ ሌላው ነው። ከኢትዮጵያ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በዲግሪና በማስተርስ ፕሮግራም የስዕል (አርት) የሚያስተምር ብቸኛው ትምህርት ቤት ነው።

አለ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ነው። ረጅም ዓመትን ያስቆጠረ ትምህርት ቤት ነው። ሆኖም አሁንም ድረስ የሚቀበለው የተማሪ ብዛት በጣም ጥቂት ነው። ቀደም ሲል በዓመት የሚቀበለው እስከ 15 የነበረው አሁን ግን ከመላው ሀገሪቱ የሚቀበለው 40 ተማሪ ደርሷል። ትምህርቱን ፈልጎ የሚመጣው ተማሪ ቁጥር ማነስ እንዲሁ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ተማሪዎች የቅበላና የተግባር ፈተና ይፈተናሉ። ፈተናው ምን ያህል ይችላሉ ወይም ምን ያህል በትምህርቱ መቀየር ይችላሉ የሚለውን የሚለዩበት ነው።

ያም ሆኖ ግን ሴቶች ደግሞ በተለይ ወደ ሥነ-ጥበቡ ለምን አይመጡም ሲባል ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው አርትን እንደትምህርት አለመቁጠር ነው። የቤተሰብ ጫናም ይኖራል። የቤተሰብ ፍላጎት ዶክተር ወይም ኢንጂነር ወይም ሌሎች ሙያዎች ላይ ነው። ሴቶች ወደ አርቱ የማይመጡት ፈጣሪ ሳይሆኑ ቀርተው አይደለም። እንዳውም ሴቶች በጣም ክሬቲቭ ናቸው። በዓለም ላይ ከታዋቂ ሰዎች የሚበዛው የሴቶች ነው።

መምህርት ሜሮን ወደፊት ነገሮች እየተለወጡ እንደሚመጡ ታምናለች። እሷ በተማሪነት ከነበረችበት ጊዜ በበለጠ አሁን የሴት ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል፤ አሁን ላይ መሻሻሎች አሉ። ሴቶች ይመጣሉ ፣ አሪፍ አሪፍ ሥራዎችን ይሠራሉ፤ በጥሩ ውጤት ይመረቃሉ። የፈጠራ ክህሎት ማነስ ሳይሆን ምናልባት የመረጃ ማጣት የመሳሰሉ ብዙም ለውጥ የሚያመጡ የማይመስሉ ነገር ግን ለውጥ የሚያመጡ ነገሮች ናቸው ሴቶችን እየጎተቱ ያሉት ብላም ታስባለች።

መረጃን በማግኘት ዙሪያ ሴት ወንድ ተብሎ የሚለቀቅ መረጃ አይኖርም፤ ነገር ግን ወንዶች መረጃን በማግኘት ረገድ ከሴቶች የተሻሉ ናቸው። ከትምህርት ቤት ቆይታ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር የመገናኘት የመጨዋወት ሁኔታ ይኖራል። በዚህ የውጪውን ዓለም የመተዋወቁ ሁኔታ ይኖራል። ሴቶቹ አካባቢ ደግሞ ሁላችንም እንደምናደርገው ከትምህርት ቤት ቆይታ በኋላ ቀሪውን ጊዜ የምናሳልፈው በቤት ውስጥ ነው፤ ጓደኛ ጋር መሄድ ፣ ከቤት ውጪ ማሳለፍ ብዙም አይታሰብም፤ በቤት ውስጥ ሥራ እና ቤተሰብ በመርዳት ላይ ነው ትኩረቱ። ስለዚህ የወንዶቹን ያክል መረጃ የማግኘት ሁኔታ አይኖርም። አሁን ግን በተለይ ማንበብ መጻፍ የሚችለው የተንቀሳቃሽ ስልክ በእጃቸው ያላቸው ሴቶች መረጃን ለማግኘት ያንን ያክል ከባድ አይሆንባቸውም። ግን ደግሞ ያለን ሰፊ ሀገር በመሆኑ አብዛኛው ዜጋ በተለይ በገጠር አካባቢ ያልተማረው ማህበረሰብ ጋር ለመረጃ ቅርብ እንዳይሆኑ የሚያንቃቸው ጉዳይ አለ።

ሴቶችን ለመሪነት

ሜሮን እንደምትለው፤ ማህበረሰቡ የሚያምንበት ፣ ሴት የተቀረጸችበት እና አሁንም እየኖርንበት ያለው መንገድ ሴቶች ወደፊት እንዲወጡ የሚያደርግ አይደለም። ሆኖም ደግሞ ሁሉንም ነገር በጭፍን መካድ አይገባም፤ በተወሰነ መጠንም ቢሆንም ለውጦች ይታያሉ። ፊደል ቆጠረ ተማረ በሚባለው ማህበረሰብ አካባቢ ግን አሁንም ቢሆን የምር የሆነ ለውጥ ሳይሆን የማስመሰል አይነት ሁኔታ ነው የሚታየው ። ሴቶች የሚፈልጉትን ነገር መሆን እንዳይችሉ የሚያደርጉ፣ ማንነትንና ራስን ፈልጎ የማግኘቱ መንገድ ገና በጣም ብዙ ያንሳል።

ሴቶች ራሳቸውን ፈልገው ማግኘት ራሳቸውን ሆነው መቆም እንዲችሉ ማድረግ ጊዜ ይወስዳል ። «እኔ ራሴን ፈልጌ ለማግኘት አሁን ትግል ላይ ነኝ። ግን ደግሞ ባለንበት ደረጃ ላይ ሆነንም በየደረጃው የምናጣጥመው ከመማር ከማገናዘብ ነጻ የሆነ ጭንቅላትን ከመፍጠር ባሻገር ራስን ማየት የትጋር ነው የቆምኩት ? ምንድነው የምፈልገው? እንዴት ነው ማሳካት የምችለው ? የሚለውን መንገዶች ማየት እና ለእሱ መጣር ይገባል።

አርአያዎቼ

ስለሴቶች ስናስብ ሞዴሎቻችን ማናቸው ስንል በቅርብ ካለችው እናታችን መጀመር አለብን። መጥፎ የሆኑ አስተሳሰቦች ቢኖሩም እንኳን እሱም ፈልገውት ያመጠት አይደለም። ጭለማ በሆነ ሕይወት ውስጥ የኖረ ሰው ለምን እንትን ትወዳለህ ማለት አይቻልም። ነገር ግን እናቶቻችን ትልቅ ሞዴሎቻችን ናቸው። ሌላው ዓለም ላይ ጭምር ሞዴል የሚሆኑ ሴቶች አሉ። ነገር ግን ከአጠገባችን በራቅን ቁጥር ድርሰት መስሎ ይሰማናል። ሁላችንም ቤት በቅርብ ያሉንን እህት፣ እናት፣ አክስት፣ አያትና ጎረቤት ብናይ አርዓያዎቻችን (ሞዴሎቻችን) ናቸው፤ እናቶቻችን ሲያስተምሩን እኮ ከእነሱ ኑሮ የተሻልን ሆነን እንድንፈጠር ነው። ስለዚህ አጠገባችን ካለው ቤተሰብ የምንወስደውን መውሰድ ያስፈልጋል። በቤተሰብ ደረጃ ፣ በኢትዮጵያ ካሉም ከሀገር ውጭም አርአያ መሆን የሚችሉ አሉ። ለእኩልነት ለነጻነት የታገሉ አሉ፤ ከዛም ደግሞ ማህበረሰብን መልሰው የሚረዱ አሉ። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለእኔ ጥሩ አርአያ ናቸው። የመጡበት መንገድ ፣የደረሱበት ደረጃ አስተማሪ ነው። ይሄ ብዙ ነገሮችን አልፎ የተደረሰበትን ደረጃ ያሳያል። ሌሎችም አምባሳደሮች፣ በህክምናው፣ በሚኒስትሮች…አሉ በስልጣን ደረጃም።

ከሙያዬ አንጻር ሳየው ደግሞ ከበላዬ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ ከበታቼም ያሉት በጣም ያስደስቱኛል፤ በጣም የማደንቃቸው አሉ። ከእኔ በፊት የነበሩ ለሙያው በር የከፈቱልኝ ሰዎች ለእኔ አርአያዎቼ ናቸው። ሰዓሊ ደስታ ሀጎስ ለሙያው በሴቶች መንገድ የቀደደች ናት። ሌሎችም አሉ ፤ «እኛ እዚህ ደርሰናል እናንተም ትችላላችሁ» የሚለውን መልዕክት ወደ ውስጣችን የከተቱ ናቸው።

በብዙ የሥራ ዘርፎች ላይ የወንዶች ዓለም በሆነበትና የወንዶች ተጽዕኖ በበዛበት ዓለም ነው ያለነው። ያም ሆኖ አርት ከወንዶች እኩል ወይም በተሻለ መልኩ ለዘርፉ የሠሩ ብዙ የስዕል አውደ ርዕይ ያሳዩ በሀገር ውስጥም በውጪም አሉ።

ማርች 8

ማርች 8 ሴቶች ለእኩልነት፣ ለነጻነት እና ለመብታቸው ታግለው መብታቸው እንዲከበር ያደረጉበት ቀን ነው። የሴቶች ቀን ሲባል ታዲያ ይሄ ቀን ብቻ አይደለም ፤ 365ም ቀን የሴቶች ቀን ነው። ነገር ግን ሴቶች ለመብታቸው ታግለው መብታቸውን ያስከበሩበት ቀን በመሆኑ ነው ቀኑን አስበነው የምንውለው እንጂ የሴቶች ቀን አንድ ቀን ብቻ አይደለም። ስለዚህ ቀኑን የምናከብረው በሥራ ነው። ከዚህ ቀደም የስዕል ሥራዎቼን ኤግዚቢሽን አሳይቻለሁ።

እኔ አሁን የምታገለው የራሴን ዓለም ለማግኘት ነው፤ አሁን ያለው የወንዶች ዓለም ነው። ይሄ ማለት ግን በወንዶች መለኪያ በወንዶች መነጽር ያለችው ዓለም ትቀራለች ማለት አይደለም። እኔ እራሴን ከዛ ውስጥ ባልወጣ የእኔ ልጆች ከእዛ ውስጥ ይወጣሉ ማለት አይደለም፤ እንደ እድል ሆኖ ዓለም በጠቅላላ የወንዶች የበላይነት የሚመሯት ናት። ሴቶችን እኩል ሊያስደርግ የሚችል እኩልነትን የሚያረጋግጥ መብትን የሚያስከብር ሌሎች ብዙ ማርች 8 ያስፈልገናል ትላለች።

የችግሩን ስፋት በምሳሌነት ስታስረዳም ፤ ለምሳሌ ያህል አስገድዶ መድፈርን እንመልከት ወንዶችም የዚህ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን የትኞቹ ላይ ይበረታል? ማነው ተጠቂው? ማነው አጥቂው? ብለን ስናስብ ዛሬም የሴቶች ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ መቀጠሉን እናያለን። ብዙ ቀልፍ የሆኑ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው ካልን ፣ ሕግ አውጪው ማን ነው፣ እያልን ጥያቄ ብናነሳ ወደድንም ጠላንም ወንዶች ይበዛሉ። እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን በወንዶቹ ልክ ብቃት እውቀትና ትምህርት ያላት ሴት ሳትኖር ቀርታ አይደለም። ሚዛኑ ወደ ወንዶች ስለሚያደላ ነው። አንድ ቦታ ላይ ሴትና ወንድ ተወዳድረው እኩል ደረጃ ቢያገኙ እድሉ የሚሰጠው ለወንዱ ነው። ለሴቷ እድል የሚሰጣት ምናልባት ወንዱን ከእጥፍ በላይ የምትበልጠው ከሆነ ነው። ምናልባት ለእኔ አርት የሰጠኝ ነጻነት አለ ብዬ አስባለሁ። በአርቱ ላይ በነጻነት እንዳሻኝ ሃሳቤን እንድገልፅ እድል ይፈቅድልኛል፤ በአርቱ በነጻነት የማድረግን እድል ይሰጠኛል። ግን ደግሞ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተጽዕኖ አያሳድርም ማለት አይደለም።

ማርች 8 መከበር ከጀመረ ጀምሮ አንዳንድ ለውጦች አሉ። ሴቶች የመምረጥ የመመረጥ፣ እኩል ሀብት የማፍራት የመካፈል የመሳሰሉ ለውጦች አሉ። ሥራ የመሥራት ነጻነቶችን አግኝተዋል። ይሄ እንደየ ሀገሩ ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ ይሆናል። በሀገራችን ደግሞ ለውጥ አለ እላለሁ። ነገር ግን ለውጡ መሠረታዊ ለውጥን በሚያመጣ መልኩ ነው ወይ ከተባለ ግን ይሄ ላይሆን ይችላል። መቀየር ይችላል ወይ ከተባለ ግን መቀየር ይችላል። በጊዜ ሂደት ማህበረሰቡ ራሱን የሚቀይርበት ሁኔታ ይኖራል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአብዮት የሚቀየር ይኖራል። ቢሆን ግን ጥሩ የሚባለው ሁለቱንም ባጣመረ መልኩ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው። በተፈጥሮ የሚፈጠር መቀየር አለ ፤ ለዚህ ትግስት አልባ መሆን መቻል አለብን። በቀጣይም የሚለወጡ ይኖራሉ። ለሁሉም ጊዜ ያስፈልጋል።

ለውጥን ስናስብ ምንጊዜም መሥራት ያለብን በሴቶች ላይ ብቻ አይደለም። ወንዶችም በሴቶች ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊ መሆን አለባቸው፤ ሴቶች ብቻቸውን የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም። የሴቶችን ጉዳይም ወንዶች ሊያጣጥሙት፣ ህመሙም ሊሰማቸው ያስፈልጋል። ያ ሲሆን ለውጡን በአጠረ ጊዜ ልናመጣው እንችላለን። ወንድ ልጅ ሲወለድ «ወንድ ወንድ» ተብሎ የተጨበጨበለት፤ ሲያድግም አንተ እኮ «ወንድ ነህ» እየተባለ ያደገ በሴት መበለጡን ላለመቀበል የሃይማኖት ጥቅሶችን ከመጽሀፍ ቅዱሱ ከቁራኑ እያጣቀሰ መብለጡን ለማሳመን ይሞክራል። ይሄ ሁሉ እኔ የበላይ ነኝ ለማለት ነው። ይሄንን አስተሳሰብ ይዞ ላደገ ወንድ ባንድ ጊዜ ተቀየርልኝ ማለት አይቻልም። በሂደት በትምህርት ግን ለውጥ ማምጣት ግን ይቻላል። በውጪው ዓለም በኩል ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። እዚህም እንደሚለወጡ ተስፋ አለን አሁን ግን ሥልጣኑ ላይ፣ ገንዘቡ ላይ፣ ውሳኔ ሰጪነት ላይ ወንዶች ሆነው ብቻችንን ለውጥ አናመጣም። ነገር ግን በጋራ ሆነን ለውጥ እናመጣለን፤ ኑ ተሳተፉ፣ ኑ ችግሮቻችንን እዩ፣ ቁስላችንን ተመልከቱ ፣ ቀረብ ብላችሁ ተረዱን ማለት መቻል አለብን። ለዚያ በጋራ መንቀሳቀስ አለብን።

በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን አመለካከት ለመቀየር ቢያንስ አሁን በልጆቻችን ላይ በደንብ መሥራት አለብን። ቀደም ሲል በዛ ውስጥ ያለፉትን በሚፈለገው ልክ ምናልባት ማረቅ ይከብድ ይሆናል። ስለዚህ በለጋዎቹ ላይ መሥራት፣ ከአሳሪ ወጎች በወጣ መልኩ መቅረጽ እና መጪውን ዘመን የሴቶች እኩልነት የተረጋገጠበት፤ መብትና ጥቅማቸው የተከበረበት እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል።

ዕድገት በሙሉነት

መምህርት ሜሮን ሁሉም ነገር ከቤት ይጀምራል የሚል ሃሳብ አላት። በቤት ውስጥ ወንዶችን ለመቀየር መሥራት በማህበረሰብ ደረጃ ይሄን አስተሳሰብ ማስፋት፣ በትምህርትና ንባብም የሚቀይሩ ናቸው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ሴቶች የቤተሰባቸው መሪ ናቸው፤ የቤተሰባቸው አስተዳዳሪ ናቸው። በማንኛውም መልኩ ብቁ ናቸው። መሪነት ደግሞ የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። ሴቶቹም የመሪነት ብቃት እንዳላቸው ሳያውቁ አልቀሩም። ነገር ግን በሌሎች የመሪነት ቦታ ላይ ለመቀመጥ እድሉን ማግኘት አይችሉም፤ በሩ ይዘጋባቸዋል።

እኔ ተወልጄ ያደኩት የተማርኩትም ጅማ ነው። ወላጆቼ መምህራን ስለሆኑ ይመስለኛል ብዙም የቤተሰብ ተጽእኖ አላረፈብኝም። በራሴም እንድቆም ያደረገኝ ይሄ ነው ብዬ አስባለሁ። አሁን ያለኝን ማንነት እንዳገኝ ደግፈውኛል። ዝምበይ ዝምበይ ተብዬ አላደኩም። ስማር ሳነብ ስጫወት ነው። በፍላጎቴ መሆን የምፈልገውን ሆኜ እንዳድግ አድርጎኛል።

ወላጆቼ ገቢያቸው ትንሽም ስለሆነ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ የትምህርትን ጥቅም ስላጣጣሙ «እኛ የምናወርሳችሁ ምንም ነገር የለም፤ የምናወርሳችሁ ትምህርት ነው ተማሩ » እያሉ ነው ያሳደጉን። አስተማሪዎች ስለሆኑ ምንም የሚያስቀምጡልን የላቸውም። ለሶስት ልጆቻቸው ሊያወርሱ የሚችሉት መማር፣ በራስ መቆምን ነው። ይሄንን አዳምጠናል መሰለኝ እንዳሰቡት ሆኖላቸዋል።

ቤተሰቦቼ አሁን ባለሁበት ደረጃ ደስተኛ ናቸው። ስዕል ሰዓሊነት ገብቷቸው ነው የሚል እምነት የለኝም ፤ በጣም የማመሰግናቸው አርት ስኩል ልገባ ነው ስላቸው እነሱ ተቋውሞ አላሰሙም ከጎረቤት ግን የተለያየ አስተያየት ሲሰጣቸውም ያንን ተቀብለው አላንጸባረቁም በዚህ በኩል ትልቅ እገዛ አድርገውልኛል ፤ በፍላጎቴ እንድማር ትልቅ ድጋፍ አድርገውልኛል አሁን ያለሁበትን ማንነቴን እንዳገኝ።

አሁን ስለ ስራዬ ሲጠየቁ ታስተምራለች፤ በቤቷ ስዕል ትሠራለች ፤ ኤግዚቢሽን ታቀርባለች ይላሉ። ኤግዚቢሽን ሲኖረኝ እጋብዛቸዋለሁ። አንድ ጊዜ ሲመጡ ብዙ ሰዎችን ሲያዩ ደነገጡ፤ እንደእዛ አልጠበቁም ነበር።

ቀጣይ እቅድ

ሜሮን በቀጣይ መሆን የምትፈልገው ልትደርስበት የምትመኘው እቅድ አላት። ይህንንም እንደሚከተለው ትገልፀዋለች። የራሴን ሥራዎች ፍልስፍናዎች ከማህበረሰቡ ጋር እያገናኘሁ የምሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ። ማስተማር ደግሞ በጣም የምወደው ሥራ ነው፤ እሱን እቀጥላለሁ። ማስተማር ትውልድ መቅረጽ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የራሴን ትናንሽ ጡቦች አስቀምጣለሁ ብዬ አስባለሁ ስትል ሃሳቧን ቋጭታለች።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You