የልጅነት ህልሟን ያሳካች የብርቱዎች አርአያ

ዶክተር፣ ፓይለት፣ ኢንጂነር ወዘተ… የጎበዝ ተማሪዎች መገለጫና እድል ፈንታቸው እንደሆነ ጭምር ይታመናል:: የአብዛኛው ማኅበረሰብ አስተሳሰብም ከዚህ የተለየ አይደለም:: ዶክተርነት፣ ኢንጂነርና ፓይለትነትን ለቀለሜዋ ተማሪዎች ታጭተው ተድረዋል::

በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው በተለይም ለትምህርት ትኩረት የሚሰጡና ዝንባሌያቸው ወደ ትምህርት ካጋደለ ‹‹ዶክተር›› ብሎ መጥራት የተለመደ ነው:: ይህን የተረዱ የሚመስሉት ሕፃናትም ‹‹ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?›› ተብለው ሲጠየቁ በኮልታፋ አንደበታቸው ‹‹ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለትና ወዘተ…›› የሁልጊዜ መልሳቸው ነው::

ዶክተር ኤልሳቤጥ አርአያም በዚህ መንገድ ተለክታ የተሠራች ብርቅዬ ወጣት ናት:: ቤተሰቦቿ ገና በጠዋቱ ዶክተር የሚለውን መጠሪያ የቸሯት በምክንያት ነው:: ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ለትምህርት ያላት መሰጠት ጥልቅ ነው:: ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንዲሉ ይህን የተረዱ ወላጆቿም ዛሬን አሻግረው በመመልከት ‹‹አንቺማ ስታድጊ ዶክተር ነው የምትሆኚው›› አሏት:: እርሷም አላመነታችም ዶክተርነትን አሜን! ይሁን ይደረግልኝ ብላ በመቀበል ራዕይ ሰነቀች::

ኤልሳቤጥ ከወላጆቿ የተቸራትን ዶክተር የሚል ስያሜ መጠሪያ ብቻ አላደረገችውም:: በተግባር ኖረችው እንጂ:: ምኞቷን በስኬት ለማድመቅ ገና በለጋነት ዕድሜዋ የዛሬ መሠረቷን አጸናች:: ከልጅነት እስከ ዕውቀት ዶክተር በሚል መጠሪያ የተገነባው የጸና መሠረቷም ዶክተርነትን ከነሙሉ ማዕረጉ መሸከም አልከበደውም:: እንዲያውም ከፍተኛ የተባለውን 3 ነጥብ 93 ውጤት በማምጣት ከሴቶች እንዲሁም ከአጠቃላይ ተማሪዎች መካከል በማዕረግ ተመርቃለች:: እውነትም ዶክተር ተብላለች::

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ቤት በቅድመ ምረቃ ካሰለጠናቸው 95 ሴት ተማሪዎች መካከል ነጥራ የወጣችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የልጅነት ህልሟን ማሳካት የቻለች ክንደ ብርቱ ናት:: ይህም በወረሃ የካቲት መገባደጃ እንዲሁም በሴቶች ቀን መዳረሻ በመሆኑ የሴቶች ቀን እንግዳ መሆኗ በምክንያት ነው:: ከጠቅላላ ተማሪ እንዲሁም ከሴቶች የላቀ ውጤት ያስመዘገበችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ትምህርት ቤቱ ያዘጋጀውን ሽልማት ጠቅልላ በመውሰድ ድርብ ድርብርብ ስኬት ማስመዝገብ ችላለች::

አዲስ አበባ 22 አካባቢ ተወልዳ ሲኤምሲ ያደገችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የሕክምና ትምህርት ከሚጠይቀው ብሩህ አዕምሮ ባሻገር ውስጣዊ መሻትን የሚፈልግ በመሆኑ ያ አቅም ነበረኝ ትላለች:: ከልጅነቷ ጀምሮ ለሙያው ጥልቅ ፍቅር እንደነበራት በማንሳት ዛሬ ላይ ለመድረሷም ወላጆቿ የላቀ ሚና እንደነበራቸው ስታስረዳ፤ ‹‹ወላጆቼ በትምህርት አልገፉም፤ ነገር ግን ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ:: ስለሆነም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እኔም ሳይማር ከሚያስተምር ቤተሰብ የተገኘሁ ነኝ ብል ማጋነን አይሆንም›› በማለት ነው::

ሀገር የምትሠራው ከቤተሰብ በሚጀምር አንድ ርምጃ እንደ መሆኑ ሀገር ብቁ ዜጋ እንዲኖራት ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: ዶክተር ኤልሳቤጥም ዛሬ ለደረሰችበት ስኬት ቤተሰቦቿ ኃላፊነት ሲወስዱ ጓደኞቿና በዙሪያዋ የሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቿም እንዲሁ ሚና ነበራቸው:: ለትምህርት ያላትን ቅርበት ከግምት ያስገቡት ቤተሰቦቿ፣ ጓደኞቿና ዘመድ ወዳጆቿ ገና በጠዋት ነው ‹‹የሐኪምነት›› መጠሪያን የሰጧት:: ዶክተር ኤልሳቤጥም አላሳፈረቻቸውም የዶክተርነት ስጦታዋን በከፍተኛ ማዕረግ ተቀብላ አኩርታቸዋለች::

ላለፉት ስምንት ዓመታት የሕክምና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት በዚህ ሳምንት ብዙ ወላጆች ተደስተዋል:: ልፋታቸው ለፍሬ በመብቃቱ ከቤተሰብ አልፎ ለሀገር ኩራት ሆኗል:: በተለይም የልጅነት ህልሟን በከፍተኛ ውጤት ማሳካት ለቻለችው ለዶክተር ኤልሳቤጥ ስሜቱ ይለያል::

ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የልጅነት የትምህርት ጊዜዋን ስታስታውስ የደረጃ ተማሪ እንደነበረችና በትምህርት ዓለም ያልተሸለመችበት ጊዜ እንዳልነበር ነው:: ለዚህም የተማረችባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሁም መምህራኖቿ መሠረት እንደጣሉላት ትናገራለች:: እሷ እንዳለችው፤ በወቅቱ በሕይወቴ የጣሉት መሠረት ትልቅ ነው:: ይህም ለሕክምና ትምህርቴ በእጅጉ ጠቅሞኛል::

ከሁሉ በላይ ግን ቤተሰቦቿ ለትምህርት የሚሰጡት ግምት እንዲሁም ያደርጉላት የነበረው ተከታታይነት ያለው ድጋፍ በኤልሳ አንደበት ለመነገር ቃላት ያንሳሉ:: በተለይም ታላቅ ወንድሟ የሁለተኛ አባትነት ሚናን በመወጣት ዓላማዋን እንድታሳካ በብዙ ያገዛትና ያበረታታት ነበር::

ዶክተር ኤልሳቤጥ እየተባለች ያደገችውና የትናንት ሐኪም የመሆን ባለራዕይዋ፤ ዛሬ የጠቅላላ ሐኪምነት ምሩቅ ሆናለች:: ለሕክምና የሰጠችውን ቦታ በማሰብ ‹‹ሕክምና ባልማር ኖሮ ምን እሆን ነበር?›› ስትል እራሷን ትጠይቃለች።‹‹እግዚአብሔር ፈቅዶ የልጅነት ህልሜን ማሳካት ችያለሁ:: ይህ እኔንም በጣም ያስገርመኛል›› የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ በትምህርት ሕይወቷ የመጀመሪያም የመጨረሻም ምርጫዋ ጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መማር እንደነበር ታስታውሳለች::

በወቅቱ የመጣው ይምጣ ብላ የወሰነችው ውሳኔም ትክክል ሆኖ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አድርሷታል:: ይህን ትልቅ ደስታ በውስጧ ሸሽጋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅን የተቀላቀለችው የያኔዋ ባለራዕይ ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ስምንት ዓመታትን በሕክምና ትምህርት አሳልፋለች::

የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ትምህርት ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውጭ በመሆኑ ሐኪም ሐኪም የመሽተት ዕድሉ አልነበረም የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የቲዮሪ ትምህርት አብቅቶ ወደ ተግባር ትምህርት እንደገቡ ሐኪም ሐኪም የሚለው ሽታ አወዳቸው:: ያን ጊዜ ታዲያ ከነበራት ደስታና ጉጉት ይልቅ በፍርሃት ተውጣ እንደነበር ታስታውሳለች::

ጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅን የተቀላቀሉ ጓደኞቿ በሙሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ታካሚዎችን የማየት ዕድል የገጠማቸው ቢሆንም ታካሚዎችን ለማናገር ፍርሃት ሸብቦ ያዛቸው አቅም አጡ:: ይሁንና ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ በሂደት ታካሚ ፊት ቆሞ ስለህመሙ መረዳትና መፍትሔ በመስጠት የማይቻል የሚመስለውን ችለው ሁሉን ተቋቋሙ::

ታማሚዎችን ምን አመማችሁ ብሎ ለመጠየቅ በፍርሃት ይናጡ የነበሩት ዕጩ ዶክተሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከሩ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ማሳየት ጀመሩ:: ለዚህም የመምህራኖች ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልነበር ያነሳችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ‹‹ስንሳሳት እያረሙን እንደ ልጅ ተንከባክበውናል›› ትላለች::

ሰባት ዓመታትን የሚጠይቀው የሕክምና ትምህርት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ስምንት ዓመት መገፋቱን የጠቀሰችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የስምንት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋን ስታስታውስ በሥነ ምግባርና በዕውቀት የጎለበተ እንደነበር ስታጫውተን፤ ከጓደኞቿ ጋር በጋራ በመሆን ሙሉ ጊዜዋን ለትምህርቱ በመስጠት አሳልፋለች::

ትምህርቱ ሁልጊዜም ቢሆን ንቁና ብቁ መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁልጊዜ ለሥራው ዝግጁ ነበርኩ ትላለች:: በጊዜ ሂደትም ተማሪና ሠራተኛ በመሆን በተለያዩ ሆስፒታሎች ተለማማጅ ሐኪም ሆና የማጠቃለያ ፈተናው ተፈትናለች:: እንዲህ ዓይነቱ ፈተና ታዲያ የምዕራፉ ማጠቃለያ እንደመሆኑ የሌት ተቀን ትጋትን የሚጠይቅ በመሆኑ ተገቢውን ሁሉ አድርጋለች።

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ የካቲት፣ ዘውዲቱና ምኒልክ ሆስፒታሎች ላይ ተማሪም ሠራተኛም ሆኜ ሰርቻለሁ የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ተማሪም ሠራተኛም ሆኖ መሥራት እጅጉን አድካሚ ቢሆንም ምላሹ ግን በጣም አስደሳች ነው ትላለች:: እሷ እንዳለችው የሕክምና ሙያን በተግባር ማየት የሚቻለው ከመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ በመሆኑ በዚህ ጊዜ ምኞትና ፍላጎት በተግባር ይዋሃዳሉ::

ይህ ደግሞ ሐኪም የመሆን ጉጉትን በእጥፍ ይጨምራል:: በራስ መተማመንን ይፈጥራል:: በዚህ ጊዜ ታዲያ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች እዚህጋዬን አመመኝ፤ እንዲህ ተሰማኝ እንዲያ ሆንኩ ቢሉ በደስታና በጉጉት ሙያዊ ምክር ይለገሳል፤ እነሆ መፍትሔ ይባላል እንጂ፤ ማፈግፈግ የለም::

በሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ ጥሩ የሆነ የጓደኝነት ሕብረት ከሌለ በጣም ከባድ ነው የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንደሚጠይቅ ትናገራለች:: በተለይም ተማሪና ሠራተኛ ሆነው ሲሠሩ ብዙ አስጨናቂ፣ አሳዛኝ፣ ተስፋ አስቆራጭና ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥማሉ:: በመሆኑም የማይነጉ የሚመስሉ ሌሊቶችም ያልፋሉ:: ይሁንና እነዚህ አስቸጋሪና አስጨናቂ ሁኔታዎች ከጓደኞቻቸው ጋር በመመካከርና ሃሳብ በመለዋወጥ ቀላል ሆነው እንዲያልፉ ይደረጋል::

ከቀዶ ጥገና ውጭ ያሉትን ማንኛውንም ሕክምና መስጠት የሚያስችል ዕውቀት ሰንቃ በአብላጫ ውጤት የተመረቀችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ በትምህርት ቆይታዋ ከዕውቀት አባቶቿ ብዙ እንደተማረች ትናገራለች:: እሷ እንዳለችው መምህራኑ በዕውቀት፣ በሥነ ምግባርና ከታካሚ ጋር ከነበራቸው ተግባቦት ብዙ አትርፋለች:: ስለዚህ በስምንት ዓመታት ቆይታ የመምህራኑ አስተዋጽኦ ይህ ቀረው የሚባል አይደለም::

የሕክምና ትምህርትን ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች ለየት ልዩ የሚያደርገው ክቡር በሆነው የሰው ሕይወት ላይ የሚሠራ በመሆኑ ነው:: የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የሕክምና ትምህርት መተኪያ በሌለው በሰው ሕይወት ላይ የሚሠራ፣ ሰፊ ጊዜ የሚወስድና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው በመሆኑ ከሌሎቹ የሙያ ዘርፎች ለየት ያደርገዋል ትላለች:: ይህ ለየት ያለው ሙያ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ለማዳን ያለመ በመሆኑ ሐኪሞች የተማሩትን ትምህርትና የገቡትን ቃል መሠረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸውና ታካሚዎችም ሐኪሞች ያለባቸውን ጫና በመረዳት በመካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ ማድረግ እንደሚገባ መክራለች::

የልጅነት ህልሟን ዕውን ያደረገችው ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ በስምንት ዓመታት የሕክምና ትምህርት ቤት ቆይታዋ ወደፊት ስፔሻላይዝድ የምታደርግበትን ሙያ መለየት እንዳስቻላት ትናገራለች:: እሷ እንዳለችው፤ ውስጧ ዘልቆ የገባው የሕክምና ዘርፍ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ነው:: ምክንያቱም ተማሪና ሠራተኛ ሆና በቆየችበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እጅግ ከተደሰተችባቸውና ውስጧ ከረካባቸው የሥራ ክፍሎች መካከል ይህ ክፍል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው::

ሌላው ምክንያቷ ደግሞ ሁሉን ለማወቅ ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ይመስላል:: ይህም የተለያየ ዓይነት ሕክምና የሚፈልጉ በርካታ ታካሚዎች የሚገኙበት ክፍል በመሆኑ ነው:: በዚያው ልክ ፈጣን፣ ንቁና ብቁ መሆንንም የሚጠይቅ የሕክምና ክፍል እንደሆነም ታምናለች:: ያም ቢሆን ታዲያ ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ በቀጣይ በድንገተኛ ሕክምና ስፔሻላይዝድ ማድረግን መርጣለች::

የድንገተኛ ሕክምና ክፍልን ብዙዎች የሚፈሩትና የሚሸሹት ክፍል ቢሆንም እኔ ግን ምርጫዬ አድርጌዋለሁ የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ የሕክምና ክፍሉ አዕምሮን በማሠራት ፈጣን ምላሽ የሚፈልግና ለነገሮች ፈጥኖ መድረስን ይጠይቃል:: ይህም ታካሚው ሕክምናው ጋር በደረሰበት ፍጥነት ሕይወቱን ለማትረፍ የሚቻልበት የመጀመሪያው የሕክምና ክፍል በመሆኑ ርካታን ይሰጠኛል ትላለች::

ድንገተኛ የሕክምና ክፍል ፈጣን የሆነ አስተሳሰብን እና ፈጣን የሆነ ርምጃን በመውሰድ ታካሚን በሕይወት ለማትረፍ ሙሉ አቅምን አሟጦ መጠቀምን ይፈልጋል:: በዛው ልክ ግን ሩጫ ብቻ ሳይሆን ማስተዋልን ይጠይቃል:: የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ አዕምሮን የሚያሠራና ፈጣን የሚያደርግ በመሆኑ ምርጫዋ አድርጋዋለች:: ከዚሁ በተጨማሪም በድንገተኛ ሕክምና ክፍል ያገኘቻቸው ሐኪሞች በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩባት በመሆኑ የእነሱን ፈለግ ለመከተል አልማለች::

በመጨረሻም ለሴት እህቶቼ ያለችውን እንካችሁ ብላለች፤ ሰዎች ከስኬት ማማው ላይ እንዲወጡ በዋነኝነት ዝንባሌያቸውን ማወቅ ቀዳሚው ጉዳይ ነው:: ማንም ሰው በቤተሰብ ግፊት በማይፈልገው መንገድ መሄድ የለበትም:: የውስጥ ፍላጎታቸውን ለይተው ለዛ ጊዜ ሰጥተው ሲሠሩ ውጤታማ መሆን ይችላሉ::

ከዚህ በተጨማሪም ማንም ሰው ለመጠየቅም ሆነ ለመሳሳት መፍራት የለበትም:: የምትለው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ማንኛውንም ጥያቄ ለመጠየቅ እንዲሁም መልስ የመሰለኝን ሁሉ ለመመለስና ለመሳሳት ወደኋላ አልልም:: ምክንያቱም ከስህተቴ የተማርኳቸውን ለረዥም ጊዜ አልረሳቸውም:: ይህ መለያዬ ሆኖ በብዙ አትርፌበታለሁ ትላለች:: ብዙ ማጥናት ተገቢና የግድ እንደሆነ ሁሉ በቂ እረፍት ማግኘትም ውጤትን በስኬት ለማጠናቀቅ ተገቢ እንደሆነ መክራለች::

አስቸጋሪና የማያልፉ የሚመስሉ ስምንት ፈታኝ ዓመታትን በብርቱ ጥረት አልፋ ህልሟን ዕውን ያደረገችው ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በማዕረግ የተመረቀችው የሴቶች ቀን በሚከበርበት የማርች 8 (የካቲት 29 ዓ.ም) ሰሞን ነው:: ዶክተር ኤልሳቤጥ፤ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች እንዲሁም ከጠቅላላ ተማሪዎች ብልጫ ውጤት በማምጣቷ ከትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እጅ የክብር ሽልማቷን ተቀብላለች።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You