
የሴትን ልጅ ማንነት በሚዛን አስቀምጠው ዋጋዋን የተረዱ ሁሉ ስለእርሷ የሚሠጡት ትርጓሜ በእጅጉ ይለያል:: ሴት ልጅ ‹‹ሀገር፣እናት እህት፣ልጅና ሚስት ናት›› ከሚለው ተለምዷዊ አባባል የዘለለ ክብሯን ከፍ የሚያደርጉም ማንነቷን በመልከ ብዙ ቁምነገሮች ይፈርጁታል::
በታላቁ ቅዱስ መጽሀፍ – መጽሀፈ ምሳሌ ላይ ‹‹ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል፣ የባልዋ ልብ ይታመንባታል፣ ምርኮም አይጎድልባትም፣ ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች ፣ ክፉም አታደርግም›› የሚል ቃል ተቀምጧል::
ይህን ቃል መሠረት አድርገው መርሁን የተቀበሉ በርካቶች የሴትን ልጅ ማንነት አክብረው ሃሳብ ዕውቀቷን ያከብራሉ:: መንገዳቸውን በበጎ ቀይሰውም ለማንነቷ ክብር ይሰጣሉ:: በየትኛውም ሰው ኑሮና ቤት መሀል የሴት ልጅ ዐሻራና መሠረት መኖሩ አይቀሬ ነው:: በየቤቱ እናት፣ እህት፣ ሚስት፣ አልያም ሴት ልጅ የሌለው አይገኝምና :: ለዚህም ይመስላል ሕይወትን ያለሴቶች መኖርና መግፋት አዳጋች ነው ቢባል ማጋነን የማይሆነው::
አንዲት ሴት ለአንድ ቤተሰብ ህልውና ዋልታና ማገር ሆና ትገለጻለች:: እንደ ሚስት የባሏ አጋርና ቀኝ እጅ፣ እንደ እናት የልጆች አሳዳጊና ተንከባካቢ ፣ እንደልጅ የእናት አባቷ ፍሬና የወንድሞቿ እህት ሆናም ቤቱን ታቆማለች:: ይህ እውነት ደግሞ ለአንድ ቤተሰብ መኖር የጀርባ አጥንት ያህል ጥንካሬው ሃያል ነው:: ጉዳዩ በጥልቅ ይታይ ፣ይመርመር ከተባለም ከዚህ ማንነት በላይ የሚገለጽ የህልውና ማሳያ ሊኖር አይችልም::
ይህ እውነት ከቤት አልፎ ወደ ማህበረሰብ፣ ብሎም ወደሕዝብና ሀገር ሲሻገር ደግሞ ትርጓሜው ይሰፋል:: ከቤት የጀመረ ታላቅ ሃላፊነት ግንዱ ሰፍቶ፣ ቅርንጫፉ ልቆ ብዙሃንን ሲደርስ የመነሻ ሥሩ የሴት ልጅ አስተዋጽኦና ታላቅ አበርክቶ መሆኑን ልብ ይሏል::
በሀገራችን በተለያዩ ዘመናት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ተጽእኖና ጫና ከፍ ያለ መሆኑ ይታወቃል:: ይህ እውነት ከጥንት እስከዛሬ የነበረና ወደፊትም በቀላሉ ሊገታ የማይችል መሆኑ ይታወቃል:: ይህ አይነቱ ሀቅ እንዳለ ሆኖ ሴት ልጅ በሰውነቷ መብቷ ተከብሮ በፆታዊ ማንነቷ እኩልነቷ ይረጋገጥ ዘንድ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል::
በኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄ ከተነሳባቸው አበይት ጉዳዮች መሀል የሴቶች መብት አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል:: ለጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ሴቶችን ጨምሮ ‹‹ችግሩ ‹ያገባናል› ሲሉ ትግል የጀመሩ ብዙሃንም ውሎ አድሮ የድካማቸው ፍሬ ውጤት አስገኝቷል::
በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንጽ 35 ሴቶች በሕግ የተደነገጉ መብቶችና ጥበቃዎችን እንዲያገኙ ከወንዶች እኩል መብት እንዳላቸው ይደነግጋል:: በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ኢ-እኩልነትና አድሏዊ አሠራር በእርግጠኝነት ለማስተካከልም አወንታዊ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተቀምጧል::
ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እኩል ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ያረጋግጣል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመንግሥትና የግል ተቋማት ከወንዶች ጋር በእኩል እንዲሳተፉና እንዲወዳደሩ ሕገመንግሥታዊ መብታቸው እንደሚፈቅድ በግልጽ ሠፍሯል:: የሴቶች መብት ከሕገመንግሥቱ ድንጋጌዎች ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ማዕቀፎች ውስጥም ትኩረት አግኝቷል::
ይህ መብት ከሕገመንግሥቱ ድንጋጌዎችና ከተለያዩ ማዕቀፎች ባሻገር ሀገራችን በስምምነት ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለምአቀፍ ድንጋጌዎች ጭምር ተካቷል:: ይህም በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 9/4 ላይ የሀገሪቱ የሕግ አካል ሆኖ እንደሚታከል በግልጽ ሠፍሯል::
እነዚህ የሴቶችን ማንነት መሠረት አድርገው የጸደቁ የመብት እውነታዎች ግን ብዙ ጊዜ በተግባር እውን ሆነው የማይታዩባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ:: ብዙ ጊዜ ሴቶች ከወንዶች እኩል ሥልጣን የመያዝ፣ ሃላፊነትን የመጋራት መብት እንዳላቸው ተደጋግሞ ይነገራል:: በእኩል የመምራትና ከፊት የመቅደም መብት ጭምር እንደተሰጣቸውም እንዲሁ::
በታሰበው አግባብ ተግባር ሆኖ ሲገለጽ ግን ወንዶች በረገጡበት፣ ባለፉበት መንገድ ሁሉ ሴቶችም በእኩል የመራመድ መብታቸው ሲስተጓጎል ይታያል:: አንዳንዴም በትክክል ሴቶች ሊይዙትና ሊመሩት የሚገባውን ሃላፊነት በወንዶች የበላይነት ሲሸራረፍና በግልጽ ሲነጠቅ ይታያል::
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ በአግባቡ ለሴቶች የተላለፈው መብት አግባብ ባልሆነ መልኩ ለወንዶች ተላልፎ ሲሰጥ ለምን የሚል ጠያቂ ሲኖር አይስተዋልም:: ይህ አይነቱ አካሄድ ያለመለመዱም አሠራሩ ሕጋዊ እስኪመስል በተጽዕኖ እንዲቀጥል ዕድልን ችሯል::
በሀገራችን ተደጋግሞ እንደሚነገረው ‹‹ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው››:: በቃሉ ላይ እንደተጠቀሰው ሃሳብም ለወንዶች የሚሰጠውን ማንኛውንም መብት ሴቶችም በእኩል ድርሻ ይጋራሉ:: ሥልጣን የመያዝ፣ ሃላፊነትን የመጨበጥ፣ በዕውቀት ችሎታቸውን የመምራት መ ብቱ በሙሉ ተ ሠጥቷቸዋል::
በአብዛኛው ግን እውነታው ወደ ተግባር ተመልሶ ሲረጋገጥ አባባሉ ከመርህ ያልዘለለ ሆኖ ይገኛል:: ዕድል ሁሉ በወንዶች ዓለም ላይ የተመሠረተ እኪመስል ቃሉ ታልፎ ድርጊቱ ሲከሽፍ ይስተዋላል::
ሴቶች ብዙ ጊዜ በሕገመንግሥቱ ላይ በተረጋገጠው መብት ልክ ማንነታቸው ሲለካ አይታይም:: በተመሳሳይ የሥራ ድርሻና ሙያ ላይ ሳይቀር ተሳትፎው ጎልቶ የሚታየው ለወንዶች ብቻ ይሆናል:: እርግጥ ነው ከአምስት ዓመት ወዲህ ባለው እንቅስቃሴ የሴቶች ተሳትፎ እስከዛሬ ከነበረው ገጽታ በላይ በእጅጉ ተለውጧል::
እንደ ጅማሬው በያዘው ፍጥነት ለመቀጠል ግን ለውጡ በሌሎች ዘርፎች ጭምር ሊተገበር የግድ ይላል:: አንድ ሺህ ወንዶች ባሉበት መሀል አንዲት ሴት፣ ለምልክት በምትታይበት አግባብ ሀገርን መቀየር እኩልነትን ማረጋገጥ አይቻልም:: ‹‹ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው››:: ይሉትን አባባል ከንግግር አልፎ ባህል ለማድረግም የተለመደው መርህ በተግባር ሊቀየር ይገባል::
ሴቶች ትኩረት እንጂ ችሎታ ባላጡበት ዘመን አድላዊነት ዕውን ሊሆን አይገባም:: በተለያዩ የትምህርትና የሥራ ውድድር አጋጣሚዎች ቅድሚያውን ለሴቶች ሲባል በሕይወት አጋጣሚ የሚሸከሟቸውን ማህበራዊ ሃላፊነቶች ለማቅለል ታስቦ ነው:: ይህ ለዓመታት በተለምዶ የተያዘ እውነታ ግን ራሳቸው ሴቶች ሳይቀሩ ጠባቂነትን እንዲለማመዱት ሲያደርግ ቆይቷል::
ሴቶች ቅድሚያውን ዕድል ማግኘታቸው ሙሉ ለሙሉ ከዕውቀት ነጻ ናቸው ለማለት አይደለም:: ከወንዶች እኩል የመሰለፍ አቅማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በምክንያት በሚሰጣቸው የአማራጭ ዕድል ለመጠቀም ታስቦ ነው:: ይህ መንገድ በስኬት ታልፎም በሥራ አጋጣሚ በተጨባጭ የሚረጋገጥ ለውጥ ማሳየታቸው አዲስ አይደለም::
ብዙ ጊዜ ስለ ስኬት ሲነሳ በርካታው ማህበረሰብ ታላላቅ ሙያዎችን መሠረት አድርጎ የሴቶችን አሸናፊነት በተለየ ኩራት የሚያወሳው ይሆናል:: እንዲህ ማድረጉ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለአሸናፊነት የራቁና ለአዳዲስ ጉዳዮች እንግዳ የሆኑ ተደርጎ እንዲቀረጹ ያስገድዳል:: ሁሌም የሚገኘው ደማቅ ውጤትም ከወንዶች የተሻገረ እንዳይመስልም ግርዶሹን ያበረታል::
ይህ በተለምዶ ሲወራረድ የመጣ ተጽዕኖ ሴቶችን በአይችሉም ልማድ ሸብቦ ከሃላፊነት ድርሻ እንዲያርቃቸው ተጽዕኖው ልቆ ቆይቷል:: ይሁን እንጂ ለሴቶች በሕገመንግሥቱና በዓለም አቀፉ ሕግ ተረጋግጦ የተሰጣቸውን ተጨባጭ መብቶች ዕውን ለማድረግ አመለካከቱን ማስወገድ የግድ ይላል::
የሴቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተግባራዊ ለማድረግም ቃሉን ከመርህ አባባል አርቆ ባህል የማድረግ ልማድ ሊስፋፋ ያስፈልጋል:: ሁሌም እንደሚባለው ሴቶች ዕድል እንጂ ችሎታ አጥተው አያውቁም:: ሀገርን በእኩል መርቶ በአንድነት ለማደግ ደግሞ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተግባር ማረጋገጥ የግድ ይላል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም