
እልፍነሽ ሙለታ (ዶ/ር) -በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ከፍተኛ ተመራማሪ
አዲስ አበባ፡- ሴቶች አትችሉም የሚለውን ትርክት ያለመቀበላችንን በተግባር እናሳይ ሲሉ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ እልፍነሽ ሙለታ (ዶ/ር) አስታወቁ።
በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ተመራማዋ እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ በዓለም ለ114ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ ዛሬ የሚከበረውን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ሴቶች አይችሉም የሚል ትርክት ሲሰነዘር ቆይቷል፤ ይህን ትርክት ባለመቀበል ሴቶች መቻላችንን በተግባር ለማሳየት መጣር ያስፈልጋል።
ሴት ከሆነች አትችልም የሚለው የተሳሳተ ትርክት በተደጋጋሚ የምንሰማ ከሆነ ውሸት ሲደጋገም እውነት ለመሆን እንደሚዳዳው ሁሉ እኛም “አዎ! አልችልም፤ ምክንያቱም ሴት ነኝ፤ ምን ይደረጋል በቃ!” ወደሚለው እንዳይወስደን መቻላችንን በመሥራት እናረጋግጥ ብለዋል።
“እንችላለን” የሚለውን የሚያጀግነውን ቃል በመያዝ የሚጠበቅብን እንወጣ ሲሉም ተናግረዋል። የሴቶች እኩልነት የሚለውን አባባል፤ ከአባባል በዘለለ በተግባር በማሳየት መቻላችንን እናጽናው ሲሉ ገልጸዋል።
ከፍተኛ ተመራማሪዋ እልፍነሽ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሴቶች ይችላሉ፤ ችለውም አሳይተዋል። እንዲያውም ሴቶች ያለን ልዩ የሆነ ተሰጥኦ ነው። በአንድ ጊዜ ብዙ ተግባራትን መከወን የምትችለው ሴት ናት። ይህ ደግሞ ለሴት ልጅ የተቸራት ልዩ ስጦታዋ ነው።
ሴትነት፣ ጠንካራ የተባሉ ሥራዎችንም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ጾታ አይገድበንም ያሉት እልፍለሽ (ዶ/ር)፤ ሴት ልጅ ቤቷ ስትገባ እናትነቱ ስላለ ለልጆቿ የሚጠበቅባትን ታከናውናለች። ከእናትነት እና ከሚስትነት በተጨማሪ የምትወጣቸው ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ስላሉ ያንንም ሳታስተጓጉል ትተገብራለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የሴቶች ቁጥር አለ ተብሎ እንደሚነገር የጠቀሱት ከፍተኛ ተመራማሪዋ፣ አብሮ በመሥራት ኢትዮጵያን ለማሳደግ ይህን የሴቶችን አቅም መጠቀም መቻል አለብን ነው ያሉት።
“እኛ ሴቶች ጠንካሮች፤ ደግሞም ቁርጠኞች ነን። ሴቶችን በሚገባቸው መንገድ ሁሉ ማሳተፍ ከቻልን እና መንግሥትም የሴቶችን አቅም ከተጠቀመበት ወደ አስቀመጥነው ርዕይ የማንደርስበት አንዳች ምክንያት አይኖርም ሲሉ አስረድተዋል።
ዓምና በዓለም አቀፍ ለ113ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የተከበረው የሴቶች ቀን “ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የሚከበረው የሴቶች ቀን “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!” በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑ ይታወቃል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም