
በአሜሪካ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ሰዎች የ75 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጣለባቸው። የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደገለጸው፤ በቻይና የሚደገፉ የበይነ መረብ መንታፊዎች የተለያዩ ተቋማትን እና ግለሰቦችን ዒላማ አድርገው ቆይተዋል ብሏል፡፡
ሀገሪቱ በተለይም መሠረቱን በቻይና ያደረገ እና በመንግሥት ይደገፋል የሚባለው አይ-ሱን የተሰኘው የበይነ መረብ መረጃ መንታፊ ቡድን ባለሙያዎችን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እንደምትከፍል ከዓመታት በፊት ገልጻ ነበር፡፡ ለዓመታት በተደረገው ምርመራ ይህ ቡድን የአሜሪካ ተቋማትን፣ የቻይና መንግሥትን ይተቻሉ የተባሉ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሚዲያዎች የጥቃቱ ዒላማ ሆነው ቆይተዋል ተብሏል፡፡
በእነዚህ አካላት ላይ መረጃዎችን የመነተፉ አካላት በቻይና መንግሥት ሽልማት ሳይቀር ይሰጣቸው እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ሥራ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ቻይናውያን ለፈጸሙት ወንጀል ከ10 ሺህ እስከ 75 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተገልጿል፡፡
ቻይና በአሜሪካ በሚቀርብባት ተደጋጋሚ የመይነ መረብ ጥቃት እና ቴክኖሎጂ ስርቆት ክስ አንዱንም ያልተቀበለች ሲሆን የአሁኑን ስለመቀበሏ በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም፡፡ አሜሪካ እና ቻይና እርስ በርሳቸው በመረጃ ምንተፋ እና ቴክኖሎጂ ስርቆት የሚወነጃጀሉ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ቻይናን ሲከሱ ይደመጣሉ፡፡
ለአብነትም በቅርቡ ይፋ የሆነው ዲፕ ሲክ የተሰኘው የኤአይ ሞዴል የተወሰኑ መረጃዎች ከአሜሪካ ኩባንያዎች የተቀዱ መሆናቸው ሲገለጽ እንደነበር አል ዐይን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም