
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በብራስልስ ለመከላከያ ልዩ ምክር ቤት ለተሰበሰቡ የአውሮፓ መሪዎች ‹አውሮፓ የታሪክ እጥፋት ላይ ትገኛለች› ሲሉ ተናገሩ። ስለዩክሬን ጉዳይ ለመምከር የተገናኙት የአውሮፓ መሪዎች ሀገሪቱን ከማስታጠቅ ባሻገር ከአሜሪካ ታገኝ የነበረው ርዳታ እንደሚቋረጥ በፕሬዚዳንት ትራምፕ መርዶ የተነገራትን ኪዬቭ በምን አይነት መንገድ መደገፍ እንደሚችሉ ይወያያሉ ተብሏል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አሜሪካ ከአሁን በኋላ ከጎናችን የማትሆን ከሆነ ፈረንሳይ እና አውሮፓ መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ራሳችንን ለመጠበቅ አንድ እና ቁርጠኛ መሆን አለብን ያሉት ማክሮን የአውሮፓ እጣ ፈንታ ከዋሽንግተን እና ሞስኮ ጋር መታሰብ የለበትም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በተጨማሪም ‹አሜሪካ ከእኛ ጎን እንደምትቆም እምነት ያለኝ ቢሆንም ይህ የማይሆን ከሆነ ለአብሮነታችን እና ለጠንካራዋ አውሮፓ መዘጋጀት አለብን› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ያደረጉት የነጩ ቤተመንግሥት አጨቃጫቂ ውይይት የአውሮፓ መሪዎች ላይ ስጋት ማሳረፉ የታወቀ ሲሆን በተለይ ደግሞ የትራምፕ አስተዳደር ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያሳዩት አቀራረብ አውሮፓ አሜሪካ ላይ መተማመን እንዳትችል ምላሽ የሰጠ ነው ተብሏል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማክሮን ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ያላትን የኒውክሌር መሣሪያ በመጠቀም ለአውሮፓ አጋር ሀገራት የምትሰጠውን ከለላ ለማራዘም መፍቀዷን እና ይሄን በተመለከተም ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ ቀጣዩ የጀርመን ቻንስለር ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁት ፍሬድሪክ ሜርዝ በበኩላቸው የኒውክሌር ክፍፍል እንዲጨምር ጥሪ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
እንደዚሁ የአውሮፓ ኮሚሽን ሃላፊ ኡርሳላ ቮን ዴር ሌይን ‹በአዋቂነት እድሜያችን አይተን በማናውቀው መጠን አውሮፓ ግልጽ እና አስጊ አደጋ ተጋርጦባታል› ማለታቸው የተሰማ ሲሆን የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ‹ለዩክሬን እና አውሮፓ ደህንነት ወሳኝ ጊዜ› ነው ሲሉ መደመጣቸው ተሰምቷል፡፡
የአውሮፓ ኮሚሽን ሃላፊው ኡርሳላ ቮን ዴር ሌይን ለአውሮፓ መሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ‹ሀገሪቱ ጊዜውን መዋጀት እንዲሁም ያላትን ኢንዱስትሪያል እና ምርታማ ሃይል በማቀናጀት ወደ የጸጥታ ግቦች መምራት› እንደሚገባት ማሳሰባቸው ተሰምቷል፡፡ ሃላፊው ሪአርም ኢውሮፕ የተሰኘ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የመከላከያ ድጋፍ ይፋ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ አክለውም አውሮፓ የመከላከያ በጀቷን በግዙፍ እና በአስፈላጊ ፍጥነት እንዲሁም ፍላጎት ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ቮን ዴር ሌይን በሪአርም ኢውሮፕ እቅድ ውስጥ የተካተቱት ሶስት ውጥኖች ዩክሬንን ለመደገፍ እንዲሁም ለአውሮፓ ደህንነት በረጅም ጊዜ ሊመጣ ለሚችል ፍላጎት የበለጠ ሃላፊነት ለመውሰድ እንደሚረዳ መጠቆማቸው ነው የተገለጸው፡፡ ይህ ሃሳባቸው አውሮፓ ከአሁን በኋላ የአሜሪካ ርዳታ ላይ መተማመን እንደማትችል በብዙዎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ይህ ሪአርም ኢውሮፕ እቅድ የአውሮፓ ሀገራት የመከላከያ ወጪያቸውን ለማሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ ሲባል የበጀት ጉድለታቸው እንዲሟላ ሲፈቅድ አውሮፓን በሙሉ ሊጠቅም በሚችል የመከላከያ ኢንቨስትመንት ላይ የሚፈጠር ጉድለትን ለመሙላትም 125 ቢሊዮን ፓውንድ ብድርን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡
በተጨማሪም ሀገራት በተለያዩ ግዛቶች ያለውን የእድገት ልዩነት ለማጥበብ የመደቡትን ገንዘብ ወደ መከላከያ ወጪዎች ማዞር እንዲችሉ እንደሚፈቅድ ነው የተገለጸው፡፡ በዚህ እውድ መሠረት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ወታደራዊ ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ የሚፈቅድ ሲሆን እንደቮን ዴር ሌይን ገለጻ እቅዱ ለመከላከያ ወጪዎች ሊውል የሚችል እስከ 860 ቢሊዮን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል ተብሏል፡፡ የመረጃ ምንጫችን ቢቢሲ ነው፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም