
ሰላሙ ለተሻለ ሹመት ታጭቶ በሥራ ላይ ያለበትን ክፍተት ለማወቅ ይረዳው ዘንድ ጥሩም ይሁን መጥፎ አስተያየት እንዲሰጡት ለሠራተኞቹ የበተነውን መጠይቅ ሰብስቦ ቢሮው ውስጥ ብቻውን ቁጭ ብሎ አንዴ ፈገግ አንዴ ኮስተር እያለ የጻፉለትን ነገር ያነባል።
ሁሉም በሚባል ደረጃ “ያላንተ ተቋሙ ምንም ነው፤ እንዳንተ ያለ አለቃ የት ይገኛል?” ሲሉ በከንፈራቸው ይክቡታል እንጂ ቅንጣት ያህል ከልባቸው ደጅ አላቀረቡትም። በመጠይቁ ላይ ኮድ ስላሰፈረበት ማን ምን እንዳለ በቀላሉ ለማወቅ ችሏል። መላኩ፣ አዲሱና ወርቅነሽ ከማር አጣፍጠው ስለሱ ያላቸውን አክብሮት ቢገልጹለትም ወረቀቱ ግን ያስነበበው ያፋቸውን ቃል ሳይሆን ሌባና ሙሰኛ እንደሆነ ነው። ፈትለወርቅ ብቻ ጎበዝና ታታሪ ሠራተኛ መሆኑን አንስታ ሊያስተካክል የሚገባውንም ጭምር አክላለታለች።
ሰላሙ እጅግ ተገርሞ ስልኩን አነሳና የፈትለወርቅን ቁጥሮች ከሰሌዳው ደረደራቸው። በሩን አልፋ ከቢሮው ስትዘልቅ ወንበር እንድትወስድ እየጋበዛት ስለአድራጎቷ ያስብ ጀመር።
“በደህና ነው የፈለከኝ?” ስትል ከሃሳቡ አናጥባ ወደራሷ መለሰችው። “አንድም ቀን ሥራዬ ጥሞሽ የማያውቀውን እንዲህ ያለ ልብን የሚያሞቅ አስተያየት ስትሰጭኝ ተደንቄ ነው መጥራቴ” አለ ስስ ፈገግታ እየለገሳት። “አንተን በማስተካከል ውስጥ ሀገሬን እንዳገዝኳት ነውና የሚሰማኝ ፊት ለፊት መናገሬን ካልጠላኸው በቀር ያሉብህን ችግሮች እስክታርም ድረስ ያለመታከት እወተውትሃለሁ” አለችው ብሩህ ጸዳል እያሳየችው።
“ላንቺ አልመሰለሽም እንጂ ግልጸኝነትሽን አብዝቼ ነው የምወደው፤ በከንቱ ውዳሴ እየሸረደዱ በቁም ከሚቀብሩኝ እንድጠበቅ መስታወት ሆነሽኛልና የማወራለት ሳይሆን የምሠራለት ተቋም በቅርቡ አብቦ ታይዋለሽ” ሲል ቃሉን ሰጣትና ጠቅላላ ሠራተኛውን ስብሰባ የሚጠራ ማስታወቂያ እንድትለጥፍለት አቀብሏት ተሰናበታት።
ሰላሙ በሰፊው ክፍል ውስጥ ወዲያ ወዲህ እንደፎካሪ እየተንጎራደደ ከሠራተኛው የተጻፈለትን ሆድ የሚያሻክር አስተያየት ከጥላቻ በጸዳ መልኩ ለመገንዘብ እየታገለ ነው። በ1685 በአሜሪካው አብዮት የጦር ሜዳ ጀግና የነበረው ናታን ሄል እትብቱን የቀበረባት እንግሊዝ በሰላይነት ጠርጥራው ስትሰቅለው ከሞት ጋር ተፋጥጦ እንኳን “ለሀገሬ የምሰጣት ውድ ህይወቴ አንድ ብቻ ባትሆን ኖሮ ደጋግሜ እሞትላት ነበር” በማለት ህያው ፍቅሩን ተናዘዘላት። ይህን ሃሳብ በአዕምሮው ሲያንሰላስል ከመቃብር በላይ ተተክሎ ስለሚቀር ስምና ስለዘመን አይሽሬ ሥራ ልብ እያለ ነበር።
ሮጦ ባልጠገበበት ሠርቶ ባልደከመበት በወጣትነት እድሜው በዚያን ጊዜ የደርግ አገዛዝ ቢጎረብጠው ወደሱዳን ለመሰደድ ከቤት ሲወጣ የነፍስ አባቱ ርዕሰ/ርዑሳን አባ ቃለጽድቅ ላንብብም ካለ ከዋርካ ጥላ ስር ተቀምጦ ካልሆነ በቀር ላፍታም እንዳይገልጠው አስጠንቅቀው ዓይናቸውን እየጨመቁ በዕንባ ያቀለሙትን ደብዳቤ አሲዘው ሸኙት። ጀንበር የጨለማ ካባ ስትደርብ ጎንደር ክፍለ ሀገር ደርሶ ከዣንተከል ዋርካ ቆሞ ጎኑን የሚያሳርፍበት ሁነኛ ቦታ ሲያማትር ደብዳቤው ትዝ ብሎት ከኮሮጆው አወጣና የዕጅ ባትሪውን ከወረቀቱ ደረት ላይ አንቀለቀለው።
ፍርሃት ተጭኖት እያመነታ ከእግር እስከራሱ ሲገርፈው “አያትህ ያቆይዋቸውን ባድማ አባትህ ተረክበው ደመቁበት ኳሉበት፤ አባትህ ደግሞ ጉርጓዳቸው ተምሶ ልጣቸው ርሶ ቀናቸው መምሸቱን ሲረዱ በሞፈር ቀንበሩ ሊተኩህ አስበው ሳለ አንተ ግን አመል አወጣህ፤ እናም ልጄ ሆይ! ሀገር ገፍቶ ሀገር የለምና ሳትውል ሳታድር ተመለስ” ይላል። አንብቦ እንደጨረሰ ያጠመቀውን የዕንባ ዶፍ አደራርቆ “እንዲህ እያሉኝ ብሄድስ መቼ ይቀናኛል?” አለና ምክራቸውን አላምጦ ጥሪያቸውን አዳምጦ ወደኋላ ተጓዘ።
“መካሪ ዘካሪ ስለነበረኝ በሀገሬ ሠርቼ ለመክበር በቃሁ፤ እኔስ አሁን ለሠራተኞቼ ምን አስተምራለሁ?” ሲል ራሱን ጠየቀና ለሃሜት ያበቃቸውን ህጸጹን አርቆ ምሳሌ ሊሆናቸው ቆርጦ ወደስብሰባው አዳራሽ አቀና። “ቁርሿቸው የቱንም ያህል ደንድኖ ቢያስቸግረኝ እንኳን ተስፋ በመቁረጥ መዛል የለብኝም” ብሎ የጆን ስቲፋኒን ጽናት ለልቦናው ነገረው። በሜክሲኮ አበበ ቢቂላ ጋር የሮጠው ታንዛኒያዊው ጆን ስቲፋኒ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙን ማስፈር የቻለው መጨረሻ በመውጣቱ ሳይሆን ውድድሩን ለመጨረስ በነበረው ጽናት ነው። እንደዥረት ደም የሚፈሰውን እግሩን እየጎተተ 1000 ተመልካቾች በቀሩበት ስቴዲዮም ሲደርስ ያግራሞት ጭብጨባ ተቀበለው። ይህን የተመለከቱ ጋዜጠኞች የጥያቄ መዓት ሲያሸክሙት “ከኔ ሀገሬ ታንዛኒያ ብዙ ጉዳይ አላት። እዚህ የላከችኝ ውድድሩን እንድጨርስ እንጂ እንዳቋርጥ አይደለምና ምንም እንኳን ባይሳካልኝም ለሀገሬ ልጆች ፈተናን ለመሻገር ህልምን ለመኖር ጽናት እንደሚጠበቅባቸው አስተምሪያቸዋለሁ” በማለት ከልቦና ጽላት የማይሰረዝ ከህሊና የማይደበዝዝ መልስ ሰጣቸው።
ሰላሙም በስህተቱ ችንካር የደማ ልባቸው እስኪሽር ድረስ በጽናት ለመሥራት ሞራሉን ከብረት አጠንክሮ መድረኩ ላይ ተሰየመ። መላኩ፣ አዲሱና ወርቅነሽ አፋቸውን በጃቸው ሸፍነው እየተንሾካሾኩ ሲመለከት ሳቅ እየቀደመው አጀንዳውን ካሲያዛቸው በኋላ የዕለቱን ስብሰባ ከፈተው።
“ሁላችሁም ብትሆኑ የመጣውን የትምህርት እድል ለመጠቀም ስትሉ እንደንብ ስትዞሩኝና እንደዕሬት የመረረ ባህሪዬን በማር ለማጣፈጥ ደክማችኋል፤ ይሁን እንጂ አልተሳካላችሁም” ብሎ ንግግሩን ሲገታ አዳራሹን ጉምጉምታ ሞላው። ሁከቱ ጋብ ሲል “በሥራ ዓለም ውስጥ ስንኖር ከጀርባ በሚደረግ አሉባልታ ሳይሆን በግልጽ ተነጋግረን ለችግሮቻችን መፍትሄ ስናስቀምጥ ነው እድገትና ለውጥ ልናመጣ የምንችለው፤ እናንተ ግን ቡና መጠጫ ታደርጉኛላችሁ እንጂ እንደፈትለወርቅ ፊት ለፊት ጥፋቴን ልታርሙኝ አልደፈራችሁም” አለና ሁኔታቸውን ሲታዘብ ዓይናቸውን በፈትለወርቅ ላይ ተክለዋል። በመጨረሻም ከበላይ አካል ጋር ተወያይተው የትምህርት እድሉ ለፈትለወርቅ እንደተሰጠ ገልጾ ታዳሚውን ሲቃኝ ብርሃን ከሚተፉ የፈትለወርቅ አይኖች ጋር ተገጣጥመው ሰውነቱን አንዳች መግነጢሳዊ ሃይል ሲመዘልገው ተሰማው።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም