
አዲስ አበባ፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በወጣቶች ዘንድ እየተነሳ ያለውን ሰላምን የማፅናትና ልማትን የማስቀጠል ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመቀሌ ከተማ ከሰባት ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በሰላምና ልማት፣ በሥራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
በመድረኩም ወጣቶቹ በክልሉ ሰላምን ከማፅናት፣ ልማትን ከማፋጠን እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር መስፈን ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም፥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላምን የማፅናትና ልማትን የማስቀጠል እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር በማጠናከር የተቋረጡ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ እየተስተዋሉ የሚገኙ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተወሰዱ የሚገኙ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።
ወጣቶች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የተጀመረውን ሰላምን የማፅናትና ልማትን የማፋጠን እንቅስቃሴ ሊሳተፉና ሊደግፉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይም ወጣቶቹ በክልላቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊዎች በመሆን ለክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም