የተስፋፊዎችን ቅስም የሰበረ አኩሪ ድል!

ከትናንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች እና ተስፋፊዎች ስትፈተን ኖራለች። ውብ መልክዓ- ምድሯ አማሏቸው፤ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ ስቧቸው ድንበር ተሻግረው ቢቻል ሙሉ ለሙሉ ካልሆነም በከፊል ቆርሰው ሊወስዷት የተመኙ በርካታ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን ሲፈትኗት ቆይተዋል፤ አሁንም እየፈተኗት ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሉአላዊነቷን የሚጋፉ፤ አንድነቷን የሚፈታተኑ ጠላቶች ቢያጋጥሟትም ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶቹን አሳፍሮ በመመለስ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና አንድነት አስጠብቆ ኖሯል።

ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እስከ ማይጨው፤ ዶጋሊና ሶማሊያ ወረራ ድረስ ህይወታቸውን በመገበር፤ ደማቸውን በማፍሰስ እና አጥንታቸውን በመከስከስ በመስዋዕትነት ሀገራቸውን አጽንተዋል፤ አይበገሬነታቸውን አሳይተዋል። ከእነዚህ የአይበገሬነት ታሪኮች ውስጥ ዛሬ ለ47ኛ ጊዜ የሚከበረው የካራማራ ድል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የሰው ሀገር ወርራ እና ተዳፍራ ባታውቅም በየዘመናቱ ድንበሯን አልፈው መሬቷን ሊቆርሱ የሚመኙ ተስፋፊዎች አጥታ አታውቅም። ከእነዚህ ተስፋፊዎች መካከል በ1961 በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው የቀድሞው የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ ዚያድባሬ ይገኝበታል። መሀመድ ዚያድ ባሬ ከሶቪየት ኅብረት የተበረከተለትን መጠነ ሰፊ የጦር መሳሪያ እና ሰፊ የሠራዊት ግንባታውን በመተማመን ኢትዮጵያን ወረረና እስከ አዋሽ ድረስ የሶማሊያ ግዛት አካል መሆኑን አወጀ፡፡

በሀገር ውስጥ በተለያዩ የፖለቲካ ልዩነቶች ሲታመስ የቆየው የደርግ መንግሥት ከውጭም ብዙ ድጋፍ ስላልነበረው የሶማሊያ ወረራ እጅግ አስጊ ነበር። በሰሜን ከነበረው ጦርነት ባሻገር የዚያድ ባሬ ወራሪ ኃይል ሌላ የራስ ምታት ሆኖ ብቅ አለ። በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጰያ በሶማሊያ የሚደገፉ ታጣቂዎች ጥቃት ከፈቱ። የሶማሊያ ተስፋፊ ኃይልም ወረራውን እያሰፋ እስከ ድሬዳዋ ዘለቀ። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ፡፡

የዚያድባሬ ጦር ሐምሌ 3 ቀን 1969 በደቡብ 300 ኪ.ሜ በደቡብ ምሥራቅ ደግሞ 700 ኪ.ሜ ዘልቆ በመግባት ወረራውን አስፋፋ። በገላዲን፤ በሙስታሂል፤ በጎዴ፤ በዋርዴር፤ በአዋሬ፤ በቀብሪደሀርና በደገሃቡር የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር ክፍሎች በጠላት ላይ ጉዳት ቢያደርሱም እስከ አፍንጫው ታጥቆ የነበረውን ወራሪ ኃይል ማቆም አልቻሉም። ይህም ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለት የጠላት ጦር ወደ ጅግጅጋ፤ ሐረርና ድሬዳዋ ለመጠጋት ቻለ።

ሆኖም በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራቱም አቅጣጫ እምቢ ለሀገሬ ብሎ ተመመ። ደሙን በማፍሰስ፤ አጥንቱን በመከስከስ ከሶማሊያ ወራሪ ኃይል ሀገሩን ለማዳን ከየቦታው እንደንብ ሆḷ ብሎ ተነሳ። እስከ 300ሺ የሚጠጋ ሰልጣኝም በታጠቅ ጦር ሰፈር ገብቶ ለሀገሩ ለመዋደቅ ሌት ተቀን የሚሊሺያ ስልጠና ወስዶ ለግዳጅ ተዘጋጀ፡፡

ከሚሊሺያው ጎን ለጎንም በእናት ሀገር ጥሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዕድሮች፣ በሴቶችና እናቶች የተቀናጀ እንቅስቃሴ ስንቁን አሟልቶ በጥር ወር 1970 ዓ.ም ከገጠሩ ገበሬ እስከ ከተማው ፖሊስ ሠራዊት፣ ከሕክምና ባለሙያው እስከ መንግሥት ሠራተኛው፣ ከመምህሩ እስከ ተማሪው ለግዙፍ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሰናዳ። በወቅቱም በየአካባቢው ያለው ሕዝብ የዕድር ድንኳኖቹን እያወጣ ስንቅ በቻለው አቅም እያቀረበ ሀገሩን ከጠላት መንጋጋ ለማላቀቅ ተነሳሳ፡፡

በዚህ መልኩ ዝግጅት ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀውን የሶማሊያ ወራሪ ኃይልን ከመመከት አልፎ እያሳደደ ማጥቃት ጀመረ። የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በጀግንነት ተፋልሞ በጠላት ሠራዊት ላይ መጠነ ሰፊ ኪሳራ አደ ረሰ፡፡

ባልጠበቁት ሰዓት ጥቃት የደረሰባቸው የሶማሊያ ወታደሮች ያበሰሉትን ምግብ እንኳ ሳይበሉ በርካታ ታንኮችን፣ ብረት ለበሶችን፤ መድፎችን፣ መትረየሶችንና ብዙ ስንቅ ጥለው ሸሹ። ያፈገፈጉ በርካታ ብረት ለበሶች ደግሞ በተዋጊ አውሮፕላኖች እየተመቱ ወደሙ። በገደል እየተንከባለሉም ከጥቅም ውጪ ሆኑ፡፡

ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት ሀገራቸውን ከዚያድ ባሬ ጦር ነጻ አወጡ። የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪው አስለቅቀው ባንዲራዋ በካራማራ ተራራ በድል ብስራት ዜና ታጅቦ ለመውለብለብ ቻለ። ይህ ድልም ዘንድሮ ለ47ኛ ጊዜ ታስቦ ይውላል፡፡

ለእዚህም ነው ካራማራ ኢትዮጵያውያን ብሔር፣ ሃይማኖት እና ጎሳ ሳይለያቸው በአንድነት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስከበሩበት እና ተስ ፋፊን ድል የመቱበት አኩሪ ታሪ ክ ነው የሚባለው።

 አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You