
ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች መገኛ ብትሆንም፤ ዘመናዊ የቱሪዝም ታሪክ በኢትዮጵያ ከተጀመረ ግማሽ ምእት ዓመት እንኳን እንደማይሞላ ይነገራል:: አሁን ላይ የቱሪዝም ዘርፉን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሶሶ አድርጎ በመውሰድ ዘርፉን የማሳደግ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል::
በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተገንብተዋል:: እየተገኑቡም ይገኛሉ:: እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ እና ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ሚና የጎላ ነው::
ይህን መሠረት አድርጎም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጓዙ መንገደኞች፤ እግረ መንገዳቸውን ኢትዮጵያ እንዲጎበኙ የሚያስችል ስምምነት በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ትናንት ተፈራርመዋል::
በወቅቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ እንደሚገልጹት፤ ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ያላት ሀገር ናት:: ይህን የቱሪዝም ሀብት ገልጦ በማየት እና በማስተዋወቅ፤ እንደ ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተገነቡ ነው:: በዚህም ከመሰረተ ልማት ግንባታ አንስቶ ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ላይም ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ ያወሳሉ::
የቱሪም ዘርፉ ካሉት እምቅ አቅሞች እና እምብዛም ያልተጠቀምንበት አንደኛው ደግሞ የእግረ መንገድ (ስቶፕ ኦቨር) የቱሪዝም ዘርፍ ነው:: ከዚህ ጋር በተያያዘ በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል አዲስ አባባን ረግጠው የሚያልፉ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ቁጥር ከ12 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ያስረዳሉ::
ይህም መረጃ ዘርፉ ትልቅ አቅም እንዳለው የሚያሳይነው የሚሉት ሚኒስትሯ፤ እነዚህም 85 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚጠቀሙ ናቸው:: ከዚህ አኳያም ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁሉንም እድሎች መጠቀም ተገቢ ነው:: ከእነዚህ እድሎች አንዱ ደግሞ የእግረ መንገድ ቱሪዝም ዘርፍ ነው:: ይህንንም እድል ጥቅም ላይ ለማዋል አንዱ ትልቁ ሀብት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ::
አየር መንገዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎች የሚጠቀሙት እንደመሆኑ፤ በሀገራችን የሚገኙትን ታሪካዊና፣ ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶች ጎብኚዎች እንዲያዩ ፣ ዓለም እንዲያውቅ እና ኢትዮጵያ በትክክል ከቱሪዝም ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ቦታና ጥቅም እንድታገኝ ትልቅ እድል ነው ይላሉ::
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 140 የሚሆኑ መዳረሻዎች አሉት:: በሀገር አቀፍ ደረጃም በተመሳሳይ መዳረሻዎቹ እየጨመሩና በዓለም ላይም ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል:: ከዚህም ጋር ተያይዞ የተሳፋሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ በአጭር ጊዜ ቆይታ ብዙ መዳረሻዎችን ማየት እንደሚያስችልም ይጠቁማሉ::
ሚኒስትሯ እንደሚገልጹት፤ የስምምነቱ ዓላማ ጎብኚዎች አዲስ አበባን ከረገጡበት ሰዓት አንስቶ የተቀናጀ ሥርዓት በመዘርጋት የቱሪዝም መስህቦችን የሚጎበኙበት ሁኔታ ስለሆነ በርካታ አካላት ይሳተፋሉ:: በዚህ ሂደት ውስጥ ትልቁ ሥርዓት የቪዛ አሰጣጥ የማቅለሉ እና የማሻሻል ጉዳይ ነው::
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፤ የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ እንደሚገኝ በማንሳት፤ የአየር መንገድ ቱሪዝምን ተከትሎ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ይህን ማስተናገድ የሚያስችሉ አሠራሮችን እንደሚተገበር በስምምነቱ ተመላክቷል ይላሉ::
የመግባቢያ ሰነዱ ከዚህ ሥራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እነዚህ ተቋማት በተናበበ መልኩ የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት አቅም የሚፈጥር ነው:: በተጨማሪም የእግረ መንገድ ቱሪዝም እንዲያድግ የሚያስችል የትብብር ማሕቀፍ መሆኑንም ይገልጻሉ::
ይህን የትብብር ማሕቀፍ በተደራጀ መልኩ ለመሥራት ቀጣይ የሥራ መመሪያዎች እና የሚደራጁ ቴክኒካል ቡድኖች እንደሚኖሩ በመግለጽ፤ ስምምነቱ በሶስት አካላት ቢደረግም በቀጣይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከተለያዩ ከፌዴራል እና ከክልል ተቋማት ጋር ይሠራል:: የግል ዘርፉም በቀጥታ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ይላሉ::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ኢትዮጰያ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን እና ከቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን በመንግሥት ደረጃ የተጀመረ እንቅስቃሴ መኖሩን ያነሳሉ:: ይህም እንቅስቃሴ በተለይ ሶስቱ ተቋማት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት በጋራ የሚሠሩበት እና ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ኢንዱስትሪ ነው ይላሉ::
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም ዓመታት ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል:: በዚህም ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል:: በሌላ በኩል ቱሪስቶች እንዲመጡ የተቀላጠፈ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት እና ወደ ሀገርም ከገቡ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ የቱሪስት መዳረሻዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ይላሉ::
አቶ መስፍን እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያጓጉዛቸው ዓለም አቀፍ መንገደኞች መሀከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት አዲስ አበባ ሳይገቡ በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሚተላለፉ ናቸው:: የስምምነቱ ትልቁ ዓላማ እነዚህ በአየር መንገዱ የሚተላለፉ መንገደኞች፤ አዲስ አበባ አርፈው የተወሰኑ ሰዓታትን ወይም ቀናትን የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ እና የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ እንዲመለከቱ ለማስቻል ነው ሲሉ ያስረዳሉ::
በዚህም ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞቹ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ “ኢትዮጵያን ሆሊደይስ” በሚል የጉብኝት ጥቅሎችን በማዘጋጀት ለመንገደኞች ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉንም ይጠቁማሉ::
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደሚናገሩት፤ እንደ ሀገር የቱሪስት መዳረሻዎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ፤ ተቋሙ ለጎብኚዎች የሚሰጠው የቪዛ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው ያለው:: በተለይ አዲስ አበባ ላይ ኮንፍረንስ ለመሳተፍ ቪዛ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በሰፊው እየጨመረ መሆኑ ለአገልግሎቱ በየጊዜው ከሚቀርቡ የቪዛ ጥያቄ መረጃ ላይ ይስተዋላል:: በዚህም ሰዎች እግረ መንገዳቸውን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሲመጡ ከቪዛ ዋጋ ነጻ እንዲሆኑ የሚያስችሉ መመሪያዎች ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ይጠቅሳሉ::
ይህን መመሪያ በምን መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከአየር መንገድ ጋር ሲሠራ መቆየቱን የሚገልጹት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ ስምምነቱ ዘርፉን በተመለከተ የበለጠ ለመሥራት የሚያስችል ነው ይላሉ::
በጋራ ለመሥራት መስማማቱ ተጨማሪ ጎብኚዎች ለማግኘት፤ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ እና ከቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን የሚያስችል እንደሆነም አመልክተዋል::
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም