“ሕዝቡ የመንግሥትን የክተት ጥሪ የተቀበለው በታላቅ የሀገር ፍቅር በመነሳሳት ነበር” – ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ

አዲስ ዘመን ፦ በዚያድ ባሬ መንግሥት ወረራ ወቅት ሕዝቡ ለነጻነቱ ካለው ክብር እና ለነጻነቱ ካለው ቀናኢ ነት የተነሳ የመንግሥትን የክተት ጥሪ የተቀበለው በተደፈርኩ ስሜት እና በታላቅ የሀገር ፍቅር መነሳሳት መሆኑን ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን አስታወቁ ። ሕዝቡ ለክተት አዋጁ የሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ለተገኘው አንጸባራቂ ድል ትልቁ አቅም እንደሆነ አስታውቀዋል።

በጦርነቱ ወቅት በታንከኝነት ሀገራቸውን ያገለገሉት ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን 47ኛውን ዓመት የካራማራ ድል አስመልክተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳመለከቱት፤ሕዝቡ ለነጻነቱ ካለው ክብር እና ለነጻነቱ ካለው ቀናኢ ነት የተነሳ የመንግሥትን የክተት ጥሪ የተቀበለው በተደፈርኩ ስሜት እና በታላቅ የሀገር ፍቅር መነሳሳት ነው።

ዚያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረው አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ 1953 በኋላ በ1956 እና በ1961 ዓ.ም ወረራ ፈጽሟል ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፤ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ግን “ታላቋ ሶማሊያ” የሚል ቅዥት ይዞ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩበትን መሬት በሙሉ በኃይል ለመጠቅለል መሞከሩን አመልክተዋል::

ውጊያው የተደረገው በተለምዶ እንደሚባለው በካራማራ ብቻ እንዳልሆነ፤ በሙስታሂል፣ በጎዴ፣ በዋርዴር፣ በአዋሬ፣ በቀብሪደሀርና በደገሃቡር በሚባሉ በተለያዩ ግንባሮች ጦርነቶች መካሄዳቸውን፤ ከፍ ባለ መስዋእትነት አንጸባራቂ ድል መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡

በወቅቱ የሀገሪቱ አየር ኃይሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ተጋድሎም አድርጓል፡፡ በዓለም ታሪክም አምስት አውሮፕላን የጣለ ጀግና የጦር ኃይል ተዋጊ አላውቅም፡፡ በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ጊዜ የራሺያ አብራሪ ሶስት አውሮፕላን መጣሉን አውቃለሁ፡፡ ለገሰ ተፈራ ግን በወቅቱ አምስት የጦር አውሮፕላን በመጣል ሀገሪቱን ባለታሪክ ማድረጉን ጠቁመዋል ፡፡

ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን በ1956 የታንክ መቶ አለቃ ሆነው በካራማራ ውጊያ ተዋግተዋል፡፡ በ1969 የታንክ ሺ አለቃ ሆነው በባቢሌ ግንባር ሐረር እና ባቢሌን ሊይዝ ከነበረው ከዚያድ ባሬ መንግሥት ጋር ተዋግተዋል፡፡ በውጊያው ግንባራቸው ቆስሎ ወደ ሃንጋሪ ሄደው እንዲታከሙ ተደርጓል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You