
ኢትዮጵያ በበርካታ ድልና የአርበኝነት ታሪኮች በዓለም መድረክ በሰፊው የምትታወቅ። ነፃነቷንና ክብሯን በማስጠበቅ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ቀንዲል የሆነች ሀገር ነች። የውጭ ወራሪ ኃይል ሉዓላዊነቷን ለመድፈር በመጣ ቁጥር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከዳር እስከዳር በመነቃነቅ በአንድነትና በአብሮነት በመሰለፍ ጠላትን አሳፍሮ የመመለስ አኩሪ ባህል ያለው ሕዝብ ባለቤትም ነች።
ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ፤መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ መሠረት የጣለው የዓድዋ ድል ባለቤት ነች ።
ዛሬም የዓድዋ ፍሬ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከዛሬ 14 ዓመት በፊት የጀመሩትን የህዳሴ ግድብ ወደ ፍጻሜ እያደረሱ ነው፤ የግድቡ ግንባታ የዚህ ትውልድ ዓድዋ እንደሆነም የብዙዎች እሳቤ ነው። የድሉ ቀን እና የግንባታው የፍጻሜ ቀን መቀራረቡ አሁን ላለው ትውልድ ትርጉሙ ከፍያለ ነው።
አዎ ዓድዋና ሕዳሴ ግድብ በብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ሁለቱም የአልበገርነት ተምሳሌት ናቸው፤ የተከወኑት አልበገር ባይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ዓድዋ ወራሪውን የፋሽስት ኃይል ኢትዮጵያውን አሳፍረው የመለሱበት እና አይበገሬነታቸውን ለዓለም ሕዝብ ያሳዩበት የድል በዓል ነው።
በተመሳሳይም የሕዳሴ ግድብ ለውጤት መብቃት ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ላይ ተጥሎ የነበረውን ኢፍትሐዊ ውሃ ክፍፍል እልባት የሰጠ እና ኢትዮጵያውያንም በአንድነት ከቆሙ የተጫነባቸውን ቀንበር አሽቀንጥረው መጣል እንደሚችሉ ያሳዩበት ድል ነው።
እኛም የዓድዋ ድልና የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት ናቸው? ስንል ለታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ጥያቄዎችን አቅርበን እንደሚከተለው አጠናክረነዋል
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ትልቅ ታሪክ ሠርታለች። ይህ ደግሞ ሁሌም በየዓመቱ ይዘከራል፤ እርሶ አሁን ላይ ትውልዱ ከዓድዋ ምን መማር አለበት ይላሉ ?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ኢትዮጵያውናን ሁሌም ቢሆን ከባዕድ ሀገር የተሰነዘረባቸውን ወረራ አንድነትና ኅብረታቸውን ይዘው መመከት ያውቁበታል፤ አንድ ላይ ሲቆሙ ደግሞ ሁልጊዜም አሸናፊዎች ናቸው። ጣሊያን የቅኝ ግዛት ፍላጎቷን ለማርካት ኢትዮጵያን ምርጫዋ አደረገች። እንደሌላው የአፍሪካ ሀገር በቀላሉ አንበርክካ አስተዳደሯን ለመመስረት እና ሀቷን ለመመዝበር ቋምጣ ተነሳች።
ይህን የሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሪውን ትዕዛዝ በመቀበል ደሙን ለማፍሰስ፣ አጥንቱን ለመከስከስ ቆርጦ ተነሳ። ከአራቱም ማዕዘናት የተመመው ሕዝብ ወራኢሉ ላይ በመገኘት ለሀገሩ ለመሰዋት ተሰናዳ። ኢትዮጵያን ለመውረር እያደባ ባለው የጣሊያን ጦር ላይ ርምጃ ለመውሰድ አንድነቱን ኅብረቱን አጠናክሮ በእጁ ባለው ባህላዊ መሳሪያ ቢላዋና ገጀራ ሳይቀር ወደ ፍልሚያ ገባ። አስደማሚ ከሆነ ተጋድሎ በኋላ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ተውለበለበ።
ጣሊያኖችም ባልጠበቁት ሁኔታ የካቲት 23 ቀን ኢትዮጵያ ድሉን ተጎናጸፈች። ይህ ደግሞ ጣሊያንን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ቅኝ ገዢዎችን ሁሉ ቅስም የሰበረ ሲሆን፤ በአንጻሩ በቅኝ ግዛት ሲሰቃዩ ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ኩራትና በራስ መተማመንን የፈጠረ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህ መልኩ የተጠናቀቀው የዓድዋ ድል በርካታ ቁም ነገሮችን ትቶ አልፏል። ከምንም በላይ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ መሆኑንና አንድነቱ ደግሞ ብርታት በመሆኑ ማንም እንደማያሸንፈው ትልቅ ግንዛቤ የሰጠ ነበር። የዓድዋ ውጤት በተለይም በምዕራቡ ዓለም በፈረንሳይ በጀርመን በእንግሊዝ በመሳሰሉት የአውሮፓ ሀገራት ዘንድ ድንጋጤን ፈጠረ።
እነዚህ ጥቁሮች ተሰባስበው ዘመናዊ መሳሪያን በታጠቀው ጣሊያን ላይ ይህንን የመሰለ ውጤት ካመጡ ሌሎቹም የአፍሪካ ሀገራት ይህንን ፈለግ ተከትለው ለነጻነታቸው መፋለም ይጀምራሉ በሚል ስጋት ገብቷቸው ነበር። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን በልዩ ዓይን ለመመልከት ተገደዋል።
የተለያዩ ልኡኮችንም በመላክ የዓድዋ ድል ጎልቶ እንዳይነገር እና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦችን እንዳያነሳሳ የማግባባት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል። ለኢትዮጵያም የተለያዩ ማባባያዎችን በማቅረብ ድሉ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሕዝቦች አርአያ እንዳይሆን ትብብር እንድታደርግ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ሆኖም የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል መሆኑን በማብሰር የቅኝ ገዢዎችን ሃሳብ ሳትቀበል ኖራለች።
ይልቁንም በቅኝ አገዛዝ ውስጥ የነበሩ ሕዝቦችን በማንቃት፣ በማስታጠቅ እና በማሰልጠን ለጥቁር ሕዝቦች ያላትን ወገንተኝነት አሳይታለች። ከዚህም አልፋ የአፍሪካ ሀገራትን በአንድነት የሚያሰባስብ እና በችግሮቻቸው ላይ በጋራ እንዲመክሩ የሚያስችል ተቋም እንዲመሰረት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ተንቀሳቅሳለች። ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ አንድነትን በመመስረት ትልቅ ሚና ተጫውታለች፤ በተባበሩት መንግሥታት ምስረታም ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በየመድረኩ ለጥቁር ሕዝቦች መብት እና ነጻነት ጥብቅና ቆማለች።
በየመድረኩም ራሷን ብቻ ወክላ ሳይሆን ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራትና የጥቁር ሕዝቦችን መብት ወክላ ተከራክራለች። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለአፍሪካውን አለኝታ እና መከታ በመሆን ብዙ አፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።
የዓድዋ ድል በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ከነበሩት አፍሪካ ሀገራት በተጨማሪ ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ታፍሰው በመርከብ ተጭነው በጨረታ ለተሸጡት ጥቁር ሕዝቦች ታላቅ የምሥራችም ነበር። ይህ ደግሞ አፍሪካውያን በጊዜ ሂደት ነጻነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ የኢትዮጵያን ባንዲራ በመውሰድ እና የራሳቸውን በማከል የሀገሮቻቸው መለያ አድርገው እስከ አሁን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በጠቅላላው ዓድዋ እኛ በዓመት አንደ ጊዜ እናክብረው እንጂ በመላው የጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ታሪክና ክብር ያለው የድል በዓል ነው።
አዲስ ዘመን፦ ድህነት እና መሰል ችግሮችን ታግሎ ለማሸነፍ ዓድዋ የሚሰጠን ትምህርት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አደም፦ በጣም ትክክል ነውḷ አሁን ላይ በሀገራችን የዓድዋውን አይነት ቁርጠኝነትና አንድነታችንን የሚፈልጉ በርካታ ችግሮች አሉብን። እናም እነዚህን ችግሮቻችንን ልንወጣና ልናልፋቸው የምንችለው በአንድነታችን ብቻ ነው። አንድነታችን ጠንካራ ከሆነ እና ብሔር፣ ቋንቋ፣ ቀለም ሆነ ሌላ ሳይለየን በአንድነት መጓዝ ከቻልን የማናሸንፈው ችግር እንደሌለ ዓድዋ ምስክር ነው።
በበኩሌ ሰሞኑን የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታችን ምን እንደሚመስል ለማየት ወደ ዱባይ ጉዞ አድርጌ ነበር፤ ዱባይ ውስጥ ከ150 ሺ የሚልቅ ኢትዮጵያዊ ይኖራሉ፤ በሚገርም ሁኔታ ግን በዚህ መድረክ ላይ እስከ ዛሬ የትኛውም ዓለም ላይ ዞሬ ያላገኘኋትን ሀገሬን ያገኘሁበት መድረክ ሆኖልኛል። ኮሚኒቲው ስለ ሀገሩ ታላቅነት፤ ስለ ሕዝቧ ጀግንነት ግንዛቤ እንዲኖረው በመደረጉ ሕዝቡ የጋለ የሀገር ፍቅር አለው። ይህ እንደ ዜጋ ትልቅ ክብር እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
ኢትዮጵያውያን ታሪካችንም ሆነ ኅብረታችን ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ካሉት ሀገሮች በሕዝብ ብዛት ከፍ ያልን እንደ መሆናችን እና የሀገራችን አቀማመጧም በጣም ስትራቴጂካዊ የሆነች ሀገር ስለሆነች የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችለናል። በቅርቡ በአረብ ምሁራን በተደረገ ምርምር ኢትዮጵያ በሰላም በፍቅርና በአንድነት ከኖረች ለገልፍ ሀገራትም ሆነ ለጎረቤት ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና ያላት እንደሆነች እና በዚህች ሀገር ላይ ግን አንድ ችግር ከመጣ ለአካባቢው ሀገራት ሁሉ መዘዙ ይተርፋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
አዲስ ዘመን፦ ዓለም በዚህ ልክ የሚረዳትን ሀገር ልጆቿ በአግባቡ ያውቋታል ማለት ይቻላል?
ፕሮፌሰር አደም፦ በፍጹም። ኢትዮጵያውያን እናውቃታለን ለማለት አያስደፍርም። በጣም በሚገርም ሁኔታ ግን የውጪ ጎብኚዎች በታሪኳ ተስበው ፣ በሕዝቦቿ በባህል በቋንቋ ተደምመው፣ በጀግንነቷ ተደንቀው ይመጣሉ፤ ከመጡም በኋላ ለመመለስ እስኪከብዳቸው ድረስ ኢትዮጵያን ምርጫቸው ያደርጋሉ። በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል እንደሚባለው እኛ የምንኖርባትን ሀገር በአግባቡ አናከብራትም። ክብር እና ዝናዋን አንረዳውም። ይባስ ብሎም ምኞታችን ሁሉ ከኢትዮጵያ መሰደድ ነው።
ነገር ግን አዲሱ ትውልድ ስለ አባት እናቶቹ የተጋድሎ ታሪክ ቢያውቅ፤ታሪክ ቢያነብ የሀገሩን ክብርና ሞገስ ቢረዳ ኖሮ ሀገሩ እንቁ እንደሆነች ይገነዘብ ነበር። ብዙዎች የእዚህችን ሀገር ክብር እና ውለታ የሚረዱት በስደት በሰው ሀገር መኖር ሲጀምሩ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የእዚህ ዘመን ዓድዋ እንግዲህ ሕዳሴ ግድብ ነው ይባላልና እነዚህ ሁለት ነገሮች የሚመሳሰሉበት መንገድ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር አደም ፦ የሕዳሴ ግድብና ዓድዋ በብዙ መንገድ ይመሳሰላሉ። የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ የአልበገርነት ተምሳሌቶች ናቸው። ሁለቱም የኢትዮጵያውያን ቆራጥነትና አንድነት ማሳያዎች ናቸው።
ዓድዋ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ ነው። ከዓድዋ ጦርነት በፊት በነጮችና ጥቁሮች መካከል የነበረው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተዛባ ነበር። ነጮቹ ራሳቸውን እንደ ገዢ ሲቆጠሩ፣ ጥቁሮቹን ደግሞ እንደ ተገዢ ሕዝብ ይቆጥሩት ነበር።
ጥቁሮቹ ራሳቸውን የማስተዳደር አቅምና ችሎታ እንደሌላቸው ሲቆጥሩ ነጮች ደግሞ ጥቁሮችን የመግዛት ሙሉ መብት እንዳላቸው ያምኑ ነበር። በተጨማሪም ጥቁሮች ባህልና ታሪክ አልባ፤ እንዲሁም በተፈጥሯቸው ያልተሟሉ የሰው ዘሮች እንደሆኑ ተደርጎ ይነገር ነበር። ዓድዋ ይህን ሁሉ ቀይሯል። በአውሮፓውያን በኩል፣ ነጮች ይከተሉት የነብረው የተዛባ ትርክት “የነጭ ዘር የበላይነት” መንኮታኮትና እርቃኑን መቅረት የጀመረው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። ከዚህ ድል በኋላ ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካ ላይ የነበራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች ተናግተዋል።የጭቆና መረባቸው ስጋት ውስጥ ወድቋል።
ይህ ሁሉ ድል የተገኘው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰውና ሕይወታቸውን ገብረው በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። ድሉ ለሁሉም ጥቁር ሕዝቦች እኩልነት የተከፈለ የደም ዋጋ ነው።ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን የዓድዋ ድል በሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት የሚያምን ማንኛውም የሰው ዘር ሊያከብረውና ሊዘክረው የሚገባ ክስተት ነው።
በተመሳሳይ መጋቢት 24 ቀን በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳክቶ ከመገባደጃው ጫፍ ደርሷል።ተማሪዎች ከዕለት ጉርሳቸው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ የጉሊት ተዳዳሪዎች ከመቀነታቸው ፣ የጉልበት ሠራተኞች ከዕለት ምንዳቸው፣ የፀጥታ ኃይሎች ከሬሽናቸው፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከፍሬያቸው እየቀነሱ ግድቡን ከማጠናቀቂያ ምዕራፉ አድርሰውታል። በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ይገባዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዘመኗ ከሠራቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አቻ አይገኝለትም። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሰባተኛ የሆነው ይህ ግዙፍ ግድብ ያለማንም የፋይናንስ ድጋፍ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፍስ ወከፍ ባዋጣው ገንዘብ የተሠራ ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ከግድቡ ኋላ የሚተኛው የውሃ መጠን 256 ኪሎ ሜትር ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺ 759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት ለሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ኤሌክትሪክ ያልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግና አቅርቦቱን አሁን ካለበት 44 በመቶ ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የዚህ ፕሮጀክት ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የሕዳሴ ግድቡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲታይ በባሕር ትራንስፖርትና በዓሳ ሀብት ልማት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ስለሚፈጠር በአካባቢው በታንኳ እና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ እንዲሁም በዓለማችንም ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻም የመሆን አቅም አለው። በተለይም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ ኃይቅ እየሰፋ ሲሄድና ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም ከ78 በላይ ደሴቶች የሚፈጠሩ በመሆናቸው ይህም ዋነኛ የቱሪስት ማዕከል እንዲሆን ያስችለዋል። ከፍተኛ የዓሳ ሀብትም ይኖረዋል።
ይህ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ግዙፍ ግድብ እዚህ የደረሰው በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው። የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እዚህ እስኪደርስ ድረስ የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያም ሆነች ግድቡ በጥርጣሬ እንዲታዩና አልፎ ተርፎም ጦርነት እንዲከፈትባቸው የሚነሳሱ ሰፋፊ ዘመቻዎች ተካሂዶባቸዋል። ሆኖም የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችለዋል።
አልበገር ባይ የሆኑት እና ለአመኑበት ጉዳይ ወደኋላ ማለት የማያውቁት ኢትዮጵያውያን ከጎዶላቸው ላይ ቀንሰው ግድቡን ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል። በአሁኑ ወቅትም የግድቡ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል።
እዚህ ላይ ላነሳ የምፈልገው ነገር ግብጾች ወታደሮቻቸውን አሰልጥነው ሲያስመርቁ ቃለ መሀላ የሚያደርጉት “ለዓባይ እሰዋለሁ” በማለት ነው፤ ለግብጽ አልያም ለሕዝቧ አይሉም፤ በዚህን ያህል ነው ጥቅማቸውን የሚያውቁት፤ወደኛ የመጣን እንደሆነ ግን ለልጆቻችን “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚል ዘፈን ነው ያወረስነው። ይህ የታሪክ ክፍተት ደግሞ ዋጋ እያስከፈለን ስለመሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህም የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን ስነቃላችንን እና ተረቶቻችንን ጭምር የሚያድስልን ነው።
ግብጾች በዓለም ላይ የሌሉበት ቦታ ስላልነበር ግድቡን ለመገደብ ስንነሳ እንኳን ዓለም አቀፍ ርዳታን እንዳናገኝ አድርገዋል፤ ይህ ባለበት በሁኔታ ግን ሕዝቡ ተባብሮ አቅሙን አሳይቶ ዓድዋን ደገመው።
ይህ ሁሉ ማዕቀብ ባለበት ወቅት፤ ከውጭ ርዳታ በተከለከልንበት ሁኔታ ከታች እስከ ላይ፣ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከደሃ እስከ ሀብታም ፣ ከተራው ሠራተኛ እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናት ድረስ ያላቸውን አዋጥተው በአፍሪካ ግዙፉን ግድብ መሥራት ቻሉ። በዚህም የመጀመሪያው ሙሌት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲሞላ ግብጾች ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ነበር የገቡት፤ ከዛ በኋላ 2፣3፣4፣5 እያለ የሙሌት ሥራው በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ፤ እንግዲህ ግድቡ አሁን ባለው ሁኔታ ከመሬት ወለል በላይ 602 ሜትር ይገኛል።
ይህም ማለት ከሱዳን በላይ 320 ከግብጽ በላይ ደግሞ 222 ሜትር ማለት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ግድብ የሆነ ነገር እናደርጋለን ማለት 150 ኪሎ ሜትር ወደጎን 26
ሜትር ወደላይ ፈንድቶ ታይቶ በማይታወቅ ማዕበል ከሱዳን 30 ሚሊዮን ሕዝብ ጠራርጎ ከሰባት ሰዓት በኋላ አስዋን ግድብ ይደርሳል። ይህ ማለት እንግዲህ አሁን ላይ ግድቡ ራሱን መከላከል ችሏል ማለት ነው።
አሁን ላይ ግብዖች ይህ እድል ሲያመልጣቸው እንደገና በሱማሌ በኩል የእሷን አጀንዳ በማንሳት የግድብ ፖለቲካው ማስቀየሻ መንገድ እየፈለጉ ነው። ይህም ቢሆን ግን በኢትዮጵያ መሪዎች በሳል ዲፕሎማሲ አካሄድ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ መቀየር ተችሏል።
አሁንም ኢትዮጵያውያን የአባት የእናቶቻቸውን ታሪክ እያስቀጠሉ ከመሆኑም በላይ ይህ ግድብ የዓድዋ ምሳሌ ነው መባል የሚችል ነው። በመሆኑም ከዓድዋም ይሁን ከህዳሴው ግድብ የተማርነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ልዩነቱን አጥብቦ ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ግንባር ቀደምትነት ምክንያት ሳያበዛ ወደፊት የሚቆምና ችግሯን ለመፍታት የሚጋፈጥ መሆኑን ትምህርት አግኝተንበታል።
አዲስ ዘመን፦ የህዳሴ ግድባችን የተጓዘው መንገድ ረጅም ከመሆኑም በላይ ብዙ ውጤቶችንም አሳይቷል፤ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ሲያዩ ምን ተሰማዎ?
ፕሮፌሰር አደም፦ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። አሁን ላይ ግድቡ 97 በመቶ ተጠናቋል፤ ከዚህ በኋላ ያለው ሥራ በጣም ጥቂት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ በቀን አንድ ብር አዋጣ ቢባል እኮ 130 ሚሊዮን ብር አዋጥቶ የሚውል ነው። በመሆኑም በመሪዎቹ ካመነ የቀደመ አንድነቱንና ኅብረቱን ማምጣት ከቻለ እንኳን ህዳሴ ግድብን ሌላም ይሠራል። ይህ ደግሞ በተሞክሮ የተረጋገጠ እውነት ነው።
እዚህ ላይ ግን ትወልዱ ምን ያህል ሀገሩን ጠንቅቆ ያውቃል? የሚለው የቤት ሥራ አሁንም ትኩረት አግኝቶ ሊሠራ የሚገባው ነው። ይህንን ኃላፊነት ወስዶ መሥራት ከተቻለና ትውልዱ ስለ እናት አባቶቹ ጀግንነት ስለ ሀገሩ ታላቅነት ተሰሚነትና ተፈሪነት ካወቀ የሰው ሀገር በመናፈቅ መሰደዱን ትቶ አሜሪካንም፣አውሮፓንም፣ ጅዳንም፣ ዱባይንም ሀገሩ ላይ አምጥቶ የሚኖር ይሆናል ። ይሄ እንዲሆን ግን መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ያገባኛል የሚሉ ሁሉ ዋጋ ከፍለው መሥራት አለባቸው።
በሌላ በኩልም ሁላችንም ያላወቅነው ወይም ያልተረዳነው አንድ ነገር ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ሀብት የአየር ጸባይ ሕዝቧ ሥራ ወዳድነት አንጻር እንኳን 130 ሚሊዮን 270 ሚሊዮንን ከዛ በላይ ሕዝብን መግቦ ማሳደር የሚችል አቅም እንዳላት ነው። ይህንን ደግሞ እኔ ሳልሆን ያልኩት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች ያረጋገጡት ሀቅ ነው። በመሆኑም ይህንን በእጃችን ያለን ወርቅ ወደ ሥራና ውጤት ቀይረን ዳቦ ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ዓድዋን በየዓመቱ ስንዘክር ወደልባችን ሊመጣ የሚገባው ነገር ምን ሊሆን ይገባል?
ፕሮፌሰር አደም፦ በየዓመቱ ዓድዋን መዘከር በጣም ጥሩና አስፈላጊ ነው። ትውልዱ ላይም ጥሩ መነቃቃትና ትምህርት ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን እያንዳንዱ ቀናችን ዓድዋ ሆኖ ሊውል ይገባል የሚልም የግል አስተያየት አለኝ። ዓድዋ በጦር ሜዳ የተገኘ የጀግንነት አርማ ነው፤ እኛ ደግሞ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ሀገራችንን በማሰብ‹‹ እኔ ለሀገሬ ምን ባደርግ ነው አንድ ርምጃ ልትራመድልኝ የምትችለው?›› በሚል መንፈስ ሥራን መከወን ዓድዋን የመዘከር አንዱ ማሳያ ነው።
በሌላ በኩልም በተለያዩ ምክንያቶች በሀገራችን ላይ እየታዩና እየተሰሙ ያሉትን ግጭቶች እና ያለመግባባቶች እንዲቆሙ የሰላም አምባሳደር በመሆን የሚጠበቅብንን ማድረግ ወደ ህሊናችን ሊመጣ የሚገባው ጉዳይ ነው። ዋናው ነገር ግን የሃይማኖት አባቶች ፖለቲከኞች ሌሎችም አካላት ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን ማስቀደም ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ አባት እናቶቻችን በዱር በገደሉ ተንከራተው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከታጠቀ የባዕድ ጠላት ጋር ተጋድለው ተፋልመው ያመጡልንን ድል ማጣጣም ለትውልድም ማውረስ ያስችለናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አደም፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም