«የዓባይ ግድብን ወደ ፍጻሜ አድርሰን የዓድዋን ድል እየዘከርን ነን» – ፕሮፌሰር ጤናዓለም አየነው

የዓድዋ ድል ይሄ ትውልዶች እየኮራበት የሚቀጥል፤ የጥቁር ሕዝቦች የሥነልቦና ትጥቅ፤ የአንድነት ማሳያና የሕብረት ዋጋ የታየበት አንጸባራቂ ድል ነው። በትውልዶች ላይ ጽኑ የሀገር ፍቅርንና አርበኝነትን ያላበሰ በባህልና ታሪክ መኩራ

ትን ያስተማረ ሕያው ታሪክ ነውአርበኝነትን የሚያጎናጽፍ የፍስሃ ቀን ብስራትም ነው።

ድሉ መነሻ ድልድይ፤ ይቻላልን አስተማሪም ነው። የዛሬው ትውልድ በእርሱ መነሻነት ሌላ ታሪክ እንዲሠራ አስችሏል። የኢኮኖሚው ምሰሶ የሚሆነውን መሰረት አቁሟል። አትችልም ቢባልም፤ ጫና ቢበዛበትም በአንድነቱ «እችላለሁኝ» ለዓለም ሁሉ አሳይቷል። መሐንዲሱም፣ የፋይናንስ ምንጩም ባለሙያውም ራሱ ሆኖ የአንድነቱ ውጤት የሆነውን የዓባይ ግድብ ገንብቶ በተግባር እያሳየ፤ እያስመሰከረ ነው።

የዓባይ ግድብ እንደ ዓድዋ ድል የዳግም አሸናፊነት ተምሳሌ ነው። ያሰብነውን ልናሳካ እንደምንችል ማሳያ ነው። የውሃ ሀብታችንና ዓድዋ ምን አይነት ትስስር አላቸው፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታቸውስ እንዴት ይገለጻል የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነምድር ትምህርት ክፍል መምህርና በውሃ ዘርፍ ፕሮፌሰር እንዲሁም ተመራማሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ጤናዓለም አየነው ጋር ቆይታን አድርገናል። የዓድዋን ድል አስመልክተንም ያሉንን እነሆ ብለናል።

አዲስ ዘመን፡የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት እንዴት ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡የኢትዮጵያን የውሃ ሀብት በሁለት መልኩ ከፍለን ልንመለከት እንችላለን። የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውሃ ብለን ልናየው የምንችለው ነው። በእነዚህ የውሃ ሀብቶች ሀገራችን ከአፍሪካ በአንጻራዊ መልኩ የተሻለ ሀብት አላት። በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀዳሚነት ከፍተኛ የውሃ ሀብት አላቸው ከሚባሉት መካከል የምትጠቀስ ነች።

እያንዳንዱን ዘርዘር አድርገን ስንመለከተው ደግሞ ከገጸ ምድር ስንጀምር እስከ አሁን ባለው ግምት በየዓመቱ ከወንዞቿ ከ122 ቢሊዮን ኪዊቢክ ሜትር በላይ የገጸ ምድር ውሃ ይፈሳል። ውሃው በአብዛኛው ሀገር አቋርጦና ድንበር ተሻግሮ የሚሄድ ነው። በዚህም ከሀገሪቱ አልፎ ሌሎች ሀገራትን ያረሰርሳል። ለም አፈሩን ሳይቀር ሸርሽሮ ለሌሎች ሀገራት ይመግባል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በቀዳሚነት ለዓመታት ሲዘፈንለት፤ ሲተረትበት የቆየው ዓባይ ተጠቃሽ ነው።

ከዚያ ሻገር ብሎ ደግሞ እንደ ዋቢ ሸበሌ፣ ተከዜ፣ ገናሌ፣ ዳዋ ፣ አኮቦ፣ ባሮ፣ አዋሽ፣ ኦሞን የመሳሰሉ ታላላቅ ወንዞችንና ብዙ ሃይቆችን ስናነሳ ኢትዮጵያ በገጸ ምድር ውሃ ሀብቷ ገደብ የማይገኝላት ባለጠጋ እንደሆነች እንረዳለን። ወደ ከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ስንመጣም በትክክለኛ መጠኑ በጥናት ተለይቶ ባይታወቅም አሁን ባለው ግምት ከ30 እስከ 45 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ልትጠቀምበት የምትችለው እምቅ የውሃ ሀብት ያላት ሀገር እንደሆነች መናገር ይቻላል። በአጠቃላይ በሁለቱም መልኩ ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የውሃ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን መገንዘብ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡ይህንያ ህልየውሃ ሀብት ካለን ታዲያ ምን ያህሉን ተጠቅመንበታል?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡እንደውሃ ባለሙያነቴ ካለን የውሃ ሀብት ብዛት አንጻር በአግባቡ ተጠቅመንበታል የሚያስብል ነገር የለንም። ይህንንም በሁለት መልኩ ለይቶ ማንሳት ይቻላል። አንዱ በአካል የሚታየው የውሃ መጠን (Physical water) ሲሆን፤ ሌላኛው ጥቅም ላይ የዋለ የውሃ መጠን (Eco­nomical usage of water) የሚባለው ነው። ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያ ፊዚካሉ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ አይነሳባትም። ምክንያቱም የውሃ ሀብቷ ሲታይ ብዙና ለዜጎቹ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራት ጭምር ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ነው።

ከፍተኛ ጥያቄ የሚሆነው ውሃችንን ምን ያህል ወደ ጥቅም መቀየር ችለናል? የሚለው ነው። ከዚህ አንጻር ብዙም አልተጠቀምንበትም ወደሚለው ድምዳሜ ያደርሰናል። እንዲያውም ኢትዮጵያ Eco­nomic water sacristy›› ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደብ ናት። ይህ ማለት ውሃ ቢኖራትም ወደ ጥቅም፤ ወደ ልማት አልቀየረችውም ማለት ነው። በየመንደሩ የሚፈሱ ወንዞች ተጠራቅመው ሀገር አቋርጠው በመሄድ ለውጪው ጥቅም ላይ ሲውሉ፤ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧን በጨለማ ውስጥ የሚኖር ነው።

በንጹህ ውሃ እጦት የሚሰቃየው ሕዝቧም ካለው ሀብት እንዲጠቀም ለማድረግ ብዙ ተግዳሮቶች አሉባት። ንጹህ የሚለውን በመተው የመጠጥ ውሃ ብቻ በሚለው ቢወሰድ 80 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን ውሃ የምታገኘው ከገጸ ምድር ሳይሆን ብዙም የማያስለፋውን፤ ብዙ ኢንቨስትመንት የማይጠይቀውንና ሊያልቅ የሚችለውን የከርሰ ምድር ውሃ ነው። ከዚህ አንጻርም እንደ ልብ በየመንደሩ የሚፈሰውና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምሰሶ የሆነው የገጸ ምድር ውሃ በብዙ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም። ጥቅም ሰጥቷል ከተባለም 20 በመቶው አካባቢ ብቻ ነው። ለመስኖ የምንጠቀመውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ኢትዮጵያ በጣም ለም መሬት ያላት ሀገር ናት። መልክዓ ምድሯም ለሁሉም ሰብል የሚመች ነው። ነገር ግን የውሃ ሀብቷን ተጠቅማ ኢኮኖሚዋን መገንባት አልቻለችም። ይብሱንም 80 በመቶ የሚሆነውን ለመስኖ መጠቀም የምትችለውን የገጸ ምድር ውሃ ስታባክን ትታያለች። ጥቅም ላይ ያዋለችውም ትክክለኛውን መጠን ማስቀመጥ ባይቻልም ከሚሠራው ሥራ አንጻር ሲታይ 20 በመቶ እንኳን አይሞላም።

ይህ ደግሞ በሀገራችን ሊታዩ የሚችሉ ትልልቅ እርሻዎች እንዳይኖሩ አድርጓል። በሀገር ደረጃ የከርሰ ምድርንም ሆነ የገጸ ምድር ውሃን ተጠቀምን ቢባልም እርሱም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ምክንያቱም ጅምር ሥራዎቹ አካባቢን በማይጎዳ መንገድ፤ ወጪንና ውጤታማነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሲሠራባቸው አይታይም።

በተጨማሪም የውሃ ማኔጅመንቱን መሰረት ባደረገ መልኩና በፕላንና እቅድ እንዲሁም ክትትልና ድጋፍም በሚጠበቀው መጠን አይመራም። ከባህላዊ መንገዱ የተላቀቀና ዘመኑን የዋጀም አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀጣይነቱና ዘላቂነቱ አልተረጋገጠም። በመሆኑም የውሃ ሀብቱ ተጠቃሚነት እጥረት ያለበት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡የውሃ ሀብታችንን እንዳንጠቀምባቸው የገደቡን ዋና ዋና ችግሮች ምንድናቸው?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡ብዙን ጊዜ የውሃ አስፈላጊነትን አለማወቅ፤ ጥቅሙን አለመረዳት ነው ይባላል። ይህ ሃሳብ ግን ትክክል አይደለም። ኢትዮጵያውያን ስለውሃ አስፈላጊነት ከጥንት ጀምሮ ያውቃሉ። በባህላዊ መንገድም ቢሆን ሲጠቀሙበት ዘመናትን አስቆጥረዋል። ከቅርቡ እንኳን ብንነሳ ከ1960ዎቹ በኃይለሥላሴ ዘመን “ዓባይ ማስተር ፕላን” በሚል የውሃ ሀብት ጥናት በማስተር ፕላን ደረጃ ተጀምሮ ነበር። ከዚህ አንጻር ዋና ችግር ነው የሚባለው የውሃ ሀብት አጠቃቀምን በሚገባ ተረድቶ ዘመኑ በሚፈልገው በዘመናዊና በስፋት እንዲሁም በዘላቂነት መጠቀም አለመቻል ነው።

የውሃ ሀብት የሰለጠነ የሰው ኃይል ይፈልጋል፤ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ጭምር በካሪኩለም አስገብቶ ለተማሪዎች ጥቅሙን ማስገንዘብንም ይጠይቃል። ውሃን በባለቤትነት ወስዶ በስትራቴጂ እቅድና ክትትል እንዲሁም ድጋፍ መሥራትን ግድ ይላል። በቂ ኢንቨስትመንት መድቦ ወደ ሥራው መግባትንም የሚሻ ነው። ነገር ግን በእኛ ሀገር ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ ስላልሆነ በዋና ችግርነት ይጠቀሳል። ነገር ግን ውሃችን የእድገታችን መሰረት ነው።

ሌላው ችግር የውሃ ሀብትን አልምቶ ከመጠቀም ይልቅ የለማው ላይ መረባረብና ግጭት መብዛቱ ነው። በተለይ የገጸ ምድር ውሃን በተመለከተ በበር እየፈሰሰ ትቶ የሌሎችን ማማተሩ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም ያላስቻለን ጉዳይ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ያለንን ሀብት አውቆ፤ በዚያ ኮርቶ ለመለወጥ አለመነሳሳት ነው። በዚህ ደግሞ የውጪ ጎብኚዎች ዛሬ ድረስ ይገረሙብናል። ወደ ሀገራችን ሲመጡ የተፈጥሮ ሀብታችንን ሲመለከቱ በምግብ እንኳን ራሳችንን አለመቻላችንን ሲመለከቱ ይገረማሉ። ይህን እንቆቅልሽ መመለስ የሁላችንም የቤት ሥራ ነው።

ዓለም አቀፍዊ ጫናዎች ሌላው ሀብታችንን እንዳንጠቀም የገደቡን ችግሮች ናቸው። ለዚህም ለአብነት ዓባይን ማንሳት እንችላለን። እስከ ዛሬ በቆየንባቸው ዘመናት በዓባይ ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጫናዎች ተበራክተው ነበር። ከጎረቤቶቻችን ጭምር ችግር የሆኑብን ነበሩ። ጫናውን ዛሬ ላይ በመጠኑ ተሻግረነዋል። በዚህም የዓባይ ግድብን ወደ ፍጻሜ አድርሰን የዓድዋን ድል እየዘከርን ነን።

ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል የገነነች፤ አንድነቷ የሚያስቀና፣ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ነጻነትን ያላበሰች፣ ለሁሉም የጥቁር ሕዝብ ይቻላልን ያጎናጸፈች ሀገር እንደሆነች በዓባይ ግድቡ ተረጋግጧል። ፈተናዎች ቢበዙም ታግለን የተስፋ ብርሃን ማብራት ጀምረናል። ተረካቢውን ትውልድ በጀግንነትና በኩራት ሊንቀሳቀስበት የሚችልበትን የድል ብስራት አሰምተናል።

ከአለን የውሃ ሀብት አንጻር ግን ዓባይ ብቻ በቂ ነው ብሎ መዘናጋት አይገባንም። ሌሎች ብዙ ዓባዮችን በመሥራት ታሪክ ኩራትም፤ ብርታትም፤ ልማትም መሆኑን ማሳየት ይገባናል። ችግሮቻችንን ለይቶ ማወቅና ለመፍትሄው በጽናትና በኅብረት መሥራት ግድ ይላል።

አዲስ ዘመን፡ከውሃ ሀብት አጠቃቀም አንጻር ያለውን ጅምር ሥራ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡በሀገር ደረጃ ውሃ ለውበት፣ ለመጠጥ፣ ለመስኖ፣ ለኃይል ማመንጫነት ወዘተ እየተባለ በተለያየ መልኩ በጅምር ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ጅምሩ ደግሞ ዓመታት ብቻ ሳይሆን ዘመናትን አስቆጥሯል። ለአብነት ዛሬ ድረስ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆነው የቀጠሉ የገጸ ምድርምና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት አሉን።

ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት በ1960ዎቹ የነበሩት ጀምር ሥራዎች ናቸው። እንደ አዋሽ ተፋሰስ (ቆቃ ግድብን በመገደብ)፣ ኦሞ፣ ዋቢሸበሌ፣ ባሮና መሰል ወንዞችን ይዘን ትልልቅ የመንግሥት እርሻዎችን ስናለማ ነበር። ከዚህም ባሻገር ኦሞ (ግቤ) እስከ ሦስት፣ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌና መሰል ወንዞቻችንን ተጠቅመንም በኃይል አቅርቦቱ የሀገር ኢኮኖሚ እድገታችንን እያፋጠንን እንገኛለን።

በከርሰ ምድር የውሃ ሀብታችንም ጥሩ ጅምር ሥራዎችን ሠርተናል። ለምሳሌ፡- የተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሉ የውሃ ሀብትን በማጥናት ለከተማ መጠጥ ውሃና ለመስኖ መጠቀም ጀምረናል። በተመሳሳይ በፓንፕና ጉድጓድ ቆፍሮ በማቆር ጭምር የመስኖ ሥራዎች ለሕይወታችን የለውጥ መሰረት እየሆኑ እንደሚገኙ በየመንደሩ በዝቅተኛ ደረጃ የሚሠሩት ሥራዎች አመላካች ናቸው።

ጅምር ሥራዎቹ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው ሲባል ነው ነገሩ ወገቤን የሚያስብለው። ምክንያቱም በርካታ ጅምሮች ወደ ሥራ ሲገባባቸው በፓይለት ደረጃ ነው። ፕላን ተደርጎ ፣ ቀጣይነቱ ተረጋግጦ አይደለም፤ እስከ መጨረሻው የልማት ሥራ ሆነው የሚዘልቁት ሁኔታ አይታይም። ይህ ደግሞ ሰፊውን የውሃ ሀብታችንን ሳንጠቀመው ጊዜያችን እንዲያልፍ ያደርገዋል። እድገታችንንም ይገተዋል። ስለዚህም ሥራዎቻችንን እንደ ዓባይ ግድቡ አመራር ያለው፣ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት እንዲሁም በስትራቴጂክ እቅድ የሚመራ ማድረግ አለብን።

አዲስ ዘመን፡እንደ ሀገር ታሪካዊ ከሚያደርጉን ሥራዎች መካከል አንዱ የዓባይ ግድቡ ነው። እርሶ ታሪካዊነቱን እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡ታሪክ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን አሻግሮ ማየት ነው። ታሪክ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገ መሥራት ነው። ከዚህም አንጻር ትናንት የነበሩ አባቶች ዛሬን አሻግረው አይተው ሠርቶ ማሳየትን፣ ባህልን፣ ሥርዓትን፣ አልሸነፍ ባይነትን፣ ፍቅርንና በኅብረት መቆምን፣ ለነገዎቹ መልካም ነገሮችን ማበርከትን ዋጋ ከፍለው ጭምር አስተምረውናል። ትናንት ላይ ሆነው ነጻነትን፣ ጀግንነትን፣ እችላለሁ ባይነትን አጎናጽፈውናል። በዚህም እኛም ታሪክ ሠሪነትን ከእነርሱ ወስደን የዓባይ ግድብን ሠርተናል።

የዓባይ ግድቡ ግንባታ ጉዞ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያየንበት ነው። ነገ ለተተኪዎቹ ለማስረከብ የተከፈለን ዋጋ የምንገነዘብበትም ነው። በኢትዮጵያውያን ዘንድ አልችልም የሚባል ነገር እንደሌለ የተረጋገጠበት፣ እኔ የአባቶቼ ልጅ ነኝና ተአምር እሠራለሁ የሚባልበት፣ ጎረቤቶቹን ጠቅሞ፤ ለዓለም መለወጥ የሚታትር ሕዝብ እንደሆነ የሚነገርበት፤ የማንም ጫና እና ማስፈራሪያ የራስን ሀብት ተጥቅሞ ከመልማት የሚገድብ እንደማይኖር የታየበት ታሪክ ነው።

ዓባይ ግድብ እንደ ስሙ የታደስንበት፤ አቅማችንን የገነባንበትም ነው። ኃይልም፣ ታሪክም ሆኖን የልማት ምሰሶዎችን ያቆምንበትም ነው። ከሁሉም በላይ በዓለም ደረጃ ልዩ የሆንበትን ድል ነው። እንዴት ከተባለ ማንም ሀገር በራሱ ዜጎች ሀብት ብቻ በዓባይ ግድብ መጠን ሠርቶ አያውቅም። ኢትዮጵያ ግን በኅብረት፣ እያንዳንዱን ዜጋ በማሳተፍ ዓለም ያላየውን፣ በመጠንም በቴክኖሎጂም ግዝፈት ያለውን በዓለም ተጠቃሽና ተወዳዳሪ የሆነውን ግድብ ገንብታ አሳይታለች።

ታሪክ ለነገዎቹ ምሳሌ መሆን ነው። መንገድን መምራት፣ ማስተካከልም ነው። የትናንትና ኢትዮጵያውያን በማንም ያልተደፈረች፣ ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያን ያስረከቡትም እነዚህን ተግባራት በመከወን ነው። ይህ ደግሞ በዓባይ ግድቡ እውን ሆኗል። የሺዎች ዓመታት ቁጭት የነበረው ዓባይ የድሮው ዓባይነቱ ቀርቶ ዐብይነቱን ብርሃን በመለገስ አሳይቶ ለበለጠ ድል ጋብዞናል።

ሌላው የዓባይ ታሪካዊነት ማኅበራዊ ልማትን ማምጣት ነው። የፖለቲካ ተፅዕኖን ተቋቁሞ የራስ ሀብትን መጠቀም ይቻላል የሚለውን ማሳየት ነው። በኃይል እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ቀደመ ሥራቸው መመለስም ነው። ከተጠቃሚነት ጋር በተያያዘም የግብርና ዘርፉን፣ የቱሪዝምና ሌሎች ፀጋዎችን እንድናይ እንድንበለጽግበት መፍቀድ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፖለቲካ እና ከምጣኔ ሀብት ተፅዕኖዎች ራስን ማላቀቅ መቻል ነው። ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መውጣት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢኮኖሚ ሀብታም አይደለም። ታሪኩን የሚያስቀምጠው በገንዘቡ ሳይሆን ባለው ሀብት ላይ ነው። ሀብቱን ተጠቅሞ ትውልዱን መሥራት ይችላል። ነገውን ለማስተካከልም የሚገድበው አይኖርም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የዘመናት ቁጭት የነበረውን ዓባይ ገንብቶ ገንዘብም፤ ታሪክም አስቀምጧል። ረጅም ዓመታት አትችልም ሲባል ቢቆይም መቻል እንደሚችል አረጋግጧል።

በአጠቃላይ የዓድዋ ድል አለመገዛትን በጦርነት፣ በአንድነት ድል ያደረግንበትና ነጻነታችንን ያረጋገጥንበት ነው። ዓባይ ግድቡ ደግሞ በአንድነት የኢኮኖሚ ነጻነታችንን የምናረጋግጥበትን ድልድይ የገነባንበት ድላችን፣ ዓርማችን ፣ ታሪካችን ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡ዓባይ ግድቡ ዳግማዊ (ሁለተኛው) ዓድዋ ነው። እርሶ ይህንን ሃሳብ እንዴት ያብራሩታል?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡የዓባይ ግድቡ ካለው በረከትና የሥራ ውጤት አንጻር ዳግማዊ ዓድዋ ሊያስብሉት የሚችሉ በርካታ ባህሪያት ቢኖሩትም የዓድዋ ድል እጅግ ግዙፍ ነው። ሙሉ ዓድዋን ወክሎ ሁለተኛ የሚለው ሙሉነት የጎደለው ሃሳብ ይመስለኛል። ምክንያቱም የዓድዋ ድል ሁሉም ጥቁር ሕዝብ፤ የተጨቆነ ሁሉ የራሱ አድርጎ ለነጻነቱ ታግሎበት ያሸነፈበት ድል ነው። በራሱ አግባብ የእኔም ነው ብሎ ኮርቶ እያከበረው ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም አዲስ ነገር እየሠራ የዘለቀበት የነጻነቱ ዓርማ ነው።

የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን በማይተናንስ መልኩ በብዙ የዓለም ክፍል የሚከበር፣ የሚነገርና ስሜትን የገዛ ድል ነው። በአኩሪነቱ ትውልድ የተሻገረበትና አሁንም የቀጠለ ታሪክ ነው። ለሁሉም ሰው በትግል ተከብረው የመኖር ምስጢር የተገለጠበት ነው።

ግድቡ ግን አሁን ገና የተፈጠረና ከኢትዮጵያውያን ልብ ባሻገር ሌሎችን በስፋት የገዛ አይደለም። እያደር እኔም እችላለሁ ብሎ ተነስቶ የራሱን ሀብት በራሱ አቅም የሚያለማ ዜጋን ይፈጥራል እንጂ የፈጠረ ነው ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህም አሁን ላይ ሠርተው ስላሳዩ በዓባይ ግድቡ ስኬት መኩራት የሚችሉት ኢትዮጵያውያንና ውስን የኢትዮጵያውያንን በራስ መተማመን የሚያደንቁ አፍሪካውያንና የሌላ ሀገር ዜጎች ብቻ ናቸው። የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ መንደርደሪያ የሚያገኙት እነርሱ ብቻ ይሆናሉ።

ዓባይ ግድቡን ዳግማዊ ዓድዋ ሳይሆን ማለት ያለብን ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን ከአሳካቻቸው ድሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። ምክንያቱም በእርሱ መነሻነት ገና የምንሠራቸው ብዙ ልማቶች አሉ። በእርሱ መነሻነት ገና ብዙ የምንጓዝበት ማህበራዊ መስተጋብር አለ። በእርሱ መነሻነት ገና ኢኮኖሚያችንን፣ ፖለቲካችንን ልንገነባበት የምንችልባቸው ጉዞዎች ይፈጠራሉ።

የዓባይ ግድቡ ልክ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ከማሸነፋችን ጋር ተያይዞ ሌሎች የልማት ሥራዎችን እንድንሠራ የሚያበረታን ነው። ለሌሎች የውሃ ሀብት ልማቶች የምንቀሳቀስበት ድልድይም ነው። ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖርም የሚያደርጋት ነው። ምክንያቱም እስከዛሬ አታደርጉትም ሲሉ የቆዩት እንደ ዓድዋው ሁሉ አድርገን ስላሳየናቸው ከዚህ በኋላ ለሚኖረው የመልማት ጥያቄዎች መንጫጫትን ያስቆማል።

የሌሎች ሀገራትን ‹‹አይችሉም›› ስሜት ወደ ‹‹ይችላሉ›› ይቀይራል። የመልማት ጥያቄዎቻችንን የሚቀበሏቸው ሀገራትንም ያበራክታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎ አይነካም፤ ሲነኩት አይወድም የሚለው አመለካከት በሁሉም ዘንድ ይሰርጽና ልክ እንደ ዓድዋው ሁሉ መልማት መብት ነው የሚለውንም ያረጋግጣል።

አዲስ ዘመን፡ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ ዓባይ ግድቡ መነቃቃትን፣ የይቻላል መንፈስን፣ የኅብረትን ዋጋ ያረጋገጠ ነው። ከዚህ አንጻር የቀጣይ ትውልዱ የቤት ሥራ ምንድነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡– በመጀመሪያ ይህ ትውልድ ማድረግ ያለበት ሁለቱም ድሎች የኅብረት ፍሬዎች መሆናቸውንም መረዳት ነው። ከዚያ የዓባይ ግድቡን በረከቶችና ጥሎት ያለፋቸውን አሻራዎች በሚገባ አክብሮ ወደ ቀጣዮቹ የቤት ሥራዎች መግባት ነው። ለአዲስ ሥራ በቁጭት መነሳት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም አንዱን የውሃ ሀብቱን ተጠቅሞ ምን እንዳተረፈ ዛሬ ያለ ትውልድ በሚገባ ያውቀዋል። በዓባይ ግድቡ መገንባት ምን ምን በረከቶችን እንዳፈሰም ይረዳዋል።

ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል በጨለማ ውስጥ ያለው 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ያገኛል። ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም በእጥፍ በማሳደግ ለተቋማት የማያቋርጥ የኃይል አቅርቦት በማድረግ ልማቱን ያፋጥናል። ወጣቱ የተለያዩ የሥራ እድሎችን እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል። ኢንቨስትመንቶች እንዲሰፉ ያግዛል። ከራስ ታልፎ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን ያስችላል።

ተፈጥሮ ሀብት በመጠቀሟ ውስጥም በአፍሪካ አህጉር የነበረውን የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ ከስሩ በመቀየር የተዛባውን የሀገራት ግንኙነትን ያሻሽላል። የኢትዮጵያን ከዚህ በኋላ የመደራደር አቅም ከፍ ያደርጋል። በአካባቢዋ ያለውን ጸጋ አይታ እንድትጠቀምም መንገድ ይከፍታል። ተጽእኖ ፈጣሪነትን፣ ተቀባይነትን ይጨምራል። ተስፋ ማድረግ የት እንደሚያደርስም ያስተምራል። የቀደመውን የፖለቲካ ተጽዕኖ ሰብሮ የአፍሪካ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለጋራ ጥቅማቸው እንዲነሱ ያደርጋል።

ታዲያ ይህንን በረከት እንዴት ተጠቅመንበት ወደፊት እንጓዝ ከተባለ መሰረታዊ መልሱ መሆን ያለበት በቁጭት ለልማት መነሳት፣ አብዝቶ መሥራትን ልምድ ማድረግ የሚለው ነው። ‹‹እየኮሩ መቀመጥ ዋጋ ያስከፍላል። እየኮሩ መሥራት ግን ስኬታማ ያደርጋል።›› የሚለውን ሃሳብ መርህ ማድረግ ነው።

ትናንት በዓድዋ ጊዜ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በድሎቻቸው ውስጥ በርካታ ተግባራትን አከናውነው ዛሬን ለእኛ ሰጥተዋል። እኛ ደግሞ እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ የተፈጥሮ ሀብታችንን ተጠቅመን በማልማት ለሚያመሰግነን ተተኪ ትውልድ ማስረከብ አለብን። ለዚህ ደግሞ በድሎቻችን ውስጥ አብሮ መሥራትን፣ የራስ ታሪክ ማስቀመጥን፣ ልዩ የሆኑ ፈጠራዎችን ማፍለቅን፣ የከበረ ባህልንና ትስስሩን ማስረከብን፣ የጠነከረ አኩሪ እሴቶቻችን አስተምሮን መስጠትን፣ ሌሎችን የመቀበል ሰፊ ልምድን ማስተማርን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።

ዘመኑ ተወዳዳሪነትን የሚፈልግ፣ ዓለምን በአንድ መንደር ውስጥ ያስቀመጠ በመሆኑም አሸንፎ አሸናፊነትን ማውረስንም ይጠይቀናል። የዓባይ ግድቡ ስኬት የሚያኮራ ቢሆንም ዛሬ ላይ ከኩራቱ ይልቅ ዓለምን መቃኘትና የት ላይ እንዳለን አይቶ ወደፊት መራመድም የቀጣይ ሥራችን መሆን ይገባዋል።

የዓድዋንም ሆነ የዓባይ ግድቡን አስበንና አክብረን ስንውል ከማክበሩ ባሻገር ያሉ በረከቶችንም ማየት ያስፈልጋል። ቃል ገብቶ ለሥራው መፋጠንም ይገባል። ትናንት ‹‹የዓድዋ ድል በኢኮኖሚ ድል ይደገማል›› ብለን ዓባይ ግድቡን ሠርተን እንዳሳየን ሁሉ በቀጣይም ሌሎች ዓለምን ጉድ የሚያስብሉ ልማቶችን ሠርተን ማሳየት አለብን።

አሻጋሪነት የሚመነጨው ከታሪክ በመሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ታሪክ ኩራት ብቻ ሳይሆን መሥራትም እንደሆነ ማረጋገጥ ያስፈልገዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ለኅብረት ዋጋ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ግድ ይላል። ጊዜውን በጋራ ለመሥራት እንጂ በጋራ ለመጥፋት፤ ለግጭት ማዋል እንደማይበጅ ከእስከ ዛሬው ጉዞ ትምህርት መውሰድ ይጠበቅበታል። የትኛውም የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረን ፍቅርና ኅብረት ከሌለን ምንም እንደሆነ መገንዘብ ይገባዋል። ቅድሚያ ለመተሳሰብ መስጠት ይኖርበታል። ከዚያ ባሻገር በሀብቶቻችን ዙሪያ በግለሰብ፣ በቡድንና በኢንተርፕራይዝ ደረጃ መሥራትን አበክሮ ሊተገብር ይገባል።

አዲስ ዘመን፡ስለሰጡን ሰፊ ሃሳብ እናመሰግናለን።

ፕሮፌሰር ጤናዓለም፡– እኔም በዚህ ታላቅ የድል በዓል ላይ እንድናገር እድል ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You