‹‹የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተረጋገጠባቸው ታላላቅ ስኬቶች ናቸው›› – ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር

ዛሬ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነው ዓድዋ የሚከበርበት ቀን ነው፤ ይህ በኢትዮጵያውያኑ አንድነት የመጣው ታላቅ የድል ቀን ነው:: የዓድዋ ድል፤ የአሸናፊነት መለያ ምልክት ሆኖ ሲከበር የመጣ፣ በቀጣይም ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ዝንተዓለም ሲዘከር ይኖራል::

በተመሳሳይ የኢትዮጵያውያኑ ሌላኛው ዓድዋ ነው የተባለው ታላቁ የዓባይ ግድብ በምጥ ተወልዶ እውን መሆኑ የሚታወቅ ነው:: እነዚህ ሁለቱም ታላላቅ የኢትዮጵያውያን ስኬቶች የውጪውን ጫና እና መቋመጥ ያኮላሹ ድሎች ናቸው::

ኢትዮጵያ ሁለቱን ታላላቅ መለያዎቿን በአንድነት መንፈስና በጽናት ተግብራ የሕዝቦቿ የማንነት መገለጫዎች አድርጋቸዋለች:: አዲስ ዘመንም በዛሬው ልዩ ዕትሙ የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ ስለሚያመሳስላቸው ጉዳይ እና ተያያዥ ርዕሶች ዙሪያ ከኢፌዴሪ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጎ ተከታዩን ይዞ ቀርቧል::

አዲስ ዘመን፡- ከቀናት በፊት በተከበረው የናይል ቀን ዋነኛ ትኩረቱ ምንድን ነበር?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ዘንድሮ በኢትዮጵያ የተከበረው የናይል ቀን፤ መከበር የጀመረው እኤአ በ1999 ሲሆን፣ የተካሔደውም በታንዛንያ ዳሬሰላም ላይ ነው:: በወቅቱ እንደአቅጣጫ የተቀመጠው የናይል ተፋሰስ ሀገራት በየዓመቱ የናይል ቀን ማክበር እንደሚያስፈልጋቸው ነው::

አከባበሩ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እና በዓሉንም በዙር እንዲካሄድ ተወስኖ የሚከበርበት ሀገርም በዓሉን እንዲያስተባብር ውሳኔ ተላልፎ ነበር:: ኢትዮጵያ ይህን ኢንሼቲቭ ወስዳ እያከበረች ያለችው ለአራተኛ ጊዜ ነው:: እኛ ባለፈው ዓመት በነበረን ስብሰባ ዕድሉን ወስደን የዘንድሮውን ለማክበር በቅተናል::

የናይል ቀን በየዓመቱ ሲከበር አንድ ቀን ቀደም ተብሎ የሚኒስትሮች ጉባኤ የሚካሔድ መሆኑ ይታወቃል:: ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የመጡ የውሃ ሚኒስትሮች ወሳኝ ናቸው በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ:: እኛ ግን የዘንድሮውን ለማክበር ስናቅድ ሦስት ጉዳዮችን አስበን ነው:: የመጀመሪያው የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ ሌላው ጉብኝቱ፤ ሦስተኛው ደግሞ ዋናው ጉባኤ ነው::

የናይል ቀንን የተከበረው በደመቀ ሁኔታ ነበር:: ከስካይላይት እስከ ሳይንስ ሙዚየም በክፍት መኪና ተወዛዋዦች የኢትዮጵያን የውሃ ሀብት በተመለከተ እያስተጋቡ ከግብፁ የውሃ ሚኒስትር በስተቀር ሁሉም የውሃ ሚኒስትሮች እያጀቡን ወደስፍራው ደርሰናል::

ከዚህ ጎን ለጎን በማርሽ ባንድ የታገዘ ከሸራተን ጀምሮ በአራት ኪሎ በኩል እስከ ሳይንስ ሙዚየም የእግር ጉዞ ነበር:: በዚህ የእግር ጉዞም የተፋሰሱ ሀገራት ሚኒስትሮች ሁሉ ተንቀሳቅሰዋል:: በዚህ መልኩ ሁሉም ዝግጅቱንና የአዲስ አበባን ገጽታን በማድነቅ አስተያየት ሲሰጡ ነበር::

በዕለቱ ከሱዳን በስተቀር ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል:: አገርን ወክለው የመጡ ሚኒስትሮች ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ያብራሩት ነገር ቢኖር ሁሉም መተባበር እንደሚገባውና ውሃው የጋራ ሀብታችን እንደሆነ ነው:: ናይል የሁሉም እንጂ የአንድ ሀገር ብቻ አለመሆኑን ማንጸባረቅ ችለዋል:: ናይል የሁላችንም እንደሆነና በጋራ መልማት እንደሚቻልም ገልጸዋል::

አንዳንድ አገሮች በራሳቸው ውሳኔ ብቻ በስመ ሉዓላዊነት ፕሮጀክቶችን እየቀረጹ ይፈጽማሉ የሚል ነገርም ጠቅሰዋል:: በዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ክቡር ፕሬዚዳንታችን ናቸው:: እርሳቸውም በወቅቱ ድንቅ መልዕክት አስተላልፈዋል:: በተለይ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት መተባበር እንዳለባቸውና ውሃን በፍትሐዊነት መጠቀም እንደሚገባ ትኩረት አድርገው መልዕክት አስተላልፈዋል::

ከዚህ ጋር አያይዘው ኢትዮጵያ ለትብብር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል:: ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ በቀጣይ ኢትዮጵያ ተባብራ መሥራት እንደምትፈልግ አስረግጠው ተናግረዋል:: እኩል ውሃ መጠቀም እንዳለብን ብቻ ሳይሆን ውሃ ማበልፀግ እንደሚገባንም ጭምር አብራርተዋል::

ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኝ ሲተከል 11 ነጥብ ሁለት ቢሊዮኑ ችግኝ የተተከለው በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ መሆኑን አመልክተዋል:: ይህ ማለት የዓባይ ተፋሰስን በማበልጸግ ላይ ትልቅ ድርሻ ነበረን ማለት ነው:: ምክንያቱም ብዙ ምንጮች ይጎለብታሉ፤ ሊከሰት ያለውም ጎርፍ ይቀንሳል:: ከእኛም አልፎ ለታችኞቹ ሀገራት ጭምር በቂ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው የሚል መልዕክት ተላልፎላቸዋል::

ከዚህ የተነሳ ስኬታማ ቀን ማሳለፍ ችለናል:: በዕለቱ በሌላ ተቋም አማካይነት ለሥልጠና መጥተው ኢትዮጵያ የነበሩ ጋዜጠኞች ስለነበሩ እነርሱንም የዓባይ ግድብ ጉብኝት ላይ አሳትፈናቸው ስለነበር ተገርመው ሔደዋል::

አዲስ ዘመን፡- የናይል ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴን ጉብኝት በተመለከተ ግብፅ ማከላከሏ ምን ጥቅም ለማግኘት አስባ ነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ግብፆች ምን እንደሚነካቸው ባናውቅም ለስብሰባ ሲመጡ ከሰብዓዊነት አመለካከት ወጣ በሚል ስሜት ተሞልተው ነው:: ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የሚያስቆማቸውን አስተሳሰብ ይዘው ይመጣሉ:: እኛ የተፋሰሱ ሀገራት ወደ ናይል ቀን ጉባኤ ሲመጡ እግረ መንገዳቸውን የዓባይ ግድብንም እንዲጎበኙ በደብዳቤ አስቀድመን ገልጸንላቸዋል::

ይህንን መልዕክታችንን የግብፁ የውሃ ሚኒስትር በደብዳቤ የተቃወሙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው:: ለሁሉም ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ በኩል የህዳሴን ጎበኙ ጥሪን መቀበል የለባችሁም በሚል ገልጸዋል:: አንድ አካል ጤነኛ አዕምሮ ካለው እንዲህ አይነት ተግባር ይፈጽማል የሚል አተያይ የለንም:: እኛ ግን ይህን የግብፅን በደብዳቤ የታጀበ የአትጎብኙ መልዕክት የመልስ ምት አልሰጠንበትም፤ ንቀን ትተነው አልፈናል:: ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የተፋሰሱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮችም ምላሽ አልሰጡም::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የናይል ቀን ስብሰባ ላይ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር በግልጽ ሚኒስትሮቹ ግድቡን እንዳይጎበኙ ጥያቄ አቅርበዋል:: ጥሩነቱ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር ንግግር ያደረጉት ከእኔ በፊት በመሆኑ እኔ በንግግሬ ሁለት ጉዳዮችን አስረግጬ ለመናገር ዕድሉ አግኝቻለሁ:: የህዳሴ ግድቡ እንዳይጎበኝ በግብፁ ሚኒስትር የቀረበው ጥያቄ ትርጉሙ ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ንቀት ማሳያ ነው፤ እኛ መጋበዝ መብታችን እንደሆነ ሁሉ እነርሱ ደግሞ የኢትዮጵያን ግብዣ መቀበል አለመቀበል መብታቸው ነው:: በመጀመሪያም ቢሆን ዓባይ ግድብን እንዲጎበኝ የጋበዝነው እኛ እንጂ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አይደለም:: ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ኢንሼቲቩ መብት የለውም በሚል ሃሳባችንን ቋጭተናል::

በጣም የሚያሳዝነው የግብፁ ሚኒስትር የአትጎብኙ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ አንድም ሀገር ያልተቀበለ መሆኑ ነው:: ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው:: ግብፃውያን በእኛ ሜዳ ለመጫወት ፈልገው በራሳቸው ላይ ግብ ማስቆጠራቸው የአደባባይ ምስጢር ለመሆን ችሏል:: ይህ ማለት አላስፈላጊ ጥይት ተኩሰው እራሳቸውን እንደማቁሰል የሚቆጠር ነው:: እኔ የሚገባኝ በዚህ ልክ ነው:: ሱዳን ስላልመጣች ምርጫዋ የቱ እንደሆነ ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም::

አስገራሚው ነገር እንዳትሔዱ ብለው ያሏቸው ሚኒስትሮች ወደ ዓባይ ግድብ የሔዱት እንዲያውም በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው:: በሚኒስትር ደረጃ የሆኑ ለስብሰባው የመጡት በሙሉ ግድቡን ጎብኝተዋል:: የታንዛኒያው የውሃ ሚኒስትር በሀገራቸው አስቸኳይ የምርጫ ጉዳይ ገጥሟቸው ከመሄዳቸው በስተቀር ሁሉም ወደ ዓባይ ግድብ አቅንተዋል::

ሚኒስትሮቹ ዓባይ ግድብ ከደረሱ በኋላ የነበራቸው አግራሞት በግልጽ የሚታይ ነበር:: ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረው ወሬ እና መሬት ላይ ያዩት እውነታ አስደንቋቸዋል:: ያንን የሚያክል ግድብ ኢትዮጵያ መገንባት መቻሏ እንደ ተዓምር የሚቆጠር ነው የሚል አስተያየት ነበራቸው::

አንደኛ የግድቡ መጠን ከጠበቁት በላይ ሆኖባቸዋል:: ስፋቱና የውሃ መጠኑ አስደምሟቸዋል:: ከምንም በላይ የሥራው ጥራት ትንግርት ሆኖባቸዋል:: ትልቁ ስኬት ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን ለመገንባት ስትል የተጋፈጠችው ፈተና ያለፈችበት ብልሃት የሚያስደነቅ እንደሆነ ገልጸዋል::

አንዳንዶቹ እንዲያውም ሲናገሩ የነበረው ነገር ተመልሰን ሀገራችን ስንሔድ እንዴት አድርገን ነው በሀገራችን ላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክት የምንቀርጸው? በሚል ቁጭት ነው:: ስለዚህ ግብፆች ያደረጉት ዘመቻ መልሶ የጎዳው እነርሱኑ እንጂ ኢትዮጵያን አይደለም::

በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ እንዳልኩሽ ለሥልጠና የመጡ ጋዜጠኞች ነበሩ:: ስፖንሰር ያደረጋቸው ድርጅት፣ ጋዜጠኞቹን ህዳሴ እንዳይወስዳቸው በግብፆቹ አማካይነት የድርጅቱ እጅ ተጠምዝዞ ጋዜጠኞች ሊቀሩ ችለዋል:: እነዚያ ጋዜጠኞች ወደ 22 አካባቢ የሚጠጉ ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ በእኛ ግብዣ ስምንቱ ወደ ህዳሴ አብረውን ሔደው ጐብኝተዋል:: ግድቡን ባዩት ጊዜም ተገርመዋል:: በዚህም የተሳካ ጉብኝት ነበር ማለት ይቻላል::

በወቅቱ የዑጋንዳ የውሃ ሚኒስትር፣ የኬንያው የውሃ ሚኒስትር፣ የደቡብ ሱዳን የውሃ ሚኒስትር ነበሩ፤ በወቅቱ በሀገራቸው በአጋጠማቸው አጣዳፊ ሥራ ምክንያት የታንዛንያው የውሃ ሚኒስትር ወደሀገራቸው ከመመለሳቸው በስተቀር ሌሎቹ የውሃ ሚኒስትሮች ህዳሴን ጎብኝተዋል:: እንደሚታወቀው ሲያከላክሉ የነበሩት የግብፁ የውሃ ሚኒስትር ወደጉብኝቱ ስፍራ ለመሔድ ፈቃደኛ አልነበሩም::

ግድቡን ገና እንዳዩት የብዙዎች ስሜት የአድናቆት ሲሆን፣ ግብፆች ሲያራግቡት የነበረው ፕሮፓጋንዳ ሐሰት መሆኑን ተገንዝበዋል፤ ስም መጥራት ባያስፈልገንም አንዳንዶቹ ሚኒስትሮች ይናገሩ የነበረው በንዴት ውስጥ ሆነውም ጭምር ነበር:: ይህን መሬት ላይ ያየነውን ጉዳይ ለየሀገሮቻችን መሪዎች ብንገልጽላቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት ይቻላል ሲሉም ሲናገሩ ነበር::

ምክንያቱም ውሃ ከሚጠበቀው በላይ ይሄድላቸዋል:: ያውም ወጥ የሆነ እና ለልማት በሚመች መልኩ ሊጠቀሙበት የሚያስችላቸው የውሃ ፍሰት ነው:: ቀደም ሲል ከነበረው በሦስትና በአራት እጥፍ ሲሔድላቸው ለግብፆችም ለሱዳኖች በረከት ነው:: ሁለቱም ኢትዮጵያ በገነባችው ግድብ መስኖን በመጠቀምም ከፍተኛ እርሻ ማስፋፋት ይችላሉ::

ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው ክረምት በገባ ቁጥር ሱዳንን የጎርፍ ስጋት ሁሌም ያስጨንቃት ነበር:: ይህን ሁለት ዓመት ግን እንደዚያ አይነት የጎርፍ ስጋት አጋጠመን ሲሉ አልተደመጡም:: እንዲያውም ባለፉት ሁለት ዓመት የዝናቡ መጠን ጨምሯል፤ ይሁንና የተፈራው ጎርፍ አልነበረም:: ስለዚህ ጎርፍን ሊከላከል የቻለው የእኛ ግድብ ነው:: ሊደርስባቸው የነበረው ቀውስ በዓባይ ግድብ አማካይነት ሳይደርስባቸው ቀርቷል:: ይህ ትርፋቸው ነው:: ለግብፆቹ ሰፊ የውሃ መጠን ይሄድላቸዋል:: ስለዚህም ተጠቃሚ እንደሆኑም በሰፊው በጉብኝቱ ወቅት ገለጻ አድርገንላቸዋል::

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትሮቹ ከሰማይ በታች፤ ከምድር በላይ አለኝ የሚሉ ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ ጠይቀው ምላሽ ተሰጥቶበታል:: ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሚመለከታቸው አካላት ስለነበሩ ሁላችንም ለጠየቋቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ሰጥተናቸዋል:: በዚህም ትልቅ እምነት አድሮባቸውና ግልጽነት ተፈጥሮላቸው ወደመጡበት ተመልሰዋል:: በመሆኑም ጉብኝቱ በኢትዮጵያ በኩል በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ ግልጽነት የፈጠረችበት ሲሆን፣ ለግብፆች ደግሞ ትልቅ ኪሳራ ያጋጠማቸው ጊዜ ሆኖ ጉብኝቱ አልፏል ማለት ይቻላል::

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ በተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የመጎብኘቱ ፋይዳ ምንድን ነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አንዱ ፋይዳ ከዚህ ቀደም ግብፆቹ ሲያራግቡት የነበረውን ፕሮፖጋንዳ ብዙዎቹ ያዳምጧቸው ነበር:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ነገር ትክክል ነው ብሎ ለመናገር መተማመኛ አልነበራቸውም:: አሁን ግን በዓይናቸው አይተው አረጋግጠዋል:: ምክንያቱም የዓባይ ግድብ ግብፆችን እንደማይጎዳቸው በቦታው ተገኝተው አጢነዋል:: በተጨባጭ በቁጥር እና በመረጃ አስደግፈን ስለሁኔታው ሁሉ አስረድተናቸዋል:: ስለዚህም ኢትዮጵያን ደጋፊ አካል አገኘን ማለት ነው::

ሁለተኛው ፋይዳ የዓባይ ግድብን የጎበኙ ስምንቱ ጋዜጠኞች በተለያየ ስፍራ ሆነው ስለህዳሴ ግድቡ ሲዘግቡ ካዩት እውነታ ጋር መጣላትን አይፈልጉም:: ምክንያቱም የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር የተላበሰ ጋዜጠኛ ከእውነታው አይሸሽም::

ሦስተኛ ፋይዳ ደግሞ ለእኛም ለሌሎችም የሚሠራ ነው፤ እንደሚመስለኝ ከኢትዮጵያ ልምድ አግኝተዋል:: የመጡት ሚኒስትሮች በሙሉ የፖለቲካ አመራር ናቸው:: ኢትዮጵያ የሄደችባቸውን መንገድ ስንነግራቸው ብዙዎቹ ትልቅም ባይሆን መሰል ፕሮጀክት ለመጀመር እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ነበር:: ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ በቀጣይ ተመሳሳይ ሥራ ለሚሠሩ የተፋሰሱ ሀገራት ልምዷን ለማካፈል የሚያስችል ዕድል ይፈጥርላታል:: .

አዲስ ዘመን፡- ሚኒስትሮቹ በሰነድ ደረጃ ሲያውቁት የነበረውን የዓባይ ግድብ በተጨባጭ በተግባር ሲያዩት የነበራቸው ስሜት ምን ይመስል ነበር?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ስሜታቸውን በግልጽ ተናግረዋል:: ለምሳሌ የቴክኒካል አድቫይዘሪ ኮሚቴ (Technical Advisory Committees) አባላት የተውጣጡት ከሁሉም ሀገራት ነው:: በእርግጥ ግድቡን በፊትም ያውቁታል፤ ነገር ግን አሁን ላይ መሬት ላይ ሲያዩት ግድቡን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል በጣም የሚገርም ነው:: ያሉት “ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ነው፤ የኢትዮጵያ ክብር የአፍሪካም ኩራት ነው::›› ሲሉ ስሜታዊ ሆነው ተናግረዋል:: ‹‹በአግባቡ ከውናችሁታል፤ በእናንተ ኩራት ይሰማናል” በማለት ስሜታቸውን አጋርተውናል::

ሌሎቹ ደግሞ “ኢትዮጵያ ሁሌም መሪ ናት፤ እናንተ ኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያን መገንባት ከጀመራችሁ ቆይቷችኋል” ሲሉ ተናግረዋል:: ከዚህ የተነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን የት እንዳለንና አቅማችን የት እንደደረሰ እንዲሁም በራስ መተማመናችንን የተረዱበት ጉብኝት ነበር ማለት ይቻላል:: የተሰማቸውን ስሜት ለሀገር ውስጥና ይዘዋቸው ለመጡ ለየራሳቸው መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል:: ጋዜጠኞቹም በተመሳሳይ የራሳቸውን አዎንታዊ አስተያየት አጋርተዋል:: በጥቅሉ “የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ፤ “ምክንያቱም ሕልማችሁን አሳክታችኋል” ብለዋል::

ከምንም በላይ በዓባይ ግድብ ላይ የተካሔደው ጉብኝት በኢትዮጵያ ተቃራኒ የቆመውን አካል ያሽመደመደ ነው:: በሌላ ጊዜም በተለይ ግብፅ የምትናገረውን ንግግር አስባበት እንድታደርግ ያደረገም ጭምር ነው:: ብዙዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች፤ የግብፁ ሚኒስትር እንዳይጎበኙ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ የመሔድ ተነሳሽነታቸው ጨምሮ መሄዳቸውንም ተናግረዋል::

ለጉብኝቱ ወደስፍራው ሊያደርሱ የሚችሉ ሁለት አውሮፕላኖች ብቻ ተከራይተን ነበረ፤ ከግብፅ ጥሪ በኋላ ግን የመጐብኘት ፍላጎቱ በመጨመሩ ምክንያት ሦስተኛ አውሮፕላን መጨመር ግድ ብሎናል:: ምክንያቱም ቀደም ሲል እኛ አስበን የነበረው ሃያ ሰው ይጎበኘዋል በሚል ቢሆንም፤ ‹እንዳትጎበኙ›› የሚለው ጥሪ ከተላለፈ በኋላ የሰዎች ቁጥሩ ወደ30 ከፍ በማለቱ ሌላ ተጨማሪ አውሮፕላን መከራየት ግድ ብሎናል:: ስለዚህ በአንደኛው አውሮፕላን ውስጥ ያለው ቡድን ከግብጽ ጥሪ በኋላ ለመጎብኘት የመጣ ነው:: ስለዚህም ግብፃውያን ነጥብ ጥለው ሄደዋል::

አዲስ ዘመን፡- የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ሕግ ከሆነና በኮሚሽን ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለአፍሪካ ኅብረት እንደመሆኑ በጉባኤው ወቅት የመጣ አዲስ ነገር ይኖር ይሆን?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- እንደተባለው የትብብር ማሕቀፉ ከፀደቀ በኋላ የስድስቱ ሀገሮች ሕግ ነው:: ስለዚህ ኮሚሽኑ ይኖራል ማለት ነው:: ከዚያ በኋላ ዑጋንዳ ላይ የሀገር መሪዎች ይሰበሰቡና ኮሚሽኑን ያፀድቁታል፤ ኮሚሽኑ ተቋም ይሆናል::

በአሁኑ ወቅት ስንሰበሰብ የምንባለው የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ ነው:: ኢንሼቲቭ ማለት ደግሞ በፈቃደኝነት ተሰብስበን የምናወራበት መድረክ እንጂ አስገዳጅ የሆነ ሕግ የለውም:: የትኛውም አካል እንደፈለገው መናገር ይችላል:: ግብፆችም የሚፈነጩት ለዚህ ነው:: ኮሚሽን ከሆነ በኋላ ግን ሰው ሥርዓት ይይዛል:: እኛም ሆንን ብዙዎቹ ይህንን ስለምንፈልግ ሕግ አድርገነዋል፤ እንቀጥልበታለን::

ይህ ጉዳይ የሚፀድቀው በሀገር መሪዎች ነው:: ይህን ደግሞ የሚያደርጉት የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ናቸው:: በአሁኑ ሰዓት እርሳቸው ያሉት ለቀሩ ሀገራት ትንሽ ጊዜ ሰጥተናቸው እንያቸው ነው:: ይህ ደግሞ ተገቢ ሐሳብ ነውና በዚሁ ረገድ ኮሚቴ ተቋቁሟል:: የደቡብ ሱዳን፣ የቡሩንዲና የዑጋንዳ ሚኒስትሮች የቀሩትን ሀገራት እንዲያናግሯቸው ጊዜ ተሰጥቷል::

ያልፈረሙት ግብፅ፣ ሱዳንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው:: እነዚህን ለማግባባት ጥረት እየተደረገ ነው:: በወቅቱ የሰጠናቸው ጊዜ ዘጠኝ ወር ነው:: አሁን የቀረው አምስት ወር ያህል ነውና በፍጥነት የማግባባት ሥራ እንዲሠራ ቀጠሮ ተይዟል::

ጎን ለጎን ግን የፈረምን ስድስቱ ሀገራት ሮድማፕ እየሠራን ነው:: የእኛ ሥራ ኮሚሽኑን ማቋቋም ነው:: ስለዚህ አሁን ካለው ከናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ ወደ ናይል ሪቨር ኮሚሽን ሲሸጋገር እንዴት ይሆናል? ገንዘብ፣ የሰው ኃይል አለና እሱን የመሥራት ሥራ ጀምረናል:: እናም ኮሚቴ አዋቅረናል:: በመጨረሻ የማግባባት ሥራ እየሠራ ያለ ኮሚቴ ሥራውን አጠናቅቆ ሲያመጣ ስድስታችን አካሄዳችንን እየገመገምን የምንሔድበት ይሆናል::

ግብፆቹ ይህን አካሔድ አምርረው ይጠሉታል:: በግልጽም ተቃውመውታልም:: እኛ እስከምንመጣ መነጋገር የለባችሁም ይላሉ:: ይሁንና በጊዜ ወስነው መምጣት የራሳቸው ድርሻ ነው እንጂ መቃወም አይችሉም:: ኮሚሽን ከሆነ በኋላ ድምፅ አይኖራቸውም:: መናገርም አይፈቀድላቸውም፤ ሊሆኑ የሚችሉት ተሳታፊ ብቻ ነው:: የመወሰን ሥልጣን አይኖራቸውም:: በአሁኑ ሰዓት እንደሚበጠብጡት ዓይነት አካሔድ አይኖርም:: ሥርዓት ይይዛሉ:: ኬንያውያን ግን የቀራቸው ትንሽ ነገር ነው፤ ፈርመውታልም፤ እነርሱ የበለጠ ተስፋ አላቸው::

አዲስ ዘመን፡- ከዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ህዳሴ ሌላ ህዳሴን ይወልድ ይሆን?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ለእኛ ከዓባይ ግድብ ላይ ያገኘነው ትምህርትና ልምድ በጣም ትልቅ ነው:: አንዱ እና የመጀመሪያው ጉዳይ የመፈጸም አቅም፣ ብቃትና ችሎታ ማግኘት መቻላችን ነው:: ይህ የሆነው በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው::

ህዳሴው ሲያልቅ የሚይዘው ውሃ በጣም ትልቅ ነው:: የፈጠረው ሐይቅ ከፍተኛ ነው:: በሐይቁ ላይ ዓሣ ማምረት ይቻላል፤ እየታሸገም ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው:: ቱና የሚመጣው ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሪ ነው:: በዚህ ዙሪያ በሥርዓት ለመምራት የተጀመረ ሥራ አለ:: ሌላው በሐይቁ ከ70 በላይ የሆኑ ደሴቶች አሉ:: እነዚህ ደሴቶች የቱሪስት መስሕብ ይሆናሉ:: በተጨማሪም የውሃው ርዝማኔ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ ነው:: በዚህ ላይ የትራንስፖርት አቅርቦት መፍጠር ይቻላል:: በዚህ ዙሪያም እቅድ አለን:: የተለያየ መዝናኛዎችም ይኖራል::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም ያላት ነች:: በህዳሴ ልምድ በማግኘታችን ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉ የተለዩ ቦታዎች አሉ፤ ለምሳሌ ዳቡስ ወንዝ ላይ እና ዴዴሳ ወንዝ ላይ እንዲሁም በዓባይ ወንዝም አካባቢ የተለዩ ቦታዎች አሉ:: በቀጣይ የሚኬድበት ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድልንና የዓባይ ግድብን የሚያያይዛቸው ምንድን ነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የዓድዋ ድልና ህዳሴ የአንድነት ተምሳሌት ናቸው፤ ሁለቱም የኢትዮጵያውያን አንድነት የተረጋገጠባቸው ናቸው:: ዓድዋ ላይ እንደ አሁኑ ጊዜ ቴክኖሎጂ አልነበረም:: ተንቀሳቃሽ ስልኩ፣ ኢንተርኔቱ እና ሌላ ሌላው አልነበረም:: እንዲያም ሆኖ ከጥግ ጥግ ንቅናቄ በመፍጠር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሕዝቡ መንቀሳቀስ ችሏል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ የእኔ ናት ብሎ ስለሚያምን ኅብረቱን አሳይቷል:: በወቅቱ ሕዝቡ የራሱ የሆነና እንዲፈታለት የሚፈልገው ችግር ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቅም ነበር::

ህዳሴም በተመሳሳይ የሚጠቀስ ነው:: የዓባይ ግድብ በየትኛውም ክልል ሆኖ የትኛውም ቀበሌ ውስጥ ያለ ሰው ህዳሴ ሲባል አንዳች የአንድነትና የመተባበር መንፈስ ውስጡ እንዳለ ይታወቀዋል:: የእኔነት ስሜቱ የጎላ ነው:: ምክንያቱም ከሌለው ነገር ላይ ለዓባይ ግድብ አቋድሷል:: ሕዝቡ ዓድዋ ላይ እራሱ አሊያም ልጆቹን ወደግንባር እንደላከ ሁሉ ለዓባይ ግድብም እንዲሁ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሀብቱ ተሳትፏል:: ስለዚህ ዓድዋና ህዳሴ የአንድነት ማሳያ ናቸው:: የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማሰሪያ እና ምልክት ናቸው::

ሌላው ጉዳይ የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ የውጭ ጫና የፈተናቸውና የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተረጋገጠባቸው ታላላቅ ስኬቶች ናቸው:: ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የተዋጋችው አንድን ሀገር ብቻ አይደለም:: በወቅቱ ከጣሊያን ጋር ኅብረት ከፈጠሩትና የቅኝ ግዛትን ማስፋፋት ከሚፈልጉት ጋር ሁሉ ነበር:: ኢትዮጵያ በወቅቱ ያሸነፈችው የተነሱባትን ኃይሎች ሁሉ ነው::

ስለዚህ ይህ ትልቅ ስኬት ነው:: የዓባይ ግድብን በተመለከተ ደግሞ እኛን ስትገዳደረን የነበረችው ግብፅ ብቻ አይደለችም:: ኢትዮጵያ በድኅነቷ እንድትዘልቅ የሚፈልጉ ኃይሎች ጭምር ናቸው:: ይሁንና ኢትዮጵያ ማሸነፍ የቻለችው ሁሉንም ነው:: ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ምክንያት በፀጥታው ምክር ቤት ስትወሰድ ዓላማው ኢትዮጵያን በዚያ ደረጃ ማብጠልጠል ነበር:: ስለዚህ በኢትዮጵያ ጥንካሬ እሱን ወደ አፍሪካ ኅብረት መመለስ መቻል ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: ስለዚህ በዓድዋ ጊዜ በውጊያ የነበረው የቅኝ መግዛት ሕልም ኢትዮጵያ እንዳጨናገፈች ሁሉ፤ አሁን ደግሞ በኢኮኖሚው በኩል በቅኝ ለመግዛት የተቋመጠውን አካሔድ ኢትዮጵያ ያሽመደመደችው መሆኑ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ነው::

በሌላ በኩል ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ነገር ዓድዋ ላይ ሰው የዘመተው ባለው አቅም ነው:: ይህም ሲባል በጦር፣ በጎራዴና በእጁ ላይ በሚገኘው መሣሪያ ጭምር ነው:: በተመሳሳይ ህዳሴንም ኢትዮጵያዊ የገነባው ከተረፈው ነገር ላይ አይደለም:: የትኛውም አካል ኢትዮጵያን ሳያግዛትና ድጋፍ ሳይደርግላት በመንግሥቷና በዜጎቿ የተሠራ ግድብ ነው:: ይህ ትልቅ ስኬት ነው::

በጣም ወሳኙ ጉዳይ በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ታሪክ ዛሬ ያመጣነውን ስኬት በአንድ ጀምበር ያመጣነው ጉዳይ አለመሆኑ ነው:: ስኬቱ የመጣው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው:: በዚህ ስኬት ውስጥ የመሪዎች ቅብብሎሽ አለ:: ንጉሡ ዓፄ ኃይለሥላሴ አንድ የአሜሪካ ኩባንያ ቀጥረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ግድቦችን ካስጠኑ በኋላ ለዓለም ባንክ ብድር እንዲሰጣቸው ቢያቀርቡም ‹‹እኛ ብድር ሰጥተናችሁ ግድቡን ከምትገነቡ እናንተን በስንዴ ብናግዝ ይሻላል፤ ምክንያቱም እኛ ግብፆችን ማስቀየም አንፈልግም::›› የሚል ዓይነት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል::

በወቅቱ ደግሞ በዓለም ባንክም በአፍሪካ ባንክም በጥቅሉ አበዳሪ በሚባሉት ደረጃ ባሉ ውስጥ ግብፆች ተሳትፎ ያደርጋሉ:: ዓፄ ኃይለሥላሴም ‹‹አንድ ቀን ኢትዮጵያውያን ይገነቡታል›› በሚል ጽናት አልፈውታል፤ ምክንያቱም ቦታው ቢጠናም አቅም ባለመኖሩ የጀመሩትን ማሳካት አልቻሉም:: ሊያሳካ የሚችል ትውልድ እንደሚመጣ ግን እርግጠኛ ነበሩ::

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደሥልጣን ሲመጡ በአዎንታዊም በአሉታዊም የሠሯቸው ነገሮች አሉ፤ ከሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ግን አንድ መደነቅ የሚገባው ነገር ቢኖር “እኛ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረንም አቅም ሳይኖረን መጠቀም ያስቸግራልና የሰው ኃይል ላይ መሥራት ይጠበቅብናል” በሚል በአርባ ምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂን አቋቁመዋል:: ይህ ደግሞ ወሳኝ ነው::

የውሃ ሀብት ስላለ ብቻ ሥራ ሊሠራ አይችልም በሚል የውሃ መሐንዲስ፣ የመስኖ መሐንዲስ፣ የመጠጥ ውሃ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግ መሐንዲስ አምስት ዓመት ውሃ ላይ ብቻ በማተኮር መማር እንዲቻል ተፈልጎ የአርባ ምንጩ ከፍተኛ ተቋም ተከፈተ፤ ዛሬ ላይ እኔን ጨምሮ የዚያ ተቋም ምሩቃን በርካታ ነን:: ይህ እውነቱን ለመናገር ትልቅ ስኬት ነው::

በኢሕአዴግ ዘመንም በተመሳሳይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ሕዝቡን በማስተባበር የዓባይ ግድብ እንዲጀመር ማድረግ በመቻላቸው ትልቅ ስኬት ነው:: የጋራ ስምምነቱን ተፈጻሚ ማድረግ የተቻለው ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሠሩት ሥራ ነው፤ ሦስቱ ሀገራት ለስምምነት የተጨባበጡት በእርሳቸው ጊዜ ነው:: ሦስቱ ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ተፈራርመው ህዳሴን ህዳሴ እንድናደርግ የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል::

ህዳሴ በመሐል የራሱ ችግር ነበረበት፤ በመሐል ላይ ተስተጓጉሎ ነበር:: እሱ ችግር ተፈትቶ ህዳሴ ህዳሴ እንዲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በየቀኑ የሚያደርጉት ክትትል እንደ አንድ ፕሮጀክት ብቻ የሚታይ አይደለም፤ በየዕለቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ክትትል የሚደረግበት ፕሮጀክት ነው:: የተበላሸን አስተካክሎ ማስፈጸም መቻል በመሪ ቅብብሎሽ የመጣ ሥራ ነው:: ይህ ትልቅ ትምህርት የሚሰጠን አሠራር ነው::

ዓድዋም እንዲሁ ነው:: በሁሉም ነገር ላይ ከተባበርን ብዙ ማድረግ ይቻላል፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን ፈጽመውታል፤ ዛሬም ማድረግ ይቻላል:: ስለዚህ ህዳሴና ዓድዋ የአንድነት ማሠሪያ ናቸው፤ የቁጭትም ማሳያ ናቸው:: ሁለቱም የውጪው ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አመለካከት ያኮላሹ ናቸው:: በዓድዋ ላይ የተገኘው ስኬት የቅኝ ገዥዎችን አስተሳሰብ ያመከነ ነው፤ ህዳሴ ላይ ግብፅና ግብረአበሮቿ ጭምር የተሸነፉበት ስኬት ተመዝግቧል:: ስለዚህ ሁለቱም በብቃት የተጫወትንባቸው ሜዳዎች ሲሆን፣ ጠላትን በዝረራ ከጨዋታ ወጪ ያደረግንበትን ስኬት ያስመዘገብንባቸው መለያችን ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ::

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You