አጽዋማቱ በሚፈልጉት ሥብዕና ውስጥ እንገኝ ḷ

ጾም ማለት ሰውነትን ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ መከልከል፣ ለሥጋ የሚመቸውን ነገር መተው ማለት ነው። በማንኛውም እምነት የጾም መሠረታዊ ዕሳቤዎች ከሚባሉት ውስጥ መፋቀር፤ መዋደድ ፤ መረዳዳት እና መተዛዘን ተጠቃሾች ናቸው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአዋጅ ከሚጾሙት 7ቱ አጽዋማት አንዱና ትልቁ ዐብይ ጾም ይባላል። ይህ ጾም ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ኢየሱስ ፣ ጾመ ሁዳዴ ፣ አርባ ጾም በመባል ይታወቃል ።

የእምነቱ አባቶችና ቅዱስ መጻህፍት እንደሚያስረዱት ዐብይ ጾም መባሉ ትልቅና ታላቅ ጾም መሆኑን ለማሳወቅና አምላካችን ለሰዎች በመጀመሪያ አብነት ለመሆን የጾመው ስለሆነና በቁጥርም ከሌሎች አጽዋማት በቁጥርም ከፍ ስለሚል ነው።

ጾመ ኢየሱስ መባሉ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ጾመ ኢየሱስ ተብሏል (ማቴ ፬᎓፩)፤ሁዳዴ ጾም መባሉ ይህ ስያሜ የወጣው ሁዳድ ከሚለው ሲሆን ሁዳድ ማለት ሰፊ የእርሻ ቦታ ማለት ሲሆን ዐብይ ጾምም የሥላሴን ልጅነት ያገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ሰፊና ትልቅ ወደሆነው ካገኙት የማያጡት ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ ሁሉም ምዕመን የሚጾመው ጾም በመሆኑ አባቶቻችን ጾመ ሁዳዴ ብለው ሰይመውታል።

በተመሳሳይም በእስልምና ኃይማኖት ረመዳን የተቀደሰ የጾም ወር ነው። ከእስልምና እምነት አምስቱ መሠረቶች ውስጥም አንዱ ነው። በረመዳን ወር ሙስሊሞች በሙሉ የስጋ አምሮታቸውን ወደ ጎን በመተው ለነፍሳቸው የሚጠቅማቸውን ተግባራት የሚፈጽሙበት ጊዜ ነው።

በአሁኑ ወቅት የሁዳዴ ጾም በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ እየተጾመ ነው። የረመዳን ጾምም ተይዟል። የእነዚህ ሁለት ታላላቅ ጾሞች በአንድ ላይ መግባት ለኢትዮጵያውያን ትልቅ በረከት እና እድል ነው። በተለይም እነዚህ ሁለት ታላላቅ ጾሞች የሚያዟቸውን ሰናይ ተግባራት መፈጸም ከቻልን ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ታላቅ በረከት ማግኘት እንችላለን።

በየትኛውም ኃይማኖት ከሚታዘዙ በተለይም በጾም ወቅቶች በጥብቅ እንዲተገበሩ ከሚፈለጉ ተግባራት ውስጥ አንዱ እርስ በእርስ መፈቃቀር እና መዋደድ ነው። ሁሉም ኃይማኖቶች መፈቃቀር እና መዋደድን አጥብቀው ያዛሉ፤ እንዲተገበሩም ይወተውታሉ።

ስለዚህም በጾም ውስጥ የሚገኙ አማኞች እርስ በእርስ መፈቀርን እና መዋደድን አብዝተው ሊተገበሩ የሚገባቸው ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ፍቅር እና መዋደድ ያስፈልጋታል። ሰላም ለራቃት ሀገራችን ብቸኛው መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው እርስ በእርሳችን በምንለዋወጠው ፍቅር እና መዋደድ ብቻ ነው።

በብሄር ፣ በኃይማኖት እና በተለያዩ ልዩነቶች ውስጥ ተዘፍቀን አንዳችን ለአንዳችን ችግር ከመሆን ወጥተን ፍቅር በመለዋወጥ የራቀውን ሰላማችንን ልናቀርበው ይገባል። በአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያ ፍቅር ርቋታል፤ ሰላሟ ደፍርሷል፤ አብሮነት ደንዝዟል፤ መለያየት ነግሷል። ስለዚህም እነዚህ እኩይ ተግባራት ሊወገዱ የሚችሉት ደግሞ በፍቅር እና በመዋደድ ብቻ ነው። ስለዚህም በእነዚህ ታላላቅ ጾሞች ወቅት አብሮነታችንን ለመመለስ፤ አንድነታችንን ለማጽናት፤ ሰላማችንን ለመመለስ ፍቅር መለዋወጥ ያስፈልገናል። ይህ ሲሆን የጾሙን በረከት እናገኛለን፤ ሰላማችንንም እንጎናጸፋለን።

በጾም ወቅት ልንተግብራቸው ከሚገቡ ተግባራት ውስጥ መረዳዳት እና መደጋገፍ ዋነኛውን ሥፍራ ይይዛሉ። ኢትዮጵያውያን ዘር ፤ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው።

ስለዚህም ይህ አኩሪ በህላችን በእነዚህ ታላላቅ የጾም ወቅቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በአሁኑ ወቅት ልንደርስላቸው እና አለሁ ልንላቸው የሚገባን በርካታ አቅመ ደካሞች በየቦታው አሉ። ስለዚህም ያለንን ማቋደስ እና ወገንተኝነትን ማሳየት በእነዚህ የጾም ወቅቶች የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው።

ከ98 በመቶ በላይ አማኝ የሆነው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን በማካፈል ያምናል። ሰዎች ሲቸገሩ የሚጨክን አንጀት የለውም። ከመሶቡ ቆርሶ፤ ከኪሱ ቀንሶ ያለውን ይሰጣል። የእርሱ ቤት ደምቆ የጎረቤቱ እንዲቀዘቅዝ አይፈቅድም። ይህም አኩሪ ባህል ኢትዮጵያውያን በችግር እንዳይንበረከኩና ችግርን ድል አድርገው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ይህ የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም በአጽዋማት ወቅቶች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ቀድሞ ሲደረጉ ከነበሩ ተግባራት ወጣ በማለትም ከእለት ጉርስ ባለፈ ዘላቂ ድጋፍ በሚያስገኙ ተግባራት ውስጥ መሳተፍ ሊለመድ ይገባል።

ለአብነት በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የማድረግ ሥራዎች በጾም ወቅቶች ቢዘወተሩ ዘላቂ የሆነ ዐሻራ ትቶ ማለፍ ይቻላል። በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው። አሁን ደግሞ በጾም ወቅቶች በአዲስ መልኩ ቢጀመሩ በቀላሉ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ ማድረግም የአጽዋማቱ መገለጫ ሊሆኑ ይገባል። ያለምንም የእምነት ልዩነት የተቸገሩ ሰዎች በአንድነት ማዕድ እንዲቆርሱ ቢደረጉ አብሮነታችን ያብባል፤ ኢትዮጵያዊነት ይደምቃል። በተጓዳኝም ከጾም በረከት ተቋዳሽ ያደርጋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከመረዳዳትና ከመደጋገፍ ውጪ መገለጫም የላቸውም። ኢትዮጵያም ቆማ መቀጠል የቻለችው ዜጎቿ በሚከውኗቸው መልካም ተግባራት ነውና በሁዳዴም ሆነ በረመዳን የጾም ወቅቶች ይህ አኩሪ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ኢትዮጵያዊነት ባለብዙ ቀለማትና ባለብዙ ፈርጅ ሆኖ ትናንትን ተሻግሮ ለዛሬውም ትውልድ ኩራትና ድምቀት ሆኗል። ኢትዮጵያዊነት ሲታሰብ መረዳዳት፤ እንግዳ ተቀባይነት፤ ጀግንነት፣መስጠት፣ደግነት፣መከባበር ፣ ለሀገር እና ወገን እራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የዘለቀ ምስጥር ነው።

ታላቅን ማክበር ፣ ለታናሽ ማዘን፣ የተቸገረን መርዳት፣ የታመመን ማስታመም፣ የሞተን መቅበር፣ የታሰረን መጠየቅ፣ ኀዘንተኛን ማስተዛዘን፣ የህጻናትን ባህሪ በጋራ ማረቅ፣ ሌብነትን መጠየፍ፤ የመሳሰሉት አኩሪ እሴቶችንም የያዘ ነው። እነዚህ አኩሪ እሴቶችም የእኛነታችን መለያ ሆነው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል። እነዚህ ሰናይ ተግባራትም በሁዳዴ እና በረመዳን የጾም ወቅቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You