
ወቅቱ ኢምፔሪያሊስት አውሮፓ በመላው ዓለም የሚገኙ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ተቀራምተው ለመግዛት የተንቀሳቀሱበት ነው:: አውሮፓውያኑ አፍሪካን በመካከላቸው ያለምንም ግጭት እና ደም መፋሰስ ተቀራምተው በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ አጀንዳ ቀርፀው በ1884/85 ዓ.ም የበርሊን ኮንፈረንስን ተሰብስበው ውሳኔ አሳልፈዋል።
በጊዜው ሜዲትራኒያን እና ቀይ ባሕርን በማገናኘት ግዙፉን የዓለም ንግድ መስመር ያሳጠረው በ1869 የስዊዝ ካናል መከፈት መልካም አጋጣሚ ነበር። ጣሊያን ዋና ዋና ኢምፔሪያሊስት ሀገራት የሚባሉትን እንግሊዝን እና ፈረንሳይን በማግባባት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ የጀመረችበት ወቅት ነበር::
ጣሊያን ዓላማዋን ለማሳካት ወደ ቀይ ባሕር አካባቢ በመግባት ለመጀመሪያ ግዜ ሩባቲኖ ሽፒንግ ካምፓኒ በሚባል የነዳጅ ኩባንያ ያቋቋመች ሲሆን ወደ አካባቢው ማሽነሪዎችን እና ነጋዴዎችን በመላክ እንቅስቃሴዋን ጀመረች:: በመቀጠልም በቀይ ባሕር በኩል ወደ ኤርትራ ብሎም ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃ መግባት ችላለች:: ሕዝቡን ስለ ቅኝ ግዛት ጠቀሜታ በመስበክ እና በመሪዎቹ መካከል ደግሞ ግጭትን በማባባስ እና የጦር መሣሪያ በማቀበል ርስ በርስ እንዲዋጉ ታደርግ ነበር::
በጣሊያን እና ዳግማዊ ምኒልክ መካከል ሁለት ስምምነቶች የተፈረሙ ሲሆን ዓላማቸውም የነበራቸውን ግንኙነት ለማተኮር ነበር:: የመጀመሪያው ስምምነት አንኮበር ላይ የተፈረመው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የውጫሌ ውል ነበር::
የውጫሌ ውል ለግጭቱ በጊዜያዊ መንስኤነት ሊወሰድ የሚችል ነው። በተለይ ደግሞ የዚሁ ውል አንቀፅ 17 ትርጓሜ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የበላይ ጠባቂነት ሚና እንዲኖራት የሚያደርግ ትርጓሜ ያለው ነበር። ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ እንዲሆን በመደረጉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ግጭት በመፍጠሩ ምክንያት ወደ ጦርነት አመራ::
በኢትዮጵያ በኩል ዳግማዊ ምኒልክ የጣሊያኖቹን ፍላጎት ከተገነዘቡ በኋላ በጣም በርካታ የታጠቀ ኃይልን ከመላው ኢትዮጵያ አሰባስበዋል። እንዲሁም በርካታ የአካባቢ መሪዎች እና በሥራቸው የነበሩ ሠራዊት በማሰባሰብ ለጦርነቱ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ::
በሌላ በኩል የጣሊያን ወታደሮች በጀኔራል ኦርስት ባራቴሪ እየተመሩ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘልቀው በመግባት ከሚሴ አካባቢ መድረስ የቻሉ ሲሆን በተወሰኑ ቦታዎችም የታጠሩ ምሽጎችን አዘጋጅተው ሊመሽጉ ችለዋል::
ይሄንንም የተገነዘቡት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ፤ እቴጌ ጣይቱ ራስ መኮንን እና ራስ አሉላ የመሳሰሉት የጦር መሪዎች የጣሊያኖቹን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ በመመርመር የራሳቸውን የጦር ስልት ነድፈው እንቅስቃሴ ጀመሩ:: የኢትዮጵያ ሠራዊት የገበሬ ሠራዊት የነበረ ሆኖ ባጠቃላይ 100 ሺህ አካባቢ የሚገመት በንግድ እና በልዩ ልዩ ዘዴ የተገኙ ዘመናዊ ነብስ ወከፍ ጠብ-መንጃ እና የተወሰኑ መድፎችን የታጠቀ ነበር::
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት የተደረገው ከ1887-1888 ድረስ ሲሆን የመጀመሪያው ውጊያ ደቡብ ትግራይ አምባላጌ ተራራ አካባቢ የተደረገ ነበር:: አምባ አላጌ ደቡብ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ በተራራ ላይ የተቋቋመ ምሽግ ሆኖ ይሄም ተራራ በዚህ ጦርነት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የነበረው ተራራ ነበር::
ታኅሣሥ 1887 የኢትዮጵያ ኃይሎች በራስ መኮንን እየተመሩ አምባላጌ ላይ መሽጎ የነበረውን የጣሊያን ሠራዊት ከበው ተቆጣጥረውታል:: በዚህ ውጊያ የጣሊያን ሠራዊት በፔትሮ ቶሰሊ እየተመራ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ሠራዊት በቁጥር እጅግ በመበለጡ ሊሸነፍ ችሏል::
ቀጣዩ ኢትዮጵያ እና የጣሊያን ወታደሮች ውጊያ የመቀሌ ከበባ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም 1888 የተደረገ ውጊያ ነው:: በዚህ ውጊያ የጣሊያን ሠራዊት በሻለቃ ዮሴፕ ጋሊያኖ እየተመራ መቀሌን ተቆጣጠረ:: የመቀሌ ከተማ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የነበረው ሲሆን የኢትዮጵያ ሠራዊት የመቀሌ ከተማን በመክበብ የስንቅ እና ትጥቅ የሚቀርብባቸውን መስመሮች መቁረጥ ችሏል:: ከሳምንታት ከበባ በኋላ የተከበበው የጣሊያን ጦር የምግብ እና ውሃ እጥረት ስለገጠመው በኢትዮጵያ በኩል የጣሊያን ሠራዊት በሰላም እንዲለቅ ፈቅደውለታል:: ይህም የጦር ስልቱን ጥበብ ያሳየ እና አላስፈላጊ ግጭት እና ደም መፋሰስን ለማስወገድ ያለመ ነበር:: የመቀሌ ከተማ የጣሊያኖችን ሞራል ይበልጥ እንዲወድቅ ያደረገ ሲሆን የወሳኙን የዓድዋ ጦርነት መንገድ ጠርጓል::
በመቀጠል የጣሊያን ሠራዊት ወደ አዲግራት በማፈግፈግ በከፍተኛ ቦታ ላይ የመሸገ ሲሆን:: የኢትዮጵያ ሠራዊት በበኩሉ በቀጥታ ወደ አዲግራት በመጓዝ ከጣሊያኖቹ ሠራዊት ጋር መግጠም አልፈለገም። ምክንያቱም በመሐል ያለው ዝቅተኛ ቦታ ለጥቃት የሚያጋልጠው በመሆኑ ነበር:: ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተምቤን በኩል ወደ ዓድዋ ተራራማ ቦታዎች በመሄድ ሰፍሯል:: በዚህ ሁኔታ ለወራት ያህል ማዶ ለማዶ ሆነው አንደኛው የሌላኛውን ኃይል ጥቃት መጀመር ሲጠባበቁ ቆይተው በመጨረሻም የጣሊያን ጦር ጄኔራሎች የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲግራት በመነሳት ሲጓዝ አድሮ በሦስት አቅጣጫ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጥቃቱን ከፍቷል::
የኢትዮጵያ ሠራዊትም በዓድዋ አቅራቢያ በሚገኙ ተራራማ ቦታዎቹ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ ጠቀሜታ በነበራቸው ተራራማ ቦታዎች በመመሸግ ሲጠባበቅ ቆይቶ በተለያዩ አቅጣጫዎች የዘመተውን የጣሊያን ጦር ርስ በርሱ እንዳይናበብ እና እንዳይረዳዳ በማድረግ በወሰደው የመልሶ ማጥቃት ርምጃ ሊደመስሰው ችሏል:: በመጨረሻም የኢትዮጵያውያኑን መልሶ ማጥቃት ሊቋቋመው ያልቻለው የጣሊያን ጦር ሽንፈቱን ተከናንቦ ወደ ኤርትራ ሊያፈገፍግ ችሏል::
የዓድዋ ድል በኢትዮጵያውያን፤ አፍሪካውያን እና በመላው ዓለም ይገኙ ለነበሩት ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል እና አንድነት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበረው:: ድሉ የኢትዮጵያን በጋራ በመሆን ፀረ ኮሎኒያሊዝም ትግል መግለጫ የሆነ ድል ነው:: ኢትዮጵያውያን በፀረ ኮሎኒያሊዝም ትግል ከፍተኛ ተጋድሎ የተደረገበት ምልክት ነው:: የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ሕዝብ ደፋርነት እና ጀግንነት መለያ ምልክት ሲሆን ድሉ በአፍሪካ የኮሎኒያሊዝም ታሪክ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር የሚል ትርክት እንዲፈጠር አድርጓል::
ከዚህም ባሻገር ድሉ በወረራ ቀንበር ስር መውደቅ የአፍሪካውያን ሀገራት ዕጣ ፈንታ ብቻ እንዳልሆነ እና አፍሪካውያን ባሕላቸውን፤ ቋንቋ እና ማንነት ጠብቀው ለመቆየት የሚያስችል ኃይል አላቸው የሚል እሳቤ እንዲይዙ አድርጓቸዋል:: በዓድዋ ጦርነት ወቅት የታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እና ጥንካሬ ከድሉ በኋላ በነበሩት አሰርተ ዓመታት የፓን አፍሪካኒዝም እና ኢትዮጵያኒዝም የተባሉትን እንቅስቃሴዎች ለማበረታታት ጥቅም ላይ ውሏል:: በዚህ ረገድ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የነበረው ማርከስ ጋርቬ እ.ኤ.አ በ1929 “ወደ አፍሪካ ዞራችሁ የጥቁር ንጉሥ ኩራትን ተመልከቱ:: እርሱም የሚዋጃችሁ ይሆናል በማለት ጽፏል::
ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካን ሕዝብ እና በዓለም ላይ የሚገኙ አፍሪካውያን ዲያስፖራ ነፃ ለማውጣት እና ለማስተባበር ያለመ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ፤ ርዕዮተ ዓለም እና ጂኦ ፖለቲካዊ ፕሮጀክት ነው:: የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ በሁሉም የአፍሪካ ዝርያ ባላቸው አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ እና ትውልደ አፍሪካ ዲያስፖራን ለማበረታታት እና በመካከላቸው ያለውን ትስስር ማጠናከርን ነው::
የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ለአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረትም መንገድ የጠረገ እንቅስቃሴ ነው:: ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ሀገሮች ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ እና በመላው ዓለም የሚኖረው ጥቁር ሕዝብ ኅብረትም እንዲያጠናክር ቁርጠኛኝነቱን ያረጋገጠ እንቅስቃሴ ነበር::
አንዳንድ ጸሐፊያን ፓን አፍሪካኒዝም በዓድዋ ድል ምክንያት ብቻ የተጀመረ እንቅስቃሴ አድርገው ያስቀምጡታል:: በርግጥ የዓድዋ ድል ለዚህ የመላው ጥቁር ሕዝብ እንቅስቃሴ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅዖ የነበረው ቢሆንም የፓን አፍሪካኒዝም ዘር የተዘራው በ18ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካውያን በባርነት ላይ በተባበረ መልኩ ጠንካራ አመጽ ማካሄድ በጀመሩበት ወቅት ነበር::
የነፃነት መሻት እንቅስቃሴ የ1968ቱ የአሜሪካን የነፃነት ጦርነት፤ የ1781 የፈረንሳይ አብዮት እና በሊቢያ የመጀመሪያው የጥቁሮች ነፃ ሀገር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው የሃይቲያውያን አብዮት ነበር:: አዲ ሐኪም እና ሥርዉድ የተባሉት ምሑራን እንደጻፉት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የተጀመረው ራሳቸው የባርነት ሰለባ በሆኑ ጥቁሮች አማካኝነት ሲሆን ጥቁሮች የዘመናዊ ትምህርት ከተገኘው ግንዛቤ ጋር ከፈረንሳይ እንግሊዝ እና አሜሪካ አብዮቶች በተገኙት የነፃነት እሳቤዎች የመነጨ የነፃነት እንቅስቃሴ እንደሆነ ፅፈዋል::
የፓን አፍሪካኒዝም ውልደት በሎንዶን በ1900፤1919፤1921 እና 1923 በተካሄዱት ኮንፈረንሶች እና በሌሎች ከተሞች በተደረጉ ጉባኤዎች ሲሆን ከመሥራች ዋና ዋና የመጀመሪያዎቹ መሪዎች በዋናነት የሚጠቀሱት ደብሊው ዱ ቦይስ ነበር፤ ፍሬደሪክ ዳግላስ፤ ኩብና ኦቶባህ ኩግዋኖ እና ቶሴይንት ኤል ኢቨርቹር የተሰኙ የፀረ ባርነት ታጋዮች እና ምሑራን ነበሩ:: ይሁን እንጂ የዓድዋ ድል ከዚህ የሚከተሉትን ወሳኝ የፅንሰ ሀሳቡ አስኳሎችን አበርክቷል።
የዓድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ በልዩ ልዩ መንገድ አስተዋፅዖዎችን አሳድሯል። እነዚህን የሚከተሉት ሃሳቦች ምን ያክል ተፅዕኖ ማሳደር እንደቻለ ምሳሌ መሆን ይችላሉ። የመጀመሪያው የአፍሪካ (ኅብረት) ማስተዋወቂያና ማብሰሪያ ነበር የዓድዋ ድል አፍሪካውያን በአንድነት ቢቆሙ እንደሚያሸንፉ የሚያሳይ ታሪካዊ ምሳሌ ሆኖ ያገለገለበት ነው። ይህ የድል ታሪክ የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዋና መርሕ ነበር። አፍሪካውያን በተቀናጀ ሁኔታ ለነፃነት እና ለፍትሕ እንዲታገሉ የሚያበረታታ ነበር።
ሌላው የአፍሪካ ታሪክ እና ባሕል ማስተዋወቂያ ምልክት መሆን ችሏል። የዓድዋ ድል አፍሪካውያን ታሪካቸውን እና ባሕላቸውን እንዲጠብቁና ለማንነታቸው ቀናዒ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህ ድል አፍሪካውያን የራሳቸው ታሪክ እና ባሕል እንደ ኃይል ሊያገለግል እንደሚችል ማሳየት ችሏል። የድሉ ፅንሰ ሀሳብ የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዋና አካል ሆኖ አገልግሏል።
በተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ማስፈን ከምንም በላይ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ እንዲወጣ የዓድዋ ድል አስተዋፅዖው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የዓድዋ ድል ለሌሎች አፍሪካዊ ሀገራት ነፃነት ለማግኘት የሚደረግ ትግል ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ሲያገኙ፣ የዓድዋ ድል እንደ መሪ ምሳሌ ተደርጎ ተመልክቷል።
ሌላው የአፍሪካ ልጆች (ወጣቶች) በራስ መተማመን እንዲኖራቸው የሥነ ልቦና ውቅር የተከለ ነው። የዓድዋ ድል አፍሪካውያን በራሳቸው ላይ እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ ድል አፍሪካውያን የራሳቸው ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ የሚያበረታታ ነበር። ይህ ሀሳብ የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዋና መርሕ ሆኖ አገልግሏል።
አሉላ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም