
ዓድዋ የቆራጥነት ተጋድሎ ትርክት ነው:: የድሉ ባለቤት እኛ ኢትዮጵያውያን ነን:: ይህ የተጋድሎ ትርክት እንዴት ሕያው ሆነ ብለን ከጠየቅን የምናገኘው መልስ አብሮነትን ነው:: አብሮነት ከኃይልና ከብርታት ባለፈ በየትኛውም ዘመን የሀገርና የሉዓላዊነት ዳር ድንበር ማስከበሪያ ነው::
ዓድዋ ከድልና ከነፃነት ዓውዱ ባለፈ የሚያስተምረን ብዙ ነገር አለው:: ባለፉት መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ስለዓድዋ ስንናገርም ሆነ ስንሰማ ቀድሞ የሚመጣው የአባቶቻችን አንድነትና የወንድማማችነት ኅብረት ነው:: ዓድዋን እያከበርን ላለንው ለእኛ ከዓድዋ ልንማረው የሚገባ ትልቁ ነገር የወንድማማችነት መንፈስን ነው:: በወንድማማችነት መንፈስ ሀገራችን ኢትዮጵያ የእኛን አዲስ ዓድዋ ትፈልጋለች::
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የዓድዋ ውርስ ብዙ ነው:: በዓድዋ የድል ጀብድ ውስጥ ኅብረትና ወንድማማችነት የወለደው የመተሳሰብና የመከባበር ሀበሻዊ ባሕልም ጎልቶ ይታያል:: ይሄ ውርስ አሁን ላለችው ሀገራችን በእጅጉ ያስፈልጋታል:: ሀገራችን ኢትዮጵያ በልማት፣ በእድገት፣ በብልፅግና ወደፊት እየሄደች ያለች ሀገር ናት::
ከቀጣናው አልፋ በአፍሪካ እና በዓለም ላይ ተፅዕኖዋን ለማሳረፍ የዳበረ ኢኮኖሚ እና በሃሳብ የደረጀ የፖለቲካ ምሕዳር በመሰነድ ላይ ትገኛለች:: እነኚህ ሀገራዊና ሕዝባዊ የለውጥ እርምጃዎች ደግሞ እንደ ዓድዋ ካሉ ኅብረብሔራዊነት ከወለዳቸው የጅጋኔና የትብብር መንፈስ የሚታቀፉ ናቸው::
የአብሮነት መንፈስ የተጀመረውን ሀገራዊ እድገት ከማፋጠን አኳያ ሚናው ከፍ ያለ ነው:: ዓድዋ ውርሳችን፣ ቅርሳችን፣ ትርፋችን በመሆን ለዚህ ትውልድ እንደንቃት ሊወሰድ የሚገባው ነው::
በዓድዋ ዳዋችንን እንሻገር ስል እንደሀገር ልንሻገራቸው የሚገቡ የዘረኝነት፣ የእኔነት፣ የብቻነት፣ ያለመከባበር፣ ያለመነጋገር ዳዋዎች ስላሉ ነው:: ዳዋ ጫካ ነው:: ዳዋ አበባን የደበቀ እሾሃማ ጢሻ ነው:: በሰው ልጅ የልብ እርሻ ላይ የበቀሉ የጥላቻ መርዞች እንደዳዋ ናቸው:: ፍቅር የሌለው ልብ ዳዋ እንደዋጠው አበባ ነው:: መከባበር የሌለው ፖለቲካ ደመና እንደከለለው ብርሃን ነው::
ዳዋ ውጦናል:: የዘረኝነት፣ የፉክክር ዳዋ ለብሰናል:: ያለመነጋገር፣ ያለመደማመጥ ዳዋ ስር ነን:: ዳዋችንን ሳናርም በኢትዮጵያዊነት ከዘራነው የትስስር ቋጠሮ ዘንድ አንደርስም:: ፍቅር ዘራሽ ዘሮቻችን በወፍ ዘራሽ አሉባልታዎች ተውጠዋል:: ስለዚህም የዓድዋ ውርስ ያስፈልገናል:: የጀመርናቸው የልማት አቅጣጫዎች፣ ነገን ተስፋ በማድረግ እየሠራናቸው ያሉ የብልፅግና ጉዞዎች እንዲሰምሩ የወንድማማችነት መንፈስ ወሳኝ ነው::
በዘረኝነት ዳዋ ተሸፍነው ያልታዩ እልፍ የአብሮነት ጌጦች አሉን:: በፖለቲካ ትርምስምስ ተከልለው ያልተገለጡ የብዙ የጋራ ፀዳሎች አሉን:: እነኚህ የጋራ ውበቶቻችን ትንቅንቅ የሌለበት በመከባበር የተደነቀ ኅብረት የሚፈልጉ ናቸው:: በእስከ አሁን ጉዟችን ወደ ከፍታ ለመውጣት ጥሩ በሚባል መንገድ ላይ እንገኛለን:: ርካብ ስተን ከደረጃችን እንዳንወርድ እንደዓድዋ ያሉ ከብዙኃነት ውስጥ የተፀነሱ የጋራ ትውፊቶች ያስፈልጉናል::
ካለውርስ ዓድዋን ሻማ አብርቶ፣ ጀግኖቻችንን አስታውሶ ማለፍ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም:: መንፈሳቸውን ወርሰን፣ እምነትና ጽናታቸው ተጋብቶብን አሁን ካለንበት የቡዳኔ ልክፍት ወጥተን በኅብረብሔራዊነት ስንቆም ነው ዋጋ የሚኖረው:: ዝክረ ዓድዋ ዝክረ ኢትዮጵያ፣ ዝክረ አፍሪካ፣ ዝክረ ጥቁርነት ነው:: ትርጉም ያለው እንዲሆን ትርጉም ባለው ሀገራዊ አስተሳሰብ ስር መሳባሰብ ያስፈልጋል::
ፖለቲካ ወለድ ልዩነቶቻችን ሀገር አኮስሰው፣ ሕዝብ ገምሰው አይደለም አዲስ ዓድዋ መፍጠር ቀርቶ የነበረውንም በፍቅር እንዳንቀበል ሲያደርጉን እያየን ነው:: ዓድዋ እንዲህ አልተጀመረም:: ዓድዋ ፍቅር የወለደው፣ አንድነት ያጸናው የታሪክ አንጓ ነው:: ቡዳኔያችንን እንደአባቶቻችን ለሀገርና ሕዝብ ክብር እስካላደረግን ድረስ በጎራና በጎጥ ቆመን ነፃ መውጣት አንችልም::
የዓድዋ የአብሮነት ዜማ በዓለም የተሰማ የድል ዜማ ነው:: ይሄ የድል ዜማ ብዙ ጭቁን ሕዝቦችን ነፃ አውጥቷል:: እኛ የድሉ ባለቤቶች ግን አሁንም ድህነት ውስጥ፣ አሁንም ፖለቲካ ወለድ የትንቅንቅ ሽኩቻ ውስጥ ነን:: ነፃ ወጥተን ፈለጋችን ላይ የቆሙትን ነፃ ለማውጣት ከማንም በላይ ኃላፊነት ያለብን ሕዝቦች ነን::
ታሪክን በዘመን ስናሰላው መነሻና መድረሻው በዛን ሰሞን ይሆናል:: ከመጀመሪያው ዓድዋ እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ አርባ ዓመታት በመሐል አሉ:: አባቶቻችን ሁለተኛውን የጣሊያን እብሪት ለማብረድ አርባ ዓመት ነው የበቃቸው:: ጣሊያን ከዛ ቀድሞ ቢመጣም የማሸነፍና የመመከት ሙሉ ልዕልና ነበራቸው:: ለዚህ ምክንያት ሆኖ ከፊት የሚመጣው ደግሞ የሀገር ፍቅርና የነፃነት ጥያቄ ነው::
በአርባ ዓመታት ውስጥ ሁለት አይነት ድሎችን መቀዳጀት ትርጉሙ በምን እንደሚለካ ዛሬም ድረስ አልመጣልኝም:: አባቶቻችን በጽኑ ተጋድሎ ሀገር ሲጠብቁና ሉዓላዊነትን ሲያውጁ ኖረው ያለፉ ናቸው:: እኔና እናንተ ግን መቶ ዓመታት አልፈውን ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን የትላንት ታሪክ የምንጠራ ነን:: የእኛ ዓድዋ የታለ? የእኛ ዓድዋ መቼ ነው የሚጀምረው? መቼ ነው በድህነት ላይ ታሪክ የምንሠራው? መቼ ነው በመነጋገር እና በመግባባት ሞት እና ደም የሌለበትን ፖለቲካ የምናጸናው?
በዓድዋ የአንድነት ውርስ ከትዕቢታችን ቀድማ፣ ከጥላቻችን ቀድማ ኢትዮጵያ እንድትመጣ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል:: እንደሀገር የተጀመሩ ብዙ ዕድሎች አሉን:: የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያበስሩ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ:: እኚህ ጅማሬዎች ፍጻሜ አግኝተው ሀገራችንን ከፍ ለማድረግ ሁለንተናዊ ተግባቦትና ምክክር ያለበት የወንድማማችነት ኅብረት ያስፈልጋል::
በዓድዋ ሰፍተናል፣ ገዝፈናል በዘረኝነት ግን አንሰን ጠበናል:: በጠበበ ፖለቲካ ደግሞ የሰፋ ሀገር ትርጉም የለውም:: እንደ ፖለቲከኛ ከሰፋን፣ እንደ ሕዝብ ከገዘፍን እንደሀገር የማንበረታበት ምንም ምክንያት የለም:: ዓድዋ የሰፉና የገዘፉ ልቦች ነፀብራቅ ነው:: ይሄ ነፀብራቅም ሀገር አድምቆ አፍሪካ ላይ ተንፀባርቋል:: ዓለም ላይ መልሕቁን ጥሏል:: የፖለቲካ ስፋት..የማኅበረሰብ ግዝፈት ማለት ይሄ ነው:: የአባቶቻችን ግዝፈት ነው ጠባቧን ዓለም ያገዘፋት:: በዓድዋ ድል መግዘፍ እንጂ ታሪክ እያወሩ ነበርን መዘከር ትርጉም የለውም::
ከልዩነታችን ሀገራችንን ማስቀደም አለብን:: የእኛ ዓድዋ በዚህ መንገድ ካልሆነ በምንም እንደማይፈጠር ስነግራችሁ ከልቤ ነው:: ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ዛሬም ድረስ ነጮች ስለዓድዋ ድል ምርምር ላይ ናቸው:: አንዲት ድሃና ኋላቀር ሀገር የሥልጣኔ ፈርቀዳጅዋን ጣሊያንን እንዴት ልታሸንፍ ቻለች? በሚል ትካዜ ላይ ናቸው:: ዓድዋ ለእኛ ለጥቁሮች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ኩራት ሲሆን ለመላው ነጭ ደግሞ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የቁጭትና የውርደት ታሪክ ነው::
ታሪክ ተዓምር አይደለም ታሪክ የሚፈጠረው በፍቅር ነው:: ታሪክ የሚጻፈው በአንድነት ነው:: በመደማመጥ የከበረ ሕዝብ ታሪክ መሥራት ይቻለዋል:: ከተደማመጥንና ችግሮቻችንን በመነጋገር ለመፍታት ድፍረት ካገኘን ታሪክ መሥራት አያቅተንም:: ከድህነት ለመውጣት እያደረግነው ባለው ብርቱ ጥረት ውስጥ መደማመጥ ትልቅ ዋጋ አለው:: ባለመደማመጥ ብዙ ካቦችን አፍርሰናል:: በኃይል ብዙ ክብሮችን ንደናል:: ዛሬም ግን እነዛን የናድናቸውንና ያፈረስናቸውን ክብሮች እየካብን እንገኛለን::
በዓድዋ ከዳዋ መውጣት አለብን:: ወደበለፀገች እና ወደታፈረች ኢትዮጵያ ለምናደርገው የጋራ ጉዞ የዓድዋ መንፈስ እንደብርታት ነው:: ከፊታችን ያሉ የከፍታ ዘመኖች በመነጋገር፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበር የሚደረሱ ናቸው:: የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በውይይት እየፈታን የጋራ ሀገር ለመፍጠር በሚደረግ ትግል ውስጥ አስተዋፅዖ ካላደረግን ታሪክ ከመተረክ ባለፈ ታሪክ ለመሥራት አንታደልም::
ዓድዋ አጥቢያ ነው..የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የነፃነት ዜማ የሚደመጥበት:: የጽናት፣ የሉዓላዊነት ቅኔ መወድስ የሚሰማበት..የክብር፣ የኅብር..ደብር:: ዓድዋ ታቦት ነው ኢትዮጵያዊነት የተቀረጸበት የብኩርና ጽላት:: ሞት የዋጀው፣ ጉስቁልና ያረታው የማንነት ዓውድ:: ዓድዋ ዋርካ ነው የኩራት፣ የክብርና የትሕትና የነፃነትም የመምሬ አድባር:: ዓድዋ ተራራ ነው..ትልቅና ጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ሥጋና ደም፡ ነው።
ጽናት እምነትና አሸናፊነት የከተቡት:: ዓድዋ ጌጥ ነው..የመቶ ሃያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሸንክታብ:: የሰማኒያና ከዛ በላይ ብሔረሰብ የኩራትና የልዕልና ምንጭ:: የመላው ጥቁር ሕዝብ መታበያ..መመፃደቂያ:: ዓድዋ ይሄን ሁሉ ነው..እኛም ይሄን ሁሉ ነን:: እናም እንውረሰው::
ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳል ፤መልካም ውርስ ግን ከታሪክ አብራክ ውስጥ የሚመዘዝ ነው:: ስለሀገር ከሆነ የምናወራው መልካም ውርሳችን ዓድዋ ነው:: ስለትውልድ ከሆነ የምንናገረው ትውልዱ ከዓድዋ የወንድማማችነት ውርስ የላቀ ውርስ የለውም:: ኢትዮጵያን ለመታደግ የአባቶቻችን አይነት የክብርና የትቅቅፍ ውርስ ያስፈልገናል:: የታፈረችና የበለፀገች ሀገር እውን ለማድረግ ምክክርና ውይይት ወሳኝነት አላቸው:: ጊዜው በሀገር ፍቅር ስሜት ኢትዮጵያን የምናዋልድበት ነው:: በፖለቲካ ሴራ በጎጥና በብሔር ተቧድነን ነፃ ያልወጣንባቸውን በርካታ የመከራ ጊዜያት ክፉ ትዝታ ሆነው አሉ::
አሸናፊነት ያለው በቅደም ተከተል ውስጥ ነው:: ከሀገር መጀመር አለብን:: ከሀገር የጀመረ ሁሉ እንዳይፎርሽ የሆነ ነው:: እንነጋገር፣ እንመካከር የምንለው ከሀገር ለመጀመር ነው:: በሀሳብ የበላይነት እንሸናነፍ የምንለው በጎጥ እና በዘረኝነት የተያዘውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ወደሀገር እሳቤ ለማውረድ ነው:: ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት የዓድዋ ውርስ ያስፈልገናል የምንለው ከመናናቅ ወደመከባበር፣ ከመገፋፋት ወደተመቃቀፍ እንድንመለስ ነው::
ከዓድዋ መማር አለብን፣ ከአባቶቻችን መማር አለብን..እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግሥት፣ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ዓድዋና አርበኞቻችን የሚያስተምሩን ብዙ ነገሮች አሉ:: ዓድዋ የኅብረ ብሔራዊነት፣ የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ ነው:: ለሀገርና ሕዝብ ቅድሚያ የመስጠት ዋጋ ነው:: የእምነት፣ የጽናት፣ የአይበገሬነት ንቅናቄ ነው:: እንደ ሀገር ከታሪካችን የምንማረው ብዙ ነገር አለ:: ሀገራችን በእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች:: እድገቱ እንዲፋጠን ደግሞ ሃሳብ ያነገበ፣ በሃሳብ የሚያምኑ ሃሳባውያን ያስፈልጋሉ::
ተማሪ ብንሆን አባቶቻችን አስተማሪዎቻችን ነበሩ:: ቀናዒ ብንሆን ዓድዋ ቃል ኪዳናችን መሆን ይችል ነበር:: ለለውጥ ብንዘጋጅ ታሪኮቻችን እኛን ለማስተሳሰር በቂዎች ነበሩ:: ከዓድዋና ከአርበኞቻችን ሀገር የማቆየት ተጋድሎ እንማር:: ለጥቁርነት ጌጥ ከሆነው፣ ነጮችን ካስጎነበሰው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እንማር:: በዓድዋ ላይ ቆመን መለያየት አይታሰብም:: የተጀመረው የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን የዓድዋን መንፈስ መውረስ ያስፈልገናል::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም