
ዓድዋ ለሰላም የተደረገ ዘመቻ ነው።
ከዓድዋ ዘመቻ በፊት ኢትዮጵያውያን ለሰላም ያላቸውን የጸና አቋም ደጋግመው ገልጸዋል። ለሰላም ያላቸው አቋም የጠላት ፉከራዎችንና ትንኮሳዎችን በትዕግሥት እስከማለፍ የደረሰ ነበር።
እንደሚታወሰው የወራሪው የጣሊያን ጦር ባንዳ ይመለምል ነበር። ባንዳ ያስታጥቅ ነበር። የባንዳ ተላላኪዎችን በመንግሥት ውስጥ ለማስረግ ይሞክር ነበር። ሽብር ይነዛ ነበር።
የኢትዮጵያን መንግሥት ይከስ ነበር። አንዳንድ ቦታዎችን ለመያዝ ይሞክር ነበር። በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ለማሳጣት ይፍጨረጨር ነበር።
ኢትዮጵያ ይሄንን ሁሉ በትዕግሥት እና በዝግጅት ትመለከተው ነበር።
ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በጦርነት ኖረዋል። በዚህ የተነሣ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ያውቁታል። ስለሚያውቁትም በቻሉት አማራጭ ሁሉ ይሸሹታል። ለሰላማዊ አማራጭ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜም ለሰላም ሲሉ ከአስፈላጊው በላይም ያደርጋሉ። ይሄንን ሁሉ ገፍቶ የሚመጣ ጠላት ሲገጥማቸው ግን ለሰላም ሲሉ ዘምተው፤ ለሰላም ሲሉ ያሸንፋሉ።
የዓድዋ ዘመቻም እንደዚሁ ነው። የወራሪው የኢጣሊያ ጦር ወደ ጦርነት እንዳይገባ ተለምኗል። የሰላም አማራጮች ቀርበውለታል። “ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት፣ ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት” እንደሚሉት ሆነ። የኢትዮጵያን ትዕግሥት እንደ ፍርሃት፣ የኢትዮጵያን የሰላም መንገድ እንደ ሽንፈት ቆጠረው።
ጠላቶቻችን ምንጊዜም የስሌት ስሕተት ይሠራሉ። ትሕትናችን፣ ትዕግሥታችንና ሰላም ወዳድነታችን ያሳስታቸዋል። ወራሪው የጣሊያን ጦርም ተሳሳተ።
ኢትዮጵያውያን ግን እየታገሡ ይዘጋጁ ነበሩ። በሁሉም ረገድ ሰላማቸውን ለመጠበቅ ዝግጁ ነበሩ። ነፃነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር የሚገኙት የሀገር ሰላምን በመጠበቅ መሆኑን ያውቃሉ። ስለዚህ ሰላማቸውን በክንዳቸው ለመጠበቅ ተዘጋጁ።
የዓድዋ ጦርነት ለሰላምና ለጦርነት በሚዋጉ ኃይሎች መካከል የተደረገ ጦርነት ነው። የአሸናፊነታችን አንዱ ምሥጢርም ይሄው ነው።
ከጦርነቱ በኋላ ወደ በቀልና ጥላቻ እንዳናመራ ያደረገንም ይሄው ነው። ለሰላም ስንል እንጂ ለጦርነት ስንል አልተዋጋንምና።
የዓድዋ ድል ለሰው ልጅ ሉላዊ ዕሴቶች ያለንን ዋጋ አሳይተንበታል። በምርኮኛ አያያዛችን፣ ከተዋጉን ጋር መልሰን ለሰላማዊ ውይይት በመቀመጣችን፣ ለዘላቂ ሰላም በመሥራታችን።
እናቶቻችንንና አባቶቻችንን በድል አድራጊነታቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ዕሴቶች በከፈሉት ዋጋ ጭምር እናመሰግናቸዋለን። የተዋጉት ለሰላም ሲሉ ነው። የተዋጉት ሰላምን እና ሰላማዊ መንገድን እምቢ ካለ ኃይል ጋር ነው።
የዓድዋ ዘማቾች ልጆች ነን። ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን። ዛሬም ጠላቶቻችን ከተሳሳተ ስሌት እንዳልወጡ እናውቃለን። በሰላማዊ መንገድ የሚመጡትን መቀበል ከዓድዋ ዘማቾች ተምረናል። በሰላም የማይመጡትንም መቅጣት ከዓድዋ ዘማቾች አይተናል። እኛም እንደቀደምቶቻችን የሰላሙን መንገድ እንመርጣለን። ነገር ግን እንደ ቀደምቶቻችን ሁሉ፣ ለሁለቱም ምንጊዜም ዝግጁዎች ነን። የዓድዋ ዘማቾች ልጆች ነንና።
መልካም በዓል ይሁን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 22/2017 ዓ.ም
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም