የእግረኞች ደህንነት ዋስትናው የመሬት ውስጥ መተላለፊያ መንገድ

ቃል በተግባር እንዲሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን እንደ ስሟ አዲስ የማድረግ፣ ከተማዋን የማስዋብና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ከተማ እንድትሆን የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ከሥራዎቹ መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተሸጋገረው ውጤታማው የኮሪደር ልማት ስራ ይጠቀሳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ የኮሪደር ልማት ሥራ ለከተማዋ ካጎናጸፈው ውበት ባለፈ ስር የሰደዱ የመሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታት አስችሏል። ከዚህ በተገኘው ተሞክሮ ላይ ተመስርቶም ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት በከተማዋ ከተጀመረ ወራት ያለፉት ሲሆን፣ በተፋጠነ መልኩም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህም የከተማዋን ደረጃ ከፍ ከማድረግ ጎን ለጎን ለነዋሪዎች፣ እንግዶችና ጎብኚዎች የሚኖረው አበርክቶ የጎላ ነው፡፡

በከተማዋ ከተሰሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መካከል የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶችን ደረጃ የማሳደግ እና የማስፋት፣ የብስክሌት መንገዶችን የመገንባት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የውሃና ፍሳሽ እንዲሁም ለስማርት ከተማ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት ሌሎች የተከናወኑ ተግባሮች ናቸው። የቀለም፣ የሕንፃ ደረጃዎችን ማሻሻል፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና የሕዝብ የጋራ መገልገያ ስፍራዎችን፣ የታክሲና የአውቶብስ ተርሚናሎችን መገንባት እና የመሳሰሉት ተግባራት በስፋት ተከናውነዋል፡ በእዚህ ሁሉ ግንባታው የተካሄደባቸውን የከተማዋን አካባቢዎች ውብ ማድረግ ተችሏል፡፡ በአራት ኪሎ በአንዳንድ አካባቢዎች ለእግረኞች መተላለፊያ እንዲሆኑ የተገነቡት የመሬት ውስጥ መተላለፊያዎችም ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው የኮሪደር ልማቱ ውጤቶች ናቸው፡፡ ግንባታው አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በኮሪደር ልማት ሥራዎች ደምቀው የሚታዩት የመንገድ ሥራዎች በተለይም የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ በማድረግና የእግረኞችን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ስለመሆኑ ህዝቡም አሽከርካሪዎችም እየመሰከሩ ናቸው፡፡ የከተማዋን የመንገድ ትራፊክ እንቅስቃሴ የሚመራውና የሚከታተለው የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣንም አረጋግጧል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ያስገነባቸው የተለያዩ የመንገድ መሰረተ ልማት ሥራዎች ባለስልጣኑ ለሚሰራቸው ሥራዎች ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት ባለስልጣኑ የትራፊክ አደጋ ከመድረሱ አስቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራት ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡ ግንዛቤ ከማስጨበጥና ከማስተማር በኋላም የቁጥጥር ሥራን የሚሰራው ባለስልጣኑ የትራፊክ ህግን ተከትሎ የማያሽከረክሩ አሸከርካሪዎችንም ሆነ እግረኞችን በመቆጣጠር ህግ የማስከበር ሥራን ይሰራል፡፡ ህግ ከማስከበር ሥራ አስቀድሞም የትራፊክ ፍሰቱ ጤናማ እንዲሆን አስቻይ ሥራዎችን በጥናት ያካሂዳል፡፡ ለአብነትም መጋጠሚያ የሆኑ አደባባዮችን በትራፊክ መብራት የመቀየር እና የተለያዩ አመላካቾችን ቀለም በመቀባት መንገዶችና አደባባዮች ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ አደጋዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተቀዳሚ ተግባሩ የከተማዋን ህብረተሰብ ደህንነት መጠበቅና የትራፊክ እንቅስቃሴውን ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው ማድረግ ነው፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ ባለስልጣኑ ከዚህ ሲሰራ እንደቆየና ይህን ስራውንም በመጀመሪያው ዙር የተገነቡ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በእጅጉ እንዳገዙት ተናግረዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ በዋናነት እግረኞችና ተሽከርካሪዎች ተራርቀው እንዲጓዙ በማድረግ ትልቅ ድርሻ ማበርከቱንም አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከዚህ ቀደም ምቹ የእግረኛ መንገዶች ባለመኖራቸው እግረኞች በተሽከርካሪ መንገድ ውስጥ ገብተው ይጓዙ ነበር፡፡ ይህም እግረኞች ተሽከርካሪ ለጉዳት እንዲዳረጉ ምክንያት ሲሆን ቆይቷል፡፡

አሁን ግን የእግረኞች መንገድ ከተሽከርካሪ መንገድ በብዙ እንዲርቅ ሆኖ መገንባቱ እግረኞች ከተሽከርካሪ መንገድ ወጥተው ምቹ በሆነው የእግረኞች መንገድ መጓዝ ችለዋል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ይከሰት የነበረን አደጋ በብዙ እጥፍ መቀነስ አስችሏል፡፡ ከእግረኞች መንገድ በተጨማሪም የሳይክል መንገድ መገንባቱ አማራጭ ትራንስፖርትን ከመጠቀም አንጻር ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ትርጉም ባለው መልኩ የትራፊክ አደጋ መቀነስ እንደቻለ የጠቀሱት ወይዘሮ ገነት፤ ይህም ባለስልጣኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ሌላው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሲሆን ይህም በተመሳሳይ ከአደጋ የጸዳ፣ ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሏል፡፡ ይህም ሲባል የዜብራና ሌሎች የቀለም ቅቦችና የመንገድ ምልክቶች በአግባቡ በመሰራታቸው ተሽከርካሪዎች ህግና ደንብ አክብረው መጓዝ በመቻላቸው የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ ከትራፊክ ፍሰት አንጻርም ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ የመንገድ ማሻሻያ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ለአብነትም አደባባይ የነበሩ ቦታዎች በትራፊክ መብራት እንዲተኩ የማድረግ ሥራ መሰራቱ ትልቅ ውጤት አምጥቷል፡፡ ይህም በጥናት የተሰራ ሥራ ሲሆን፤ ለአብነትም በተለምዶ ሳህሊተ ምህረት አደባባይ ተብሎ ይጠራ የነበረው አደባባይ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህም ጊዜያዊ መፍትሔ በሚል ጠዋትና ማታ ተቃራኒ መንገዶችን በአንድ ጊዜ መጠቀም እንዲችሉ የተፈቀደበት ሁኔታ ነበር፡፡

ይሁንና ጥናትን መነሻ በማድረግ በኮሪደር ልማቱ አደባባዩ ፈርሶ በትራፊክ መብራት ተተክቷል፡፡ በዚህም ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ በመቻሉ ትልቅ እፎይታ ተገኝቷል፤ አደጋንም መቀነስ ተችሏል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በትራፊክ ፍሰትና ደህንነት ላይ እንደመስራቱ በከተማዋ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑና እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ትልቅ እገዛ አድርገዋል›› የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መሸጋገሪያ መንገዶችም እንዲሁ ለትራፊክ ፍሰትና ለእግረኞች ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማዋ እየተገነቡ ካሉ የውስጥ ለውስጥ የእግረኞች መሸጋገሪያ መንገዶች መካከል በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአራት ኪሎ የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያ መንገድ ይጠቀሳል፡፡ ይህ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እግረኛ እና ተሽከርካሪ እንዲራራቅ ከማድረግ ባለፈ እንዳይገናኝ በማድረግ ከፍሰትም ሆነ ከደህንነት አንጻር ትልቅ እፎይታን እየሰጠ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም አራት ኪሎ አካባቢ መንገድ ለመሻገር ሲባል ከፍተኛ የሆነ የእግረኞች እንቅስቀሴ ይታይ ነበር። በአሁኑ ወቅት ለእዚህ ከፍተኛ የእግረኞች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት በመሆኑ እግረኞች ከተሽከርካሪ ጋር ሳይገናኙ ደህንነታቸው ተጠብቆ በምድር ውስጥ መተላለፊያው መሻገር እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

ባለስልጣኑም እግረኞች ይህን ምቹ ሁኔታ እንዲያውቁና እንዲጠቀሙ የማስተዋወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ገነት፤ ለዚህም የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም ማህበራዊ ሚዲያዎችን፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በመጠቀም የማስተማርና የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለስልጣኑ እግረኞች የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያ መንገዱን እንዲጠቀሙና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የማድረግ እንዲሁም የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሥራውን በተግባር ለመደገፍም ሰራተኞቹ በየጊዜው መስክ ላይ በመውጣት ክትትል እንደሚያደርጉ ያነሱት ወይዘሮ ገነት፤ ሥራቸውን በዋናነት የሚሰሩት ከከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተሰማሩ 850 የሚደርሱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች አሉ፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ሲጀመር አንድ መቶ ያህል በጎ ፈቃደኞች ብቻ ነበሩ፡፡ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተሰሩ የእግረኛ መንገዶችና የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያዎች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ጭምር ትልቅ እፎይታን ሰጥተዋል፤ የዕለት ተዕለት የሥራ ጫናቸውን ማቅለል ችለዋል፡፡

ከተጠቃሚዎች አንጻርም እንዲሁ፤ በመስክ ምልከታ ያገኙትን ግብረመልስ ዋቢ አድርገው ሲገልጹ፤ እግረኞች የኮሪደር ልማቱን ተከትለው በተሰሩ የእግረኛ መሸጋገሪያ መንገዶች በጣም ደስተኛ እንደሆኑና ትልቅ እርካታን እንዳገኙ አስታውቀዋል፡፡ ለእንቅስቃሴያቸውም ምቹ ሁኔታ ከመፈጠሩ ባሻገር ከአደጋ እንዲጠበቁ ማስቻሉን መግለጻቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአራት ኪሎ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ከሆነ ቅርብ ጊዜ እንደመሆኑ እግረኞች የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገዱን አውቀው እንዲጠቀሙ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ የመሬት ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገድ በተጨማሪ ከፍተኛ የእግረኞች እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች መሰል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆኑም የጠቀሱት ወይዘሮ ገነት፤ ሃያትና መገናኛ አካባቢ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የመሬት ውስጥ የእግረኞች መተላለፊያ መንገዶቹ አጠቃላይ ግንባታው የሚከናወነው በከተማ አስተዳደሩ ነው፤ የሁሉም ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ በማድረግ፣ አደጋን በመከላከልና የህብረተሰቡን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የሚኖራቸው አበርክቶ እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣኑ በጥናት እየለየ የሚሰራቸው መሰል ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል፡፡

የባለስልጣኑ ተቀዳሚ ተግባር እግረኛን ከትራፊክ አደጋ መጠበቅ እንደመሆኑ የማስተማር፣ የማሳወቅና የማስገንዘብ ኃላፊነት አለበት የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአራት ኪሎ የመሬት ውስጥ ለውስጥ የእግረኞች መተላለፊያ መንገድ የእግረኞችን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡

በውስጥ ለውስጥ መንገዱ የተለያዩ የንግድ ሱቆች እንዲሁም አረፍ ብሎ ሻይ ቡና ማለት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም እግረኞች አረፍ ብለው ሻይ ቡና እንዲሉና የተለያዩ የስጦታና ሌሎች ዕቃዎችን መሸመት እንዲችሉ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ይላሉ፡፡

እግረኞች የውስጥ ለውስጥ መንገዱን እንዲጠቀሙና ደህንነታቸውን እንዲጠብቁ በሚል ባለስልጣኑ እየሰራ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በስፋት አልተዳረሰም። የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ እግረኞች ግንዛቤ አግኝተው መንገዱን በመጠቀም ደህንነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ በቀጣይ ሰፊ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ለአብነትም በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ አጫጭር መልዕክቶችን በመቅረጽና ቦታውን በማሳየት ሰፋ ያለ የግንዛቤ መስጫ ሥራዎች ተከታታይነት ባለው መንገድ ይሰራሉ የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ በተለይም ህብረተሰቡ ለእግረኛ ተብሎ በተዘጋጀው የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገድን መጠቀም ልምድ እንዲያደርግ ሰፊ ሥራ መስራት የግድ ነው ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከማስተማር ባለፈም የቁጥጥር ሥራ ይሰራል የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ የትራፊክ ህግና ደንብ የማያከብሩ አሽከርካሪዎች እንደሚቀጡ ሁሉ እግረኞችንም መቅጣት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡ ከመሸጋገሪያ ውጭ መንገድ የሚያቋርጥ እንዲሁም አጠቃላይ የትራፊክ ህጉን ተላልፎ የተገኘ እግረኛ አንድ መቶ ብር እንደሚቀጣም አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በተያዘው በጀት አመት ባለፉት ስድስት ወራት ከ18 ሺ በላይ እግረኞች መቀጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የትራፊክ ህግና ደንብ የተላለፉ እግረኞች የሚቀጡበት መንገድ የተለያየ እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ገነት፤ የቅጣቱ መጠን መቶ ብር ቢሆንም፣ መቶ ብር የለኝም ያለ ማንኛውም ሰው የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለአብነትም አረጋውያንን መንገድ ማሻገር፣ የጽዳት ሥራ መስራትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ገነት እንዳብራሩት፤ በአንድ ጊዜ ለውጥ ማምጣት የማይቻል እንደመሆኑ ግንዛቤ የማስጨበጥና የማስተማር ሥራው በተከታታይ ይሰጣል፡፡ በተለይም በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአራት ኪሎ የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያ መንገድ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፋ ያለና ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ማካሄድን ይጠይቃል፡፡

አሽከርካሪውም ሆነ እግረኛው አደጋ ከመድረሱ አስቀድሞ አደጋን መከላከል እንደሚችሉ የጠቀሱት ወይዘሮ ገነት፤ ህብረተሰቡ የትራፊክ ህግና ደንብን በማክበር በተፈቀደለት መንገድና ፍጥነት በመጓዝ ራሱን ከአደጋ መከላከል እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ እግረኞች ከተሽከርካሪ ጋር እንዳይገናኙ በተመቻቹላቸው የእግረኛ መንገዶች በመጓዝ ደህንነታቸውን እንዲጠብቁም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You