
አዲስ አበባ፦ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ድርጊቶችንና የኃይል ጥቃቶችን ለመቀነስ እና ለማስወገድ እየተሠራ ባለው ሥራ አበረታች ለውጥ መምጣቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሴቶች መብቶች ስርፀት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌትነት አበብል እንደገለጹት፤ መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ሥራ ላይ ማዋሉን ተከትሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግና አመለካከቱን ለመቀየር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በተሠራው ጠንካራ ሥራ ጎጂና ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም የኃይል ጥቃቶች እየቀነሱ መጥተዋል።
አበረታች ውጤት ከመጣባቸው መካከል ግርዛት ዋናው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ ለአብነት እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በተካሄደው የሥነ-ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ 79 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ግርዛት የተፈፀመባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
እ.ኤ.አ በ2005 በተካሄደው ዳሰሳዊ ጥናት ደግሞ 74 ነጥብ 3 በመቶ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው ጥናት 65 በመቶ በሚሆኑት ሴቶች ላይ ድርጊቱ መፈፀሙን አብራርተዋል። እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የሴት ልጅ ግርዛት ምጣኔው 14 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን እ.ኤ.አ በ2016 የተጠናው የሥነ-ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት ማመላከቱን ባለሙያው ገልጸዋል። በክልሎች ደረጃ ከፍተኛ የሴትልጅ ግርዛት በሶማሌ ክልል 99 በመቶ እና በአፋር ክልል 91 በመቶ ሲሆን፤ ዝቅተኛ ደግሞ በትግራይ ክልል 24 በመቶ በሴቶች ላይ ግርዛት መፈፀሙን መረጃው ማመላከቱን ተናግረዋል።
የሴት ልጅ ግርዛት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፤ እንደ ሀገር መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ሥራ ላይ አውሎ ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት ጥረት አድርጓል ብለዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አማካኝነት አደረጃጀቶች ተዘርግተው በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም አመልክተው፤ በዚህም በርካታ ቀበሌዎችን ከሴት ልጅ ግርዛት ነፃ ማድረግና ምጣኔውን ወደ 65 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜም በተደረጉ ጥናቶች ምጣኔው አሁን ካለበት ደረጃ የሚቀንስ መሆኑን ባለሙያው አመላክተዋል።
በሀገር ደረጃ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ ጥምረት በመፍጠር፣ በክልል ደረጃ ክልላዊ ጥምረት እና በወረዳና ቀበሌ ደረጃ የጎጂ ድርጊቶች አስወጋጅ ጥምረትን በማቋቋም የኅብረተሰቡን አመለካከት ለመለወጥ በተደረገው ንቅናቄ የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻ የመቀነስ ሁኔታ ታይቶበታል ብለዋል።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ድርጊቶችንና የኃይል ጥቃቶችን ለመቀነስና ለማስወገድ በተሠራው ሥራ አበረታች ለውጥ በመገኘቱ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የእኤአ 2024 የሥነ-ሕዝብ አዋርድ ተሸላሚ መሆኗን አውስተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም