ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች

አካል ጉዳተኝነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይከሰታል። ሰዎች በድንገት በሚደርስባቸው አደጋና በሚያጋጥማቸው ሕመም ሳቢያ ለአካል ጉዳት የመዳረግ ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል። ተደጋግሞ እንደሚነገረው ማንም በምን አጋጣሚ አካል ጉዳትን እንደሚያስተናግድ አይታወቅም፡፡ ትናንት ጤነኛ ሆኖ ሲራመድ የታየ ዛሬ በሚደርስበት ክፉ አጋጣሚ የአካል ጉዳትን ሊያስተናግድ ይችላል፡፡

ከአካል ጉዳት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ይነሳሉ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንዳንዶች የሚያንፀባርቁት ያልተገባ አመለካከት ከጉዳቱ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች የሥነልቦና ስብራትን ያሻግራል፡፡ ለነዚህ ወገኖች የተመቻቸ አገልግሎት ያለመኖሩም በየጊዜው ለሚደርስባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያትና መነሻ ነው፡፡

ከሁሉም የሚከፋው ግን ሲወለዱ አንስቶ የአካል ጉዳት ባለባቸው አንዳንድ ሕጻናት ላይ የሚደርሰው የከፋ በደል ነው፡፡ ይህ እውነታ በሁሉም ላይ ይከሰታል ባይባልም ጥቂት የማይባሉ ሕጻናት በወላጆቻቸው አስተሳሰብ ምክንያት ላልተገባ ድርጊት እንዲጋለጡ ይሆናል፡፡ እነዚህ ወላጆች የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ከእይታ በማራቅ ለዓመታት በቤት ውስጥ ይደብቋቸዋል፡፡

የዚህ ጉዳት ሰለባ የሆኑ አካል ጉዳተኛ ልጆች ሁሌም ከፀሐይ ብርሃን የራቁ፣ ከሰዎች እይታ የተደበቁ ናቸው። መኖራቸው ቀርቶ መወለዳቸው ሳይታወቅ ይህችን ዓለም ሊሰናበቱም ይችላሉ፡፡ ይህ አይነቱ እውነታ በበርካታ ቤተሰቦች መሐል የሚከሰት አጋጣሚ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁንም ድረስ በወላጆቻቸው ያልተገባ አመለካከት በርካታ አካል ጉዳተኛ ሕጻናት በየቤቱ ታስረውና ተደብቀው ይኖራሉ፡፡

‹‹ሀርቨር ግሮዘስ›› በባቱ ከተማ የሚገኝ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች አሰባስቦ ያስተምራል፡፡ የትምህርት ቤቱ መከፈት ዋና ዓላማ በየቤቱ ተደብቀው የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ሕጻናትን በትምህርት ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ በዘንድሮ ዓመት መስከረም ላይ ተከፍቶ ሥራ የጀመረው ይህ ትምህርት ቤት ከችግሩ ጋር ለሚኖሩ በርካታ ሕጻናትና ወላጆቻቸው እፎይታን አጎናጽፏል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከአካባቢው የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ልጆቹን    ወደ ትምህርት ገበታ ለማሳተፍ ያደረገው ሂደትም ተሳክቶለታል። በዚህ ዓመት በሃምሳ ተማሪዎች ሥራውን ለመጀመር ዕቅድ የያዘው ትምህርት ቤት አርባ ሁለት የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች አሰባስቦ የመማር ማስተማሩን ሂደት ቀጥሏል፡፡

በትምህርት ቤቱ መስማት የተሳነውን አንድ መምህር ጨምሮ ሦስት መምህራን በማስተማር ሂደቱ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ መምህራን ለሁሉም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተለየ ቅርበት አላቸው፡፡ ፍላጎታቸውን በወጉ ተረድተው ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡም ድርሻቸው ከፍተኛ ነው።

በልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቱ ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ አስራ ሁለት ዓመት የሆኑ ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከአንድ በላይ የአካል ጉዳትን ጨምሮ የኦቲዝም፣ የመስማትና ማየት፣ እንዲሁም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ በዚህ ዓመት የተቀበላቸው ተማሪዎች ብዛት የከተማውን የፍላጎት አቅም ያማከለ አይደለም፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከከተማው ከስድስት መቶ በላይ የአካል ጉዳትና የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በነበረው የጥናት ቆይታም ከአንድ ቤት እናትን ጨምሮ አራት መስማት የተሳናቸው ልጆችን የማግኘት አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህ እውነታም ወደፊት በአካል ጉዳተኛ ወገኖች ሕይወት ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡

በከተማዋ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ለማግኘት በተደረገው ጥረት ጥቂት የማይባሉ ልጆች ለተጨማሪ ጉዳት ተጋልጠው ተገኝተዋል፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች በእነሱ መወለድ ተሳቀውና የማኅበረሰቡን አመለካከት ፈርተው ልጆቹን ለዓመታት ደብቀዋቸው ኖረዋል፡፡ በዚህ ችግር ላይ ተመርኩዞ ጥናት ያደረገው ይህ ትምህርት ቤት የተወሰኑ ወላጆችን ተቀጣሪ በማድረግ ራሳቸውን ለማስቻል እገዛ አበርክቷል፡፡ ቀሪዎቹን ደግሞ በማኅበር በማደራጀት ሥራ የሚፈጥሩበትን ዕድል አመቻችቷል፡፡

በባቱ ከተማና አካባቢው የተስተዋለው ሐቅ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ ወገን ኃላፊነት ብቻ ያለመሆኑን አመላካች ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የትምህርት ሥርዓትን እንዲዘረጉና ቀጣይነት ያለው ሂደት እንዲጠናከርም ያግዛል። በዚህ በጎ ጅማሬ የባቱ ከተማ አስተዳደር ለትምህርት ቤቱ ግንባታ መሬቱን በነፃ በማበርከት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

ሌሎች አጋር ድርጅቶችም ተገቢውን ጥያቄ በመመለስ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ አቅም ለማሳደግ ግን ተጨማሪ ለውጦችን ማካሄድ የግድ ይላል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት የቅበላ አቅሙን አጎልብቶ ፍላጎትን ለማሟላትም የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ ሊሆን እንደሚገባ አመላካች እውነታዎች እየጠቆሙ ነው፡፡

መምህርት አማረች ታደሰ በ‹‹ሀርቨር ግሮዝስ›› የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ጉዳይ ሲያስብ በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዕለቱ እሳቸውን ያገኘናቸው መስማት በተሳናቸው ተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ለዓመቱ የታቀደው አስራ አምስት ተማሪዎችን ለማስተማር መሆኑን ነግረዋናል፡፡

በአካባቢው መስማት የተሳናቸውን ተማሪዎች ለማግኘት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በየቤቱ በተደረገው አሰሳ አስራ አንድ  ልጆች በመገኘታቸው በትምህርት ዓመቱ የዕድሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን ችለዋል፡፡

ርዕሰ መምህርቷ እንደሚሉት፤ በዚህ ክፍል የተማሪዎቹ የመስማት ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ የማይሰሙትን ጨምሮ በከፊልና በውስን ደረጃ ችግር የሚታይባቸው ተማሪዎች በተገቢው ሂደት የመማር ዕድልን ተችረዋል፡፡

መስማት በተሳናቸው የትምህርት ዘርፍ ስፖርትና ሙዚቃን ጨምሮ አስር የትምህርት አይነቶች ተደራሽ ሆነዋል። ተማሪዎቹ መስማት ከተሳነው መምህራቸው ጋር በምልክት ቋንቋ በወጉ ይግባባሉ፡፡ በየቀኑ በትምህርት ማገዣዎች ተደግፈው የሚሠሯቸው የቋንቋ ማበልፀጊያዎች ዕውቀታቸውን ለማዳበር አበርክቷቸው የላቀ ነው፡፡ በየጊዜው ከወላጆቻቸው ጋር በሚኖረው ግንኙነትም የልጆቹን ውሎና የሥነ ልቦና ደረጃ ለመለካት ተችሏል፡፡

ርዕሰ መምህርቷ እንደሚሉት፣ መስማት እንደተሳናቸው የመማሪያ ክፍል ሁሉ ለሌሎችም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አስፈላጊ የሚባሉ ክፍሎች በወጉ ተዘጋጅተዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች በብሬልና በአስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶች ታግዘው ተገቢውን ትምህርት እያገኙ ነው። ከእነሱ ጎን ለጎንም የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች እውቀትን ይስማሉ፡፡

የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች በበቂ ሥነ ልቦናና የትምህርት ዝግጅት የሚመጥናቸውን የትምህርት ዝግጅት እያገኙ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የኦቲዝምና ተደራራቢ የአካል ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች የሚሰጠው ትምህርት ደግሞ ከሌሎቹ ይለያል፡፡ የእነዚህ ተማሪዎች ውሎ የሚታገዘው በወላጆቻቸው እጅ ሲሆን ለእነሱ የተዘጋጁ መምህራን ከረዳቶቻቸው ጋር በቅርብ ተገኝተው አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋሉ፡፡

ርዕሰ መምህርቷ እንደሚሉት የባቱ ከተማ ለአካል ጉዳተኞች አካቶ ትምህርት የተለየ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ባለፈው ዓመትም ለዚህ አስተዋፅዖው ከአምስት ትምህርት ቤቶች ጋር ተወዳድሮ የአሸናፊነት ዋንጫን ለመሸለም በቅቷል፡፡ በተለይ በመስማት የተሳናቸው የትምህርት ሂደት ቋንቋውን ርስ በርስ በማሠልጠን የሚያደርገው ትውውቅ ሥራውን ለማቀላጠፍ አግዞታል፡፡

ይህ ዓይነቱ ጥንካሬ በደረጃ ተሸላሚ የሆኑ መስማት የተሳናቸውን ተማሪዎች ለማፍራት አሰችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜም እስከ ኮሌጅ የደረሰ የትርጉም ሂደት በማካሄድ ተደራሽነቱን በማስፋትና በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You