
“…መረዳዳት ቢኖር
ሁሉም ቢተባበር
ሰው ለሰው ቢፋቀር
ሁሉም ቢተባበር
የት ይደረስ ነበር”
እውነትም የት በደረስን ነበር…ተባብረን፣ አነባብረን የደግነትን እንጀራ እየበላን ጥጋብ እንጂ ረሃብ፣ ቁንጣን እንጂ ችጋር ባልወቃን ነበር። ምክንያቱም የኛ የኢትዮጵያውያን ህልውና የተገነባው በማህበረሰባዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ነው። በሠብዓዊ የተፈጥሮ ሰውነታችን ነው። ከሦስቱ የተጣላን ዕለት ዋጋም የለን። ሁሉም የሚነግሩንና የሚዘምሩልን እኚህኑ በስንኙ ላይ ያሉትን ደግነቶቻችንን ነው። ደግነታችን ደግ እንጀራ ነው። “አንድነት ሃይል ነው!” እያልን እንተባበራለን። “እንብላ!” እያልን ያለችንን ተካፍለን እንቋደሳለን። መሶባችን እሴታችን ነው፤ በአንድ አሰባስቦ በፍቅር ያጎራርሰናል። እኛ ኢትዮጵያውያን በሕይወት ልንጠግብ የምንችለው እንዲህ ስንኖር ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ደግነት ከዚህም ያለፈ ነገር አለው፤ ደግነት አንዱ ላንዱ መስጠት ብቻ ሳይሆን መሰጠትም ጭምር ነው።
“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የምንል ሁላችንም ነን። ነገር ግን ይህንን አባባል የተረዳነው በየትኛው ሰው መሆን ነው? ገና “ሰው ለመሆን እየሠራሁ ነው” በምንለው? ወይንስ በተፈጥሯዊ ሰውነት? ለመስጠት በተፈጥሮ ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው። “ስጡ ይሰጣችኋል” ሲልም፤ የደግነት ቅደም ተከተሉ ከማግኘት መስጠት ይቀድማል። ኢትዮጵያውያን ሁላችን ደግ ነን፤ ችግሩ ግን ደግነታችን “መጀመሪያ ለራሴ ሰው ልሁን” የሚል ሰበብ ያለበት ነው። ለመስጠት በንዋይ መከበብን እንጠብቃለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ እያለን ለመስጠት አስተዋሽ እንፈልጋለን።
ሁሉን ያሟላ ደግነት ግን በደጉ ሳምራዊ፣ በደጉ ኢትዮጵያዊ ተመለከትኩ። እንደምን ባለው ደግነት ውስጥ እንደተወለደ ለኔ ሁሌም ግርምትን ያጭርብኛል። ብዙዎቻችን “ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የምንለው በቃላት ሽንገላ ውስጥ ነው። እርሱ ግን ከዚህ ቃል በላይ የኖረውም መሰለኝ። የተማረውን ትምህርቱን፣ በውጭ ሀገር የነበረውን የድሎት ሕይወቱን…ሁሉን ጥሎ የወደቁትን ለማንሳት ሲል ሀገሩ ገባ።
ገና በመጀመሪያው 20 አረጋውያንን ከጎዳና ላይ በማንሳት፣ የነብሱን አዱኛ ማጨድ ጀመረ። ዛሬ ከ4 ሺህ በላይ የሆኑትን ሲያነሳ፣ ራሱን ጥሎ ነው። ታሞ ረዳት የሚሻው እሱ ሆኖ ሳለ የሰዎች ህመም ለመሸከም ቆርጦ ተነሳ። የተሰበረውን ልቡን በአንድ እጁ ደግፎ፣ በሌላ እጁ የሌሎችን እንባ ለማበስ ዘረጋው። እየኖሩ ሰውን ያኖሩ ብዙዎችን ተመልክተናል፤ እየሞተ ለሰው የሚኖር ግን እርሱን ነው። ገና በወጣትነቱ የብዙ ሺህ አረጋውያን አባት ነው። ሰው ገንዘቡን ይሰጥ ይሆናል፤ ራሱን ዕድሜውን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ይህ ደጉ ሳምራዊ ነው። መቼም ስለዚህ ደጉ ኢትዮጵያዊ ማነው ተባብለን እንደማንጠያየቅ ተስፋ አደርጋለሁ።
የማለዳው የሰውነት ጀንበር፣ የጠዋት ብርሃን ጮራ የምትፈነጥቀው መቄዶንያ ውስጥ መሆኑንም አይቻለሁ። ምናልባት እጅግ የዛሉና የቆሰሉ የአካል ክፍሎች፣ ማንነታቸውን የማያውቁ ልጅነቶች፣ መጥፎ ትዝታን የተሸከሙ ጭንቅላቶች፣ ህመም ያዘሉ ልቦች…ብዙዎች እዚህ ይኖሩ ይሆናል። ነገር ግን የትም የማናገኘው የመንፈስ ተድላና ፍሰሀም እዚህ ነው። ከወዴትም ልንሸምተው የማንችለው ደጉ ኢትዮጵያዊነት፣ በመቄዶንያ ውስጥ ነፍስ ዘርቶ በአካለ ስጋ እንመለከተዋለን።
ደግነት መቀመጫ ካለውም ዙፋኑ እዚያ ውስጥ ነው። ደጉ ሳምራዊ፣ ደጉ ኢትዮጵያዊ ቢኒያም ዘውዴ የመሠረታት መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል፤ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ዞሮ መግቢያና መጠለያ ሆኗል። ገና ደጁን ከመርገጣችን ሰው ሰው የሚሸት ኢትዮጵያዊነት ቆሞ እንመለከታለን። ገብተን ሁሉን ባየንበት ቅጽበት የሰውነት ሚስጢር ይገባናል።
በመቄዶንያ ውስጥ ያሉ ህሙማን አይደሉም። ደካማ አረጋውያን ከመሰሉን ተሳስተናል። ከውስጥ ዞር ዞር ብለን ማን እንደሆኑ ለመጠየቅ ከጀመርንባት ደቂቃ አንስቶ የልባችን መሰበር፣ በዓይኖቻችን እንባ ብቻ አይወጣልንም። በብዙዎቹ ውስጥ የተዳፈነ ድምጽም “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚል እንጉርጉሮ ነው። በልዩ ልዩ መስኮች ውስጥ ኢትዮጵያን ያቀኑ፣ ለሀገር የተዋደቁ ተራና ባለ ማዕረግ ወታደሮች፣ ትውልድ የቀረጹ መምህራን፣ ያላቸውን ከድሃው ጋር ተካፍለው ሲበሉ ቆይተው ሀብት ንብረታቸውን ያጡ፣ በደረሰባቸው የአዕምሮ መታወክ ከነበሩበት ከፍታ ወርደው ጎዳና ላይ የወደቁ….ብቻ በዚያ ውስጥ የማይገኝ ማንም የለም። ነጋ በዚያ ላለመገኘታችን እርግጠኞች የምንሆን ማናችንም የለንም። መቄዶንያን መሥራት የራሳችንን ቤት ከመሥራት ያነሰ ዋጋ የለውም። ምክንያቱም ቤት ኖሮት፣ ሕይወቱን በማጣት የገባም አለና።
በመጀመሪያም ከመቄዶንያ እና ከመሥራቿ ቢኒያም በለጠ ልንማር የሚገቡን ነገሮች አሉ። ኢትዮጵያዊ ድሃ ቢሆን ሀብታም፣ ተማሪ ቢሆን ነጋዴ፣ ፖሊስ ቢሆን ቀማኛ…በሁሉም ልብ እንደ መጠኑ ደግነት አለ። ስለመስጠት የሚነገረው አይደለም። በመስጠት ባህል ውስጥ ያደገ ነው። ሃይማኖቱ የመስጠትን ዋጋ ይነግረዋል። ከሁለቱ ቢያመልጥ ሠብዓዊነቱ ስለመርዳት ያስገድደዋል። በእነዚህ ሦስት ምክንያቶችም፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ በደግነት ያምናል፤ የብዙ ኢትዮጵያዊ እጅ ግን ለደግነት ያጥራል። ይህ የሆነውም፤ አንድም ለመስጠት አጋጣሚዎችን ፈላጊ በመሆናችን፣ ሁለትም የምንሰጠው የኛን ጓዳ ሞልቶ እስኪፈስ የምንጠብቅ ስላለን ነው። ለመርዳት ሰው መሆናችን በቂ መሆኑን ከቢኒያም መማር ይኖርብናል። የኛ ህመም የሌላውን ህመም ከመሻር አያግደንም። መቄዶንያን ያህል ግዙፍ የሀገር ዋርካ ለማቆም፣ የነበረበትን ሁሉ ጥሎ ሲነሳ ምንም አነበረውም። የነበረው ነገር ቢኖር በደግነት የተገነባ ሰውነት፣ ሰውን በመረዳት የተጠማ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር።
“ሁሉም ቢተባበር…” የምትለዋ ስንኝ፣ የኢትዮጵያዊነት ዋጋው ተተምኖ የሚደረስበት አይደለም። የምናውቃቸው ብዙ ነገሮች ገና ምንም አልገቡንም። በዓድዋ ያገኘነው ድል በአንድነት በመተባበራችን የተገኘ እንደሆን እየሰበክን፣ ግን አንኖረውም። ያለፈበትና አሁን ላይ የማይሠራ መስሎ ይሰማን እንደሆን እንጃ…አሁንም በመቄዶንያ ውስጥ የምንመለከተው ነገር በአንድ የመተባበርን ሃይል የሚያሳየን ነው። ራሱን መስዋዕት አድርጎ ሲነሳ፣ አንዱ ቢኒያም በለጠ ለ4 ሺህ ወገኖች እደርሳለሁ ብሎ አነበረም። በኢትዮጵያዊነት ልብ ውስጥ ያለውን ደግነት በመተማመን ነው። አባቶቻችን ስጋና ደማቸውን ለሀገራቸው ለመስጠት በኩራት እንደተሰለፉ ሁሉ፣ እርሱም እኔን ምኔን ሳይል ከወጣትነት አንስቶ ያለውን ዕድሜ ለወጎኖቹ ሰጥቷል። ዛሬ የምንመለከታት መቄዶንያ የቆመችው፣ በሰው እንጂ በገንዘብ ሃይል አይደለም። ምክንያቱም መቄዶንያ እዚህ እስክትደርስ፣ በአንድ ቢኒያም አሊያም በሀብታሞች ኪስ ብቻ ተይዛ አይደለም። መሠረቷ ቢኒያም በለጠ ቢሆንም፤ ማገር ወጋግራ እየሆነ፣ በግራ በቀኝ በላይና በታች የሞላው የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ደጋግ ልቦች ናቸው። የእኚህ ልቦች መተባበርና መተዛዘን በፈጠረው አንድነት የመጣ ታላቅ ነገር ነው።
ይህን ስንመለከት የመተባበርና የመረዳዳት ትርጓሜንም ማሳመር ያለብን ይመስለኛል። ብዙ ደጋግ ልቦች የመረዳዳትን ፈተና ያለፉ ቢሆኑም፤ መተባበር ላይ ግን ገና ይቀራቸዋል። ምክንያቱም መረዳዳት ብዙውን ጊዜ የአንድ ለአንድ የሆነ ግላዊ ሠብዓዊነት ነው። በመንገድም ሆነ በጎረቤት ለተቸገረው በግላችን እጅ እንዘረጋለታለን። ከኪሳችን ያለችውን አውጥተን ጣል ስናደርግ ደስ እያለን ነው። መተባበር ግን ከዚህ ይለያል። በተመሳሳይ ፍላጎት ውስጥ ያሉ ደጋግ ልቦች አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው፣ ለአንድ በጎ ተግባር መሳተፍ ነው። በግላችን ደግነትን የምናዘወትር አብዛኛዎቻችን አስማት የሚሆንብንም ይህ ነው። ሰጪዎች ሆነን ሳለን እንዴት መስጠት እንዳለብን ባለማወቃችን ወይም ችላ ብለን፤ እንደ ሀገር እጀ ሰባራ አድርጎናል። “በኢትዮጵያዊነት መልካምነት ድሮ ቀረ” እያልን የምናማርረውም ደጋጎች ጠፍተው ሳይሆን፤ የደጋጎች ልብ በአንድነት መጣመር ስለተሳነው ነው። እኚህን ደጋግ ልቦች ወደ አንድነት የሚያመጣውን መንገድ የሚሠሩ፣ እንደ ቢኒያም በለጠ ያሉ ጥቂቶች ብቻ በመሆናቸው ነው።
ለምሳሌ፤ ቢኒያም በለጠ በግል ከኪሱ ያለውን ሁሉ እያወጣ ለተቸገረው የሚሰጥ፣ መንገድ እየሄደ ድንገት ለታረዘው ልብሱን አውልቆ የሚያለብስ፣ በራሱ አቅም ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ የሚያደርግ ብቻ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የምንመለከተው ምንስ መቄዶንያ ይኖረን ነበር? መቄዶንያን በማሰቡ የሠራው የርዳታ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለደጋጎች የሚሆን መንገድና አደባባይም ጭምር ነው።
የሠራው መንገድም የመርዳት ብቻ ሳይሆን በአንድነት የመተባበርን ሃይል የያዘ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያውያን በግል ከመርዳት በላይ ተአምራዊ ሃይላቸው የሚገለጠው በአንድነት በመተባበር ውስጥ ነው። ድንገት አምስት አምስት ብር ላከፋፈልናቸው 10 የኔ ቢጤዎች፣ በድምሩ 50 ብር አወጣን ማለት ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ በያዘው 5 ብር ምንድነው ሊያደርግበት የሚችለው? የሁሉም አንድ ላይ ቢሰበሰብ ግን፤ በሃምሳ ብሩ ለረሃባቸው ማስታገሻ የሚሆን ዳቦ ልንገዛበት እንችላለን። ሃሳቤ የመረዳዳትን ትንሽነት ማሳየት ሳይሆን፤ የመተባበርን ትልቅነት ማመልከት ነው።
በእውነትም ደግነታችን ደግ ነው! እንድል ካደረጉኝ ነገሮች አንደኛው ከሰሞኑ ስለ መቄዶንያ የተጀመረው ዘመቻ ነበር። ከአርቲስቶችና ጋዜጠኞች እስከ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ድረስ ብዙዎች በየፊናው ዘመቻ ላይ ነበሩ። በቡድን በቡድን ሆነው፣ በስልክና በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉ ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ በሃላፊነት ሲያሳልጡ ብዙ ተመልክተናል። ኢትዮጵያዊነት ደግነት፣ ደግነትም ራስን እስከ መስጠት እንደሆን የሚያሳይ፣ የአንድ ደዋይ ሁኔታ ልብን የሚነካ ነበር። አስተባባሪዎቹ ስልኩን አንስተው ሃሎ! አሉ። ሰውየውም ከወዴት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “…አሁን የምሰጣችሁ ከእጄ ላይ ምንም ብር የለም። ነገር ግን ኩላሊቴን ለመስጠት እፈልጋለሁና እባካችሁን ፍቀዱልኝ” በማለት ከልቡ በሆነ ድምጸት ተማጸነ። ከዚህ ሰው ከተመለከትናቸው ነገሮች ውስጥ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የሚለው ትንሹ ነው።
ብዙውን ጊዜ ቀስቃሽና አንቀሳቃሽ እንፈልጋለን እንጂ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግነታችን እንኳን ደግ እንጀራ ነበረች። ከፊት ቆመው እጅ እስኪያውለበልቡ እንጠብቃለን እንጂ፤ ስንዘረጋስ ከልባችን ነበር። የሚያሰባስበን ካለ ለመሰብሰቡ ግድ የለንም። ሁሌም ከፊት የሚቀድም እንጠብቃለንና የሚያስተባብር ካለ ለመተባበር ወደኋላ የምንል አይደለንም። ሰሞኑን በተደረገው የመቄዶንያ ዘመቻም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ367 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን ስንመለከት፣ ተባብሮ የመኖር ኢትዮጵያዊነታችን፤ ለካስ ገደልነው እንጂ አልሞተም ያስብላል። በስድስት ሰዓታት ውስጥ የዓድዋን ድል ላስመዘገበ ሕዝብ፣ በእርግጥ በቀናት ውስጥ ምን ተአምር ቢሠራ ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም። በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን ይህን ደግ እንጀራ ቆርሰው አብልተውናል። የሚያጠግብና እጅግ ደስ የሚያሰኝ እንጀራ ነበር።
ነገር ግን እስከመቼስ ነው እንዲህ ባለ መልኩ ስላቦ እያልን የምንቀጥለው? ምንም እንኳን የሚያገኘው ገቢ ለሚያስፈልገው በቂ ባይሆንም፤ መቄዶንያ የራስን የገቢ ምንጭ በመፍጠሩ የሚታማ አይደለም። በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ከሚሰበሰበው ገንዘብ ጎን ለጎን፣ ለገቢ ምንጭነት የሚያገለግሉ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይታወቃል። እንቅስቃሴውን እንደተሞክሮ የምናደንቀው ቢሆንም፤ እንደሚጠብቀው የቤት ሥራ ግን ገና ነው። የራሱ የሆኑ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ግዙፍና ዘላቂ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ማበጀት ይኖርብናል።
ይህ ታዲያ የአንድ የቢኒያም በለጠ አሊያም በቅርብ ላለው ብቻ የሚሰጥ የቤት ሥራ አይደለም። መሥራቹ ለዚህ ደረጃ አብቅቶታል፤ አሁን ግን ከጫንቃው ላይ አውርደን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት ልናግዘው ይገባል። ቢኒያም እየታገለ ካለበት የራሱ ህመም አንጻርም፣ እንደበፊቱ ገንዘባችንን እየሰጠን አይዞህ ብቻ በማለት የምናልፈው አይደለም። ይህን ሁሉ የለፋው ለሀገርና ለወገኑ መሆኑን ተረድተን፣ በተራ መንግሥትና ሕዝብ ሃላፊነቱን ሊሸከም ግድ ነው። መቄዶንያ የእያንዳንዳችን መሆኑን ዘንግተን የአንድ የቢኒያም ዘውዴ አሊያም የጥቂቶች ብቻ አድርገን የምንቆጥር ከሆነ የመቄዶንያ ህልውና አደጋ ላይ ነው።
አንድ ሳይሆን እልፍ መቄዶንያዎችን ልንገነባ ግድ ነው። እንዲህ ያሉ ድርጅቶች በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ደረጃም መታሰብ አለባቸው። በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሀብትና ማንኛውም ግለሰብ ወገኑን ለመርዳት የሚታክት አይደለም። በባለቤትነት መርቶ የሚያገናኘውን ድልድይ የሚሠራለትን ግን የሚጠብቅ ነው። መንግሥት ሃላፊነት ወስዶ ሕዝብ ለሕዝብ የሚረዳዳበትን መዋቅር መፍጠር ይችላል። መንግሥት ክትትልና ድጋፍ ብቻ የሚያደርግበትን ተቋም ገንብቶ ለሕዝብ የሚያስረክብበትን መላ ቢዘይድ የራሱንም ሸክም ለማቅለል ይረዳዋል።
ካመኑና ከተማመኑ፣ እንደ መቄዶንያ ያሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ዩኤስኤይድ ያሉትንም ተቋማት ለመፍጠር ይቻላል። ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ትንፋሽ ለመሆን የበቃውና አሁን ላይ ስንቱን እያንገበገበው ያለው ይሄው ዩኤስኤይድ፤ የተመሠረተው በአሜሪካ ሕዝቦች የጋራ ትብብር ነው። ካሰብንበት የማይሆን የለም። ሃሳቡ ምግቡን ሳይሠሩ እጅ እንደመታጠብ ቢሆንም፤ የሃሳብ ጭራና ጅራት የለም። መኪና ከተመኙ አይቀር ከነመንገዱ ነው። ቢከፋም ቢለማም፣ ውጭ ውጪውን መመልከትን ትተን ሀገር በቀል ሕዝባዊ የርዳታ ተቋማትን ብንሠራ፣ እሱ ነው መድኃኒታችን።
መንግሥት መቄዶንያን አጠንክሮ፣ ሌላ መቄዶንያዎችን ስለመገንባት ማሰብ ይኖርበታል ስንል የገንዘቡ ምንጭ ራሱ ሕዝብ መሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ከአንድ ካፍቴሪያ ገብቶ ለተጠቀማት አንዲት ማኪያቶ በፐርሰንት ግብር ይከፍላል። ልክ እንደዚሁ ለዚህ ዓላማ የሚውል 25 ሳንቲም ጣል ብናደርግበት፣ የሚያስቆጣው ኢትዮጵያዊ የቱ ነው? በዓመት አንድ ጊዜ ግብር በሚከፍለው ሀገር ወዳድ ገበሬ ላይ በስምምነት 1 ብር ብንጨምርበት፣ የሚያስከፋው ምንስ ይኖራል? ለችግረኛው በዓመት 5 ብር አልረዳም የሚል ነጋዴስ ማነው? ለስፖርት፣ ለትምህርት…ወዘተርፈ ግብር በፐርሰንት የሚከፍለው የመንግሥት ሠራተኛ፣ ለዚህ በጎነት ከደሞዙ 2 ብር ብትቆረጥ እጄን ይቁመጠው እንጂ ወገኔን አልረዳም የሚል አንድ ይገኝ ይሆን? ልጁን ትምህርት ቤት የሰደደው ወላጅ በሚከፍለው የማህበረሰብ መዋጮ፣ የእናት አባቱ ውርስ ለሆነው ደግነት 1 ብር ቀርቶ የጠየቁትን ሁሉ ይሰጥ የለም እንዴ? እንግዲህ ሌላውን ሁሉ ትተን ይህን ብቻ እየሰበሰብን ወደ አንድ የወገን ተቋም ብናስገባው፣ አንድ ሕዝባዊ መቄዶንያ ለመሥራት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብን ይሆን? የጠፋን ብልሃትና ብልቱ እንጂ፤ ዓሣውማ ከባህር ዳርቻው ሞልቶ ነበር። አስጋሪ ሳይኖር ዓሣው፣ በተአምር ብቻ መረቡን አይሞላም።
ደግነታችን የዘለዓለም እንጀራችን ናትና ዛሬ በጋራ እያበሰልን፣ ነገ አብረን በፍቅር እንብላት!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም