አዲስ ዘመን ድሮ

በቀደሙት ዓመታት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሲወጡ የነበሩ የመረጃና የመዝናኛ ርዕሰ ጉዳዮች፣ የኋልዮሽ የሚያስተምሩን የሚያዝናኑና ትናንትን እንድናውቅ የሚያደርጉን ናቸው። ዛሬም ባላገሮቹን ስላታለሉ እነ ቁጭበሉ፣ የጋብቻ ወረቀት የሌላቸው ወንድና ሴት ሆቴል አይገቡም፣ እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ወደ 1960ዎቹ መለስ ብለን እናስታውስ።

ባላገሮችን ያታለሉ ተፈረደባቸው

“ከሀብታሞች ዘንድ ወስደን ገንዘብ እናሰጣለን” በማለት ከገጠር የሚመጡትን ገበሬዎች ከመንገድ እየጠበቁ አታለው ገንዘብ የወሰዱት ሁለት አታላዮች የ15 ዓመት እሥራት ተፈረደባቸው።

ከአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ከአርባ ጉጉ አውራጃ የመጡት አቶ ኢንካ አብዲን “ሀብታሞች ለድሃ ገንዘብ ይሰጣሉ” በማለት 30 ብርና አንድ ጋቢ አጭበርብሮ የወሰደው ታደሰ ቢነግዴ የ10 ዓመት እሥራት ትናንት ተፈረደበት። ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት ከሜታ ሮቢ የመጡት አቶ ጐንፋ ሙለታን “ትልልቅ አዛውንት ገንዘባቸውን በነፃ ለሕዝብ ስለሚያድሉ በኪስዎ ያለውን ገንዘብ ከእኔ ዘንድ አስቀምጠው ብዙ ገንዘብ ተቀብለው ሲመጡ ይወስዳሉ” በማለት 100 ብር የወሰደባቸው አሰፋ መንገሻ በ5 ዓመት እሥራት እንዲቀጣ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በየነበት።

ሁለቱም አታላዮች ወይም እንደፖሊሶቹ አጠራር “እነ ቁጭበሉ” በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ባላገሮች በማታለል “ለአርበኞች፤ ለአገለገሉ፤ ለሸመገሉና ምንም ለሌላቸው ሰዎች ገንዘብ በነፃ ይሰጣል። የያዛችሁትን ሁሉ ከኛ ዘንድ አስቀምጣችሁ ስትመለሱ ትወስዳላችሁ” በማለት ይዘው እየጠፉ የሚያታልሉ መሆናቸው ተመስክሮባቸዋል።

ወንጀለኞቹ ደኅና ልብስ እየለበሱ ታማኞችና ሽማግሌዎች በመምሰል ባላገሮችን “ገንዘብ በነፃ ለመቀበል በምትሄዱበት ጊዜ ተፈትሻችሁ ገንዘብ ከኪሳችሁ የተገኘ እንደሆነ ትወረሳላችሁ፤ ደህና ልብስ የለበሳችሁ እንደሆነ ትገፈፋላችሁ በማለት” የሚያታልሉ መሆናቸው በምስክር ተረጋግጦባቸዋል።

(አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 1964 ዓ.ም)

የጋብቻ ምስክር ወረቀት የሌላቸው ወንድና ሴት በሆቴል መኝታ አይከራዩም

ባልና ሚስት መሆናቸውን የሚያስረዳ ሕጋዊ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ካልያዙ በስተቀር በአዲስ አበባ ሴትና ወንድ ተያይዘው ወደ አልቤርጎ መኝታ ክፍል ለመሄድ የማይችሉ መሆኑ ተገለጠ።

የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የከተማውን ፅዳትና ጤና ለመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ የሞራሉንና የማኅበራዊ ኑሮውንም ጉዳይ መቆጣጠር ተግባሩ ስለሆነ የመታወቂያ ወረቀት የሌላቸው ሁለት ፆታዎች ባንድነት ወደ መኝታ ክፍል ከመግባት የሚያግዳቸው አዋጅ በዚህ ዓመት በሥራ ላይ ይውላል። ለባለአልቤርጎዎች ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር መምሪያው ይተላለፍላቸዋል ሲል የማዘጋጃ ቤቱ የሕዝብ ማስፋፊያና የማስታወቂያ ክፍል አመለከተ።

ክፍሉ ይህን መግለጫ የሰጠው ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ በብዙ መቶ የሚቆጠር ጋብቻ ሲፈጸም በማዘጋጃ ቤቱ የክብር መዝገብ የተመዘገበው ግን 302 ብቻ በመሆኑ ነው። ከዚህ ድምር ውስጥ 250 የኢትዮጵያውያን ጋብቻ ሲሆን የቀሩ የውጪ አገር ሰዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

እንዲሁም ባለፈው ዓመት በከተማው በሺ የሚቆጠሩ ሕፃናት ቢወለዱም ማዘጋጃ ቤት የሚያውቃቸው 2033 ሕፃናትን ብቻ ነው ብሎ የማስታወቂያው ክፍል አስረድቷል።

ማዘጋጃ ቤቱ፤ ለጋብቻ ለልደትና ለሞት የሚያገለግሉ የክብር መዛግብት ከአዘጋጀ ብዙ ዓመቶች አልፈዋል። እነዚህ መዛግብት ገንዘብ ሳይከፈልባቸው በነፃ ለሕዝብ የተሰጡ ከመሆኑ ሌላ የምስክር ወረቀቱ እንኳ ሳንቲም የማይከፈልበት መሆኑ ተረጋግጧል። ብቻ ምስክር የሚሆን መረጃ መያዝ ጥቅሙ ለሕዝቡ ነው።

አሁን የመታወቂያ ወረቀት የሌላቸው ባልና ሚስት ከጠቅላይ ግዛት ወደ አዲስ አበባ መጥተው አልቤርጎ ሊያርፉ ቢያስቡ ካሉበት ሀገር ባልና ሚስት መሆናቸውን የሚያስረዳ ካላሳዩ በስተቀር ተለያይተው በማደር ማዶ ለማዶ ሊተያዩ ነው ሲል የማስታወቂያ ክፍል መግለጫውን በመደምደም፤ የልጅ አበል ለማግኘት፣ ሕጋዊ ወራሽ ለመሆን፣ ትክክለኛ ዕድሜን አውቆ የጡረታ መብት ለመጠየቅ መመዝገብ አስፈላጊ ነው ይላል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 1964 ዓ.ም)

ወህኒ ቤት ገቡ

በአንዲት የሞተች ጥጃ ምክንያት በተነሣው የወንጀል ክርክር አንዲት የ፵ ዓመት ሴት፤ ዘጠኝ ልጆቻቸውን ጥለው ወህኒ ቤት መግባቸውን ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተገኘው ዜና ታውቋል።

እመት እልፍነሽ ወልደየስ የተባሉት የልጆች እናት ወህኒ ቤት ለመግባት ዋና ምክንያት የሆነባቸው አንዲት ጥጃ ገዝተው አርደዋል ተብለው ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነው።

በተከሳሿ ላይ የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው፤ ጥጃዋ ከታረደች በኋላ ተደርሶበት የቀረቡት ምስክሮች ቆዳዋ የተገኘው ጥጃ እመት ጌጤ የተባሉትን ሴት ጥጃ ትመስላለች በማለት ምስክሮች ባሰሙት ቃል ብቻ መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፫ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ይገልጣል።

እመት እልፍነሽ፤ በሞተች ጥጃ ምክንያት ተከሰው አዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀርበው በ፫ ወር እሥራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት መግባታቸውን የተከሳሿ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ ገልጠዋል።

(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 1965 ዓ.ም)

ዝንጀሮ ሰው በላ

ጅማ (ኢዜአ)፡- በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ ኮሣ ወረዳ ግዛት በርቄ በተባለው ቀበሌ አንድ ዝንጀሮ የ2 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ መብላቱ ተነገረ።

ዝንጀሮው ሕፃኑን ልጅ ከበላ በኋላ በተጨማሪ አንዲት የ3 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጅ ለመብላት ሲሞክር ሰው ደርሶ አድኗታል። ሆኖም ልጅቷን ለመብላት መሬት ጥሎ በመቦጫጨቅ የመቁሰል አደጋ ያደረሰባት መሆኑ ከቀበሌው መልከኛ ተገልጧል ሲል የወረዳው ግዛት ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገለጡ።

ዝንጀሮው አንዱን ልጅ በልቶ ሌላዋን ልጅ ያቆሰለው ልጆቹ በቤታቸው አቅራቢያ ሲጫወቱ አግኝቷቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው በተጨማሪ አረጋግጠዋል።

ይኸው ዝንጀሮ ልጆቹን ከመብላቱ በፊት፤ ከ30 ያላነሱ በጐችና ፍየሎች በልቶ ወደ ጫካ እየተሸሸገ የኖረ መሆኑ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1962 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You