ቢሮው ዋጋን ለማረጋጋት ከአርሶ አደሩ ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር ፈጠረ

አዲስ አበባ፡– ምርትን በስፋት ወደ ገበያ በማስገባት ዋጋን ለማረጋጋት በያዘው እቅድ መሠረት አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ገበያ ማዕከላት እንዲያቀርቡ የሚያስችል የገበያ ትስስር መፍጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ከትናንት በስቲያ፣ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በመዲናዋ አቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በከተማው በሚገኙ የተለያዩ የንግድ ማዕከላት በቀጥታ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የሚያስችል ስምምነት አድርጓል።

በወቅቱ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የግብይትና ገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ጥበቡ እንደገለጹት፤ የተረጋጋ ዋጋ የሚኖረው ምርት በስፋት ወደ ገበያ ሲገባ ነው። በመሆኑም አርሶ አደሮች በቀጥታ ወደ ገበያ ማዕከላት ገብተው ምርታቸውን ሲያቀርቡ ገበያው የመረጋጋት ዕድል ይፈጠርለታል።

የግብይት ሠንሠለት በተራዘመ ቁጥር አምራቹ የልፋቱን ዋጋ አያገኝም፤ ከአርሶ አደሩ ይልቅ ተጠቃሚ የሚሆነው መሐል ላይ ያለው ደላላ ነው። ደላላው በአቋራጭ ለመክበር ባለው ፍላጎት ከአርሶ አደሩ በተረከበው ምርት ላይ ዋጋ ይጨምራል፤ ይህም ጭማሪ በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል ብለዋል።

በመዲናዋ በሚገኙ የንግድ ማዕከላት በቀጥታ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ከ19 አርሶ አደሮች ጋር ስምምነት ማደረጉን አቶ ፍሰሐ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በቀጥታ ምርቱን እንዲያቀርብ ስምምነት መደረጉ፤ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ሸማቹና አምራቹ በቀጥታ እንዲገናኝ ስለሚያደርግ አርሶ አደሩን በማበረታታት ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በአሁን ወቅት እንደ ሀገር ምርት በስፋት እየተመረተ ይገኛል። ስለዚህ አርሶ አደሩ ለሕገ-ወጥ ግብይት እንዳይጋለጥ፤ ምርት በጊዜ ለመሰብሰብ የግብይት ቦታዎችን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው።

ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ምርት ከገበያ ሰብስቦ በማከማቸት የምርት እጥረት ሲኖር ዋጋ ጨምሮ የመሸጥ ልምድ አላቸው። ስምምነቱ እንደዚህ አይነት ነገር እንዳይከሰት ምርቶችን አስቀድሞ በገበያ ማዕከላት በሚገኙ መጋዘኖች በማስገባት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ስምምነት ላደረጉ አርሶ አደሮች ሦስት ዓይነት የግብይት አማራጮች መቅረባቸውን የገለጹት አቶ ፍሰሐ፤ የመጀመሪያው በሰንበት ገበያዎች ምርታቸውን የሚያቀርቡበት አማራጭ ሲሆን፤ ሌላኛው በገበያ ማዕከላት በቋሚነት መሸጥ የሚችሉበት እና በፈለጉበት ጊዜ ወደ ማዕከላቱ ቀርበው ምርታቸውን በጅምላ የሚያስረክቡበት አማራጮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከሮሜ ቀበሌ የመጡት አርሶ አደር ተሾመ ግርማ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት ምርት እንዳመረትን ለነጋዴ ስንሸጥ፤ ነጋዴው ከእኛ ተቀብሎ ለደላላ ያቀርባል በዚህ መሐል አርሶ አደሩም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ አይደለም ።

ነገር ግን አሁን በተደረገው ስምምነት መሠረት ቀጥታ አምራቹ ምርቱን የሚያቀርብበት ዕድል ሲፈጠር ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል። በተጨማሪም ሸማቹ ንፁሕ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ኃይለማሪያም ትንሳኤ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ምርት ከተመረተ በኋላ ሸማቹ ጋር እስኪደርስ አራት እና አምስት ሠንሠለቶችን አልፎ ነው ሸማቹን የሚደርሰው፤ በመሐል የሚወጡት የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች ታሳቢ የሚደረጉት አምራቹ ላይ ነው።

ስለዚህ የቀጥታ ምርት ግብይት ትስስር መፍጠሩ ለአርሶ አደሩ እና ለሸማቹ ጠቀሜታ አለው። ነገር ግን ምርት የማቅረብ ሥራው ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን በአማራም ሆነ፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኬላዎች ታሳቢ ቢያደርጉ መልካም ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You