
የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር Mia Amor Mottley በ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር የበርካቶችን ትኩረት አግኝቷል፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በሰው ኃይል ትልቅ ጉዳት የደረሰበት አህጉር ይዘው የነፃነቱን ጉዞ መጀመራቸውን አውስተው፤ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያንን ይቅርታ ጠይቀው አስፈላጊውን ማካካሻ እንዲያደርጉ ያሳሰቡበት የንግግራቸው ክፍፍል ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡
20 ደቂቃዎች የወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሯ ንግግር የተቋጨው “አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት በዓድዋ ድል የተገኘውን ውጤት ይዘን በዓድዋ መንፈስ ከሕሊና ባርነት ነፃ መውጣት አለብን” በሚል መደምደሚያ ነው። መደምደሚያው የዛሬዪቱን አፍሪካ አሳስሮ የያዛትን ትብታብ የሚበጣጥስ ሰይፍ የያዘ ኃይለ ቃል ነው፡፡
Mia Amor Mottley እንዳሉት አፍሪካ የታገረጡባትን ፈተናዎች መሻገር የምትችለው በዓድዋ መንፈስ ስትታደስ ነው፡፡ አፍሪካ ዛሬም በእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ተጠልፋ አረማመዷ አላማረም፡፡ የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሕሊና ባርነት ነፃ እንውጣ በሚል ያስተላለፉት ጥሪ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥቋቁር ወርቆችን ካሸለቡበት የሚቀሰቅስ የማንቂያ ደውል ነው፡፡
አፍሪካ በሁሉም ዘርፍ የዓድዋ መንፈስ ያስፈልጋታል። ከምድሯ የሚገኘው በረከት ከራሷ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንደሚችል ለዓለም ማሳየት አለባት፡፡ በርዳታ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ የዓድዋ መንፈስ የራቀው የእጅ አዙር ቅኝ ተገዢ የሚያደርግ ተሸናፊነት ነው፡፡ አፍሪካ በራሷ እግሮች መቆም ይኖርባታል፡፡ የትኛውንም ጉድለቷን እና ችግሯን በእጆቿ ለማበጀት አታንስም። ኢትዮጵያ የምታቀነቅነው ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የዓድዋ መንፈስ የረበበበት መርህ ነው፡፡
አፍሪካ በዩኤስ ኤይድ ርዳታ መቋረጥ ወገቧ መቆረጥ የለበትም፡፡ ለአስርት ዓመታት የተቀለበችው የርዳታ ስንዴ ጠባቂ እንጂ ችግር ፈቺ ትውልድን አላስገኘላትም። ከለጋሾች ስንዴ ይልቅ በለም መሬቷ እና በልጆቿ እጆች መተማመንን ስትመርጥ በዓድዋ መንፈስ ትታደሳለች። ስንዴ የሚለምኑ የአፍሪካ እጆች የታላላቆቻቸውን ዳና ተከትለው እምቢኝ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በማለት ትራክተር መጨበጥ አለባቸው፡፡ ያን ጊዜ ከራሳቸው አልፍው ለሌሎች ይተርፋሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ በዓድዋ መንፈስ በመታደስ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው ስኬት ተጨባጭ ተሞክሮ ነው፡፡ የኢፌዴሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደተመላከተው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላለች፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የሀገር ውስጥ ምርቷ በቂ ባለመሆኑ ምክንያት ስንዴ ከውጪ ለማስገባት በየዓመቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ታወጣ ነበር፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግን የስንዴ ምርቷን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ከውጪ የሚገባውን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ችላለች፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022/23 የምርት ዘመን ኢትዮጵያ 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ያመረተች ሲሆን የስንዴ ምርቱ መጠን በቀጣዩ ዓመት ወደ 23 ሚሊዮን ቶን አድጓል።
የኢትዮጵያ በምግብ ራስን የመቻል አጀንዳ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል መንግሥት በስንዴ ምርት ራስን በመቻል ያገኘውን ስኬት “ሀገራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሰፊ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መጎልበት ወሳኝ ርምጃ ነው” ሲል የገለጸው፡፡
መንግሥት በምግብ ምርት ራስን መቻል በራስ መተማመንን በማምጣት፤ ጥገኝነትን በመቀነስ እና በፍሪካ አህጉር ዘላቂ እድገት በማምጣት መንገድ እንደሚከፍት በጠቆመበት መግለጫው፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂ መሠረታዊ ምሰሶ ከመሆን ባለፈ ድንበር ተሻግሮ አህጉራዊ ሰፊ አንድምታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጿል።
በትክክልም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን በመቻል ያስመዘገበችው ውጤት የአፍሪካ ሀገራት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጠንክረው ከሠሩ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው ያሳየችበት ዓድዋዊ መንፈስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ስኬት ታቅዶ በተደረገ የተደራጀ እንቅስቃሴ የተገኘ ነው፡፡ ለዚህ የዛሬውን ቀን ከሁለት ዓመታት በፊት ቀድመው የተመለከቱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ላይ ”Why Ethiopia will soon be winning with wheat በሚል ርዕስ ባወጡት ጽሑፍ የጠቀሷቸው ሃሳቦች ምስክሮች ናቸው፡፡
ቢልለኔ በዚህ ጽሑፋቸው፤ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመለወጥ በምግብ እህል ራሷን መቻል እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ጥራት እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ በአስር ዓመት የልማት መሪ እቅድ እንደ ግብርና ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጋ በመንቀሳቀስዋ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗንም ገልጸዋል፡፡ በተለይ በዚህ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደ ስንዴ ያሉ ዋና ዋና የግብርና ምርቶችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የማስቀረት ጽኑ ፍላጎት መኖሩን አመላክተዋል። በማደግ ላይ ላለች እና በየጊዜው እያደገ የሚመጣ የወጣት ቁጥር ላለባት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏ እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ትልቅ ለውጥ መሆኑንም አንስተዋል። ለአየር ንብረት ለውጥና ለተደጋጋሚ ድርቅ ተጋላጭ የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሻሻሉ ፖሊሲዎች ምክንያት በፍጥነት መቀየሩንም አንስተው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በተያያዘችው ግስጋሴ ከቀጠለች በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች ሀገራት በመትረፍ ተጠቃሽ ስንዴ ላኪ አፍሪካዊት ሀገር የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ በስንዴ ምርት ራሷን በመቻል ያስመዘገበችውን ስኬት በሌሎች መስኮችም መድገም አለባት፡፡ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እስክታረጋግጥ ድረስ በዓድዋ መንፈስ የመታደስ ጉዞዋን አጠናክራ መቀጠል ይጠበቅባታል፡፡ የዓድዋ ድል በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁሮች ከባርነት እንዲወጡ መነሳሳትን እንደፈጠረ ሁሉ፣ ኢትዮጵያ የተያያዘችው በዓድዋ መንፈስ የመታደስ ጉዞ አፍሪካውያን ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በይቻላል መንፈስ ወደፊት የሚመራ ይሆናል፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም