
በራዊጋ …
ጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ:: የ‹‹በራዊጋ›› ለም ምድር ሁሌም የሰጧትን ታበቅላለች:: ከአገሬው እጅ የምርት በረከት አይነጥፍም:: እርጥቡ መሬት በቆሎና ጤፍ ያሳፍሳል:: በዚህች ቀዬ ልጅ ተወልዶ በሰላም ያድጋል:: ሽማግሌ አርጅቶ በወግ ይጦራል:: ወጣት ታዳጊው ጠዋት ማታ በሥራ መትጋቱ ያልተለወጠ ባህሉ ነው::
ከመንደሩ ነዋሪዎች ደግሞ የአቶ ሞሰበ ቤተሰብ ይለያል:: በአባወራው ቤት በርካታ ልጆች ያወኩበታል:: ገሚሶቹ የጨቅላ ዕድሜያቸው ከለቅሶና ሳቅ ጋር ያውላቸዋል:: በላይ በላዩ የተወለዱት ስድስቱ ልጆች እርስበርስ ተደጋግፈው እያደጉ ነው:: አሁን ደግሞ ወይዘሮዋ ሰባተኛ ልጃቸውን ነፍሰጡር ናቸው::
ከቀናት በአንዱ በአቶ ሞሰበ እልፍኝ አንዲት ቆንጅዬ ጨቅላ ሰፊውን ቤተሰብ ተቀላቀለች:: ይህ የቤቱ ሲሳይ ካላፉት ጊዜያት ሁሉ የላቀ ሆነ:: አዲሷ እንግዳ ከስድስቱ ወንዶች ኋላ የተሰጠች ልዩ በረከት ነች:: ሰባተኛዋ ልጅ ብርቅዬና ብቸኛ ሴት ሆና ተቆጥራለች:: ይህ ድንቅ ስጦታ የቤተሰቡን የቀደመ ታሪክ በእጅጉ ቀይሯል:: ትንሽዬዋ ጠይም ዕንቁ ለቤቱ ደማቅ ብርሀን ሆናለች:: ዓይኖች ሁሉ ወደእሷ አተኩረው ያፈጡባታል::
ማፓዎ ሰባተኛዋ በረከት
ሰባተኛዋን ብላቴና ዘወትር ቤተሰቡ በስስት እያያት ነው:: ከእሷ ቀድመው የተወለዱ ስድስቱ ወንዶች የተረሱ እስኪመስል ፍቅር ለእሷ አመዝኗል:: ጨቅላዋ ማፓዎ እጅግ ታምራለች:: በግንባሯ የተደፋው ለስላሳ ጸጉር ከመልኳ ውበት ተዳምሮ ማራኪነቷን ያጎላል:: ድንቅዬዋ ህጻን በእናቷ እቅፍ በቤቱ ልዩ ፍቅር ታጅባ ልጅነቷን ጀምራለች::
ቆንጅዬዋ ማፓዎ በዕድሜ ጨምራለች:: ከፍ ማለት ስትይዝ ትምህርት ቤት መግባት ከእኩዮቿ መዋል አለባት:: ይህን ቀን በጉጉት የሚሹት ቤተሰቦች የሚያስፈልጋትን አሟልተዋል:: ማፓዎ ጠይሟ ዕንቁ ውበቷ ዓይን ይስባል፣ ዞማ ጸጉሯ ከትከሻዋ ወርዶ ይዘናፈላል:: የቤቱ መብራት ሆና ፍቅርን እያደመቀች ነው::
ድንቴው እይታ…
በ2014 ዓ.ም ከቀናት በአንዱ:: ከትንሽዋ ቀንበጥ ገላ አንድ ነገር ተስተዋለ:: የማፓዎ ሆድ ከወትሮው በተለየ ያልተለመደ ምልክት ታየበት:: ምልክቱ በሆዷ ዙሪያ ቆዳዋን ያስቆጣ፣ ደም የለበሰ ነበር:: ቤተሰቡ ባየው ነገር ግራ ገባው:: ሁሉም የቤቱ ስስት የሆነችው ብርቅዬ ልጅ አንዳች እንዲያገኛት አይፈልጉም:: ዋል አደር ሲል ምልክቱ ሳይጠፋ ቀጠለ:: ይህኔ መላ የተባለው መፍትሔ ሊፈለግ ግድ ሆነ::
ማፓዎ ሰባተኛ ልጅ ከሆነች በኋላ ሌሎች ሶስት ልጆች ታክለዋል:: አብነት ለቤቱ የመጀመሪያ ነው:: አስራ አንድ ልጆች ተወልደው አስሩ ባደጉበት ጎጆ ይህ ወጣት የሁሉም ታላቅና የበላይ ሆኖ አድጓል:: እሱ ታናናሾቹን በተለየ ሥሥት ያያል:: እንደታላቅነቱ ከሁሉም የላቀ ኃላፊነት ይሰማዋል:: አሁን በማፓዎ አካል ያስተዋለው ምልክት እያሰጋው ነው::
ህክምናው …
አብነት ከቤተሰቦቹ ተማክሮ ማፓዎን ወደ ሕክምና ሊያደርስ ወስኗል:: የመጀመሪያው ክትትል ዛላ ወረዳ ላይ ከሚገኝ የግል ክሊኒክ ሆነ:: ትንሽዋ ማፓዎ ምርመራ አግኝታ መድሀኒቶች ታዘዙላት:: ጉዳዩ በዚህ ብቻ አልበቃም:: ለተሻለ ህክምና ወላይታ ሶዶ ወደሚገኘው የመንግስት ሆስፒታል ተጻፈላት::
አብነት የትንሽ እህቱ ጉዳይ ሰላም አልሰጠውም:: በተባለው መሰረት ማፓዎን ይዞ ወደ ሆስፒታሉ አደረሰ:: ሆስፒታሉ ለትንሽዋ ልጅ ተገቢውን ምርመራ አካሂዶ ለውጤቱ አስራ አምስት ቀናትን ቀጠረ:: አብነት ቀኑን ቆጥሮ የህክምና ውጤቱን ጠየቀ:: የእህቱ ችግር የሳምባ ህመም መሆኑ ተነገረው:: ለሶስት ወራት የታዘዘላትን መድሀኒት ተቀብሎ ወደቤት መለሳት::
ማፓዎ እንደ ቀድሞው ንቁ አልሆነችም:: የልጅነት ወዟ ገርጥቷል:: ቅልጥፍናዋ ተፋዟል:: አሁን የታዘዘላትን መድሀኒት ያለማቋረጥ መዋጥ አለባት:: በወንድሟና በቤተሰቡ ክትትል መድሀኒቷን ወስዳ አጠናቀቀች:: መድሀኒቱ በጊዜው ቢያልቅም በማፓዎ ጤና ላይ ለውጥ አልታየም:: ዛሬም ትንሽዋ ልጅ ከነህመሟ አሮጌውን ዓመት ተሻግራ አዲሱን ዘመን ይዛለች::
አቋራጩ ምክር …
የማፓዎን መክሳት መጥቆር፣ ያዩ ብዙዎች ብዙ እያሰቡ ነው:: በመድሀኒት ያለመዳኗ የገባቸው የቅርብ ሰዎች አቋራጭ ያሉትን መፍትሔ አምጥተዋል:: ማፓዎ ህክምናው ካላዳናት የእነሱ መንገድ እንደሚፈውሳት እርግጠኞች ናቸው:: አሁንም በልጅቷ ሆድ ላይ ደም ያዘለ ዕብጠት ይታያል:: ሰውነቷ ቀጭጮ ዞማ ጸጉሯ ረግፏል::
ይህ ምልክት እናውቃለን ለሚሉት ሰዎች ጥሩ ማሳያ ሆኗል:: መፍትሄው በእጃቸው ነውና ወደ ባሕላዊ መድሀኒት አዋቂ ዘንድ አድርሰዋታል:: አዋቂ ተብዬው ማፓዎ እጁ እንደገባች ባህላዊ ልማዱን ቀጥሏል:: ትንሽዋ ልጅ እጅና እግሯ ተይዞ በጋለ ብረት ቁስሏ መተኮስ ጀምሯል:: ከፍ ያለ ሥቃይ መቀበል የጀመረችው ቀንበጥ እንደታሰበው ሆኖ አልዳነችም:: በቁስሏ ላይ የፍም እሳት አክላ ዳግም በህመም ከአልጋ ወደቀች:: የሰዎቹ ምክር፣ የማፓዎ ስቃይ በዚህ ብቻ አልቆመም:: ትንሽዋ ልጅ ሌላ መንገድ ታስቦላታል::
አዋቂው…
ማፓዎ በጋለ ብረት የነፈረ ቁስሏ በወጉ ሳይድን ተጨማሪ ፈተና ልትቀበል ግድ ብሏታል:: አሁን እንደ እኩዮቿ የምትፈነድቅበት ጊዜ አይደለም:: ሮጣ ማምለጥ፣ ተዉኝ ብላ መቃወም አይቻላትም:: በዕንባና ሥቃይ የደከመ አካሏ የሰዎቹን ዕቅድ ከመከወን ያለ ምርጫ የለውም::
አሁን የሰዎቹ እግር ወደ አንድ ‹‹አዋቂ›› የሚባል ጎልማሳ ጎጆ ደርሷል:: ይህ ሰው በመንፈስ ብዙ የሚያውቅ፣ የታመመን ፈጥኖ የሚፈውስ መሆኑ ይነገርለታል:: ሰውዬው በበዛ መከራና ስቃይ የተጎዳችውን ልጅ እንዳየ ፈጣኑን ትዕዛዝ አስተላለፈ:: ስለማፓዎ አንዲት ፍየል ባስቸኳይ አርደው እንያመጡ ቀጭን ትዕዛዝ የደረሳቸው አገልጋዮች ሞራዋን ገፈው ትኩሱን ደም በኩባያ ሞልተው አመጡለት::
አዋቂ ተብዬው ሞራውን አንስቶ በማፓዎ ያልዳነ ቁስል ላይ ለጠፈው:: በጣሳ የሞላውን ትኩስ ደምም ግጥም አድርጋ እንድትጠጣ አዘዛት:: ምስኪኗ ልጅ የተባለችውን ፈጸመች:: ትኩሱን ደም እየተናነቃት ጠጣች:: የፍየሏን ሞራ በእርጥብ ቁስሏ ለጥፋ ጥርሷን ነክሳ ስቃዩን ተቀበለች:: ማፓዎ አልዳነችም:: በጤናዋ ላይ የሚጠበቀው ለውጥም አልመጣም::
መላው ቤተሰብ ማፓዎ በሆነችው ነገር ሀሳብ ገብቶታል:: ሁሉም ስለእሷ ጤና የተሻለውን ለማድረግ እየመከረ ነው:: አብነት ዝም አላለም:: ዘወትር ህክምናውን ስለመቀጠል ያስባል:: በየቀኑ ጥሩ ምርመራ የምታገኝበትን መንገድ ይፈልጋል:: የታዋቂ ሀኪሞችን ስም ያጠያይቃል:: ከቀናት በአንዱ ያሰበው ተሳካለት:: እህቱን ይዞ ከአንድ የግል ሆስፒታል ተገኘ::
ምርመራን እንደገና…
በሆስፒታሉ ለማፓዎ በአዲስ መልክ ምርመራው ተጀመረ:: ትንሽዋ ልጅ በህመም ስትደክም ሰንብታለች:: ስትወስደው የቆየችው መድሀኒትና የባህላዊው መንገድ ያለ አንዳች ፈውስ መላ አካሏን አጠውልጓል:: ቀናት የፈጀው የሀኪም ቤት ቆይታ ውሎ አድሮ አዲስ ውጤት ይዞ መጣ::
አብነት የማፓዎ ምርመራ አራተኛ ደረጃ የደም ካንሰር እንደሚያሳይ ተነገረው:: ህመሙ በውስጧ መሰራጨት መጀመሩንም ሰማ:: ማዳንን አስቦ ከቤቱ ለራቀው፣ ብዙ ለታገለው አብነት ከባድ ይሉት መርዶ ሆነ:: እሱና አገሬው እስከዛሬ ስለካንስር ሲወራ ይሰማሉ:: ሁሉም ግን ከወባና ትኩሳት የከፋ ጉዳት እንዳለው ገምተው አያውቁም::
ማፓዎ ፈጥና የካንሰር ህክምናውን መጀመር አለባት:: ይህ እንግዳ ጉዳይ በግብርና ለሚተዳደረው ቤተሰብ ደግሞ አስደንጋጭ ዜና ነው:: ህክምናው በቀላልና በአጭር ጊዜ አይቋጭም:: ልዩ ትኩረት፣ በብዙ የሚቆጠር ገንዘብና ትዕግስት ይጠይቃል::
እነ አብነት ያሉበት ሆስፒታል የግል ነው:: ከመንግስት ይልቅ በዚህ ቦታ ወጪው ይበረክታል:: መድሀኒቱ፣ አልጋው፣ የእለት ወጪው ቀላል አይደለም:: አሁን የመጀመሪያውን የኬሞ ቴራፒ እንድትጀምር ታዛለች:: ኬሞ የራሱ ሂደትና የበዛ ፈተና አለው:: አይቀሬ ህክምና መሆኑ ተነግሯቸዋል:: አሁን በስቃይ ስትዝል፣ ስትንገላታ የቆየችው ብላቴና ለሌላው መከራ ራሷን ማዘጋጀት አለባት:: እህትና ወንድም በተባለው ቀን በቦታው ተገኝተዋል:: ለስድስት ዙር የታዘዘው ኬሞ ቴራፒም አንድ ብሎ ተጀምሯል:: ትንሽዋ ማፓዎ ስቃይዋ በርትቷል:: አካል መንፈሷ በድካም ዝሏል::
ስድስተኛው ዙር አልቆ ለሰባተኛው ቀነ ቀጠሮ እንደተያዘ አብነት ከእጁ ያለው ገንዘብ መሟጠጡን አወቀ:: ከዚህ በኋላ አንድ እርምጃን የሚያርቅ ሰባራ ሳንቲም ከእሱ ዘንድ የለም:: እስካሁን ስለ ማፓዎ ጤና ቤተሰቡ ብድር ገብቷል፣ ቤት ንብረቱን ሸጧል:: አሁን ተፈላጊው ገንዘብ እስኪገኝ ደግሞ ግዜ መውስድ ግድ ነው:: እንዲህ ሲሆን ልጅቷ ያለ መፍትሔ ልትቆይ ትገደዳለች::
ገንዘቡን ለማግኘት ከወዳጅ ዘመድ፣ ርዳታ መለመኑ፣ የሰው ፊት ማየቱ ግድ ሆኗል:: የሰባተኛው ዙር ኬሞ በአቅም ችግር ምክንያት አልቀጠለም:: ለቀሪው ህክምና በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል:: በዚህ መሀል አንድ ብሎ የጀመረው ጊዜ እንደዋዛ ተቆጥሮ ነጎደ:: እንደቀልድም ሶስት ወራት ተቆጠሩ ::
ማፓዎ ያለመድሀኒትና ህክምና ያሳለፈችው ጊዜ ዋጋ እያስከፈላት ነው:: አሁን ማገገም የጀመረችው ቀንበጥ ዳግም መጠውለግ ይዛለች:: አብነት እህቱን ይዞ ወደ ሆስፒታሉ ሲመለስ ህመሟ አገርሽቶ በእጅጉ ዝላ ነበር:: በወቅቱ ሁኔታዋን ያዩ ሀኪሞች በእሱ ላይ አብዝተው ጮኹበት:: እስካሁን ለምን እንዳቆያት በመውቀስም ጥፋተኝነቱን ሊነግሩት ሞከሩ::
ይህ እውነት በግል ሕክምና፣ በገንዘብ እጦት መከራ ሲያይ ለቆየ ብቸኛ አሳካሚ ልብ ይሰብራል፣ አንገት ያስደፋል:: ታላቅ ወንድም ምርጫ አልነበረውም:: የሚባለውን ቀጣይ ትዕዛዝ ለመስማት ራሱን አዘጋጀ:: አብነት ጥቂት ቆይቶ ከሀኪሞች የደረሰው መረጃ ክፉኛ አስደነገጠው:: ከዚህ በኋላ የእህቱ ህክምና የሚቀጥለው አዲስአበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው::
አብነት እንኳን አዲስ አበባን ወላይታ ሶዶን በቅጡ አያውቅም:: አዲስ አበባ ሰፊና ግራ የሚያጋባ ከተማ መሆኑን ሰምቷል:: እሱ ከጎፋ ቋንቋ የዘለለ አማርኛን በወጉ አይናገርም:: ይህ ሁሉ ሲገባው ራሱን ይዞ አንገቱን ደፋ፤ እሱ የሰማውን ለቤተሰቦቹ መልሶ ለመናገር ቃል አንደበት አነሰው:: ወጣቱ ልጅ እህቱን በማሳከም ዓመታትን ቆጥሯል:: እስከዛሬ ወላጆቹ ለብቸኛዋ ሴት ልጃቸው የአቅማቸውን አሟጠዋል:: ሀብታቸውን ከፍለው ቤት ንብረታቸውን ሸጠዋል::
ይህን ሀቅ አሳምሮ የሚያውቀው አብነት የሰማውን እውነት ለእነሱ አድርሶ ሊያሳዝን፣ ሊያስደነግጣቸው አልፈለገም:: ራሱን አረጋግቶ ከውስጡ መክረ:: አሁን ማፓዎን ይዞ ወደ አዲስ አበባ መሄድ አለበት:: በእጁ ላይ ከስምንት ሺህ ብር የማይበልጥ ገንዘብ አለ:: ያሰበውን ለመፈጸም አፍታ አልቆየም:: ከሆስፒታሉ የተጻፈለትን ማስረጃና ማፓዎን ይዞ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገሰገሰ::
አዲስ አበባ …
አዲስ አበባና አብነት አይተዋወቁም:: በስፍራው የሚያውቀው ዘመድ የሚቀበለው ቤተሰብ የለም:: እየከፋው፣ ሆድ እየባሰው ሆስፒታሉን ተጠይቆ ከግቢው ደረሰ:: የ2017 የመስከረም ወር ፍጻሜ ከሚፈልገው አገናኘው:: ማፓዎን ያዩ የህክምና በለሙያዎች የመጀመሪያ እርዳታ አደረጉላት:: በመንገድና በበዛ እንግልት የደከመችው ልጅ ህመሙ አሸንፏታል:: አሁንም የሆዷ ላይ ዕብጠት አልጎደለም:: በድንገተኛ ክፍል አልጋ ሰጥተው ለህክምናው አመቻችዋት:: ከሰባት ቀን በኋላ እንደ አዲስ ኬሞ ቴራፒውን ጀመረች:: የሆዷ ዕብጠት መቀነስ ጀመረ:: ዓይኖቿን ገለጠች:: ትንፋሽዋ ተመልሶ አካሏ አገገመ::
ማፓዎ አሁን አስራ አራተኛ ዓመቷን ይዛለች:: እስካሁን ከሆዷ ዕብጠት ጋር ሃያ ዘጠኝ ኪሎ እየመዘነች ነበር:: ከህክምናው በኋላ ዕብጠቱ መጉደል ጀመረ:: ማፓዎ ዳግም ሚዛን ላይ ቆመች:: አስራ ስምንት ኪሎ ሆናለች:: አብነት ማፓዎን ባየ ቁጥር ውስጡ በሀዘን ይመታል:: እሷ ማለት የልጅ አዋቂ ናት:: ብዙ መከራ አሳልፋ እንኳን ፊቷ ፈገግታ አያጣውም::
ለእናቷ ታዛዥ ለቤቱ አገልጋይ የሆነችው ቀንበጥ ዛሬ የልጅነት መልኳ ከእሷ የለም:: ለዘጠኝ ጊዜ በወሰደችው ኬሞቴራፒ ዞማ ጸጉሯ ረግፎ መላ አካሏ ተለውጧል:: ከዘጠኝ ወንዶች መሀል የተገኘችው ብቸኛ ዕንቁ:: የዕድሜዋን ግማሽ ያለፈችው ተነግሮ በማያልቅ ስቃይ ነው:: ዛሬም ግን ደማቅ ፈገግታ ከፊቷ አይጠፋም:: አብነት ስለብቸኛ እህቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏል:: ስለነገዋ ደግሞ ብዙ ተስፋዎችን ሰንቋል:: እሷን አስተምሮ እስከ ዩንቨርስቲ ማድረስ ዕቅዱ ነው::
ከማፓዎ ጋር …
ማፓዎን ያገኘኋት በማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን እንግዶች ማረፊያ ውስጥ ነው:: ግቢውን አልፌ ወደሳሎኑ ስዘልቅ በልዩ ፈገግታ ተቀበለችኝ:: ሰውነቷ ተጎድቷል:: አካሏ ጠቁሯል:: ውስጤ ክፉኛ አዘነ:: የሁለተኛ ክፍል ተማሪ መሆኗን አወጋችኝ:: አተኩሬ እያየኋት በእሷ ላይ ያለፈውን መከራ አሰብኩት:: ማፓዎ የማይቻለውን ችላ ያለፈች ጠይም ዕንቁ:: ስለነገ ዛሬን በጽናት የቆመች አይበገሬዋ ቀንበጥ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም