
ከኖርኳት ኢምንት እድሜ በጨረፍታ ያገኘሁት ተሞክሮ የሕይወት ስንቅ የሞራል ትጥቅ እንዲሆናችሁ በማሰብ ከአዲስ ዘመን ወደብ የብዕር መልህቄን ጥያለሁና ዓይኖች ሁሉ ወደ ወጣቶች ዓምድ ይሁን።
ልሳኔ ለዝቦ በጥበብ ቅላጼ በሥነ ጽሑፍ ሲወዛ ብሩህ ገጼ “መጽሐፍ ያድናል ትርጉም ይገላል” የሚለውን ብሂል ልብ አልኩና የተዛነፈ የሕይወት ንባቢያችንን ለማቅናትና የበኩሌን ሃሳብ ለማዋጣት አያሌ የተለጎሙ ወረቀቶች አንደበታቸውን ይፈቱልኝ ዘንድ ደጅ ጠናሁ፤ “መጀመሪያ ሃሳብ ነበር፤ ሃሳብ ወረቀትን ተዋሃደ፤ እርሱም መጽሐፍ ሆነ” እንዳልኩ እኔ። ምንም እንኳን ደራሲነት ደምና ላብ ቢጠይቅም የሰውን ልጅ ከመጽሐፍነት ያገደው የለም፤ የቱንም ያህል በቅጡ ባይነበብም፤ በተለይ በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኘው ምዕራፍ።
ስለሆነም ውድ አንባቢያን ሆይ! እንደንስር እይታ የጠለቀ ባርቅቆተ ምናብ የመጠቀ በሃሳብ መንኮራኩር እንሳፈርና ደመናው ላይ ያረበበውን የምን አገባኝ ስሜት ሀገርና ትውልድን በሚያድን እሳቤ እንግፈፈው እስኪ? ጀምሮ የማይጨርስ ያልኖረውን ለመጻፍ የሚፍጨረጨር ግብዝ “ደራሲ ነኝ” ባይ ብቻ ነውና እስከ መጨረሻው የሃሳቤ መቋጫ ድረስ አብራችሁኝ ዝለቁ።
በቆሎና ጤፍ “እኔ እሻላለሁ” በሚል ተወራረዱ፤ ኋላም ለዳኝነቱ ሚዛን ቀርቦ ሲመዘኑ ለካስ በቆሎው ነቀዝ ወግቶት ኖሯል ባዶነቱ ተጋለጠ።
በይሆናል ያተለቅናቸው እድሜያቸውን የዕንጨት ሽበት ሲወርሰው ያውቃሉ ብለን ያስቀደምናቸው የወረቀት አርበኞች የተግባር ድሆች ሆነው እውቀታቸውን ዳዋ ሲበላው ተመልክተን
ትንሽ ሲፍጨረጨር ትልቅ ከዋተተ፣
ያክብሮት አንቱታ ምን አለ በሞተ።
እያልን የመዝፈናችን ምስጢር ተስፋ መቁረጥ የጸነሰው የመረሳት ትዝብታችን የመገፋት ብሶታችን የወለደው እንጉርጉሮ መሆኑ የተሰወረ አይደለም፤ ከዚህም የተነሳ ጣሊያን ብትገዛን ይሻል ነበር ብለን ተመኝተናል፤ ለእኛ ያልሆነች ሀገር ትውደም ስንልም እንኳን ለራሳችን ውሃ ተራጭተን ጭቃ አቡክተን ላደግንባት እናት ምድራችን ይቅርና ለጠላትም ልንመኝለት የማይገባ ክፉ ሃሳብ አሟርተናል፤ ድሮስ ሃበሻ በማለትም የገዛ ሕዝባችን ላይ ተዘባብተናል። ርግጥ ነው ይህ ሁሉ መብሰክሰክ
“ትመጫለሽ ብዬ ዞሬ ዞሬ ሳይ፣
ትንሽ ነው ብለሽ መቅረትሽ ነው ወይ።”
እንዳለው ማሽላ ጠባቂ የመዘንጋት ስሜት በልባችን ሰርጾ ቀልባችንን አሸፍቶ አድማስ ወዲያ ማዶ ከባዕዳን ምድር አሻገረው፤ ሆዳችንንም አሻከረው፤ ማሽላ ጠባቂውኮ ታዲያ የተናቀ መስሎ እንደተሰማው አልቀረም፤ ይልቁንም
“አጭር ነው ይሉኛል እድሜያቸው ይጠር፣
ኮረሪማ አይደል ወይ ወጥ የሚያሳምር።”
ሲል አካሉ ቢሆንም ደቃቃ ልቦናው የነቃ እንደሆነና ለብረት መዝጊያነቱ ቁምነገረኛ መሆኑን ገልጦ አስቆጫት እንጂ፤ እኛም ብንሆን ትንሽነታችንን ለመርገም ሳይሆን ለበረከት በማዋል እድሜያችንን የሚያስወድስ ሥራ ለመሥራት የሞራል ዝግጁነት ሊኖረን ይገባል።
ፈጣሪ እምነትን በቅንጣቷ የሰናፍጭ ፍሬ ነው የመሰላት፤ ግዙፉ ጎልያድ የወደቀው በትንሹ ዳዊት ጠጠር ነው፤ መልአኩ እንኳን የክርስቶስን መወለድ ያበሰራቸው አሳንሰን ለምናያቸው እረኞች አይደል? በብዛት የምንወስደው ስኳር ቢጣፍጥም ትርፉ በሽታ ነው፤ ለመድኃኒትነት የምንወስደው ጥቂቱ ኮሶ ግን ከህመማችን ያሽረናል፤ የኢትዮጵያ ጀግኖችም እስከ አፍንጫው ድረስ ታጥቆ የመጣውን የጣሊያንን ጦር ያሳፈሩት በተናቀ መሳሪያ ነው፡፡
እናም እኛ ወጣቶች መንገዳችን ቀንቶ አላማችን ጠርቶ ተስፋችን ጸንቶ የተገኘን እንደሆነ ሀገራችን ሰው ባጣች ጊዜ ቀድመን የምንደርሰው እኛ ነን፤ ስለዚህ ቂሎው በበረከተበት ዓለም ጥንቅሽ ሆኖ መገኘት ግድ ይለናል፡፡
ይሁን እንጂ መታዘብ እንደቻልኩት ሀገራችን የምትፈልገን ክፉ ቀን ሲገጥማት ነው ብለን እናስባለን። እውነቱን ለመናገር ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለን፣ ሬቻ ዮዮ ማስቃላ [ጊፋታ] ፍቼ ጨንበላላ፣ ጥምቀት የገና ጨዋታ የትኛው የባሕል ክዋኔ ነው ወጣቶችን ያገለለው? ሉዓላዊነቱ ተንሰራፍቶ የመንፈስ መዛል የትኩረት መዋለል ገጥሞን ወደፊት እንዳንራመድ ተበተበን እንጂ አባቶቻችን ሠርተው ያስረከቡን እሴት ሃሳባዊነትን አስጥሎ ቁስን የሚያስመልክ አልነበረም፤ “የእሳት ልጅ አመድ” ነውና ተረቱ ከነፍስያችን ጋር ካላዋሃድናት በቀር በሥጋዊ ብይን ብንኖራት ከችግራችን በታች ትውልብንና የሀገራችንን ዋጋ ያራክስብናል። ሃሳቤን እንዲያጎላልኝ የዶክተር ሪኪን የሕይወት ልምድ አንስቼ ትማሩበት ዘንድ የወጣትነት እድሜዋን ልበርብር።
በካሊፎርኒያ የብላክስበርግ ዩኒቨርሲቲን እግሯ እንደለቀቀ ሥራ ፍለጋ ብትኳትን ጠብ የሚል ነገር ጠፋ። ይህን ጊዜ የትምህርት ማስረጃዋን እያዩ የሚመልሱባትን ሰዎች አምርራ ጠላቻቸው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብላ በማመኗ የሀገሯን ውድቀት ደገፈች፤ ልቧንም ከፈጣሪ ደጅ እንዳይደርስ ከለከለች።
“አስታራቂ ሽማግሌ መካሪ የጥበብ ሥራ አታሳጣን” እንዲል የአባቶቻችን የዘወትር ጸሎት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና በጎዳናው ስትንቀዋለል አንድ አረጋዊ የፓውሎ ኮይሎን ዘአልኬሚስትን መጽሐፍ ሰጥተዋት ከዓይኗ ተሰወሩ። ካለችበት ሁኔታ የማያስፈልጋት ሆኖ ስለተሰማት ብትበሳጭም በምግብ እጦት የደከመ አካሏን እየጎተተች ከባሕሩ ዳርቻ ስትደርስ በባሕሩ መሃለኛው ክፍል ፍሬዋ ጎምርቶ የምታስጎመጅ የእንኳይ ዛፍ ተመለከተች።
ለመብላት አሰፍስፋ ከባህሩ ዓይኗን ስትጥል ዋና ካለመቻሏም በላይ አንጀቷን የቆረጠው እንኳይዋ ዛፍ ላይ ዝንጀሮ መቀመጡ ነው። ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የሚገማሸረው ውሃ እንባዋን እያዘራች ብታዋየውም ከዝምታ ሌላ ምንም ነገር አልፈየደላትም። ዶክተር ሪኪ ልትይዘው ስትል የሚያመልጣት ደረስኩ ስትል የሚርቃት እጣ ፈንታዋ እንደሆነ አምና አቅም ከድቷት ጉልበቷ ሲታጠፍ የተከተሏት እኒያ አረጋዊ በክንዳቸው ቀለቧት። ከረጅም ሰዓት ሰመመን ነቅታ ዓይኗን ስትገልጥ ከቆለሉት ድንጋይ እያነሱ ወደ እንኳይዋ ዛፍ የሚወረውሩ ሽማግሌ ተመለከተች። እሳቸው ድንጋይ ሲወረውሩ ዝንጀሮው በተራው አጸፋውን ለመመለስ እንኳይ ቀጥፎ ሲወረውር ሪኪ ምራቋን ያመረረውን ርሃብ ገታች። ከዚያም አረጋዊው ኦሊ ካጠገቧ ተቀመጡና ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ ከእዝነ ልቦናቸው አደመጧት። አውርታ እንደጨረሰች ከሳቸው የትዝታ ማህደር እየዘገኑ የሚበጃትን ፍቱን ብልሃት አካፈሏት።
ሽማግሌው የዘሩት አላሽት ያለቡት አላግት ብሎ ስኬት ፊት ስትነሳቸው የሕይወት መንገድ ቁልቁል አንደርድሯቸው ነበር። መከራ አደንድኗቸው ፈተናን ተቋቁመው ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራታቸው ባለጸጋ ለመሆን በቁ፤ ነገር ግን ያገኙት ሀብት ሃሴት ሊያጎናጽፋቸው አልቻለም። እንደስሜት አልባ የቃላት ኳኳታ ሕይወታቸው ወና ሆነ። “ደህና አደርክ” የሚላቸው ሰው እንኳን አጡ። ሰላም የራበው፤ ፍቅር የጎደለው ሕይወት ስኬታቸውን ሙሉ አላደርግልህ ቢላቸው ፈጣሪ እንዲገለጥላቸው በእንባ ሲማጸኑ የነብዩ መሐመድ በጎነት በልቦናቸው ተጻፈ።
ነብዩ መሐመድ ሁልጊዜ በመንገዳቸው እሾህ የሚከሰክስባቸው ሰው ነበር፤ ታዲያ አንድ ቀን በመጓዝ ላይ እንዳሉ የእሾህ ክስካሽ አላዩምና በድንጋጤ ወደ ሰውዬው ቤት በረሩ። ሰውዬው በጠና ታሞ አልጋ ይዞ ሲደርሱ መሪር ሀዘን ፈንቅሏቸው ተንሰቀሰቁ። ሰውዬውም ለቅሷቸውን ሲያይ እጅጉን ተደንቆ “ለእኩይ ግብሬ ቅጣት እንጂ ምህረት ይገባኛልን?” በማለት ሲጠይቃቸው ፍጹም ትህትናን ተላብሰው የአላህን ፍቅር እያሰቡ ለበጎ ሥራ እንዳበረታቸው ገልጸው በማመስገን ክፋቱን በደግነት መለሱለት።
አረጋዊውም ከህሊናቸው ለመታረቅ “ምን ያደርጉልኛል?” ብለው የገፏቸውን ሰዎች በወጣትነታቸው ዘመን የጋረጡባቸውን እንቅፋት ረስተው የለመለመ አዛውንትነታቸውን በልባቸው ከትበው እያንዳንዱ ፈተና የሕይወት ሽግግር መሆኑን በማመን የሰውን ልጅ የት አገኘዋለሁ አይባልምና ለምስጋና ሲንበረከኩ ፈጣሪ በይቅርታ ቤታቸውን ጎበኘው። ልዕልና ከፍ ባለ ቁጥር ፈተናውም አብሮ ያድጋልና በአንደኛው ቀን ምሽት በራቸው ተንኳኩቶ ሲከፍቱ ጨለማ የለበሰና የሚከረፋ ጢስ ካፉ የሚትጎለጎል ግዙፍ አካል ከፊታቸው ቆሞ ተመለከቱ፤ በድንጋጤ በሩን ጠረቀሙበትና “እንዴት አንተ እያለህ ቤቴ ሰይጣን ይመጣል?” አሉት ፍርሃት እያራዳቸው። ፈጣሪም “ቤቱ ያንተ እንጂ የኔ አይደለም” ይላቸዋል። አስከትሎ ዳግመኛ እንዳይመጣና አብሬህ እንድኖር የምትሻ ከሆነ አንድ ክፍል ስጠኝ” አላቸው። ባለጸጋው እያጉረመረሙ ያላቸውን አደረጉ፤ ይሁን እንጂ ሰይጣን ወደቤታቸው መመላለሱን ፈጣሪም “ክፍል ጨምረኝ” ማለቱ አልቀረላቸውም።
በእንዲህ መልኩ ሁሉንም ክፍል አስረክበው እንደጨረሱ ፈጣሪ በተራው መጀመሪያ ቀን ሰጥተውት የነበረውን ጠባብ ክፍል ለባለጸጋው አዙሮ ሰጣቸውና አብረው መኖር ሲጀምሩ የራቀው ቀርቦ የነኩት በርክቶ የጠየቁት ተመልሶ ተድላ በቤቱ ናኘ። በዚህም ፈጣሪ ሰውና ሀገር ከችግሮች በላይ መሆናቸውን እንደተማሩ ሲያጫውቷት ዶክተር ሪኪ ወጣትነቷን ለሀገሯና ለፈጣሪ ልትሰጥ ቃል ገብታ የሕይወት እንቅስቃሴዋን በጥበብ ቃኘች።
እናም ወጣት እህትና ወንድሞቼ ከአረጋዊውና ከሪኪ ታሪክ መገንዘብ እንደቻልነው ከምንፈልገው ከፍታ ለመገኘት ከዳገቱ የበቀሉ ቆንጥሮችን ትተን አናቱ ላይ ያለውን ደልዳላ ሜዳ አሻግረን ማየት ይኖርብናል። በዓሉ ግርማ በኦሮማይ መጽሐፉ እንደነገረን ቀይ ባሕርን ለማጣታችን ምክንያት የሆኑ ቡድኖች ከሁሉም አስቀድመው ወጣቱ በመንግሥት ላይ ያለውን ተስፋ አስጣሉና ምርጫ አልባ አድርገው ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ከሰላም ይልቅ ሁከትን ከልማት ይልቅ ጥፋትን ከአንድነት ይልቅ መለያየትን በመስበክ ለበረሃ አበቁት።
ዛሬም ድረስ “ለመኖር መግደል” የሚለውን የማክቤልን አነጋገር እንደ ወረደ ተቀብለው ወጣቱን በዘረኝነት እሳት እየማገዱ የግል ጥቅማቸውን የሚያካብቱ እልፍ ጨለምተኞች አሉ፤ ቢሆንም ግን ጀግናው የኢትዮጵያ ወጣት በጎጥ ሲያጥሩት ሀገሬን ብሎ የጋቱትን ነጣጣይ ትርክት ሽሮ አንድነትን በመዘመር ከካራማራ ጽናትን፣ ከዓድዋ ህብረትን፣ ከመቅደላ እምነትን፣ ከጣና እርጋታና ስክነትን፣ ከዓባይ ረጅም ተስፋን ተምሮ በሃይማኖቱ ተደግፎ ለህሊናው ተገዝቶ ትኩስ ጉልበቱን ለሀገሩና ለፈጣሪ የሰጠ ህልሙ የታመነ ብርቱ ትውልድ ነው።
ስለዚህም በውጭው ዓለም ብልጭልጭ ሕይወት ከመጎምዠት የሀገርን ወግ እና ባሕል ማክበር ስልታዊ ነው፡፡ ሌሎች የዓለም ሀገራት ከጭቆና ነፃ የወጡበትን ቀን ሲያከብሩ እኛ ግን ድል የነሳችበትን ቀን የምታከብር ቅድስት ሀገር ነው ያለችን፤ ስለዚህ “አካሄዱን አይተው ጓዙን ይቀሙታል” ነውና በድክመታችን ኢትዮጵያን እንዳናጣ ወጣት እህትና ወንድሞቼ አያያዛችንን እንወቅበት።
“እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል።”
እንዲል ሙዚቃችን ስንኖር ጉርሳችን ስንሞት ልብሳችን ለሆነች ሀገራችን የጎደለውን ልንሞላላት የጠመመውን ልናቀናላት ግድ ይለናልና ሳቋም ሀዘኗም ያገባናል።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም