ሰላምን ለማጽናት

ዜና ሐተታ

አዳራሹን ፍንትው ያደረገው ብርሃን ድንገት ድምቀቱን ቀነሰ፤ በውስጥ ያሉ ታዳሚያን፤ ፊት ለፊታቸው ባለው “እስክሪን” ላይ አተኩረዋል። በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ የተቀነባበረና ረጋ ብሎ የሚንቆረቆር ድምፅ ይሰማል። የሙዚቃ ቅንብሩ የብዙዎቹን ቀልብ ስቧል። በስክሪኑ የዘጋቢ ፊልሙ ርዕስ “የጫማ ለውጥ” የሚለው ሐረግ ለተወሰኑ ሰከንዶች ቆይቶ ለምስሎች ቦታውን ለቀቀ።

ደበብ ባለው ብርሃን ውስጥ የሚገኙት የዕለቱ ታዳሚያን ደመቅ ብሎ ከሚታየው ስክሪን በምስልና በድምፅ የታጀበውን ዘጋቢ ፊልም በጥሞና ይከታተሉ ጀምረዋል። ዘጋቢ ፊልሙ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሠራ ሲሆን፣ እንደ ሀገር አንዱ ሌላውን እየገፋ ባለበት በዚህ ዘመን ሁለት የማይተዋወቁ ቤተሰቦች አንዳቸው ወደሌላው ቤተሰብ በመሔድ በእንግድነት የሚያሳልፉትን ቆይታ የሚተርክ ነው።

ከሀድያ ዞን የሔደ አንድ ቤተሰብ፣ ቆይታውን ከአንድ የጉራጌ ቤተሰብ ጋር በማድረግ በሚያሳልፍበት ጊዜ የሚገጥመውን ሁኔታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ሁለቱ የማይተዋወቁ ቤተሰቦች ለቀናት አብረው በአንድ ጎጆ ሲቆዩ እርስ በእርስ ያላቸው መግባባትና መተሳሰብ ልባቸውን የነካው የሀድያ ቤተሰብ “ባሕላችን በገጠር በእግሩ ሲሄድ፤ በከተማ ደግሞ በዳዴ እየተጓዘ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

በሁለቱ ቤተሰብ መካከል የነበረው ቅብብሎሽም በስጦታ ጭምር የታጀበ በመሆኑ ፊልሙን ሲከታተሉ የነበሩ ታዳሚያን ቆም ብለው ራሳቸውን እንዲፈትሹ ያደረገ መሆኑን ስሜታቸውን መረዳት ይቻላል።

ታዳሚያኑ ሃሳባቸውን ያጋሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሁለተኛ ምዕራፍ የመጀመሪያው ዙር የ”ስለ ኢትዮጵያ” መርሐ ግብር “ሰላም እና ኢኮኖሚ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቡታጅራ ከተማ ባዘጋጀበት ወቅት ነው። በዕለቱም ከቀረቡት መርሐ ግብሮች ውስጥ አንዱ ዘጋቢ ፊልሙ ነው።

“መከባበሩ ሰፊው ማኅበረሰብ ዘንድ መኖሩን ከዘጋቢ ፊልሙ ተረድቻለሁ” የሚሉት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት እልፍነሽ ሙለታ (ዶ/ር) ናቸው። ሰላምን ማስከበርና ከሰላም መጠቀም የምችለው እኔ እራሴ ነኝ የሚል መልዕክት ውስጤ ቀርቷል ይላሉ። ሰላማችንን ልናሻሻል የምንችለው ባሕላችንን በማክበር ጭምር ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንዳሉት ከሆነ፤ ልክ በዘጋቢ ፊልሙ የተረዱት ነገር ከሚያለያየን ይልቅ የሚያቀራርበን ነገር ብዙ መሆኑን ነው። ይህ እውነት በመሆኑም በተለይ ምሑሩ አካባቢ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ መሥራት ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በ”ስለ ኢትዮጵያ” መርሐ ግብሩ ተጓዥ እንደመሆኑ መሰል አስተማሪ ጉዳዮችን አጠናክሮ መሔድ ይገባዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ ፊልሙ ትክክለኛ ማንነታችንን የሚያሳይ ነው የሚሉት ደግሞ የዕለቱ ታዳሚ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ናቸው። ነገር ግን ይህ መልካም የሆነው ማንነት እንዲሸረሸር ያደረገውን አካል ሕዝብ እራሱ ሊያስቆመው ይገባል ይላሉ።

አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ሰላም የሁሉ መሠረት መሆኑ እርግጥ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ በዘጋቢ ፊልሙ ያስተዋሉትም ሁለት በማይተዋወቁ ቤተሰቦች መካከል ስላለው መልካም የእንግዳ አቀባበል ባሕል መሆኑን ይገልጻሉ።

በዕለቱ በ”ስለ ኢትዮጵያ” መርሐ ግብር “ሰላም እና ኢኮኖሚ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከተዘጋጀው ውስጥ ሰላምን በተመለከተ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት ከባሕል መሸርሸር ጋር ተያይዞ የገጠሩም ሆነ የከተማው ክፍተት ይስተዋልበታል። በልጆች፣ በቤተሰብና በስብዕና ቀረጻ ላይ ቸልተኝነት ይታያል። ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው በገጠሩም ሆነ በከተማው ከባሕሉና ከማንነቱ ይልቅ በውጭው ባሕል የመጠመድ ነገር መኖሩ ነው።

የሀገር ሽማግሌዎች ሚና በአሁኑ ወቅት ተዳክሟል ሲሉ ጠቅሰው፤ መፍትሔውም መልከ ብዙ ነው ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ግጭት እየፈታን እንገኛለን። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የፕሪቶርያው ስምምነት ነው። ግጭትን በንግግርና በውይይት እየፈታን፤ ተንከባልለው የመጡትን ደግሞ በሽግግር ፍትሕ እየፈታን እንሔዳለን ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ግጭት ያለው ዛሬ ብቻ አይደለም፤ በዓፄ ምኒሊክም፣ በዓፄ ኃይለሥላሴም፣ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ ነበር። ከእነዚያ አኳያ ሲታይ አሁን ያለነው አንጻራዊ ሰላም ውስጥ ነው። ይህ የመጣው ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት ጥረት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከትናንት ዛሬ ትሻላለች። በቀጣይ ደግሞ የበለጠ ትሆናለች።

ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው ዜጋዋ ወጣት ነው ያሉት ኸይረዲን (ዶ/ር)፣ ይህ በራሱ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን የተረዳ አካል ኢትዮጵያ ሰላም ውላ ሰላም እንድታድር አይፈልግም ይላሉ። ለሰላም በመሥራት በሰላም ውስጥ መኖር ወሳኝ ነውና ለሰላም ትኩረት መስጠት ያሻል ብለዋል። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማጽናት እንደሚያስፈልገውም ተናግረዋል።

ለሰላማችን እንቅፋታችን ትርክታችን ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ናቸው። ከነጠላ ትርክት ይልቅ ገዥ የሆነውን ትርክት ማጉላቱ ለሁሉም ሰላም መሠረት ነው ይላሉ። ይህ በመታመኑም ገዥ ትርክት ላይ እየተሠራበት መሆኑን ይናገራሉ። መንግሥት ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ አቋም ስላለው እየሠራበት መሆኑንም ያስረዳሉ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You