ብሔራዊ መታወቂያ ለተቋማት ስኬት

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ዲጂታል ዓለም ውስጥ የብሔራዊ መታወቂያ ወይም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊነት በዚያው ልክ ሆኗል:: ይህ ደህንነቱ የተጠበቀ የአንድ ሰው የማንነት መረጃ ለተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶች እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል:: አካላዊ መገኘት ሳያስፈልግ ሥራዎችን ለማቀላጠፍም ይጠቅማል::

የብሔራዊ መታወቂያ ወይም ፋይዳ የተጭበረበረ ማንነትን ለማስወገድና መረጃው የተሟላና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያስችላል:: እንደ ጤና፣ ትምህርት እና ፋይናንስ በመሳሰሉ ዘርፎች አስፈላጊውን አገልግሎቶች ለማግኘት፤ ሁኔታዎችን ምቹ፣ ቀልጣፋ እና ለተጠቃሚ ቀላል እንዲሆኑ ያደርጋል::

ከዚህ አንጻር የዓለም ሀገራትን ተሞክሮ ብንመለከት፤ እንደ ዱባይ፣ አሜሪካ፣ ሲውዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ህንድ እና ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ አድርገው የዜጎቻቸውን ሕይወት ምቹ እና ቀላል አድርገዋል::

ኢትዮጵያም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረጉ ሂደት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን በመተግበር ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ትገኛለች:: ይህ መታወቂያ እንደ ሀገር አንድ ወጥ የሆነ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ‹‹ፋይዳ ለኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል::

በውይይቱም ፋይዳ መታወቂያ ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ምን አይነት ጥቅም እያስገኘ ነው? በሚለው ጉዳይ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አረዓያሥላሴ በመርሃ-ግብሩ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ ዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ ብሔራዊ መታወቂያ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ብሔራዊ መታወቂያ ዜጎችን ወጥ በሆነ መንገድ ከመለየት ባሻገር የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር እና የተቋማትን ሥራ የሚያቀናጅ ስለመሆኑ ተናግረዋል:: የግለሰቦችን መብት የሚያስጠብቅ የመተማመኛ ማዕቀፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የፓናሉ ተወያዮች ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የተገኙ ሲሆን በመድረኩ ላይ በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አዕምሮ ካሳ ፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ከፋዮች ምዝገባና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ፋና፣ በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር አቶ ሳሚናስ ሰይፉ ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የንግድ ወኪል አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃይለሚካኤል፤ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቶፊቅ ሻፊ የፓናሉ ተወያዮች በመሆን የተቋማቶቻቸውን አፈጻጸም አቅርበዋል::

የውይይቱ ተሳታፊዎችም እንደመጡበት ተቋም ስለ ብሄራዊ መታወቂያ አስፈላጊነት የተለያዩ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል::

በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አዕምሮ እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርቷል:: በዚህም ተቋሙ አንድ ሚሊዮን የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን መዝግቧል:: ተቋሙ ከፋይዳ ጋር አገልግሎቱን ማስተሳሰር ከጀመረ አንስቶ በርካታ የማንነት ማጭበርበር ወንጀሎችን መከላከል ተችሏል::

በገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ከፋዮች ምዝገባና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ፋና፤ በተቋሙ የፋይዳ መታወቂያ ከግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ጋር የማያያዝ ሥራ እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል::

ለገቢዎች መሥሪያ ቤት የደንበኞችን ትክክለኛ ማንነት መለየት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ተቋሙን ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው ግለሰቦች በእጅጉ ሲፈትኑት ቆይተዋል:: አሁን ግን ይህንን ችግር ለማስወገድ ዲጂታል መታወቂያ ተስፋ የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል::

አንዳንድ ዜጎችም በሞተ ሰው ንግድ ፈቃድ በማውጣት ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበረም አንስተው፤ አሁን ላይ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር አገልግሎቶችን በማስተሳሰር ትክክለኛ ማንነትን ተጠቅመው ደንበኞች አገልግሎትን እንዲያገኙ በማድረግ ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል:: በዚህም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም አብራርተዋል::

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የንግድ ወኪል አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃይለሚካኤል በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር የመግባቢያ ፊርማ ከተፈራረሙ ጀምሮ ደንበኞች አዲስ የሂሳብ ቁጥር ሲከፍቱ የዲጂታል መታወቂያ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል::

የመታወቂያውን ምዝገባም በ15 የተመረጡ ቅርንጫፎች እና በ75 የሠለጠነ የሰው ሃይል እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፤ ትግበራው ለተቋሙ ትልቅ አቅም እንደፈጠረለት ጠቁመዋል::

የፋይዳ መታወቂያ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቀላጠፍ እና ትክክለኛ የደንበኛ ማንነትን ለማወቅ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል:: ከዚህ ቀደም ሀሰተኛ የማንነት መታወቂያ እየያዙ የሚመጡ ወንጀለኞችን በመከላከል ባንኩን ከኪሳራ ፤ ሠራተኞችንም ከእንግልት የታደገ መሆኑን ጠቁመዋል::

የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቶፊቅ ሻፊ በበኩላቸው ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር ኤጀንሲው ለ162ሺህ ዜጎች የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባን ሲያካሂድ መቆየቱን ተናግረዋል::

ውሎችን ለማረጋገጥ እና ለመመዝገብ የማንነት ልየታ በጣም ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቶፊቅ፤ የተለያዩ ደንበኞች ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው በመምጣት ተቋሙ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስረድተዋል::

ነገር ግን አሁን የፋይዳ አገልግሎት ከተጀመረ አንስቶ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሙሉ በመሉ መጥፋቱን እና ከዚህ በፊት የደንበኞችን ማንነት ለማጣራት የሚባክነውን ጊዜ ማስቀረት እንደተቻለ ተናግረዋል::

በተጨማሪም አገልግሎቱን ለማሳለጥ የሚደረገውን ጉዞ ምቹ እንዳደረገላቸውም ጠቁመዋል:: ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው ለመስተናገድ የሚመጡ ወንጀለኞችን በፍርድ ቤት ለማስቀጣት የሚፈጀውን ጊዜ ፤ ጉልበት እና ገንዘብ ማስቀረት እንደተቻለም አብራርተዋል::

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You