ዩክሬንንና አጋሮቿን ያስጨነቀው ጉዳይ

‹‹ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ›› ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤

ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል:: አሜሪካና የአውሮፓ አጋሮቿ ለዩክሬን ያቀረቡት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛቶቿን በሩሲያ እንዳትነጠቅ ስለማገዙ ቢገለፅም ጦርነቱን እንዳይባባስና በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ ማድረግ ግን አልቻለም::

‹‹ምርጫውን ካሸነፍኩ ጦርነቱን በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ›› ብለው ሲፎክሩ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ጦርነቱን ማስቆሙ እንኳን በአንድ ቀን በአንድ ወርም አልተሳካላቸውም:: ፕሬዚዳንት ትራምፕ የነጩን ቤት መንበር በተረከቡ በአንደኛ ወራቸው ጦርነቱን ለማስቆም ያስችላል ያሉትን የመጀመሪያ ውይይት ዩክሬን ሳያሳትፉ ከሩሲያ ጋር በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ አስጀምረዋል::

የአልጀዚራዋ ዩሪያ ሻፖቫሎቫ ከሞስኮ ባሰራጨችው ዘገባ፣ በውይይቱ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮን ጨምሮ የሀገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል::

ከአራት ሰዓታት በላይ የዘለቀውና ዋና አጀንዳውን በጦርነቱ ምክንያት በእጅጉ የሻከረው የአሜሪካና የሩሲያ ግንኙነት በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ ያደረገው ውይይቱ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀጣይ ለሚያደርጉት የፊት ለፊት ንግግር መሠረት የሚጥል እንደሆነ ተነግሯል:: የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ሩቢዮ እና ላቭሮቭ ጦርነቱን በአፋጣኝ ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት የሚያስተባብር የአሜሪካና እና የሩስያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለማቋቋም ተስማምተዋል::

ይሁን እንጂ በፕሬዚዳንት ትራምፕ አነሳሽነት የተካሄደው ውይይት ዩክሬንንም ሆነ በጦርነቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን የአውሮፓ መንግሥታትን አለማሳተፉ አነጋጋሪ ሆኗል:: ይህም አንድ ወር እንኳ ባልሞላው ሁለተኛው የፕሬዚዳንት ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ከታዩ አስገራሚ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጦች መካከል አንዱ ሆኖ ታይቷል::

የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ዩክሬን ጦርነቱን ከተመለከቱ ውይይቶች መገለል እንደሌለባትና በሩሲያ በተያዙባት ግዛቶች በፍጹም እንደማትደራደርም በአፅንዖት ተናግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን ከአሜሪካና ከአውሮፓ ዘላቂ የደህንነት ዋስትና እንደምትፈልግም ገልጸዋል::

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው ድጋፍ ሊቋረጥና ዩክሬንም ግዛቶቿን ልታጣ እንደምትችል የተናገሩት ንግግር እና ዩክሬን ከሪያዱ ውይይት መገለሏ ለዩክሬንና አጋሮቿ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል:: ፕሬዚዳንቱ ዩክሬን በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች የማስመለስም ሆነ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ/NATO) አባል የመሆን እድል ላይኖራት እንደሚችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል::

ዩክሬን ከሦስት ዓመታት በፊት በተጀመረው ጦርነት ያጣቻቸውን አንዳንድ ግዛቶቿን በድርድር ልታስመልስ እንደምትችል ጠቁመው፣ ከ11 ዓመታት በፊት የነበረው ድንበር ግን ይመለሳል ብሎ መጠበቅ እንደማይባ ገልፀዋል::

ይህን ጉዳይ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒተር ሄግሴትም ከአንድ ሳምንት በፊት ብራሰልስ ላይ ለዩክሬን የጦር አጋሮች ነግረዋቸዋል:: አሜሪካ የኔቶ አባልነት ለዩክሬን ዘላቂ የሰላም ዋስትና ይሆናል ብላ እንደማታምን እና ሩሲያ ክሪሚያን ወደ ግዛቷ ከመቀላቀሏ በፊት የነበረው የዩክሬን ድንበር ይመለሳል ብሎ ማሰብ የማይሳካ ምኞት እንደሆነ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል::

ኔቶን የመቀላቀሉ ጉዳይ በዩክሬንም ዘንድ ተስፋ እየተቆረጠበት ይመስላል:: ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ከ ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ዩክሬን የኔቶ አባል ካልሆነች ከሩሲያ ጋር የሚስተካከል የጦር ኃይል የመገንባትን ተለዋጭ አማራጭ ገልፀዋል:: ይን ለማድረግም ገንዘብና የጦር መሣሪያ እንደሚያስፈልግና ይህንም ከአሜሪካ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል::

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን የዩክሬንን ‹‹አልተወከልኩም›› አቤቱታ አጣጥለውታል:: ‹‹ዛሬ ‹አልተወከልንም› የሚሉት ላለፉት ሶስት ዓመታት የት ነበሩ? ጦርነቱን መጀመር አልነበረባቸውም፤ ከጀመሩት በኋላም ማስቆምም አልቻሉም:: ሩሲያ ጦርነቱን ማስቆም ትፈልጋለች:: ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ እምነት አለኝ›› ብለዋል::

ከዩክሬን ባሻገር በጦርነቱ ጉዳይ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች ላይ እንድንሳተፍ እየተደረገ አይደለም ያሉት የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች፤ በዩክሬን ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን ስለሚሰፍንበት መንገድ የያዙት አቋም የተለያየ ነው::

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል:: የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ከጦርነት ቀጣና ውጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚሰማሩ ጥቂት ወታደሮችን ስለመላክ እያሰቡ እንደሆነ ገልፀዋል:: ፖላንድ ወደ ዩክሬን ጦር የመላክ ሃሳብ እንደሌላት በጠቅላይ ሚኒስትሯ ዶናልድ ተስክ በኩል ይፋ አድርጋለች:: የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከስምምነት ላይ ሳይደረስ የድህረ ጦርነት ሰላም አስከባሪ ኃይል የማሰማራቱን ጉዳይ ‹‹የማይመስል ነገር›› ብለውታል::

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ዩክሬን የመላኩን ሃሳብ ባይቃወሙትም፣ አሜሪካ ግን ወታደሮቿን እንደማታሰማራ ቁርጥ አድርገው ተናግረዋል::

የቢቢሲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች አርታኢ ጀረሚ ቦዌን፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በአጭር ጊዜ እውን የሚሆን የሰላም ተስፋ እንደሌለው አብራርቷል:: ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለዩክሬንና አውሮፓ ፖለቲከኞች ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች በትራንስአትላንቲክ ጥምረት ላይ ትልቅ ስንጥቅ እየፈጠረ እንደሆነና መሬት ላይ ያለው ክስተት ፈጣንና ዘላቂ የሰላም ስምምነትን ሩቅ እንደሚያደርገው ያስረዳል::

ቦዌን ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምትዋሰንበት ሰሜናዊ ድንበር ባሉ የጦር ግንባሮች ተዘዋውሮ ባሰናዳው ዘገባ፣ ‹‹የዩክሬን ወታደሮች እንደተለመደው በየጦር ግንባሩ እየተዋጉ ነው:: የጦር አዛዦቹም የሪያዱ ውይይት ግድ የሰጣቸው አይመስልም:: የትራምፕንና የፑቲንን ውይይት ‹ተራ ጫጫታ› አድርገው ይቆጥሩታል›› ይላል::

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ‹‹ዘ ዋይት ሃውስ›› ከተመለሱ በኋላ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ዘርፍ አስገራሚና አስደንጋጭ ክስተቶች እየታዩ ነው:: በፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን የአስተዳደር ዘመን ከአሜሪካ የጠየቀችው ሁሉ ሲቀርብላት የቆየችው ዩክሬን፣ የቢሊየነሩ ሪፐብሊካን ወደ ሥልጣን መመለስ ጦርነቱን የበለጠ እንደሚያከብድባትና የመደራደር አቅሟንም እንደሚያዳክምባት በመሰጋቱ ኪዬቭና ብራሰልስ ለከባድ ጭንቀት ተዳርገዋል::

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You