
አዲስ አበባ፡- በቀጣናው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ተጨማሪ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንደሚኖርበት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
በትናትናው እለት የተካሄደ ሲሆን ኢኒሼቲቩ አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አክብሯል።
አቶ አህመድ ሽዴ 23ኛው የአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ እንደገለፁት ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የተሰበሰበው የሀብት መጠን ምን ያህል እንደሆነና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ምን ላይ እንዳሉ ተገምግሟል። በዋናነትም በመሠረተ ልማት ትስስር ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ትኩረት ተሠጥቷቸዋል ብለዋል።
ኢኒሼቲቩ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከ20 በላይ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ አድርጓል። የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በአጠቃላይ ለምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ከ9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል ።
ከተሰበሰበው ሀብትም ኢትዮጵያ 3 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆን ችላለች ሲሉም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ተጨማሪ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተነስቷል። ይህም በቀጣናው ግዙፍ የልማት ሥራዎችን ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የተሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር የሆነው የፍጥነት መንገድ የዚሁ ኢኒሼቲቭ አካል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከጅቡቲ ጋር የሚገናኘው የኤሌክትሪክና የቴሌኮም መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክትም በኢኒሼቲቩ የሚከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚከሰት ድርቅን ለመከላከል በሁሉም አካባቢዎች የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አንስተው፤ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ድንበር ዘለል የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ፕሮግራም ተነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተዋል።
በቀጣይ በተለያዩ ሴክተሮች ላይ ያተኮረ የድንበር አካባቢ ልማት ላይ የሚያተኩር ኮር ፕሮግራም ተቀርፆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያን፤ ጅቡቲን፣ ኤርትራን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፤ ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን ያካተተ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣናው የመሠረተ ልማት ትስስር ማጎልበት፣ የንግድና ኢኮኖሚ ውህደትን ማጠናከር ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በጉባዔው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የኢጋድ ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየው፣ የተለያዩ የቀጣናው ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮችን፣ እንዲሁም አጋር አካላት ተሳትፈዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም