
ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ደምቀው አሳልፈዋል። በተለያዩ ርቀቶች ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብም አስደናቂ ብቃት አሳይተዋል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለይም በቤት ውስጥ ውድድሮች እያሳዩ የሚገኙት ብቃትም በመጪው ወር አጋማሽ በቻይና ናንጂንግ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ቻምፒዮና ከወዲሁ ለድል እንዲታጩ አድርጓቸዋል።
በቀናት ልዩነት በተለያዩ ርቀቶች የተደረጉት ውድድሮች በተለይ የሴት አትሌቶች ስኬታማነት የታየበት ነበር። ከቀናት በፊት በፈረንሳይ ቱሪን 3ሺህ ሜትር ውድድር ተሳትፋ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ከትናንት በስቲያ በፖላንድ የ 1500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ድል ቀንቷታል። በዚህም ቀደም ሲል በራሷ የተያዘውን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል ትልቅ ጥረት አድርጋለች። ክብረወሰኑን ለመስበር 0 ነጥብ 83 ሰከንድ ብትዘገይም ያስመዘገበችው 3:53.92 ሰዓት የቦታውን ክብረወሰንና የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሆናል።
የሁለት ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናዋ አትሌት ጉዳፍ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት፣ ከቀናት በፊት በሌቪን የሮጠችው በጉንፋን ህመም ውስጥ ሆና እንደነበር ጠቁማለች።
በተመሳሳይ ስፍራ በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድር ደግሞ ቢኒያም መሀሪ 3፡35.70 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። እዚያው ፖላንድ ኦርሌን ኮፐርኒከስ ካፕ በተሰኘው ሌላ ውድድር ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጽጌ ድጉማ በ8 መቶ ሜትር አሸናፊ ሆናለች። በዘንድሮው የቤት ውስጥ ውድድር በርቀቱ በአጠቃላይ ሶስተኛ ድሏን ያስመዘገበችው አትሌት ፅጌ፣ በቀናት ልዩነት በፈረንሳይ በተካሄዱት የሜዝ እና ሊቪን የቤት ውስጥ ፉክክሮች አሸናፊ ነበረች። ከትናንት በስቲያ አሸናፊ ስትሆን ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓትም 2:00.04 ሆኗል። በዚህም ጽጌ የወርቅ ደረጃ ባላቸው ሁለት የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ የቱር ውድድሮች ባስመዘገበችው 20 ነጥብ ከደቡብ አፍሪካዋ ፕሩደንስ ሴኮዲሶ ጋር በመሪነት ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በተከናወኑት ተከታታይ ውድድሮች የሴቶች 800 ሜትር የአጠቃላይ የነጥብ አሸናፊው ከሳምንታት በኋላ በማድሪድ በሚደረገው የመጨረሻ ውድድር ላይ በሚመዘገበው ውጤት የሚለይ ይሆናል።
በሌላ በኩል በስፔን ካስትሎ በተደረገ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸናፊዎች ሆነዋል። በዓለም አትሌቲክስ የ‹‹ሌብል›› ደረጃ በተሰጠውና በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ አሸናፊ ሆኗል። አትሌቱ የሮጠው የርቀቱን ክብረወሰን ለማሻሻል ቢሆንም ያደረገው ብርቱ ጥረት በስድስት ሰከንድ በመዘግየቱ ክብረወሰን ማሻሻል ሳይሳካለት ቀርቷል። ያም ሆኖ ርቀቱን የሸፈነበት 26 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ሁለተኛው የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት በሚል ተይዞለታል። ጠንካራው ተፎካካሪ ኩማ ግርማ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በተመሳሳይ እለት በባርሴሎና በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር በዮሚፍ ከወራት በፊት ተይዞ የነበረው የዓለም ክብረወሰን በዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኮፕሊሞ ተሰብራል። ኪፕሊሞ የወርቅ ደረጃ ባለው በዚህ ውድድር ክብረወሰኑን በ48 ሰከንዶች ማሻሻል ችሏል።
በሴቶችም በተመሳሳይ በተካሄደው ውድድር ወጣቷ አትሌት መዲና ኢሳ 29፡24 በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆናለች። እሷን ተከትለው ልቅና አምባው እና አይናዲስ መብራቱ ተከታትለው ገብተዋል። ከውድድሩ በኋላ ባለድሏ አትሌት ‹‹10 ኪሎ ሜትር ሩጫ የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ ፈርቼ ነበር። ይሁንና ሁሉም ነገር ተስተካክሎ ስኬታማ በመሆኔ እጅግ ተደስቻለሁ›› ማለቷን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስነብቧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም